Monday, 03 February 2014 13:53

ለገጣሚ ሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) ጥያቄ፤ አቤ ጉበኛ የሰጠው መልስ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ባለፋት አምስት ዓመታት ሦስት የግጥም መጻሕፍትን አሳትሟል - “እውነትን ስቀሏት” በ2001 ዓ.ም፣ “ከፀሐይ በታች”

በ2004 ዓ.ም እና  “ጽሞና እና ጩኸት” በያዝነው ዓመት፡፡  ሦስተኛው መጽሐፉ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በጣይቱ

ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ በተመረቀበት ወቅት በመድበሉ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት፣ መምህርና ሐያሲ አስቻለው ከበደ

በማጠቃለያቸው ላይ፤ ሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል)፤ ተስፋ የሚጣልበት ገጣሚ ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ግጥሞቻቸውን በመጽሐፍ ሰንደው የሚያቀርቡ ገጣሚያን በአብዛኛው “የእኔ ነው” የሚሉትን አሻራ ለመተው ሲታትሩ

ይታያሉ በአንድ ርዕስ ስር ተዘጋጅተው የተለያዩ ክፍሎች የተሰጣቸውን ግጥሞችን በማቅረብ፣ ግጥሞቹን ርዕስ አልባ

በማድረግ፣ ስንኞቹን በተለያየ ቅርጽ በመሰደር እንዲሁም አዲስ ይዘት፣ ቅርጽና ሃሣብ በማስተዋወቅ። ሎሬት ፀጋዬ

ገብረመድህን በ1966 ዓ.ም ባሳተመው “እሳት ወይ አበባ” የግጥም መጽሐፉ መግቢያ “…. አንዳንድ መምህራን የዚህን

ድንጋጌ ዘይቤ (ስታይል) ስም ስላላገኙለትና እኔም ስላልሰየምኩለት “የፀጋዬ ቤት” ይሉታል” ብሏል፤ ለየት ስላለ

የአገጣጠም ስታይሉ ሲገልጽ፡፡
ገጣሚያኑ በቅርጽና ይዘት ላይ አዳዲስ ነገሮችን “ለመፍጠር” የሚነሽጣቸውና የሚያተጋቸው ገጣሚነት የሚሰጣቸው

“ነጻነት” (Poetic Licesence እንዲሉ) እንደሆነ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ “ጽሞና እና ጩኸት”

በተሰኘው ሦስተኛው የሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) የግጥም መድበል፤ “በግጥም እንስከር” የሚለው  ግጥሙ ሲያበቃ በግርጌ  

ማስታወሻው ላይ ግጥሙ ቤት የማይመታ እንደሆነ ጠቁሞ ማብራሪያ ያቀርባል፡-
“ቤት ሰበር ግጥሞች አንዱ የግጥም ዘርፍ እንዲሆኑና ይህ አዲስ የግጥም መልክ በወጣት ገጣሚዎች ይበልጥ እንዲዳብር

በመመኘት፣ እንደ መነሻ በገጽ 45፣51፣56 እና 64 ያሉ ቤት ሰበር ግጥሞችን አቀርቤያለሁ፡፡ ቤት ሰበር ግጥሞች ቤት

አይምቱ እንጂ ዜማ ያላቸው፣ ምጣኔያቸውን የጠበቁና ቤት ከመምታት ውጪ የተቀሩትን የግጥም ባሕሪያት ሁሉ

የሚያሟሉ ናቸው፡፡ በከፊል ቤት የሚመታ ግን በከፊል ቤት የሚሰብር ግጥም ደግሞ ከፊል ሰበር ግጥም ልንለው

እንችላለን፡፡ ቤት አለመምታት (ቤት መስበር) አንዱ የግጥም ባህሪ ሆኖ ቢተዋወቅስ?”
ለግጥም ማስተማሪያነት የሚያገለግሉ ወይም ስለ ግጥምና ቅኔ ምንነት በማጣቀሻነት ሊቀርቡ የሚችሉ መጻሕፍትን

ያዘጋጁ ጥቂት የማይባሉ ደራሲያን አሉ። የዘሪሁን አስፋው “የሥነ ጽሁፍ መሠረታዊያን”፣ የብርሃኑ ገበየሁ “የአማርኛ ሥነ

ግጥም”፣ የአለማየሁ ሞገስ “የአማርኛ ግጥምና ዜማ ማስተማሪያ”፣ የአቤ ጉበኛ “መስኮት”፣ የፍቅረድንግል በየነ “ሰምና

ወርቅ ሰዋሰው”፣ የአስፋው ተፈራ “ፀጋዬ“፣ የታደለ ገድሌ  “ትንቅንቅ” … መጻሕፍት ይጠቀሳሉ፡፡
ገጣሚ ሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) “ቤት አለመምታት ወይም ቤት መስበር አንዱ የግጥም ባሕሪ ሆኖ ቢተዋወቅስ?” በሚል  

በአማርኛ ግጥም አጻጻፍ ላይ አዲስ ነገር ለማከል ላሳየው ጉጉነት፣ ደራሲ አቤ ጉበኛ ከ42 ዓመታት በፊት መልስ

ሰጥቶበታል፡፡ ደራሲው “መስኮት” በሚል ርዕስ በ1964 ዓ.ም  ባሳተመው የመጀመሪያ የግጥም መጽሐፉ መግቢያ ላይ፣

ቤት የማይመታ ወይም የሚሰብር አገጣጠም ቀደም ብሎ የሚታወቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡
“ቤት የማይመቱ ሁለት ግጥሞች በዚህ መጽሐፌ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነሱም በእንግሊዝኛ (ብላንክ ቨርስ) በሚባለው

የግጥም ዓይነት የሚታዩ ሲሆን፣ በሀገራችንም ይህ የግጥም ዓይነት እንግዳ አለመሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ቤት የማይመታ

ግጥም በሀገራችን በጣም የታወቀና የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ከውጪ ቋንቋ ከተተረጐሙ መጻሕፍት መካከል እንደ

መዝሙረ ዳዊት፣ መኀልየ ሰለሞን ያሉት ቤት በማይመታ ግጥም የተጻፉ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥ ከተደረሱት አብዛኞቹ

የያሬድ ቅኔዎች ቤት የላቸውም፡፡”
በመጽሐፌ ቤት የማይመቱ ወይም የሚሰብሩ ግጥሞችን ያቀረብኩት አዲስ ነገር ፈጥሬያለሁ ለማለት ሳይሆን የአሠራር

ልማዱ እንዳለ ለማሳየት ነው የሚለው አቤ ጉበኛ፤ አንድ ቃል አንድ ቤት እንድትመታ የሚደረግበት አጭር የግጥም

መንገድ እንኳ አዲስ አለመሆኗን ማወቅ ጠቃሚ ነው ብሎ የሚከተለውን የሆታ ግጥም በማሳያነት አቀርቧል፡-
በወጨፎ፤
ፈጀው ጠልፎ፤
በውጅግራ፤
ተካው ጅግራ፤
በናስ ማሰር፤
ፈጀው ነስር
“ዕውቀት ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍና የሚወራረስ በመሆኑ የፋርሳዊው ገጣሚ የኦማር ኻያምን አገጣጠም በአማርኛ

የግጥም ሥራዎቼ ለመጠቀም ሞክሬያለው፤ በአማርኛ ቋንቋ ግጥም የመጻፊያ መንገዶቻችን በጣም ብዙ ስለሆኑ ከሌላው

መዋስ የሚያስመኘን አይደለም፡፡ በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ያለው የአገጣጠም ስልት ቢጠና

ተጨማሪ ስልቶችም ሊገኙ ይችላሉ” ይላል፡፡
በአማርኛ ቋንቋ የግጥም አጻጻፍ ስልት ውስጥ ቤት የማይመቱ የአገጣጠም ዘዴዎች በብዛት እንዳሉ ሲያብራራ፤ በዝርው

ጽሁፍና ለዚያም ማሳያ ግጥሞችን ያቀረው አቤ ጉበኛ፤ ይህንን ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት “ፈረንጆች ከሚሉት ውጭ

በአገራችን ዕውቀት ያለ ለማይመስላቸው ሰዎች” ምላሽ ለመስጠት መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የሀዘንና የለቅሶ ግጥሞች እንዴት እንደሚጻፉ፣ ገጸ ባህሪ ያለውና የሌለው ግጥም አዘገጃጀት፣ ስለፉከራና ሽለላ አጻጻፍ፣

ስለ በገናና የሆታ ግጥም ምንነት፣ ስለ የእንካ ሰላንታያ ግጥም አገጣጠም፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ የ“ምሕላ”

ግጥሞች ምንነት፣ ስለ አዝናኝና አስደሳች ግጥሞች፣ ስለ ቅኔ አጻጻፍና የምክር ግጥሞች … ማብራሪያና ምሳሌዎችን

ጠቅሷል፡፡ ቤት ለማይመታ ወይም ለሚሰብር ግጥም “የቅን ሰው መዝሙር” የተሰኘ ግጥሙን በማሳያነት አቅርቧል፡፡
እጅግ ይገርመኛል እጅግ ይደንቀኛል፤
ነገሩን ሳስበው ቁሜ ተቀምጨ፡፡
አንዳንድ ግራ ሰዎች ሲጠሉኝ ሳያቸው፤
ምርር አርገው ከልብ ምንም ሳልነካቸው፤
እንዲሁ በዓለም ላይ በመኖሬ ብቻ፤
ምናልባት ምናልባት ይሆን ቆጭቷቸው፤
ዓየርን ፀሐይን በተካፈልኳቸው?
አንድ ቀን ሳላስብ በማንም ላይ ክፉ፤
ለመጉዳት ሃሣብም መንገድም ሳይኖረኝ፤
እንዲህ ያሉ ፀሮች ለማፍራት የቻልሁ፤
በሰው ክፉ አስቤ ክፉ ብፈጽም፤
ዕድል ባሰናክል ባበላሽ ጥቅም፤
ለንብረት ለሕይወት ጠላት ብሆን ኑሮ፤
ኸረ ጠላቶቼ ስንት ሊሆኑ ነበር?
ግን ጠላት ከማፍራት ግን ጠላት ከማብቀል፤
ቅንነት ይበልጣል ከክፋት ይልቅ፤
ይታገላል እንጂ ሊያሳስት ሰውን፤
ይፈታተናል ወይ ሰይጣንን ሰይጣን፣
መልአክና ሰይጣን ጓድ ይሆናሉ ወይ?
እኔ አለሁኝ እንጂ ለማንም ሰው ክፉ፤
ግድ አለኝ ጠማሞች በከንቱ ቢለፉ?
ሰሎሞን ሞገስ(ፋሲል) በ”ጽሞና እና ጩኸት” የግጥም መጽሐፉ፣ ቤት አለመምታት አንዱ የግጥም ባህሪ ሆኖ

ቢተዋወቅስ? በሚል ላቀረበው ጥያቄ ከ42 ዓመታት በፊት አቤ ጉበኛ “መስኮት” በሚል የግጥም መጽሐፉ ከላይ

በቀረበው መልኩ ማብራራቱን ለማስታወስ ያህል ነው፡፡ መምህርና ሐያሲ አስቻለው ከበደ እንደመሰከሩለት፤ ሰሎሞን

ሞገስ (ፋሲል) ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት ገጣሚያን አንዱ እንደሆነ በሦስቱ መጻሕፍቱ ባቀረባቸው ግጥሞች ብቃቱን

አሳይቷል፡፡ ግጥምና አገጣጠምን ለማሳደግ አዲስ ሃሣብና መንገድ ለመፍጠር ሲያስብ ግን የተመኘው ነገር ቀድሞ

ያልነበረ መሆኑን መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡


Read 6284 times