Print this page
Monday, 03 February 2014 13:34

በአዲስ አበባ የ“ዳይመንድ ድራማ” ተጧጡፏል!

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(10 votes)

ኔትዎርክ ያቆማል የተባለው የ“ማሾ ዳይመንድ” 4ሚ. ብር ተሸጧል
የዳይመንዱን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡት “የውጭ ኤክስፐርቶች” ናቸው
ባለሃብቶች የሚጭበረበሩት በሚያውቋቸውና  በቅርብ ባልንጀሮቻቸው ነው
በአዲስ አበባ የሚኖሩት አቶ አየለ ጣፋ እና አቶ ጎሽሜ ሁንያንተ የልብ ጓደኛሞች ሲሆኑ ሁለቱም በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ አቶ ጎሽሜ ለበርካታ አመታት በጣሊያን ኖረው ነው ወደ አገራቸው የተመለሱት፡፡ አቶ አየለ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ከውጭ እያስመጡ የሚሸጡ ሲሆን ልጆቻቸውም በስራቸው ያግዟቸዋል፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት አቶ አየለ ሰሚት አካባቢ መኖሪያ ቤት ሲገዙ፣ የልብ ጓደኛቸው አቶ ጐሽሜ አለኝታነታቸውን የገለፁት የ300ሺ ብር ስጦታ በማበርከት ነበር፡፡ ትንሽ ቆይተው ታዲያ ውለታ ጠየቁ - አቶ ጐሽሜ፡፡ በእርግጥ ውለታው ከባድ አልነበረም፡፡ ዘቢደር የተባለች ዘመዳቸው አቶ አየለ ቤት፣ በቤት ሠራተኛነት እንድትቀጠር ነው የፈለጉት፡፡
አቶ አየለም፤ “አንተ ብለህ ነው?” በማለት ዘቢደርን ለሌሎች ሠራተኞቻቸው ከሚከፍሉት ደሞዝ በእጥፍ ቀጠሩላቸው፡፡ 300ሺ ብር በስጦታ ላበረከተ ለጋስ ጓደኛ ይህቺ ምን አላት! አቶ አየለ አንድ ሴራ እየተጐነጐነላቸው መሆኑን ግን አላውቁም፡፡  
የአቶ ጐሽሜ ዘመድ ናት የተባለችው ዘቢደር፣በእንክብካቤ አንድም ነገር ሳይጐድልባት አቶ አየለ ቤት ለአንድ ዓመት ቆየች፡፡ ዋና ተልዕኮዋ የሚጀምረውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡ አጐቴ የምትላቸው አቶ አጐናፍር (ዋና ስማቸው መኮንን ሃብታሙ) ከገጠር “ሊጠይቋት” ይመጣሉ፡፡ አመጣጣቸው ግን ለሌላ ነበር፡፡
በእርግጥ የአጐትየውን አመጣጥ ከአቶ አየለ በቀር ሁሉም ያውቀዋል - ዘቢደርም፣ አቶ ጐሽሜም አጐትየውም፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ የታሰበበትና የተጠናበት ጉዳይ ነውና፡፡ እናም አጐት ዘቢደር ጋ የመጡት ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር በነበራቸው ቅርበት፣ ንጉሱ በስጦታ ያበረከቱላቸውንና ለብዙ ዓመታት አብሯቸው የኖረውን “የማሾ ዳይመንድ” ለመሸጥ ነበር፡፡ እናም ዘቢደር ስለሚሸጠው ዕቃ ለአቶ አየለ ማብራሪያ በመስጠት “እሚፈልግ ካለ ጠይቁለት” ብላ ትነግራቸዋለች፡፡ የማሾውን ዳይመንድ እንዲገዙ የሚፈለጉት ግን ራሳቸው አቶ አየለ ነበሩ - እሳቸው ነገሩ ባይገባቸውም፡፡
በእርግጥም እነ አቶ ጐሽሜ የሸረቡት ሴራ ተሳክቶላቸዋል፡፡ አቶ አየለ ስለማሾው ዳይመንድ የማወቅ ፍላጐት አደረባቸው፡፡ የንብረቱ ባለቤት ናቸው የተባሉትን የዘቢደር አጐትንም አነጋገሩ። እሳቸውም ከንጉሱ እጅ የተቀበሉትንና ለረዥም ዓመት አብሯቸው የኖረውን ዳይመንድ ለመሸጥ የወሰኑት ቤታቸው ላይ በደረሰው የጐርፍ አደጋ ምክንያት እንደሆነ ተናገሩ፡፡ በዚህ መሃል ነው የልብ ወዳጃቸው አቶ ጐሽሜ ገብተው፣ አቶ አየለ ዕቃውን እንዲገዙ የሚፋፉአቸው፡፡ “አንተ ብትገዛው እኔ 6ሚ. ብር የሚገዙ አረቦች አመጣና ትርፉን እንካፈላለን” ይላሉ፤ አቶ ጐሽሜ፡፡ ይኼኔ ልባቸው ለትርፍ የተነሳው አቶ አየለ፣ ዋጋ ይጠይቃሉ፡፡
የዘቢደር አጐትም “ከ4 ሚሊዮን አንድ ብር አልቀንስም” ብለው ይፈጠማሉ፡፡ ይሄን ያህል ለመወደዱ ምክንያቱንም ያስረዳሉ - ለአቶ አየለ፡፡ “የማሾው ዳይመንድ ኔትወርክ ያቆማል፣ሰው የሚያስበውን ተንኮል አስቀድሞ ይጠቁማል፣የፖለቲካ ድርጅቶችና በተለይ ለስብሰባ የሚመጡ ባለስልጣናት አደጋ እንዳይደርስባቸው ስለሚከላከል በቀን እስከ 50 ሺህ ዶላር ይከራያል፣ ሽያጩ ባያዋጣ እንኳን በኪራይ መጠቀም ይቻላል” ይሄን ከሰሙ በኋላ አቶ አየለ ይበልጥ ልባቸው ማለለ፡፡ የማሾውን ዳይመንድ በእጃቸው ለማስገባት ቆረጡ፡፡
ጉዳዩን ለቤተሰባቸው አማከሩ፡፡ ቤተሰቡ ለሁለት ተከፈለ፡፡ ሚስት “ቢቀርብህ ይሻላል” ስትል፣ ልጆች በበኩላቸው “ከፈለግኸው ግዴለም ግዛው” ይሏቸዋል፡፡ አቶ አየለ የልጆቹን ሃሳብ ተቀበሉ። ጊዜ ሳይፈጁ ከቤተሰባቸው 4 ሚ. ብር ያሟሉና የማሾውን ዳይመንድ ሊረከቡ ወደ አቶ ጐሽሜ ዘንድ ይሄዳሉ፡፡ ቀድመው በተነጋገሩት መሰረት፣ ማሾው በትክክል ዳይመንድ መሆኑን ለማረጋገጥ አንድ የሳውዲ የዳይመንድ ኤክስፐርት ጋ ተያይዘው ይሄዳሉ፡፡ ኤክስፐርቱም፤ እዚያው ፊታቸው ድምጽ በሚያሰማ መሳሪያ በመፈተሽ፣ ማሾው 99.9 በመቶ ትክክለኛ ዳይመንድ እንደሆነ  አረጋገጠላቸው፡፡
አቶ አየለ ማሾውን ተረክበው ወደቤታቸው ሲመጡ፣ ለሁለት ዓመት አብራቸው የኖረችው  የቤት ሰራተኛቸው ዘቢደር አልነበረችም፡፡ አባቷ ሞተው ገጠር መውረዷ ተነገራቸው፡፡ እውነቱ ግን ሌላ ነበር፡፡ ዘቢደር ስውር ተልዕኮዋን ስላጠናቀቀች ነው ከአቶ አየለ ቤት ወጥታ እብስ ያለችው፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ አቶ አየለ ወደአቅላቸው ተመለሱ፡፡ የልብ ወዳጃቸው ድምጽ ጠፍቷል። ዳይመንዱን ይገዛሉ የተባሉትን አረቦችም አላመጡላቸውም፡፡ ሲደውሉላቸው ስልካቸው አይነሳም፡፡ እንደውም ወደ ዱባይ መሄዳቸውን ሰሙ፡፡ ለእሳቸው ሳይነግሩ እንኳን ዱባይ የትም ሄደው አያውቁም፡፡ የአቶ አየለ ሚስት ደግሞ ሌላ ወሬ አመጣችላቸው፡፡ አቶ ጐሽሜ በደረቅ ቼክ ማጭበርበር በፖሊስ እየተፈለጉ እንደሆነ ሰሙ፡፡ ይኼኔ ነቁ፡፡  
የቤት ሰራተኛቸው መሰወር ያለነገር እንዳልሆነ ገባቸው፡፡ ጥርጣሬያቸው ሲያይል … “እንዳትከፍተው፤ ኔትወርክ ስለሚያጠፋ መንግስት ይይዝሃል” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር የተሰጣቸውን በብረት ሳጥን የታሸገ የማሾ ዳይመንድ ጉዱን ለማየት ወሰኑ፡፡ ሳጥኑን በድፍረት ከፈቱት፡፡ ግን ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ተራ ብረት ለበስ ማሾ ነው፡፡ 4 ሚ. ብራቸውን እንደተበሉ ገባቸው፡፡ በቤት ሰራተኛቸውና በልብ ወዳጃቸው የተፈፀመባቸውን ማጭበርበም ለፖሊስ አመለከቱ፡፡ አሁን ተጠርጣሪዎቹ ተይዘው በማረምያ ቤት እንደሚገኙ የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል፡፡
አቶ ከፍያለው አንበሴና አቶ አሸናፊ ደሞዜም እንዲሁ ወዳጆች ናቸው፡፡ ሁለቱም በንግድ ስራ ላይ ነው የተሰማሩት፡፡ አቶ አሸናፊ ከወንድማቸው ጋር መኪና ከውጭ እያስመጡ ይሸጣሉ፡፡ አቶ ከፍያለው ሚስታቸውን በሞት ያጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ልጆቻቸውን በሙሉ ውጭ አገር ልከው ብቻቸውን ነው የሚኖሩት፡፡ የወዳጃቸው የብቸኝነት ኑሮ ያሳሰባቸው አቶ አሸናፊ፤ ሚስት እንዲያገቡ በተደጋጋሚ ወትውተዋቸዋል፡፡ የማታ ማታ ግን ከደሴ የገጠር መንደር “ወንድ ያልነካት ልጃገረድ ናት” ብለው ወ/ት ሰናይት ገረመውን ያስመጡላቸዋል፡፡ እውነትም ልጅቱ ድንግል ሆና ተገኘች፡፡ በዚህ ጮቤ የረገጡት አቶ ከፍያለው፤ ውለታቸውን ለመመለስ የ260ሺ ብር ቪትስ መኪና ገዝተው ለጓደኛቸው ያበረክቱላቸዋል፡፡ እቺን ድንግል ሴት ለጓደኛቸው ያመጡት አቶ አሸናፊ ግን ሌላ ስውር ዓላማ ነበራቸው - በዕቅድና በጥናት የተደገፈ፡፡
አቶ ከፍያለው ከአዲሷ ሚስታቸው ልጅ ባይወልዱም ለ2 ዓመት ያህል በሰላም አብረው ኖሩ፡፡ በዚህ መሃል ነው አቶ አሸናፊ ገበሬዎች በጣልያን ወረራ ጊዜ ቆፍረው የቀበሩትን የማሾ ዳይመንድ እንዲገዙ ያግባቧቸው፡፡ እንግሊዞች በ5ሚ. ብር ለመግዛት ጠይቀው ገበሬዎቹ ግን “ለፈረንጅ አንሸጥም” ብለው ለእሳቸው 3 ሚ. ብር ሊሸጡላቸው መስማማታቸውንና 1ሚ ብር ቀብድ ከፍለው መምጣታቸውን ከገለፁላቸው በኋላ ቀሪውን 2 ሚ. ብር እንዲከፍሉ አቶ ከፍያለውን ጠየቋቸው፡፡
አቶ ከፍያለው ማሾውን ለመግዛት ፍላጐት ቢያድርባቸውም፤ ከመወሰናቸው በፊት ግን ሚስታቸውን ማማከር ነበረባቸው፡፡ ለዚሁ ዓላማ ታስባ ከገጠር በሚስትነት የመጣችው ወ/ሮ ሰናይትም “ጓደኛህ ላንተ አስቦ ነው እንጂ ካንተ ተበድሮ ራሱ ሊገዛው ይችል ነበር” በማለት ባለቤቷን አሳመነቻቸው፡፡ አቶ ከፍያለው ከተስማሙ በኋላም አቶ አሸናፊ ገበሬዎቹ የማሾውን ዳይመንድ ከገጠር ይዘው እንዲመጡ አደረጉ፡፡
በእርግጥ ገበሬ የተባሉት ሰዎች እውነተኛ ገበሬዎች አልነበሩም፡፡ ገበሬ መስለው እንዲተውኑ ለዓመት ያህል  ሲለማመዱ የቆዩ የከተማ ሰዎች እንጂ፡፡ በመጨረሻም እቃው አቶ አሸናፊ ባመጡት እንግሊዛዊ ኤክስፐርት፣ በመሳሪያ ተፈትሾ ትክክለኛ ዳይመንድ መሆኑ ተረጋገጠላቸው፡፡ በዚህ የተደሰቱት አቶ ከፍያለው፤ የማሾውን ዳይመንድ ቤታቸው አድርሰው ጓደኛቸው ከፈልኩ ያሉትን 1ሚ. ብርም የዚያኑ ዕለት ይሰጧቸዋል - የባለቤትነት ውዝግብ እንዳይነሳ በመፍራት፡፡
አቶ ከፍያለው ጣጣቸውን ጨርሰው ቤት ሲገቡ ግን ተልእኮዋን የተወጣችው የ2 ዓመት ሚስታቸው አልነበረችም፡፡ እሷ ብቻ ሳትሆን የሟች ባለቤታቸው ውድ ጌጣጌጦችና ንብረቶችም ተወስደዋል፡፡ ይሄኔ በጥርጣሬና ግራ በመጋባት ዋለሉ፡፡ እንደተጭበረበሩ ስለገባቸውም ለፖሊስ አመለከቱ፡፡ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች - አቶ አሸፊና የአቶ አየለ ሚስት (ሠናይት) በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ተናግሯል፡፡
አያት መሐመድ ኑር፤ በአቶ ከማል አብዱራህማን ድርጅት ውስጥ ለሶስት ዓመታት ያህል በፀሐፊነት ስታገለግል ቆይታ ከማታ ትምህርት ጋር አልመቻት ስላለ ነበር ሥራዋን ለመልቀቅ የተገደደችው፡፡ በታማኝነቷ የሚወዷትና የሚያከብሯት አለቃዋ አቶ ከማልም ባዶ እጇን አልሸኟትም፡፡ የወርቅ ሃብልና አስር ሺህ ብር ሰጥተው ምስጋናቸውን ገልፀውላታል፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው ከስምንት ዓመት በፊት ነው፡፡
በቅርቡ ግን ሃያት ወደ ቀድሞ አለቃዋ ቢሮ ጐራ ብላ ነበር፡፡ 8ሚ.ብር የሚገመት ትልቅ ጉዳይ ይዛ፡፡ የወንድሟ ሚስት አባት ከመሞታቸው በፊት ለእሳቸው የ150 ሚ.ብር ጥሬ ገንዘብ ያስገኘላቸው እና ግቢያቸው ውስጥ የቀበሩትን ሜርኩሪ እንደተናዘዙላቸው ለቀድሞ አለቃዋ የገለፀችው ሃያት፤ ይሄን ሜርኩሪ አቶ ከድር እንዲገዙ ታግባባቸዋለች፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት ከፈለጉም ዱባይ ያለው ወንድሟ እድሪስ መሐመድ ጋ ደውለው ማረጋገጥ እንደሚችሉ ነግራ፣ ቁጥር ትታላቸው ትሄዳለች፡፡
አቶ ከማል እንደተባሉት ያደርጋሉ። በስልኩ ብቻ ግን አልበቃቸውም፡፡ ብድግ ብለው ዱባይ ይሄዳሉ፤ እድሪስን ለማግኘት፡፡ ግን አልተሳካላቸውም፡፡ የአረብ ሃብታሞችን ይዞ ሜርኩሪ ለመግዛት ወደ ኢትዮጵያ ሄዷል ይባላሉ፡፡ በመጨረሻም ወደ አገራቸው ተመልሰው ከእድሪስና ከአረቦቹ ጋር አዲስ አበባ ላይ ይገናኛሉ፡፡ እድሪስም “አረቦቹ ሜርኩሪውን 12 ሚሊዮን ብር እንገዛለን ብለዋል፤ አንተ በ8 ሚሊዮን ግዛውና ሽጥላቸው፤ 4 ሚሊዮኑን ለሁለት እንካፈለዋለን” ይላቸዋል። አቶ ከማል ዓይናቸውን ሳያሹ ገንዘቡን በቼክና በካሽ ከፍለው “የሃብት ምንጭ” ይሆነኛል ያሉትን  ሜርኩሪ ይረከባሉ፡፡  
እቤት ደርሰው ሜርኩሪውን መሬት አስቆፍረው ሊቀብሩት ሲሉ ግን አንዱ ጠርሙስ አምልጦ ይወድቅና ይሰበራል፡፡ አቶ ከማል ሜርኩሪውን ሲገዙ “ብልቃጡ ከተሰበረ አፈሩን እንደሚያቃጥለውና መሬቱ እንደሚጐደጉድ” ተነግሯቸው ነበር፡፡ ሆኖም ብልቃጡ ሲሰበር የሚያብረቀርቅ ቀለም ያለው ፈሳሽ ከመውጣት በቀር ምንም ተአምር አልተፈጠረም። ተጠራጥረው እድሪስን በስልክ ለማግኘት ቢሞክሩ አልተሳካም። የድሮ ፀሃፊያቸው አያትም አልተገኘችም፡፡ ይሄኔ ነው መጭበርበራቸውን ተረድተው ለፖሊስ ያመለከቱት፡፡ ተጠርጣሪዎቹ አሉ ከተባለበት ዱባይ በኢንተርፖል በኩል ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከፖሊስ መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡  


 

Read 11429 times