Print this page
Monday, 03 February 2014 14:02

“...ክፍተቱን ማጥበብ ትልቅ ነገር ነው...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(1 Vote)

“...ክፍተቱን ማጥበብ ትልቅ ነገር ነው...”
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር (WATCH) ዋች ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅትና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሚወለዱ ጨቅላ ሕጻናትና እናቶች ዙሪያ አፋጣኝና መሰረታዊ የሆኑ ሕክምናዎችን ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና በተለያዩ መስተዳድር አካላት ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ስልጠና አስቀድሞ በየመስ ተዳድር አካላቱ የሚገኙ የዞን ...የወረዳ... አካላት እና  ሌሎች መሰል ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት የሚሰሩ አባላትን ስለጉዳዩ በቂ እውቀት እንዲያገኙ ከጤና ባለሙያዎቹ አስቀድሞ ስልጠና ሰጥቶአል፡፡ ከስልጠናው በሁዋላ ያለው የስራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? በሚል በደቡብ ብሔር ብሔረ ሰቦች ሐዋሳ ዙሪያ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ ለዚህ እትም ንባብ እነሆ ብለናል፡፡
...አንድ አባት ከመኪና ውስጥ አጠገቤ ተቀምጠዋል። በምናልፍበት አካባቢ ከርቀት አንድ ጤና ጣብያ ተመለከትን፡፡ የምንመለከተው ጤና ጣቢያ ማን ይባላል? አልኩና ጠየቅ ሁዋቸው፡፡ እሳቸውም እኔም ለአገሩ እንግዳ ስለሆንኩ አላውቀውም የሚል ነበር መል ሳቸው፡፡ ቀጠል አድርገውም ...ምን...ጤና ጣብያ በየቦታው ተሰርቶ እያለ ነገር ግን ተጠ ቃሚው በተለይም እናቶች እምብዛም ናቸው... ብዙዎቹ የሚወልዱትም በቤታቸው ነው ...አሉኝ፡፡ ለምንድነው ብዬ ስጠይቅ ...ይህንን እኔም አላውቅም...እራሳቸውን ብታገኝ ያቸው እና ብትጠይቂ ጥሩ ነው አሉኝ ...እና ተለያየን፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሄረሰቦች ዘንድ የተለያዩ ጎጂና ጎጂ ያልሆኑ ልማዳዊ ድርጊች እንደነበሩ እና አልፎ አልፎም አሁንም እንደሚፈጸሙ እሙን ነው፡፡ አንዲት የሲዳማ ሴት እንዳወጋችን ከሆነ...
“...በደቡብ ሲዳማ አካባቢ ሐሜሳ የሚባል ከእንጨት መሰል የባህል መድሀኒት የሚሰራ መጠጥ አለ፡፡ አንድ ሕጻን ሲወለድ በሳምንት እድሜ ውስጥ ሐሜሳ እንዲጠጣ ይደረ ጋል፡፡ ይህ መጠጥ ሕጻኑን ማንኛውም አይነት ሕመም ወደፊትም እንዳይገጥመው መከ ላል የሚችል ተደርጎ የሚታሰብ ነው፡፡ ማንኛዋም እናት ልጅዋን ገና ሲወለድ ካላጠጣች ልጅዋ ጎበዝ እንደማይሆን ወደፊትም ታማሚ እንደሚሆን ስለሚገመት ለዚህ ሲባል በቤት ውስጥ መውለድን የሚመርጡ ብዙ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ግን በጤና ጣቢያ ያሉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ትምህርት የሚሰጡ ስለሆነ እየቀረ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን አሁንም ይህንን የሚጠቀሙ ይኖራሉ...” ብላለች፡፡
ገ/ክርስቶስ ጤና ጣብያ ከሐዋሳ 29 ኪ/ሜትር ይርቃል። ጤና ጣብያው በባለሙያዎች የተሟላ ይመስላል። እንደማንኛውም ጤና ጣብያ የተደራጀ ነው፡፡ እስከ አምስት ሰአት ድረስ በነበረን ቆይታ ግን ለህክምና የመጣች እናት አላጋጠመንም፡፡ ከዚያም በመቀጠል ያመራነው ወደ ሞርቻ ነጋሻ ነው፡፡ በጤና ጣቢያው ስንደርስ ብዙ ታካሚዎች ይስተናገዱ ነበር፡፡ በሞርቻ ነጋሻ ያለው አሰራር ምን ይመስላል ስንል ሲ/ር የኔነሽን አነጋግረናል  ሲ/ር የኔነሽ በማዋለድ ስራ ላይ የተሰማራች ነች ፡፡
ጥ/    ምን ያህል እናቶች በጤና ጣብያው ይስተናገዳሉ?
መ/    ብዙ ወላዶች ወደ ጤና ጣብያው ይመጣሉ፡፡ አሁን በቅርቡ ማለትም በስድስት ወር ውስጥ ወደ 156/አንድ መቶ ሀምሳ ስድስት ያህል እናቶችን አዋልደናል፡፡ ለሌሎችም ክትትሎች እናቶች በብዛት ይመጣሉ፡፡ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትንም በስፋት እንሰጣለን፡፡ እናቶች የሚመጡት ከከተማው ሳይሆን እንዲያውም ከገጠር ነው፡፡
ጥ/    ህብረተሰቡ በጤና ተቋሙ እንዲገለገል የዘረጋችሁት አሰራር አለ?
መ/    እኛ በአብዛኛው ህብረተሰቡ እስኪመጣ መጠበቅ ሳይሆን ወደህብረተሰቡ እየሄድን እንሰራለን። ሁልጊዜ በጤናኬላዎች አንዳንድ ባለሙያ ይመደባል። ከዚያም ህብረተሰቡ መካከል በመግባት እናቶች በጤና ተቋም መገልገል ምን እንደሚጠቅማቸው እና ባይገለገሉ ግን ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር እንገልጽላቸዋለን። በሰለጠነ ሰው መውለድ ምን ጥቅም እንዳለው እያስተማርንም እንቀሰቅሳለን፡፡ በአካባቢው ያሉ እርጉዝ እናቶች ወደጤና ኬላ እንዲመጡና የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ እንመክራለን፡፡ ከዚያም የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ ወደጤና ጣብያ እንዲመጡ ምክር እንሰጣለን። የጤና ኤክስ..ንሽን ሰራተኛዋ አንዲትን እርጉዝ ሴት ቤት ለቤት ተከታትላ ወደ ጤና ጣብያ እንድትመጣ ታደርጋለች፡፡
ጥ/     ይህ አሰራር ምን ያህል የተቀናጀ ነው?
መ/    ይህ አሰራር በምንም ምክንያት የማይቋረጥ ተከታታይ የሆነ ስራ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጤና ጣብያችን ብዙ እናቶች እየወለዱ የሚገኙት፡፡ በእርግጥ የከተማው እናቶች ወደለኩ ሆስፒታል ቢሄዱም የገጠሩ እናቶች ግን ጥቅሙን አውቀው ወደ ሞርቻነጋሻ ጤና ጣብያ እየመጡ ነው፡፡
ጥ/    የእርግዝና ክትትል ካደረጉ በሁዋላ በቤታቸው የሚወልዱ አሉ?
መ/    አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር በብዛት በጤና ጣብያ እንዲወልዱ የምክር አገልግሎት እየሰጠን ስለሆነ ከቤታቸው ለመውለድ አይቀሩም፡፡
ጥ/    ጤና ጣብያው የማዋለድ አቅሙ እስከምን ድረስ ነው?
መ/    በእርግጥ በእጃችን ካለው የማዋለጃ መሳሪያ እና ከእኛ እውቀት በላይ ካልሆነ በስተቀር ብዙዎችን እኛ እናዋልዳለን፡፡ እንደ ደም መፍሰስ...ኢክላምፕሲያ...በመሳሰሉት ምክንያቶች ግን መድሀኒትም ለጊዜው ስላልነበረን ወደለኩ ሆስፒታል ሪፈር ብለናል፡፡ ወደፊትም አንዳንድ ያልተሟሉ ነገሮች ካልገጠሙን በስተቀር እኛ የምንችለውን እናዋልዳለን፡፡
ለእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት ተገቢውን የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስልጠና  ከወሰዱት መካከል በገ/ክርስቶስ ጤና ጣቢያ ያገኘነው ሰንበቶ ሳሰሞ ይገኝበታል፡፡ ሰንበቶ ለእናቶች ስለሚሰጠው አገልግሎት የሚከተለውን ብሎአል፡፡
ጥ/    ከስልጠና በሁዋላ የማዋለድ ተግባርህ ምን ያህል አድጎአል?
“...አንዲት እናት ሕይወት ለመስጠት ስትል ሕይወቷን ማጣት የለባትም በሚለው መሰረት እናቶች ለወሊድ አገልግሎት በሚመጡበት ጊዜ አስፈላጊውን ሙያዊ እርዳታ እሰጣለሁ፡፡   ከአሁን ቀደም ከስልጠናው አስቀድሞ በነበረኝ ልምድ ብዙውን ነገር ወደሌላ የህክምና ተቋም አስተላልፋለሁ እንጂ በድፍረት እራሴ አላዋልድም ነበር፡፡ ነገር ግን ለ18/አስራ ስምንት ቀን ያህል በተሰጠን ስልጠናና ተግባራዊ ልምምድ ምክንያት አሁን ብዙዎችን ሴቶች እኔ እራሴ እያዋለድኩኝ እገኛለሁ፡፡ እስከአሁን በስራዬ የገጠመኝ... አንዲት እናት በጣም የተራዘመ ምጥ ላይ ስለነበረች ወደለኩ ሆስፒታል ተልካ በቀዶ ሕክምና እንድትገላገል አድርገናል፡፡ እንደዚሁም ሌላዋ እናት ብዙ የወለደች ስለነበረች እና የተሻለ የህክምና እርዳታ ልታገኝ ስለሚገባት እሱዋንም ወደለኩ ሆስፒታል ሪፈር አድርገናታል፡፡ እንዲሁም የደም መፍሰስ ሲያጋጥምም ወደሆስፒታሉ እንልካለን፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ከስልጠናው በፊት ሪፈር የምናደርገውን ሁሉ አብዛኛውን በዚሁ አገል ግሎቱን መስጠት ችለናል፡፡
ጥ/    ከጤና ባለሙያዎቹ ስልጠና አስቀድሞ የሰለጠኑ የኃላፊዎች ድጋፍ ምን ይመስላል?
መ/    በዞን ወይንም በወረዳ እንዲሁም በሆስፒታል አካባቢ የሚገኙ ኃላፊዎች ምላሽ በጣም ጥሩ ነው፡፡ለሕክምናው አገልግሎት የሚያስፈልጉ ማንኛቸውንም ነገሮች በተጠየቁ ጊዜ ምላሻቸው አይዘገይም፡፡ ለስልጠናውም ተገቢውን ሰው በመላክ እንዲሰለጥን በማድረ ጋቸው ስራው በትክክል እንዲሰራ እገዛ አድርጎአል፡፡ እነዚህ ኃላፊዎች የእናቶ ችንና የኅጻናቱን ጤንነት ለመጠበቅ ያስፈልጋል የሚባሉትን ነገሮች ልክ እንደእኛ /ማለትም በስራው ላይ በቀጥታ እንዳለነው ሰዎች የሚገነዘቡ ስለሆነ አቅም የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ወደሁዋላ አይሉም፡፡ ስለዚህ ስልጠናው ለእኛ ብቻ አለመሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። እነዚህ የበላይ አለቆች ማን ...በምን እንደሰለጠነ ወይንም ለምን እንደሰለጠነ ስለሚያውቁ እና እንዲሁም የእናቶች እና የጨቅላ ሕጻናት ጉዳይ የአገር ወይንም የአለም አቀፍ ጉዳይ በመሆኑ ስልጠናው እኛን ብቻ ሳይሆን እነርሱም በትክክል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ረድቶአቸዋል ብዬ አምናለሁ። ባጠቃላይም በስራው ላይ በቀጥታ የተሰማራነውም ሆንን በኃላፊነት ቦታ ያሉት ሰዎች በመሰልጠናቸው የታለመውን እቅድ ከግቡ ለማድረስ ረድቶአል የሚል እምነት አለ።    
ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር እና በሐዋሳ ሆስፒታል የጽንስናማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እንዳብራሩት ለኃላፊዎቹ የተሰጠው ስልጠና አላማ በየጤና ጣብያው ላሉ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ምንን የሚመለከት እንደሆነ አስቀድመው እንዲያውቁ ለማድረግ ነበር፡፡
በስልጠናው የተካተቱት ኃላፊዎች የሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተሮችን ጨምሮ የጤና ጣብያ ኃላፊዎች፣ በዞን ጤና መምሪያ እና በወረዳ ያሉ ኃላፊዎችን የሚመለከት ነበር፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ ስልጠና የእናቶችንና የጨቅላ ህጻናቱን ሞት ለመቀነስ እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ማበረታታትን የሚመለከት ሲሆን ኃላፊዎችም ሁኔታውን እንዲያግዙና እንዲከታተሉ የሚያስ ችል ስልጠና ተሰጥቶአል፡፡  
እንደ ዶ/ር ይፍሩ እምነት የእናቶችንና የጨቅላ ሕጻናቱን ሞት መቀነስ የሚቻለው ግን የጤና ባለሙያዎቹ በጤና ተቋም ቁጭ ብለው በመጠበቅ አይደለም፡፡ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ለማድረግ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተ ኞች አማካኝነት ወደህብረተሰቡ ወርዶ ክፍተቱን ማጥበብ ትልቅ ነገር ነው፡፡
አሁን አልፎ አልፎ የሚታየው ክፍተት ችግሩ ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና ጤና ባለሙያዎቹ ያለመገናኘታ ቸው ሲሆን የዚህም ውጤቱ እናቶች ወደጤና ተቋም በመሄድ የወሊድ አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት ለጤና ባለሙያዎቹ ስልጠና መስጠቱ ብቻ በቂ ስለ ማይሆን ስራውን  የሚመለከተው ሁሉ በትብብር ህብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማስተ ማርን የምክር አገልግሎት መስጠት ጭምር የሚያስፈልግ በመሆኑ የብዙ ተቋማትንም ትብብር የሚጠይቅ ነው...” ብለዋል፡፡

Read 2033 times