Monday, 10 February 2014 07:58

“...ቅድሚያ... ለእናቶችና ልጆቻቸው ጤንነት...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ4ኛ ዙር 2010-2011 እና 2014-2015 ባወጣው የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራም እንደ ዋና ግቦች ከሚቆጠሩት መካከል፡-
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ከ25% ወደ 60% ማሳደግ፣
በጤና ተቋማት እና በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ከ12%-32% ማሳደግ፣
የተሟላ ጤንነት ያላቸውን ልጆች ቁጥር ከ45% ወደ 80% ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የኢትዮያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ2010-11 እና 2014-15 ባወጣው የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራም በተጨማሪ እንደተጠቆመው  በአሁኑ ወቅት
በኢትዮጵያ የእርግዝና ክትትል ወደ 68% የደረሰ ሲሆን ከወሊድ በሁዋላ ደግሞ የሚኖረው የህክምና ክትትል ወደ 34% ደርሶአል፡፡  
በኢትዮጵያ በሰለጠነ የሰው ኃይል የመውለድ ልምድ በየጊዜው ቁጥሩ መጨመሩን ብሔራዊው ፕሮግራም ይገልጻል፡፡ ይህም ወደ 18.4% ከፍ እንዳለ ያሳያል፡፡ በእርግጥ ይህ መረጃ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌም በቤንሻንጉል ጉሙዝ 5.6% ያህል ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ 62.5% ተመዝግቦአል። በተጨማሪም በአምስት መስተዳድሮች ማለትም በአዲስ አበባ፣ ሐራሪ፣ ደቡብ፣ ድሬደዋ፣ ትግራይ ከእቅድ በላይ መፈጸማቸው ተጠቁሞአል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አብሮአቸው ከሚሰራቸው ድርጅቶች መካከል WATCH  የተሰኘው አጋር ድርጅት አላማ የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናቶቻቸው ጤንነት እንዲጠበቅና ሞት እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት እትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መስተዳድር ያለውን እንቅስቃሴ ለንባብ ማለታችን ይታወሳል፡፡  ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ክልል መስተዳድሮች፡-
ምን ያህል የጤና አመራሮች ስልጠና አገኙ?
ምን ያህል የጤና ባለሙያዎች ስልጠና አገኙ?
የህክምና መሳሪያዎች ምን ያህል ተሟልተዋል?
የጤና ባለሙያዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ዘልቀው እንዲያስተምሩ ምን ተመቻችቶአል?
የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ቢንያም ጌታቸው አቅርበናል፡፡
ጥ/ WARCH  የት የት አካባቢዎች ይሰራል?
WARCH  ማለት women & their children health first  ማለት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ቅድሚያ ለእናቶችና ልጆቻቸው ጤንነት የሚል መርህ ያለው ሲሆን በኢትዮጵያም ውስጥ በሶስት መስተዳድሮች ተግባሩ እንዲከናወን ሁኔታዎችን አመቻችቶአል፡፡ ፕሮጀክቱ በደቡብ በሲዳማ ዞን በሶስት ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ  ዞን በሶስት ወረዳዎች እና በጅማ በሁለት ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የሚተገበረው ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በተጨማሪ በዋናነት በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ አማካኝት ነው፡፡
ጥ/ ፕሮጀክቱ በሚከናወንባቸው ክልሎች ምን ያህል የጤና አመራሮቸች ሰለጠኑ?
መ/ WARCH  በሚሰራባቸው ሶስት ክልላዊ መስተዳድሮች ከጤና ባለሙያዎቹ አስቀድሞ ወደ 85/የሚሆኑ የጤና አመራሮች ስለፕሮጀክቱ ማለትም የእናቶችንና ህጻናትን ሞትን ለመቀነስ በሚደረገው እንቅስቃሴ እውቀቱ እንዲኖራቸው የማነቃቂያ ስልጠና ወይም አውደጥናት ለሶስት ቀናት ያህል ተካሂዶአል፡፡ በዚያም ላይ የዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የወረዳ ጤና አመራሮች፣ የጤና ጣቢያ አመራሮች እና ከክልል ጤና ቢሮ በማቀናጀት ነበር የተሳተፉት፡፡ በወቅቱም ሁሉም ተሳታፊዎች ወደቢሮአቸው ሲመለሱ ምን መስራት እንዳለባቸው እቅድ አውጥተው የተለያዩ ስለሆነ በዚያው መሰረት ይተገብራሉ የሚል እምነት አለን፡፡
ጥ/   በሶስቱም ክልሎች ምን ያህል የጤና ባለሙያዎች ሰለጠኑ?
መ/ በሶስቱም ክልል መስተዳድሮች ለ146/ ጤና ባለሙያዎች የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናቱን እንክብካቤ ለመተግበር የሚያስችለው Basic emergency obstetric & newborn care የተሰኘው ስልጠና ተሰጥቶአል። እነዚህ ባለሙያዎች ለስምንት ቀን የቃል ትምህርቱን ከወሰዱ በሁዋላ ለአስር ቀናት ደግሞ የተግባር ስልጠና ስለሚሰጣቸው ቀደም ሲል በሚያውቁት የህክምና አሰራር ላይ ተጨማሪ እና በቂ ልምድን በመቅሰም እናቶችን በየጤና ጣቢያው በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ያስችላል ተብሎ ይገመታል፡፡
ጥ/ የጤና ባለሙያዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ዘንድ ደርሰው እንዲሰሩ ምን ተመቻችቶአል?
መ/ ወላዶች ወደ ጤና ጣቢያ የማይመጡባቸው ምክንያቶች በጥናት እንደተረጋገጠው ከሆነ     ሶስት ናቸው፡፡  እነርሱም ሶስቱ መዘግየቶች በሚል ይታወቃሉ።
እናቶች ወደጤና ተቋም ሄደው በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው ግንዛቤው ሳይኖራቸው፣
በጤና ተቋም መውለዳቸው ጠቃሚ እንደሆነ ቢያውቁትም ነገር ግን የመጉዋጉዋዣ እና ጥረት ወይንም የገንዘብ እጦት በመሳሰለው ሁኔታ መጠቀም ሳይችሉ ሲቀሩ፣
ወደም ጤና ተቋም ቢሄዱም በዚያ ባለው የአገልግሎት አናሳነት ምክንያት መጠቀም ሳይችሉ ሲቀሩ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ግን የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሮጀክቱን ሲተገብር በየክልል መስተዳድሩ ካሉ አገር በቀል ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በመተባበር በጥናት የተገለጹትን መዘግየቶች ለማስወገድ በሚያስችል መንገድ የተቀናጀ አሰራር ተዘርግቶአል፡፡ ወደህብረተሰቡ ዘንድ በመውረድ ህብረተሰቡ ወደጤና ተቋም በመሄድ ግልጋሎት የማግኘት ልምድን እንዲያዳብር እና አስቀድሞውኑ ዝግጁነት እንዲኖር የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስልጠናው ለጤና ባለሙያዎች በሚሰጥበት ወቅት ባለሙያዎችን የማነሳሳት ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም ረገድ ህብረተሰቡ ወደጤና ተቋም በማይመጣበት ጊዜ በጤና ተቋም ቁጭ ብለው እንዳይጠብቁና ወደጤና ኬላ በመሄድ እንዲሁም ከጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጋር በቅርብ በመገናኘት ህብረተሰቡን እንዲያነቃቁ ይመከራል፡፡
“...በአማራ ክልል የተገኘ አንድ ተሞክሮ እንደሚያሳየው  የጤና ባለሙያዎቹ ሰልጥነው ወደየጤናጣቢያቸው ሲመለሱ ታካሚዎችን እንደተጠበቀው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ባለሙያዎቹ ወደጤና ኬላዎች በመውረድ ከጤና አክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በመሆን በየቀበሌው ያሉ እርጉዝ እናቶችን በመመዝገብ፣ የመውለጃ ጊዜያቸውን በመለየት፣ እግር ተግር እየተከታተሉ እና ምክር እየሰጡ ወደጤና ተቋም እየሄዱ እንዲወልዱ አድርገዋል፡፡ በዚህም አሰራር አርግዘው የነበሩ  እናቶች  በአብዛኛው በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በጤና ተቋም እንዲወ ልዱ አስችሎአል፡፡”
ጥ/ የእናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቱን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የመሳሪያ እጥረት ቢገጥማቸው በምን መልክ ችግሩ ይፈታል?
መ/ በእርግጥ በጤና ጣብያዎቹ ያለውን አሰራር ለማወቅ እና ድጋፍ ለማድረግ በየተወሰነ ወቅት ጉብኝት ይደረጋል። ጉብኝቱም የሚከናወነው በጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ሲሆን ጉድለት ናቸው የሚባሉት ነገሮች በሙሉ ይመዘገባሉ፡፡ ለምሳሌ ...የህጻናት እስትንፋስ መስጫ ስለማያገኙ ለአዋቂ በሚሆን መሳሪያ ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ይህንን መሳሪያ በሚጠቀሙ ጊዜ ምናልባት ጥንቃቄ የጎደለው ከሆነ ሕጻናቱን ከአደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ጉድለቶችን በእርግጥ ጊዜ ሳይሰጡ ማስተካከል ያስፈ ልጋል፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በፕሮጀክቱ ስር የታቀፉትን 48/የጤና ጣብያዎች አቅም የሚመለከት የዳሰሳ ስራ ተሰርቶ በፕላን ኢንተርናሽናል በኩል የጎደሉ እቃዎች በተወሰነ ደረጃ እንዲሟሉ ተደርጎአል፡፡ በእርግጥ ለሁሉም ጤና ተቋማት በአንድ ጊዜ ማሟላት ስለማይቻል በሁለተኛው ግዢ ደግሞ ለተቀሩት ይዳረሳል ብለን እንገምታለን። ከዚህም ጎን ለጎን መንግስትም የጤና ጣብያዎቹን አቅም ለማጎልበት አስፈላጊውን በማድረግ ላይ ስለሆነ በዚህ መልክ በተቀናጀ ሁኔታ አገልግሎቱን ለእናቶችና ለጨቅላዎቻቸው በተገቢው ለማዳረስ ጥረት ይደረጋል፡፡
ጥ/ ፕሮጀክቶቹ በሚተገበሩባቸው መስተዳድሮች ስልጠና ያገኙ የጤና አመራሮቹ ምላሽ ምን ይመስላል?
መ/ በእርግጥ በሁሉም ወረዳዎች ያሉ አመራሮች አንድ አይነት እንቅስቃሴ አያሳዩም፡፡ አንዳንዶች ከሚገባቸው በላይ ወርደው እያንዳንዱን ስራ ሲከታተሉ አንዳንዶች ደግሞ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታይታባቸዋል፡፡ በእርግጥ ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም በስራ ዝውውር ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ለዚህ እንደመፍትሔ የተቀመጠው ከአንድ ወር በሁዋላ ቀድሞ የሰለጠኑትንም አሁን በስራው ላይ ያሉትንም በመሰብሰብ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ  የማነቃቂያ አውደጥናቱን እደገና ለመስጠት እቅድ ተይዞ አል፡፡ ይህ የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናቶቻቸውን ጤና የመጠበቅ ስራ የፕሮጀክቱ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሀገር እንዲሁም የአለም ትኩረት በመሆኑ የሁሉንም ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡

Read 1206 times