Print this page
Monday, 03 February 2014 14:06

ሼር ኢትዮጵያና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቱ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

13 ሺ ሠራተኞች ያስተዳድራል
ዘመናዊ ሆስፒታል፣ ት/ቤት፣ ስታዲየም፣ ፍ/ቤት ሠርቷል
ተባይን በአርተፊሻል ተባይ ያጠፋል
ባለቤቱ ለሕዳሴው ግድብ 25 ሚ.ብር ሰጥተዋል
ለአየር መንገድ በሳምንት 12 ሚ.ብር ይከፍላል

በኬንያ ትልቅ የአበባ እርሻ ነበራቸው። እንደቀድሞው አይሁን እንጂ አሁንም አለ፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የጋበዟቸው በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚ/ር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ናቸው፡፡ ግብዣውን ከመቀበላቸው በፊት ግን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንዳለ አስጠኑ፡፡ ፍጹም ምቹ ባይሆንም መሥራት የሚያስችል ሆኖ አገኙት፡፡ ከዚያ በ1997 ዓ.ም በምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን፣ በቱሉ ዲምቱ ወረዳ፣ በዝዋይ ከተማ በ500 ሄክታር መሬት ላይ በኢትዮጵያ ትልቁን የአበባ እርሻ በ80 ሚ.ዩሮ መሠረቱ - ሆላንዳዊው ሚ/ር ገረት ባርንሆርንና (Berrit Barnoorn) ልጃቸው ሚ/ር ፒተር ባርንሁርን፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው አበባ 65 በመቶው የዚህ እርሻ ምርት ነው፡፡ 13 ሺህ ሠራተኞች ያሉት ድርጅቱ፤40 የአበባ ዓይነት ያመርታል፡፡ ምርቱን በሙሉ የሚያቀርበው ለውጭ ገበያ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 95 በመቶውን የሚያቀርበው የአበባ ዋጋ ቢወደድም ሆነ ቢረክስ፣ በተወሰነ ዋጋ ለማቅረብ ለተስማማቸው ሱፐርማርኬቶችና ሱቆች ነው፡፡ 5 በመቶውን ብቻ ነው በጨረታ የሚሸጠው፤ ሼር ኢትዮጵያ፡፡

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር (አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ) አምራች ላኪዎች ማህበር፣ የአባሎቹን እርሻ እንድንጐበኝ በጋበዝን መሠረት፣ ጥቂቶቹን የአበባ እርሻዎች አይተናል፡፡ ለዛሬ ግን ሼር ኢትዮጵያ የአባባቢን ደህንነት ለመጠበቅና ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት እናያለን፡፡ ሼር ኢትዮጵያ ምርቱን ወደ አውሮፓ ለሚያጓጉዝለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየሳምንቱ 12 ሚሊዮን ብር እንደሚከፍል፣ የእርሻው ባለቤት ሚ/ር ገረት ባርንሆርን (በግላቸው) ለታላቁ ህዳሴ ግድብ 25 ሚሊዮን ብር መለገሳቸውንና ድርጅቱ ከቀድሞው ጠ/ሚ የኘላቲንየም ዋንጫ መሸለሙን የድርጅቱ ሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አቶ ከማል ሁሴን ገልጸዋል፡፡ አሁን በጉብኝቱ ወቅት የታዘብኩትንና አቶ ከማል የነገሩንን ላጫውታችሁ፡፡ ሼር ካሉት 96 ግሪን ሀውሶች (የአበባ ማብቀያ ዳሶች) ወደ አንዱ ስንገባ፣ አቶ ከማል “ድሮ ቢሆን የኬሚካሉ ሽታ አያስገባችሁም ነበር፤ አሁን ግን ይኸው እንደምታዩት ምንም የለም” አሉ፡፡ የምን ኬሚካል? በማለት ጠየቅን፡፡ “አበባውን የሚያጠቁትን ተባዮች ለመከላከል ኬሚካል እንጠቀም ነበር፡፡

አሁን ግን ኬሚካል የምንጠቀመው ለፈንገስ ብቻ ነው፡፡ አበባ የሚያጠቁ ጀርሞችን ለማጥፋት የምንጠቀመው የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እውቅና በሰጠው Integrated pest management control system Imps በተባለ ዘመናዊ ሰው ሠራሽ ዘዴ (አርቴፊሻል ጀርም) ነው፡፡ “ቅደም እዚያ ጋ ያያችኋት ልጅ እስካውት ትባላለች፡፡ የእሷ ሥራ፣ የአበቦቹን ቅጠሎች በሚያጐላ መነፅር (ማይክሮስኮፕ) እያየች ጀርም መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ ጀርም ካየች እዚያ ቦታ ላይ ነጭ ወረቀት ታስቀምጣለች፡፡ ‘እዚህ ቦታ አበባ የሚጠቃ ጀርም አለ’ ማለቷ ነው፡፡ ጀርሞችን ለማጥፋት የተመደቡ ሰዎች ደግሞ፣ አርቴፊሻል ጀርም ፈጣሪውን ዱቄት ነገር ያደርጉበታል፡፡ አርቴፊሻል ጀርሙ ይፈጠርና አበባ አጥቂዎቹን ጀርሞች እያሳደደ ከእነዕንቁላላቸውና ዕጫቸው ይበላቸዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች አርቴፊሻል ጀርሙስ በአባባቢ ላይ ጉዳት አይፈጥርም ወይ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን ምንም ጉዳት አይፈጥርም፡፡ ምክንያቱም እውነተኛው ጀርም ከሌለ አርቲፊሻሉ የሚበላው ነገር ስለሌለው ይሞታል” በማለት አስረድተዋል፡፡ በተንጣለለው የሼር ኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ ብቻውን አይደለም ያለው፡፡ ከሼር ውጭ የራሳቸው አስተደደር ያላቸው ዝዋይ ሮዝ፣ ኤክው፣ አርበርና ኘራም የተባሉ አበባ አምራች ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ራሳቸውን የቻሉ ድርጅቶች ቢሆኑም በሼር ስር ናቸው፡፡ ሼር 13 ሺ ሠራተኞች አሉት ሲባል የአራቱን ድርጅቶች ሠራተኞች ጨምሮ ነው፡፡ አፍሪ ፍሎራ / Afri flora / የሚለው ስም ከሼር ኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ ስላየን ምንድን ነው? ብለን ጠየቅን፡፡ የሼር ኢትዮጵያን የአበባ ምርት በመላው ዓለም የሚሸጥና የድርጅቱ የንግድ ምልክት መሆኑን አቶ ከማል ነገሩን፡፡

ይህ ብቻ አይደለም። አፍሪ ፍሎራ ከሼር ውጭ የሆነ የራሱ አስተዳደር ያለው፣ ለድሃው ሠራተኛ የቆመ፣ ሚዛናዊ የአበባ ሽያጭ ተካሂዶ ሠራተኛውም ከሽያጩ እንዲጠቀም የሚያደርግ ፌር ትሬድ (Fair Trade) አራማጅ የግል ድርጅት ነው፡፡ ሼር የዚህ ድርጅት አባል ስለሆነ፣ ሠራተኞቹም ከፌር ትሬድ ከሚገኘው ሽያጭ ገቢ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ እንዴት መሰላችሁ፣ የአንድ አበባ ዋጋ አንድ ዩሮ ቢሆን በፌር ትሬድ ዓላማ መሠረት አፍሪ ፍሎራ በሁለት ዩሮ ይሸጥና አንዷን ዩሮ ለሠራተኛው ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሠራተኛው የሽያጩን ግማሽ ያገኛል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ገንዘቡ በጥሬው መጥቶ ለሠራተኛው በጥሬው አይከፋፈልም፡፡ የሠራተኛውን ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ ሙያዊ ክህሎቱን ለማዳበርና ለማሻሻል …. በአጠቃላይ ሠራተኛውን ለሚጠቅም ነገር ይውላል፡፡ በዚህ መልኩ ከፌር ትሬድ የሚመጣውን ገንዘብ ሼር ኢትዮጵያ የሚያስተዳድረው ብቻውን ሳይሆን ከሠራተኛው ከተመረጠ ኮሚቴ ጋር ነው፡፡ ሼር ኢትዮጵያ ለሠራተኞቹና ለህብረተሰቡ ካደረገው ነገር አንዱ ሁሉም ሠራተኞች በነጻ፣ የዝዋይ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ በአነስተኛ ክፍያ የሚታከሙበት ሆስፒታል መገንባቱ ነው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተሠራው ዘመናዊ ሆስፒታል፤ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት የተገጠመለት ስለሆነ በሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ዘመናዊነት አዲስ አበባ ከሚገኘው ኮሪያ ሆስፒታል ቀጥሎ ይመደባል ተብሏል፡፡ “ከኬንያ የመጣ ሶፍትዌር የተገጠመለት ሲሆን ከካርድ ክፍል እስከ ምርመራ፣ ላቦራቶሪ፣ ፋርማሲ፣ አልጋ ክፍሎች…. ድረስ በኔትዎርክ ስለተያያዙ በሆስፒታሉ የወረቀት ሥራ የለም፣ በሽተኛው ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ የተሰጠውን ቁጥር እያሳየ አስፈላጊውን አገልግሎት ያገኛል” ይላሉ ኦፊሰሩ፡፡ እንደማንኛውም ሆስፒታል፣ ተኝተውና በተመላላሽ ለሚታከሙ ሕሙማን ሁሉን አቀፍ የመከላከልና የማከም አገልግሎት እንደሚሰጡ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ደምሳቸው ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በ100 ኪ.ሜ ዙሪያ ሆስፒታል ያለው አዳማና ሻሸመኔ ነው፡፡

የመውለጃ ቀኗ የደረሰ ሴት ሆስፒታል ወደሚገኝበት ስትወሰድ አጣዳፊ ምጥ ይዟት፣ ጨቅላውም ሆነ የእናቲቱ ጤና ችግር ላይ እንዳይወድቅ ሆስፒታሉ አማራጭ ሆኗል ብለዋል ዶ/ር ደምሳቸው፡፡ 140 አልጋ፣ ሁለት ስፔሻሊስት ሐኪም (የጽንስና የማህጸን እንዲሁም የቀዶ ሕክምና)፣ 6 ጠቅላላ ሐኪም፣ 4 የጤና መኮንን፣ 3ዐ ነርሶች፣ 7 አዋላጆች በአጠቃላይ 147 ሠራተኞች እንዳሏቸው የጠቀሱት ሚዲካል ዳይሬክተሩ፤ በቀን ከ300 በላይ ለሆኑ ተመላላሽ ታካሚዎች አገልግሎት እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ እንደማንኛውም ሆስፒታል መንግሥት በሚከተለው የጤና ፖሊሲ መሠረት የሕጻናት ክትባት፣ ለነፍሰ ጡሮች የጽንስና የማኅፀን ክትትል፣ የወባ፣ የቲቢ፣ የኤች አይቪ ኤድስ…. ሕክምና በነጻ ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ በማንኛውም በሽታ፣ ሠራተኛውን በነጻ፣ የአካባቢውን ማህበረተሰብ በአነስተኛ ክፍያ ያክማል፡፡ በሆስፒታሉ አጐቷን አስተኝታ ስታስታምም ያገኘናት ራሄል ባህሩም፤ ለካርድ 15 ብር፣ በቀን ደግሞ ለአልጋ 45 ብር እንደሚከፍሉ ገልጻ፣ ከግል ሐኪም ቤቶች ጋር ሲነጻጸር ተመጣጣኝ መሆኑን ገልጻለች፡፡ “ሆስፒታሉ የግል ቢሆንም የአካባቢውን ነዋሪ እንደ መንግሥት ሆስፒታል አነስተኛ ዋጋ ነው የምናስከፍለው፡፡ ለምሣሌ ለካርድ 15 ብር፣ ተኝቶ ለሚታከም በሽተኛ ቁርስ ምሣ ራት በልቶ፣ የሐኪምና የነርስ ክትትል ተደርጐለት በቀን 45 ብር ነው የምናስከፍለው፡፡ ክፍያው ከሌላ የሕክምና ተቋም ጋር ሲነጻጸር ነጻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለድርጅቱ ሠራተኞች ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ ሁሉም ሕክምና በነጻ ነው፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ኬንያ ልከን እናሳክማለን” ብለዋል ዶ/ር ደምሳቸው፡፡ ሌላው ሼር ኢትዮጵያ ለማህበረሰቡ እየሰጠ ያለው አገልግሎት በትምህርት ዘርፍ ነው፡፡

በመዋለ ህፃናት የጀመረው ሼር ኢትዮጵያ ት/ቤት ዘንድሮ 9ኛ ክፍል ከፍቷል፡፡ አቶ ግርማ ቢሆን የሼር ኢትዮጵያ ት/ቤት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ት/ቤቱ በዚህ ዓመት ግማሹ የሠራተኛው ልጆች፣ ቀሪው ግማሽ ደግሞ ከዝዋይ ከተማና ከአካባቢው ማህበረሰብ አቅም እንደሌላቸው አስመስክረው የተቀበሏቸውን 4,200 ተማሪዎች በነፃ እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመንግስትም ሆነ በግል ት/ቤቶች የማይታዩ አሠራሮች እዚህ ይገኛሉ፡፡ ት/ቤቱ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ቢሆንም ትምህርት የሚሰጠው በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ አቶ ግርማ፤ ወላጅ ልጁን አምጥቶ ሲያስመዘግብ ይማርልኝ ብሎ ባስመዘገበው አፍ መፍቻ ቋንቋ በኦሮምኛ ወይም በአማርኛ እናስተምራለን፡፡ በመዋለ ህፃናት በሁለቱም ቋንቋ የሚማሩ 1500 ያህል ህጻናት ሲኖሩ በ24 ክፍሎች ተደልድለው ይማራሉ፡፡ በሁለቱም ቋንቋ አሁን በ1 ኛ 2ኛ፣3ኛ፣4ኛ አራት አራት ክፍሎች እናስተምራለን፡፡ ከ8ኛ በላይ ግን የምናስተምረው በእንግሊዝኛ ነው፡፡ አሁን 89 መምህራን ሲኖሩን አብዛኞቹ በዲግሪ የተመረቁ ናቸው፡፡ ላቦራቶሪው ጥቃቅን ነገሮችን አጉልቶ በሚያሣይ ዘመናዊ አጉይ መነፅሮች (ማይክሮስኮፕ) እና ለመማር በሚረዱ ቁሣቁሶች ተሟልቷል፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ላቦራቶሪ በበርካታ ኮምፒዩተሮችና ባለሙያዎች የተደራጀ ስለሆነ፣ ህፃናት ከሁለተኛ ክፍል ነው የኮምፒዩተር ትምህርት የሚጀምሩት፡፡

የ5ኛ ክፍል ተማሪ ፎቶሾፕ ስትሠራ አይተናል፡፡ ቤተ መጻህፍቱ በትምህርት ሚኒስቴር ካሪኩለም መሠረት በአዳዲስ መጻህፍት ተሞልቷል፡፡ በት/ቤቱ የደረስነው በምሳ ሰዓት አካባቢ ስለነበር፣ መዋለ ህፃናት የሚማሩ ህፃናት ተሰልፈው ምሣ ወደ ሚበሉበት አዳራሽ ሲገቡ ተመለከትን። ህፃናቱ የድሃ ልጆች ስለሆኑ ቁርስና ምሣ በነፃ እንደሚበሉ፣ ዩኒፎርም፣ መጻሕፍት፣ ደብተርና እስክሪብቶ በነፃ እንደሚሰጣቸው ተነገረን፡፡ የሼር ኢትዮጵያ ባለቤት ሚ/ር ገረት ባርንሁርን “በአገሬ እየተራበ የሚማር ሰው አይቼ አላውቅም” ብለዋል፡፡ “በመማር ማስተማር ሂደት አንዳችም ችግር የለብንም፤ በወር አንድ ጊዜ ከእርሻው ባለቤት ጋር ተቀምጠን እንወያያለን፡፡ የሆነ ችግር ቢያጋጥመን እዚያው እናቀርብና ፈጣን ምላሽ ይሰጡናል፡፡ በቅርቡ እንኳ ለ9ኛ ክፍሎች ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣቸውን አዳዲስ መጻህፍት 93 ሺህ ብር አውጥተው ገዝተውልናል” ብለዋል አቶ ግርማ፡፡ የልጆቹስ ውጤት እንዴት ነው? አልናቸው አቶ ግርማን፡፡ “የልጆቹ ውጤት በጣም ጥሩ ነው። በቅርቡ በምስራቅ ሸዋ ዞን 13 ወረዳ ት/ቤቶች መካከል በተደረገ ውድድር 1ኛ የወጣው የእኛ ተማሪ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎቻችን 100 ፐርሰንት ነው ያለÕት። በ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም 100 ፐርሰንት ለማሣለፍ ብቻ ሳይሆን ውጤታቸውም በጣም ከፍ እንዲል እየሠራን ነው” ብለዋል፡፡ ሚ/ር ባርንሁርን፤ “ሼር ኢትዮጵያ በመላው ዓለም በጣም ተወዳጅና ስመጥር እንደሆነው ሁሉ ሼር ኢትዮጵያ ትምህርት ቤትም ታዋቂ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ ተማሪዎችን የመቀበል አቅሙ ከ10 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማደጉን አይቻለሁ፡፡ በዚህም ‘ትምህርት ለሁሉም’ የሚለውን የተባበሩት መንግስታት የሚሌኒየም ልማት ግብ እያሟላን ነው ብለዋል፡፡ሼር ኢትዮጵያ በተመሣሣይ ስም ተመዝግቦ በብሔራዊ ሊግ የሚጫወት የእግር ኳስ ቡድን አለው፡፡ ድርጅቱ ለዚህ ክለብ በዝዋይ ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ ስታዲየም ሠርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሼር ኢትዮጵያ ለአዳሚቱሉ ወረዳ ዘመናዊና ለፍርድ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ የፍ/ቤት ቁሣቁሶች የተገጠመለት እንዲሁም ብሮድባንድ ኢንተርኔት ያለው ደረጃውን የጠበቀ ፍ/ቤት ሠርቶ አስረክቧል፡፡ የአካባቢ ደህንነትን ለመጠበቅም ሠራተኞቹን በማስተባበር ዛፍ እየተከለ ነው፡፡ የዛፍ ተከላ ፕሮግራሙ የተጀመረው አምና ቢሆንም ከ26 ሺህ በላይ ችግኞች በዝዋይ ከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠሩም አካባቢ ተተክለው፣ ድርጅቱ የችግኞቹን እድገት የሚከታተሉ ሠራተኞች መመደቡን አቶ ከማል አስረድተዋል፡፡ ከአበባው እርሻ የሚፈሰው ውሃ ወደ ሐይቁ ገብቶ እንዳያበላሽ ከሆላንድ መንግሥት ጋር በመተባበር፣ ውሃ የሚጠራቀምበት ጉድጓድ ቆፍሮ፣ ውሃው ተጣርቶ በሪሳይክሊንግ ተመልሶ አበባውን እንዲያጠጣ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Read 5222 times
Administrator

Latest from Administrator