Monday, 10 February 2014 07:39

የሰውነት ዘመን አበቃ! ከዚያስ?

Written by 
Rate this item
(10 votes)

          በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሰሞኑ አበይት መነጋገርያ አጀንዳ የ62 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት መነሳታቸው ነበር፡፡ ሰውነት ከሃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ለሱፕር ስፖርት አስተያየት ሲሰጡ ለስንብታቸው በፌደሬሽን ላይ ያቀረቡት ቅሬታ የለም፡፡ በስንብታቸው ማግስት ከዋልያዎቹ በኋላ ዋንኛው ትኩረታቸው ከቤተሰባቸው ጋር ማሳለፍ እንደሆነ የተናገሩት ሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት የማይተውት ሙያቸው እንደሆነ በመግለፅ በአገር ውስጥ የሚወዳደሩ ክለቦችን ወይንም በአፍሪካ ደረጃ ብሄራዊ ቡድኖችን ለማሰልጠን ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
‹‹የአሰልጣኝነት ስራ አስቸጋሪ እና ምስጋና የሚያሳጣ ነው፡፡ የምትወደደው በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ በህይወት ውስጥ በተለያዩ  ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውጣውረዶችን በፀጋ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ መባረሬ ድንገተኛ ዜና አልሆነብኝም። በደቡብ አፍሪካ ከተደረገው የቻን ውድድር ስንመለስ ከመቅፅበት ሁኔታዎች ሲቀየሩ አስተውያለሁ፡፡ ከስንብቱ በፊት ተዘጋጅቶ በነበረው የግምገማ መድረክ፤ በብሄራዊ ቡድኑ የነበሩ ችግሮችን አስረድቼ ነበር፡፡ ይሁንና ቡድኑ በቻን ተሳትፎው ለገጠመው ውጤት ማጣት እኔ ምክንያት እንደሆንኩ አስቀድሞ የተወሰነ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በነበረኝ ሃላፊነት ባስመዘገብኳቸው ውጤቶች እኮራለሁ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ላገኛቸው ስኬቶች 100 ፐርሰንት ብቃቴን በመስጠት አገልግያለሁ፡፡ ›› በማለት አሰልጣኝ ሰውነት ለሱፕር ስፖርት የስንብት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከተሰናበቱ በኋላ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው  የት ይሄዳሉ የሚል ጥያቄ መነሳት ጀምሯል፡፡ አሰልጣኙ በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የደርሶ መልስ ትንቅንቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በናይጄርያ ከተሸነፈ በኋላ በማግስቱ ወደ ጊኒ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሊሄዱ ነው ተብሎ ተወርቶ ነበር። በዚሁ ጊዜም አሰልጣኙ አገሬን ትቼ የትም አልሄድም፤ በብዙ ሺ ዶላሮች እንድሰራላቸው የጠየቁኝ ነበር ግን አልተቀበልኳቸውም፤ ፍላጎቴ በኢትዮጵያ መቀጠል ነው ብለው አስተባብለው ነበር፡፡ ከሳምንቱ አጋማሽ ስንብታቸው በኋላ ደግሞ ከቦትስዋና እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር ለአዲስ ስራ ግንኙነት ፈጥረዋል እየተባለ ነው፡፡
የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ እለት በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ከተደረገው የግምገማና የምክክር መድረክ ከሁለት ቀናት በኋላ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ  ከቀኑ 9 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ልዩ ስብሰባ አድርጓል። ስብሰባው በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና በረዳት አሰልጣኞቻቸው  ቀጣይ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ከዚሁ የስራአስፈፃሚ ስብሰባ በኋላ በማግስቱ ረቡዕ ካሳንቺስ በሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርቷል። ከቀኑ 10 ሰዓት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በጣም በተጣበበ ጊዜ ቢጠራም በርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች መገኘታቸውን ያደነቁት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ መግለጫው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች  ስንብት ላይ ያተኮረ መሆኑን በይፋ ገልፀዋል። ከኤሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የግምገማ እና የምክክር መድረክ፤ ከማክሰኞው የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ እስከ ረቡዕ ጋዜጣዊ መግለጫ የነበሩትን ሁኔታዎች ከዚህ በታች እንደቀረበው ተዳስሰዋል፡፡
ሰውነትና ዋልያዎቹ በባለድርሻ አካላት ሲገመገሙ
ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተዘጋጀው የግምገማ እና የምክክር መድረክ ላይ ከ59 በላይ የስፖርት ጋዜጠኞች መገኘታቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ በእለቱ  በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና በብሄራዊ ቡድናቸው ላይ የሚደረገው ግምገማ የመጨረሻ ውጤት የሚዲያውን ትኩረት የሳበው ጉዳይ ነበር፡፡ በሙሉ ቀን በተካሄደው የግምገማ እና የምክክር መድረክ ላይ የስፖርት ኮሚሽን ተወካዮች፤ የሙያ ማህበራት ተወካዮች፤ የክለብ አመራሮች፤ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባላትና  ባለሙያዎችና በስፖርቱ ላይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በመክፈቻ ንግግር ባስጀመሩት በዚህ ስብሰባ ላይ በጠዋት ፕሮግራም የፌደሬሽኑ ዋና ፀሃፊ የአስተዳደር ዘርፍ ካቀረቡት ሪፖርት በኋላ በቴክኒኪ ኮሚቴ ሰብሳቢው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን የነበረውን ተሳትፎ በቁጥሮች የመዘነ ግምገማ ተሰጥቷል፡፡ በመቀጠል የቀረበው ደግሞ የቻን ተሳትፎ እንዴት እንደነበር የሚያብራራ የሰውነት ቢሻው መግለጫ ነበር፡፡ በእለቱ የነበሩ ጋዜጠኞች እነዚህ መግለጫዎች ሲቀርቡ ተከታትለዋል፡፡ የአስተዳደር ዘርፉ ሪፖርት የ2 ዓመት ተኩል ስራን በአጭሩ የተነተነ ነበር፡፡ ሪፖርቱ በሰውነት ቢሻው ዘመን የነበረው  ብሄራዊ ቡድን አጠቃላይ የአስተዳደር እና የፋይናንስ ሂደት በአጭሩ መግለፁን የታዘቡ አንዳንድ ጋዜጠኞች የአሰልጣኙ መሰናበት ፍንጭ ነው ብለው ነበር፡፡ በአንፃሩ የሚዲያ ባለሙያዎች በቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ ብሄራዊ ቡድኑን በመዘኑ በቁጥሮች መወሳሰብ ግራ ተጋብተዋል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው አሰልጣኙን ከውድድር በኋላ ከመተቸት ከውድድሩ በፊት በቂ መረጃ  በመስጠት ለምን አልሰራም በሚል ቁጭት ብዙዎች ግምገማውን አልተማረኩበትም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስገራሚ ማብራርያን ሁሉም ባለድርሻ አካል በትኩረት አዳምጦታል፡፡ ሰውነት በግምገማው መድረክ ያቀቡትን መግለጫቸውን ሲጨርሱ ከብሄራዊ ቡድን ጋር በመስራት ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት በመግለፅ ነበር፡፡ ለጋዜጠኞች ከአሰልጣኙ ማብራርያ ቀልባቸውን የወሰደው በብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት ተጠያቂ ነኝ ብለው በልበሙሉነት መናገራቸው ነበር፡፡  ይሁንና ዓላማቸው የነበሩትን ልጆች በመያዝ እና አዳዲስ ተተኪዎችን በመፈለግ ብሄራዊ ቡድኑን ለቀጣዩ የሞሮኮው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እንደሆነ ሲናገሩ ግን ማጉረምረም ነበር፡፡  ፌደሬሽኑ የግምገማ እና የምክክር  መድረኩን ያዘጋጀው በቅርቡ ይፋ ለሚያደርገው የ5 ዓመት መሪ ስትራቴጂክ እቅድ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ለማግኘት አስቦ መሆኑን በመግለፅ ሚዲያዎች በቡድን ለሚደረገው ምክክር እንዲሳተፉ ጋብዞ ነበር። ጋዜጠኞች በመድረኩ መሳተፋቸው ተገቢ አለመሆኑን አምነውበት ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡
በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ይግዛው በቀረበው የአስተዳደር ዘርፍ ሪፖርት መንግስት በስፖርቱ እየተጫወተ ያለውን ወሳኝ ሚና ጎልቶ ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና ዋና ውድድር፤ በዓለም ዋንጫ 3 ዙር የማጣርያ ምእራፎች፤ በሴካፋ እና በቻን ውድድሮች በነበረው ጉዞ ፌደሬሽኑ በአስተዳደራዊ ዘርፉ ካከናወናቸው ተግባራት የትጥቅ ድጋፎች እና ማበረታቻ ሽልማቶች ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ ዋና ፀሃፊው አቶ ይግዛው ለአሰልጣኞች፤ ለተጨዋቾች፤ ለቡድን መሪዎች፤ ለልዑካኖች እና ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ ላደረጉ ሰዎች በድምሩ 14 ሚሊዮን 875ሺ ብር ወጭ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ዋና ፀሃፊው አልገለፁትም እንጂ ብሄራዊ ቡድኑ በነበረው ስኬት በስፖንሰርሺፕ፤ በገቢ ማሰባሰብ እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተገኘው ብር ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ብሄራዊ ቡድኑን በስፖርት ትጥቆች አቅርቦት አለመቸገሩን  የገለፁት ዋና ፀሃፊው ፤ ለብሄራዊ ቡድኑ ከፌደራል ስፖርት ከ1060 በላይ የተለያዩ ትጥቆችን፤ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ 236 ቱታዎች መገኘቱን በመጥቀስ መንግስት በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በኩል   ለብሄራዊ ቡድኑ የማበረታቻ እና የምስጋና  ድጋፎችን በመስጠት የነበረው ትኩረት የሚመሰገን ነውም ብለዋል፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ስኬት የገቢ ምንጮቹን ያሰፋው ፌደሬሽኑ 1116 የስፖርት ቱታዎች ከ886ሺ በላይ በማውጣት ገዝቷል ፤ ብሄራዊ ቡድኑ በልምምድ ስፍራ እንዳይቸገር፤ በመኝታ እና በምግብ  ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሲያገኝ እንደነበርም  ዋና ፀሃፊው አቶ ይግዛው ገልፀዋል፡፡ በአስተዳደራዊ ዘርፍ የተፈጠረው ችግር የቡድን መሪዎች በየጊዜው እና በዘፈቀድ ሲቀያየሩ ከመቆየታቸው በተያያዘ እንደነበር ዋና ፀሃፊው አቶ ይግዛው በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡  ይሄው ዝርክርክ የፌደሬሽን አሰራር ታሪካዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ብሄራዊ ቡድኑ  በቢጫ ካርድ ቅጣት መሰለፍ ያልነበረበት ተጨዋች አጫውቶ በሰራው ጥፋት ለ3 ነጥብ መቀነስና ለገንዘብ ቅጣት መብቃቱ በአስተዳደር ዘርፉ የታየ የአሰራር ችግር  ነበር ብለዋል፡፡
“በቻን ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የቀረበው የሰውነት ቡድን ፋውል የሚያበዛ፤ የግብ እድሉን የማይጠቀም፤ የአካል ብቃት ችግር የታየበት፤ በስነልቦና ያልጠነከረ፤ በደንብ ያልተዘጋጀ ነበር”  በማለት አሰልጣኙን በመተቸት የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በግምገማው መድረክ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን የነበረውን ተሳትፎ በቁጥሮች ላይ በተመሰረተ ሪፖርት ፈትሸዋል ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በቻን ተሳትፎው በመብቃቱና በአህጉራዊ መድረክ ያለበትን ደረጃ በማሳየቱ ተጠቃሽ ውጤት መሆኑን የገለፁት ባለሙያው ለወጣቶች መነቃቃት የነበረው አስተዋፅኦ ትልቅ ጥንካሬ እንደሆነና የዜጎች መነጋጋርያ አጀንዳ መሆኑ ይደነቃል ብለዋል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ድክመቶች በሁለት ነጥቦች እንደሚጠቃለሉ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሲያስረዱ፤ የመጀመርያው በቻን ተሳትፎ ዋና አሰልጣኙ እና ረዳቶቻቸው ለወጣት እና ተተኪ ተጨዋቾች እድል አለመስጠታቸው በብሄራዊ ቀጣይ እድገት ተፅእኖ የሚፈጥር መሆኑን ባለመረዳት ነው ብለው፤  በሌላ በኩል የብሄራዊ ቡድኑ የተፎካካሪነት ብቃት በውጤት የታጀበ አለመሆኑ በግልፅ ከብዙ ችግሮች ጋር ታይቷል ብለዋል፡፡
የቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን ተሳትፎው ከሊቢያ፤ ከኮንጎ እና ከጋና ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ከ3ቱ ቡድኖች በድምር የሚበልጥ ፋውል እንደሰራ፤ የግብ እድሎችን መጠቀም እንዳልቻለ፤ በኳስ ቅብብል ረገድ ውጤታማ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን እንዳበዛ፤ በአጨዋወቱ ኳስ ወደ ኋላ በመመለስ መጥፎ አዝማሚያ እንዳሳየ፤ በመከላከል ላይ የጥንቃቄ ጉድለት እና ድክመት እንዳለበት፤ ኳስን በጭንቅላት መግጨት እና የተቃራኒ ቡድን ኳሶችን ከአደጋ ነፃ እንደማያወጣ፤ በመስመር ብዙም እንደማይጫወት አመልክቷል። የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በአጠቃላይ አሰልጣኞች ለብሄራዊ ቡድን በመረጧቸው ተጨዋቾች መሄድ የሚገባቸውን እድል ነፍገው የማይገባቸውን ማሰለፋቸው ዋና ስህተት እንደነበር ሲገልፁ፤ የተጨዋቾች የአካል ብቃት  አለመሟላትና ለስነልቦና ችግሮች መጋለጥ የቡድኑን አቅም ያቃወሱ ምክንያቶችእንደነበሩም ተረድተናል ብለዋል፡፡ አሰልጣኞች ቡድኑን በብቃት እንዳላዘጋጁ፤ ለዝግጅታቸውም ከክለቦች ጋር በቅንጅት ስለማይሰራ በቡድኑ ብቃት ላይ ተፅእኖ መፍጠራቸውንም የቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ አብራርቷል፡፡
ለሰውነት ምስጋና ይግባቸው
የፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ረዳቶቻቸው ቡድኑን ተረክበው ባገለገሉበት ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል እግር ኳሱን ያነቃቁ በርካታ ውጤቶች እና ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃቱ  የመጀመርያው ድንቅ ስኬት እና አበይት የታሪክ ምእራፍ ነበር፡፡ ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ እስከመጨረሻው የማጣርያ ምዕራፍ በመጓዝ ብሄራዊ ቡድኑ ከአፍሪካ 10 ምርጥ ቡድኖች ተርታ መግባቱም ይታወሳል፡፡  በአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፏም ተጠቃሽ ስኬት ነበር፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ባለፈው ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ባስመዘገበው ውጤት በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ያለቅድመ ማጣርያ በቀጥታ ለምድብ ማጣርያ የመወዳደር እድልም አግኝቷል፡፡  
አቶ ጁነዲን ባሻ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል የተገኘውን ስኬት ባጠቃለለ ንግግራቸው ‹‹ ለብዙ ዘመናት ብሄራዊ ቡድኑ ብዙ ጎል የሚገባበት፤ ተከታታይ ሽንፈቶችን የሚያስተናግድ፤ እናሸንፋለን ብለን በአዕምሯችን እንዳናስብ ያደረገን ነበር፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና መላው ቡድናቸው ይህን የቀየረ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የእግር ኳስ ስሜት አነቃቃትዋል፤ ወደ ስታድዬም  እንዲመጣ አድርገዋል፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ተብሎ መታሰብ እንዲጀምር አስችለዋል፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ከዳር እስከዳር እንዲለበስም ምክንያት ሆነዋል፡፡›› በማለት  ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በኢትዮጵያ እግር ኳስ በፈጠሩት መነቃቃት እንደ ብሄራዊ ጀግና የሚታዩ ታላቅ ሰው መሆናቸውን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛውጤት አላቸው። በ50ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዛቸው ከፍተኛው ተከፋይ ነበሩ።
በሰውነት የስራ ዘመን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ስኬት ከመመዝገቡም በላይ የአገሪቱ የእግር ኳስ ደረጃ ተሻሽሏል፤ ከዋልያዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ወደ 6 የተለያዩ አገራት ወደ የሚገኙ ክለቦች በመሰማራት በዝውውር ገበያው ተፈላጊነታቸው ጨምሯል፡፡
የሰውነት መሰናበቻ ምክንያቶች
ስራ አስፈፃሚው በዋና አሰልጣኙ ሰውነት ቢሻው እና በረዳቶቻቸው ለተገኙ ውጤቶች ክብርና ምስጋና እንደሚገባ ቢገልፅም በብሄራዊ ቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ላይ ባደረገው ልዩ ስብሰባ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል እንቅፋት የነበሩ ድክመቶችን መርምሯል፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው ብሄራዊ ቡድን ከናይጄርያ ጋር ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የባከኑ እድሎች ነበሩ፡፡ ከዚያም ኬንያ ባዘጋጀችው የሴካፋ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ለዋንጫ ተጠብቆ ከምድቡ በጊዜ የተሰናበተበት ሁኔታም ብዙ ጥያቄዎችን ፈጥሯል። በመጨረሻም  በደቡብ አፍሪካው የቻን ውድድር ቡድኑ በነበረው ተሳትፎ ደካማ አቋም ማሳየቱ እና የፉክክር ደረጃው ኋላቀር መሆኑ መረጋገጡ ሁሉንም ያሳሰበ ነበር።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሄራዊ ቡድን ዳግም ወደሽንፈት መመለሱን የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ሲታዘብ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳስፈለገው የተናገሩት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቀጣይ ወዴት ያመራል፤ መንግስት እና ህዝብ ከስፖርቱ ምን ለውጥ ይፈልጋሉ የሚለውን መክረንበት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ረዳቶቻቸው በብሄራዊ ቡድኑ ያላቸው ቆይታ ማብቃት እንዳለበት ከውሳኔ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ከስራ እንደተሰናበቱ የተገለፀላቸው   በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሃላፊዎች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግምገማ መድረክ ላይ በሃላፊነታቸው ስለመቀጠል ፍላጎታቸው ከተናገሩ 3 ቀናት በኋላ ነበር፡፡ አሰልጣኞቹ መሰናበታቸውን ካወቁ በኋላ ውይይት ተደርጎ በተሰራው ሁሉም መደሰቱን፤ ግንኙነታቸው እንደሚቀጥል፤ ከስፖርቱ ጎን በመሆን እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸው ተነግሯል፡፡
‹‹ሰዎች ጥሩ ይሰራሉ፡፡ ጊዜዎች ይቀያየራሉ፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ረዳቶቻቸው በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ደርሶ መልስ ፍልሚያ ከናይጄርያ ጋር፤ በሴካፋ እና በቻን ውድድሮች ይዘው በቀረቡት  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የማሸነፍ ስሜት ቀነሰ፤ የውጤት ማጣት ተከታታለ፤ በእርግጥ ተጨዋቾችም አሰልጣኞችም በጨዋታዎቹ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ በክለቦች መካከል ያለው ውድድር አለማደጉ፤ በታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ ተግባራት ያልጠነከሩ መሆናቸው፤ እና የአደረጃጀት እና የአሰለጣጠን ብቃት አለማደግ ለብሄራዊ ቡድኑ ድክመት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የውጤት ማጣቱ አዝማሚያ የመጣው ባለንበት ልክ እና ደረጃ ነው። እግር ኳስ ያለበትን ደረጃ ቆም ብለን ማሰብ ነበረብን ›› በማለት ለታሪካዊው ውሳኔ ያደረሱ ዝርዝር ሁኔታዎችን አቶ ጁነዲን ባሻ ገልፀዋል፡፡
 በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በኩል ብሄራዊ ቡድኑ በመቀጠል በ2015 በሞሮኮ ለሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ይፈለጋል፡፡  በታዳጊ እና ወጣት  ቡድኖች አህጉራዊ ውድድሮች ንቁ ተሳታፊ የመሆን ፍላጎትም አለ። የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ለለውጥ ተነሳስተው በዘላቂ ልማትና የእድገት ሂደት  እንዲሰሩ የማስተባበር እቅድም አለ፡፡ በአጠቃላይ የአሰልጣኝ ሰውነት ስንብት ስራውን ከጀመረ 4 ወራት የሆነው የፌዴሬሽን አመራር አዲስ የለውጥ ምእራፍ መክፈቱን ያበሰረበት ነበር፡፡
የአሰልጣኞቹ የኮንትራት ውል መቋረጡ ትልቅ ውሳኔ በመሆኑ በግልፅ መታወቅ አለበት ያሉት ጁነዲን ባሻ፤ አሰልጣኞች ስራቸውን ራሳቸው አልለቀቁም ወይም በክፉ ስሜት አልተሰናበቱም ብለዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙና ረዳቶቻቸው በማንኛውም የሰራተኛ ህግ መሰረት ስንብታቸው እንደሚከናወን የገለፁት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በክብር እና በምስጋና ይሸኛሉ እንጂ የካሳ ክፍያ የላቸውም ብለዋል፡፡ የስራ አስፈፃሚው አሰልጣኞቹን ለመቀየር መወሰኑን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሲገልፅ ሌላው የፌደሬሽን ዝርክርክ አሰራርም ተጋልጧል፡፡ የአሰልጣኞቹ የቅጥር ኮንትራት ጉዳይ ነው፡፡ የአንዱ በጥቅምት፤ የሌላው በህዳር የሌላው በታህሳስ ውል የሚያበቃበት ነበር ያሉት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ የቅጥር ኮንትራት በግልፅ የሚታወቅ መሆን ቢኖርበትም አሰልጣኞቹ ኮንትራታችሁ አልቋል ብለንና ኮንትራታቸውን አቋርጠን ለማሰናበት ያልፈለግነው፤ የቡድኑን የስራ ስሜት ላለማመሳቀል እና ላለመረበሽ በመወሰናችን ነበር ብለዋል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ፌደሬሽን ሃላፊነቱን ከተረከበ ከ3 ቀናት በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የደርሶ መልስ ማጣርያውን ከናይጄርያ ጋር በአዲስ አበባ ይጀምር ነበር። በሴካፋና በቻን ውድድሮች ከዚያ በኋላ  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መደረጋቸውን በማገናዘብ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን  በተለይ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የቅጥር ኮንትራት ውል ጥቅምት 28 አብቅቶ በይፋ ኮንትራራታቸው እንደተራዘመ ሳይገለፅ እስከ ታህሳስ 28 እየሰሩ እንዲቀጥሉ መደረጉ ፌደሬሽኑን ያስተቸዋል፡፡  
አሰልጣኞቹ እንዲሰናበቱ የተደረገው በሴካፋ እና በቻን ውድድሮች ላይ ባሳዩት ድክመት ብቻ እንዳልሆነ በመግለጫው የተናገሩት ሌላው የፌደሬሽኑ  የስራ አስፈፃሚ አባል እና ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት  አቶ ተክለወይኒ ናቸው፡፡ በቻን ውድድር የኢትዮጵያ ቡድን ለዋንጫው ትልቅ ግምት ተሰጥቶት እንደነበር ከናይጄርያ እና ጋና ተርታ ይጠቀስ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተክለወይኒ፤ ይህን በመንተራስ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ከአሰልጣኞቹ፤ ከረዳቶቻቸው እና ከተጨዋቾች ጋር ሲመካከር በቻን ያለው ግብ ዋንጫ ማምጣት ወይም ግማሽ ፍፃሜ መድረስ እንደሆነ ገልፆላቸዋል፡፡  የቡድኑ አባላት ይህን ግብ ለማሳካት ስንት ሽልማት ይጠብቀናል ብለው ሲደራደሩ ደህና ሽልማት ታገኛላችሁ ብለን ተማምነን ነበር ብለዋል፡፡  ከቻን ጉዞ በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ዋና አሰልጣኙ ዋንጫ ለማምጣት ወይም ግማሽ ፍፃሜ ለመድረስ ቃል የገቡትን ካልሆነ ተሸንፎ መመለስ የሚለውን ጨመሩበት፡፡ ተገቢ አልነበረም፡፡ ‹‹በቻን ውጤት ላይ ያደረግነው  የውስጥ ግምገማ ብሄራዊ ቡድኑ ለተሰጠው ግምት በቂ ጥረት አላደረገም ነው፡፡ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አካላት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ደረጃ በተሳተፈባቸው ውድድሮች ጥሩ መጫወቱን ገልፀውልናል፡፡ ጎንለጎን ግን የቡድኑ ደረጃ ደካማ እንደሆነና የተፎካካሪነት ብቃቱም መሻሻል እንደሚያስፈልገው መክረውናል፡፡ ስለሆነም የአሰልጣኞቹ መቀየር አስፈልጓል›› በማለት አቶ ተክለወይኒ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በየጨዋታው ብዙ የግብ እድሎች አምልጦታል፤ ተጨዋቾቹ ጥሩ ቢጫወቱም ውጤት ግን አላገኙም፤ ለውድድሮቹ በአሰልጣኞቹ የተደረገው ዝግጅት በፕሮፌሽናል መንገድ አልነበረም። ይህ ሁሉ ዝርዝር ምክንያት የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ ትልቅ ክፍተት ብለውታል። ‹‹ያሉብን ክፍተቶች የማይስተካከሉ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ውጤት መቼም ሊሳካ አይችልም ስለዚህም ስርነቀል ለውጥ ያስፈልጋል በሚል ከመግባባት ላይ ደርሰናል ››ሲሉም ተጨማሪ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወቅታዊ ብቃት ላይ የፊፋ ባለሙያዎች ያደረጉትን ትንተና ለአሰልጣኞቹ መቀየር ተጨማሪ ምክንያት እንደነበር በመግለፅም  ለእግር ኳሱ ጠቅላላ ህዳሴ የሚያመጣ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ለታመነበት አቅጣጫ ውሳኔው አስፈላጊ ነበር ብለው ተናግረዋል፡፡
የሰውነት  ተተኪ ከየት? ከአገር ውስጥ ከባህር ማዶ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፋፃሚ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቀላል ስራ አለመሆኑን ትልቅ ሃላፊነት እንደሆነ መገንዘቡን ሰሞኑን ገልጿል፡፡ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የረዳቶቻቸውን ስንብት የወሰነው ግን በአጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ ይመስላል፡፡ ስራ አስፈፃሚው በፕሬዝዳንቱ በኩል አሰልጣኞቹን ያሰናበትነው ሌላ አሰልጣኝ ለመቅጠር በመጓጓት ማለቱም ተስፋ ሰጪ አይመስልም፡፡ በአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት የሚመች አደረጃጀት ለመፍጠር መታሰቡን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ፤ ቦታውን ክፍት ማድረግ የመጀመርያው ተግባር እንደሆነ መታወቅ እንዳለበት በማስረዳት የህዝብ ጉዳይ ስለሆነ በግልፅ፤ ያለወከባ እና በጥንቃቄ ተገቢው መስፈርት ወጥቶ በሚደረግ ውድድር መሰረት የሚፈፀም እንደሚሆን ቃል ገብተዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በአዲሱ አሰልጣኝ ቅጥር የመጀመርያ ሙከራ በአገር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን ማሰስ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከሰውነት ቢሻው ስንብት በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ጋር ስማቸው እየተያያዘ ካሉ የአገር ውስጥ አሰልጣኞች መካከል ስዩም ከበደ፤ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ገብረመድህን ሃይሌ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ለአሰልጣኙ ቅጥር ወደውጭ የምንወጣበት ሁኔታ ካለ የገንዘብ ምንጮቻችን በመፈተሽ የምናደርገው ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ የቀድሞው የጊዮርጊስ ክለብ አሰልጣኝ የነበረው፤ በሱዳኑ አልሂላል ክለብ የሰራውና በምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ካለው ልምድ ባሻገር የሩዋንዳ እና የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠነው ሰርቢያዊ ሰርዶጆቪች ሚሉቲን ሚቾ ከውጭ አሰልጣኞችቀድሞ ስሙ ተጠርቷል፡፡
በቀድሞው ፌደሬሽን የተገባላቸውቃል ሳይፈፀምላቸው ቅር ተሰኝተው የነበሩት ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌንትም እየተጠቀሱ ናቸው፡፡ ቶም ሴንትፌይት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ሃላፊነት ለመረከብ በይፋ ጥሪ በማክበር የመጀመርያ የውጭ አሰልጣኝ ናቸው።  ከቤልጅዬም ለሱፕር ስፖርት በሰጡት ማብራርያ ‹‹ሰውነት ቢሻው ለብሄራዊ ቡድን ባስገኘው ስኬት ምስጋና ይገባዋል። ረዳቴ ሆኖ አብረን ስንሰራ በነበረበት ወቅት እንደ አስራት መገርሳ እና ጌታነህ ከበደን የመሳሳሉ ተጨዋቾች ለቡድኑ በመምረጥ አስተዋፅኦ ነበረኝ። በእርግጥ አገሪቱን ለቅቄ የወጣሁት ከፌደሬሽኑ ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ነበር፡፡ ተመልሼ ብሄራዊ ቡድኑን የማሰልጠን እድል ባገኝ ብዙ ልሰጠው የምችለው ነገር አለ፡፡ በተለይ ዋልያዎቹ በትልልቅ ግጥሚያዎች የሚገጥማቸውን ፈተና የሚወጡበትን አቅም ማስተካከል እችላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በፈጠራ እና በቴክኒክ የዳበረ ጥሩ አሰልጣኝ ካገኘ ምርጥ መሆን የሚችል ነው።›› በማለት ቶም ሴንትፌይት ለሱፕር ስፖርት ተናግረዋል፡፡
ፌደሬሽኑ የአሰልጣኙ ቅጥር በቀና መንገድ፤ አሳማኝ መመዘኛ እና መስፈርት ተዘጋጅቶ የሚከናወን እንደሆነ ሲያስታውቅ፤ ፍለጋውን በጋዜጦች ማስታወቂያዎችን በማውጣት፤ የተለያዩ ጥቆማዎችን ከባለድርሻ አካላት እና ከሙያተኞች በመቀበል፤ በብሮድካስት ሚዲያዎች በማስተዋወቅ ይሰራበታል ብሏል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እንደገለፁት በአሰልጣኝ አዲስ ቅጥር የማፈላለግ ተግባር ላይ  የቴክኒክ ኮሚቴ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ኮሚቴው በአንድ ሳምንት ጊዜ  ለሃላፊነቱ ብቁ የሆኑ ሰዎችን ዝርዝር እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡
ቀጣዩን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመቅጠር ፌደሬሽኑ ያሰበው የህዝብ ፍላጎት አድጓል፤  ዓለም አቀፍ ደረጃ ይዘን ተፎካካሪ ሆነን እንቅረብ ከሚል አቅጣጫ በመነሳት ነው፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መሰናበት  በኋላ ግን ለብሄራዊ ቡድኑ የሚመጥን አሰልጣኝ ፍለጋው ፈታኝ እንደሚሆን  መገመቱ  ስጋትን የጋረጠ ሆኗል፡፡
በአገር ውስጥ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ተተኪ ለማግኘት አሁን ጊዜው የሚያስቸግር ይመስላል፡፡ ብቁ ናቸው የሚባሉ አሰልጣኞች በአመዛኙ  በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ብዙም ልምድ የሌላቸው፤ የሙያ ብቃታቸው ያን ያህል የማያስመካ፤ አንዳንዶቹ በክለብ አሰልጣኝነት ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ የሚቸገሩ ናቸው፡፡ እነዚህ እና ሌሎችም ምክንያቶች ተተኪ አሰልጣኝ ከአገር ውስጥ የማግኘቱን እድሉን ያጠብበዋል፡፡ ከአገር ውጭ አሰልጣኝ ለመቅጠር ደግሞ ከዚህ በፊት ያሉ ተመክሮዎች የሁኔታውን አስቸጋሪነት በይበልጥ ያጎሉታል፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፊት ሁለት የውጭ አገር አሰልጣኞች ነበሩ፡፡  በትውልድ ናይጄርያዊ ሆነው ስኮትላንዳዊ ዜግነት ያላቸው አሰልጣኝ ኢፌም ኦኑራ እና ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌንት ናቸው፡፡
ሁለቱም አሰልጣኞች ከብሄራዊ ቡድን ጋር የነበራቸው ቆይታ አወዛግቧል፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩትን ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ዲያጎ ጋርዚዬቶ እና የፌደሬሽኑ እሰጥ አገባም በማስታወስ  ብዙ ልምድ መቅሰም ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ብቁ ናቸው ተብለው ከውጭ የመጡ አሰልጣኞች ያለው መጥፎ አመላከት ካልተወገደ የሚያሳስብ ይሆናል፡፡ የውጭ አሰልጣኞች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የማሰልጠን ሃላፊነቱ በምቹ ሁኔታ በነፃነት እንዲሰሩበት  የተሰጣቸው አልነበሩም፡፡ በቂ የስራ ጊዜ በኮንትራት ውላቸው አያገኙም ነበር፡፡  
ከአገር ውስጥ ባሉ አሰልጣኞች ምንም አይነት ክብር አይሰጣቸውም፤ ተባብሮ ከመስራት ይልቅ እንደውም ለውጥ አያመጡም በሚል አስተሳሰብ ዘመቻ ሲደረግባቸው አጋጥሟል፡፡ በሌላ በኩል ለአሰልጣኞቹ የሚከፈለው ደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መጠየቁም ይፈትናል፡፡  ብዙውን ጊዜ የውጭ አገር አሰልጣኞች ቅጥር  ለማከናወንና ክፍያ በመፈፀም ፌደሬሽኑ እቅዱን  እውን የሚያደርገው ክቡር ሼህ አላሙዲ ድጋፍ ላይ በመተማመን ነበር። ክቡር ሼህ አላሙዲ ይህን አይነቱን ድጋፍ መስጠት ካቆሙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አስቀድመው የነበሩ ድጋፎችም በተለያዩ መንገዶች ሲመዘበሩ እና ሲባክኑ ማጋጠሙም ጥሩ ታሪክ አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአሰልጣኞቹ የቅጥር ሁኔታ ላይ ፌደሬሽኑ ከየትኛው አካል ጋር ተመካክሮ እንደሚሰራ፤ በምን አይነት መስፈርት አወዳድሮ እንደሚቀጥር እና ለምን እንደቀጠረ በግልፅ ሁኔታ ያልተሰራበት ሆኖ መቆየቱን ማስታወስ ይቻላል። ሌላው ዋና አደጋ የውጭ አገር አሰልጣኞች ከተቀጠሩ በኋላ የሃላፊነት ቆይታቸው በአላስፈላጊ ጫናዎች ሲያጥር፤ በአሰለጣጠን ፍልስፍናቸው እና በቋንቋቸው ከብሄራዊ ቡድን ጋር መግባባት ሲያዳግታቸው፤ ከአገሪቱ ሚዲያዎች ጋር ተቀራርበው ለመስራት ሲቸገሩ እና ከፌደሬሽኑ አካላት ጋር መግባባት ሲሳናቸው እንደነበር ማስታወሱ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ውድደሮች በብቁ ተፎካካሪነት እንዲሳተፍ የሚያበቃውን ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ  እንዴት ሊያገኝ ይችላል ብቻ ሳይሆን ከተገኘስ የሚጠይቀውን ውድ ክፍያ ማን ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች ስጋት ይፈጥራሉ። የሊቢያን ብሄራዊ ቡድን በማሰልጠን በቻን ውድድር ዋንጫ ለማንሳት የቻሉት ፈረንሳዊው ሃቪዬር ክሌሜንቴ ደሞዛቸው እስከ 20 ሺ ዶላር ነው፡፡ በአጠቃላይ አንድ የውጭ አገር አሰልጣኝ ለመቅጠር በወቅቱ የገበያ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከ15 እስከ 20 ሺ ዶላር በወር መክፈል ሊኖርባት ይችላል፡፡ ይህ ገንዘብ ታድያ ከየት ይመጣል፤ ከሼህ አላሙዲ ወይንስ ከመንግስት መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው፡፡
ከሰውነት በኋላ ፌደሬሽኑ እና የህዳሴ ስትራቴጂው
በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው የግምገማ እና የምክክር መድረክ ላይ ከፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በመቀጠል የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አንበሴ እንየው ነበሩ። ኮሚሽኑ እንደመንግስት የእግር ኳሱ ከፍተኛ ባለድርሻ አካል መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አንበሴ፤  እግር ኳስ አንጋፋ እና ፈርቀዳጅ ስፖርት እንደሆነ በመግለፅ የህዝብ አጀንዳና አንድ የልማት ጉዳይ ስለሆነ የግምገማ እና የምክክር መድረኩ በስፖርቱ ህዝብን የሚያስደስት እና የሚያረካ ውጤት ላይ ለሚደረስበት የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቀድሞው ፌደሬሽን አማካኝነት ከ2004 እሰከ 2007 በሚል የ3 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ በሚል ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በተወሰነ መልኩ እቅዱን ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል፡፡ ወደፊትም በተሻለ ሁኔታ መሰራት ስላለበት  በአሁኑ ፌደሬሽንም በስትራቴጂክ እቅድ መመራት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ አቶ አንበሴ እንየው እግር ኳስ የእድገታችን ልዩ መገለጫ መሆን አለበት የሚል ማሳሰቢያቸው  መንግስት ለስፖርቱ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ያረጋገጠ ነበር፡፡ በየክልሉ በርካታ ስታድዬሞች እየተገነቡ ናቸው፡፡ አካዳሚዎችም ተመስርተዋል፤ እየተሰሩም ናቸው፡፡  መንግስት በስፖርቱ ሊገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እና የአገር መልካም ገፅታ ገብቶታል፡፡ የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት በመንግስት በኩል ለስፖርቱ  የተሰጠውን ትኩረት ያህል ብዙ መስራት እንዳለባቸው መረዳት ይገባል፡፡
በእግር ኳስ ኢትዮጵያ አሸንፋ እንድትወጣ ሁሉም ይፈልጋል ያሉት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ በስፖርቱ ኢንቨስትመንት እስከዛሬ ከተደረገው የበለጠ ማሳደግ አለብን ይላሉ፡፡ እንደ ጋና አይነት አገራት በርካታ ታዳጊ ፕሮፌሽናሎችን በማፍራት በአሁኑ ጊዜ ከ354 በላይ ተጨዋቾች በላይ በመላው ዓለም በማሰማራት ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን ማጥናት እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ፕሬዝዳንቱ ፤ ኢትዮጵያ ወጣት ፕሮፌሽናሎችን ለማውጣት ምን መስራት እንዳለባት፤ ስንት አካዳሚዎች ይበቁናል ስንት አካዳሚዎች አሉን እንዴት እንስራባቸው በሚል መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የስራ አስፈፃሚው እንደሚያስበው በኢትዮጵያ እግር ኳስ የወደፊት ጉዞ ላይ አሰልጣኝ መቀየር ብቻ ለውጥ አያመጣም፡፡ በእርግጥ የዋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቁልፍ ሃላፊነት ቢሆንም ጎን ለጎን በስፋት ለውጥ የሚያስፈልጋቸውም ሁኔታዎችም አሉ፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን የማስፈፀም ብቃት እና አደረጃጀት ለውጥ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል፡፡ በወጣቶች አና ታዳጊዎች ላይ ባተኮረ ስትራቴጂ ከስርመሰረቱ ካልተሰራ አሰልጣኝ ተጨዋች ሊያገኝ አይችልም በሚል አስተሳሰብም ለውጥ ለመፍጠር ታስቧል፡፡ የስራ አስፈፃሚው አባላት እንደገለፁት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ለሚያስችለው ስትራቴጂክ እቅድ የባለሙያ ቡድን ተቋቁሞ ሰነዱ እየተዘጋጀ ነው፡፡  በየካቲት ወር ሰነዱ ሙሉ ተዘጋጅቶ የሚያልቀው ይህ የስትራቴጂ እቅድ በአምስት አመት መርሃ ግብር የተነደፈ መሆኑ ተገልፆ አሁን ያለው ፌደሬሽን በስልጣን ላይ በሚቆይባቸው ቀሪዎቹ 3 ዓመታት በስፋት እንደሚሰራበት፤ ለሚቀጥለው የፌደሬሽን አመራር የሚያወርሰው እንደሚሆንም ተስፋ ተደርጓል፡፡ የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ እንደገለፁት በዚሁ የስትራቴጂ ሰነድ ላይ ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ ውይይት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ጠቁመው በስትራቴጂክ እቅዱ መሰረት የብሄራዊ ቡድኑ አጠቃላይ አደረጃጀት እና መዋቅር፤ አሰራሩ፤ የሰው ሃይል አደረጃጀቱ በአጠቃላይ እንደሚገመገም እና በተገቢው  መንገድ ከተሰራበት ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል ፅኑ እምነት አለን ብለዋል፡፡ በስትራቴጂክ እቅዱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፕሮፌሽናላይዝድ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ስራ አስፈፃሚው ተስማምቶበታል፡፡
በዚህ የፕሮፌሽናሊዝም አቅጣጫ መሰረት የፕሪሚዬር ሊግ፤ የብሄራዊ ሊግ እና ሌሎች የወጣት እና ታዳጊ ውድድሮች ፕሮፌሽናላይዝድ ማድረግ እነደሚያስፈልግ፤ የክለቦችን አቅም እና አደረጃጀት በማሳደግ ፕሮፌሽናላይዝድ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል እንደሚገባ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት እንደከፍተኛ የሰው ሃይል በመጠቀም እግር ኳሱ እንደኢኮኖሚው አድጎ እንዲታይ መሰራት አለበት በሚል ነው፡፡ በወጣት እና በታዳጊ ፕሮጀክቶች፤ መንግስት፤ ክለቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በስፋት እንዲንቀሳቀሱም ይደረጋል፡፡
የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ ሃጎስ እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል የሚችለው በእውቀት እና በስትራቴጂ እቅድ ሲሰራበት፤ የፕሮፌሽናሊዝም አቅጣጫዎችን ሲከተል ነው ፡፡ በዚህ ረገድ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የፌደሬሽን ስራ አመራር ብዙ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበትና ኢትዮጵያ ዛሬ በከፍተኛ ደረጃ የሚያፎካክረውን ስፖርት የሚመጥን ደረጃ አግኝታ እንደ ብራዚል ፤ እንደ ስፔን እና እንግሊዝ ተጠቃሚነት እንዲኖራት በመመኘት መስራት ያስፈልጋል በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

Read 4183 times