Monday, 03 February 2014 12:52

33ቱ ፓርቲዎች አንድነት ፈጥረው የተቃውሞ ሰልፍ ያደርጋሉ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

          የመግባባት አንድነትና ሠላም ማህበር (ሠላም)፤33ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድነት እንዲመሠርቱ በማድረግ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሠላማዊ ሠልፍ እንዲያካሂዱ እንደሚያተጋቸው ገለፀ፡፡ የአገሪቱን ፓርቲዎች ወደ ሁለት ጐራ ለማሰባሰብ በቅርቡ የተጠራው ስብሰባ የታሰበውን ያህል አለመሳካቱን የገለፁት የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ፤በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማካሄድ በመጪው የካቲት 1 ድጋሚ ስብሰባ መጥራት አስፈልጓል ብለዋል፡፡ ማህበሩ ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም በጠራው ስብሰባ ላይ ከተሳተፉት የፓርቲ ተወካዮችና ምሁራን ጋር በተደረገው ውይይት የተቃዋሚዎች የተናጠል ትግል የመንግስትን የስልጣን ዘመን እንዳራዘመ፣ ፓርቲዎችንም ለስልጣን እንዳላበቃና የህዝብን ስቃይና እንግልት እንዳሰፋ መግባባት ላይ ተደርሷል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤የፓርቲዎች የተናጠል ሩጫ መቆም እንዳለበትም ታምኖበታል ብለዋል፡፡

በቀጣዩ ውይይት ላይ ይገኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የየፓርቲዎቹ ተወካዮችም በዚያኑ እለት በአንድነት ለመሥራት የሚያስችል ፍንጭ መገኘቱን መነሻ በማድረግ አንድነት የመፍጠር ግዴታ አለባቸው የሚሉት አቶ ፋንታሁን፤የሚፈጠረው አንድነትም የካቲት 8 በምዕራብ ኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይና በሳውዲ ባሉ ዜጐች ላይ የደረሰውን ጉዳት በማሠብ፣በአዲስ አበባ ታላቅ የተቃውሞ ሠልፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ ፓርቲዎቹ አንድነት ፈጥረው ሠልፉን ማካሄዳቸው ጫና ማሳረፍ የሚችል ተቃውሞ ለማቅረብ እንደሚረዳ ሥራ አስኪያጁ አክለው ገልፀዋል፡፡ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በመኢአድ ጽ/ቤት ለግማሽ ቀን የሚደረገው የፓርቲዎች አንድነት የመፍጠር ውይይት በእውቅ ምሁራንና በማህበሩ ተወካዮች የሚመራ ሲሆን በውይይቱ ላይ ጋዜጠኞች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ተቃዋሚ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች እና ወጣቶች ተወካዮች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ይገኙበታል ተብሏል፡፡ ፓርቲዎች ከበቀል የፀዳች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስረክቡና በአገሪቱ እርቅና መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ የተነሣሁበት ዓላማ ስለሆነ በትጋት እታትራለሁ ብሏል - ማህበሩ፡፡

Read 2949 times