Monday, 03 February 2014 13:31

ዘንድሮ መፈንቅለ መንግስት የሚያሰጋቸው 40 የአለም አገራት ይፋ ተደረጉ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(1 Vote)

ሰላሳ ሁለቱ የአፍሪካ አገራት እንደሚሆኑ ተጠቁሟል
ኢትዮጵያ በ25ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
“ሥራ ፈት የቀባጠረው ከንቱ ሟርት ነው”

አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት ጄይ ኡልፈልደር፣ ላለፉት ሶስት አመታት ፋታ አልነበራቸውም፡፡ እነዚህን ጊዚያት እረፍት በማይሰጥ ጥናት ተጠምደው ነው ያሳለፏቸው፡፡
“በአዲሱ የፈረንጆች አመት በ2014 መፈንቅለ መንግስት ሊደረግባቸው የሚችሉ የአለም አገራት የትኞቹ ናቸው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው፣ የሰውዬው ግብ፡፡ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ አንድም ነቢይነትን አልያም ከፍተኛ ጥናትን ይጠይቃል፡፡
ሰውየው አጥኚ እንጂ ነቢይ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እንደ አጥኚ በቂ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማጤን፣ መተንተን፣ ማወዳደርና ድምዳሜ ላይ መድረስ ግድ ይላል፡፡ እሳቸውም ይሄን አድርጊያለሁ ነው የሚሉት፡፡ እነሆ ከሶስት ተከታታይ አመታት ፋታ አልቦ ጥናት በኋላም፣ አገራትን ያስደነገጠውንና በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ መሆን የያዘውን የጥናት ውጤታቸውን ከሰሞኑ ይፋ አድርገዋል፡፡
“አመቱ ለእናንተ የደግ አይደለም፣ መንግስታችሁ ነቅናቂ ይነሳበታል” የተባሉ አንዳንድ አገራት፣  “ነገርዬው ስራ ፈት ሰው የቀባጠረው ክፉ ሟርት ነው!” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ፖለቲከኛው ኡልፈልደር ግን፣ ነገሩ እንደተባለው ሟርት አለመሆኑንና በሳይንሳዊ መንገድ የተሰራ ሙያዊ ጥናት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ዋሽንግተን ፖስት በያዝነው ሳምንት ለንባብ ያበቃው ዘገባ እንደሚለው፣ ኡልፈልደር በ2014 መፈንቅለ መንግስት ሊካሄድባቸው የሚችሉ አርባ ቀዳሚ አገራትን ዝርዝር ይፋ ያደረጉት፣ በሁሉም የአለም አገራት ሊባል በሚችል ደረጃ የራሳቸውን ሂሳባዊ ቀመር በመጠቀም ጥናት ካደረጉ በኋላ ነው። በጥናቱ ትኩረት ከተሰጣቸውና እንደ መለኪያ ተደርገው ከተወሰዱ ጉዳዮች መካከል፣ በአገራት ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ስርዓቶች አጠቃላይ ይዞታ ቅድሚያ ተሰጥቶታል፡፡
የፖለቲካ ምሁሩ የአገራትን ለመፈንቅለ መንግስት የመጋለጥ እድል ለመተንበይ የተጠቀሙበት ሂሳባዊ ቀመር ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ ከ1960 እስከ 2010 በተለያዩ መንገዶች በሙከራ ደረጃ ሲጠቀሙበትና በጊዜ ሂደት ሲያሻሽሉት እንደቆዩ የዋሽንግተን ፖስቱ ዘጋቢ ማክስ ፊሸር ዘገባ ያስረዳል፡፡
ኦልፈልደር ደረስኩበት (ታይቶኛል?) እንደሚሉት፣ በዚህ አመት የተለያዩ የአለም አገራት መንግስታት ስልጣናቸውን አስገድዶ ሊነጥቃቸው ባሰበ ሃይል የሚቃጣ የመፈንቅለ መንግስት ጣጣ አያጣቸውም፡፡
በበጎ ነገር አይበሏት እንጂ፣ የፈረደባት አፍሪካ ስጋቱ ያይልባቸዋል ተብለው የተለዩ አርባ የአለማችን አገራትን በያዘው በዚህ ዝርዝር ውስጥ አገራቷን በቀዳሚነት ለማሰለፍ አልተሳናትም፡፡ የመፈንቅለ መንግስት አደጋ የመከሰት ከፍተኛ ዕድል(?) አላቸው ተብለው ከተዘረዘሩት 40 የአለማችን አገራት 32 ያህሉ በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ናቸው፡፡
በተያዘው የፈረንጆች አመት የመፈንቅለ መንግስት አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ያሰጋቸዋል ተብሎ የተነገረላቸው፣ በአብዛኛው ከሰሃራ በረሃ በታች ያሉ የምስራቅና የምዕራብ እንዲሁም የመካከለኛው አፍሪካ አገራት ናቸው፡፡ በእነዚህ አገራት ለመፈንቅለ መንግስት መከሰት ምክንያት ይሆናሉ ተብለው ከተዘረዘሩ ጉዳዮች መካከል፣ ውስብስብ የፖለቲካና የጎሳ ግጭት ሰበቦች ይገኙበታል፡፡
በ26 ነጥብ 5 በመቶ የተጋላጭነት ዕድል መሪነቱን የያዘችውን ጊኒ ጨምሮ  ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ኢኳቶሪል ጊኒ፣ ኒጀር፣ ጊኒቢሳኡ፣ ሱዳን፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ ሱዳን እና ታይላንድ በዚህ ጥናት ለመፈንቅለ መንግስት አደጋ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ተብለው የተጠቀሱ ቀዳሚዎቹ አስር አገራት ናቸው፡፡
ከዘጠኙ የአፍሪካ አገራት ለጥቃ ጣልቃ የገባችው ታይላንድ፣ በዚህ አመት መፈንቅለ መንግስት የማስተናገድ ዕድሏ 10 ነጥብ 9 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ የዋሽንግተን ፖስቱ ዘጋቢ ማክስ ፊሸር ግን፣ ታይላንድ መፈንቅለ መንግስትን ደጋግማ በማስተናገድ ከማንኛውም የአለም አገር ጋር አትወዳደርም ባይ ነው፡፡ ይህቺ አገር በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስና በተቃውሞ እየተናጠች እንደመሆኗ፣ የተባለው ነገር አይቀርላትም ይላል ዘጋቢው፡፡
አፍጋኒስታንና ፓኪስታን በየራሳቸው ፖለቲካዊ ምክንያት በዚህ አመት መፈንቅለ መንግስት የማስተናገድ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን የጠቆመው ዘገባው፣ ግብጽም በበኩሏ የአምናውን መፈንቅለ መንግስት ዘንድሮም የመድገም ዕድሏ 9 በመቶ ነው ብሏል፡፡
ሶማሊያ፣ አፍጋኒስታን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ፓኪስታን፣ ሃይቲ፣ ግብጽ፣ ቻድ፣ ኢኳዶር፣ ሞሪታኒያ እና ካሜሮን ደግሞ እስከ 20 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ኢራቅና ኢራን ከመካከለኛው ምስራቅ የዚህ ክፉ ዕጣ ገፈት ቀማሾች እንደሚሆኑ ከተገመቱ ሌሎች አገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
እኒሁ የክፉ ዕጣ አጥኝ፣ የኛዋን አገር ኢትዮጵያን በ25ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጠዋታል፡፡
“እናንተ ዕድለ ቢሶች!... ወንበራችሁን ነቅናቂ ይመጣባችኋልና አመቱ ለእናንተ የደግ አይደለም!” የተባሉ ባለ ክፉ ዕጣ መንግስታት የመኖራቸውን ያህል፣ “እናንተ የታደላችሁ!... ፈንቃይ አይነሳባችሁም!...
ስልጣንም በእጃችሁ ትቆያለችና ስለ ዘንድሮ አትጨነቁ!” የተባሉም አልጠፉም። ከነዚህ መካከል ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የገነቡም ሆኑ በአምባገነንነት የሚታሙ፣ የበለጸጉም ሆኑ ድሃ የአለማችን አገራት ይገኙባቸዋል፡፡
ኡልፈልደር በዚህ አመት የመፈንቅለ መንግስት ስጋት የለባችሁም ካሏቸው መሰል እድለኛ አገራት መካከል፣ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ አንዷ ናት፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ በዚህ አመት የዋይት ሃውስን በር በጉልበት በርግደው ገብተው ስልጣንን በሃይል ለመያዝ የሚኳሹ ፈንቃዮች የመነሳታቸው ዕድል ዜሮ ነጥብ አንድ አምስት በመቶ ነው፡፡
እናት አሜሪካስ ይሁን ግዴለም… ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና የህግ የበላነይት ስላሰፈነች ነገሩ አያሰጋትም ትባል፡፡ በፖለቲካ ቀውስ በመናጥ ላይ የሚገኙ ግሪክና ኩባን የመሳሰሉ አገራት፣ “ስለ መፈንቅለ መንግስት ሃሳብ አይግባችሁ!” መባላቸው ከምን የመነጨ ይሆን?... ጥናቱ እንደሚለው፣ ከአሜሪካ ይልቅ ግሪክ በመፈንቅለ መንግስት የመታመሷ ዕድል የበለጠ ጠባብ ነው - ዜሮ ነጥብ አንድ አራት በመቶ!!
“መፈንቅለ መንግስት ለማንኛውም አገር መጥፎ ዜና ነው፡፡ መፈንቅለ መንግስት የህግ የበላይነትን ያዳክማል፣ መንግስታትን ወደ ቀውስ ይከታል፣ ዲሞክራሲዊ ባህልንና የዲሞክራሲ ተቋማትን ያቀጭጫል ብሎም አንድን አገር ወደከፋ ብጥብጥ፣ ጭቆናና ከዚያም የከፋ ቀውስ ሊያስገባ ይችላል።” በማለት ነው፣ የዋሽንግተን ፖስቱ ዘጋቢ ማክስ ፊሸር  ይህን የመፈንቅለ መንግስት ትንበያ ዘገባ የጀመረው።
እርግጥም የተባለውንና የተጻፈውን የሰሙና ያነበቡ  ብዙዎች፣ ዘገባው መጥፎ ዜና ሆኖባቸው ደንግጠዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከንቱ ሟርት ነው ሲሉ አሽሟጠዋል፡፡
የኡልፈልደር ትንቢት ከንቱ ሟርት ይሆን?... ከመፈንቅለ መንግስት አድራጊ ኃይሎች በቀር ማንም ቢሆን እውን እንዲሆን የሚሻው ትንቢት አይደለም።  
ነገርዬው ጥናት ይሁን ትንቢት ለማረጋገጥ ግን  11 ወራትን በትዕግስት  መጠበቅ ግድ ይላል፡፡



Read 2740 times