Monday, 03 February 2014 12:49

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በጐንደር ታስረው ተፈቱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“ቅስቀሳ ማድረግ ብንከለከልም እኛ ግን ቀጥለናል”

ሰማያዊ ፓርቲ፤ “መንግስት ህዝቡ ሳያውቅ በህገወጥ መንገድ የሚያደርገውን የኢትዮ - ሱዳን የድንበር ድርድር እቃወማለሁ” በማለት ነገ በጐንደር ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ የጠራ ሲሆን ለዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ የነበሩ የፓርቲው አመራሮች ሀሙስ እለት ታስረው መፈታታቸውን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ ገለጹ፡፡ አመራሮቹ ሲታሰሩ ካሜራዎችና ላኘቶፖች እንደተወሰዱባቸው የገለጹት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ በኋላ ላይ የቀረፁዋቸው ሰነዶች ተሰርዘው ንብረቶቹ እንደተመለሱላቸው ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው አመራሮች በጐንደር ከተማ በሚገኘው መስቀል አደባባይ ላይ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት “ህገወጥ ቅስቀሳ ነው” ነው በሚል ከፖሊስ ጋር በተነሳ አለመግባባት ለእስር መዳረጋቸውን ሃላፊው ይገልፃሉ፡፡

“እሁድ ጥር 25 ለጠራነው ሰላማዊ ሰልፍ ጥር 14 ቀን ለከንቲባው ጽ/ቤት ማሳወቂያ ደብዳቤ አስገብተን አሳውቀን እያለ፤ “ህገ ወጥ ቅስቀሳ ነው ተብሎ መታሰራችን አግባብ አይደለም” ብሏል - የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፡፡ የፓርቲው የካሜራ ባለሙያ “ካሜራዬን አልሰጥም” በሚል ከፖሊስ ጋር ተጋጭቶ ትላንት ፍ/ቤት መቅረቡን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ “እኛ ግን በአዘዞና በሌሎች የከተማው አካባቢዎች በራሪ ወረቀቶችን መበተንና መቀስቀስ ቀጥለናል፤ ሰልፉንም እናካሂዳለን” ብለዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡን የከተማው ከንቲባ ሞባይል ላይ ደውለን “መልሼ እደውላለሁ” የሚል የጽሁፍ መልዕክት ቢልኩም መልሰን ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡  

Read 1747 times