Monday, 10 February 2014 08:02

አያዎ NGOር አያዎ ከሰል

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(1 Vote)

“ውቅያኖሱ በተቃርኖ የተሞላ ነው”
“ውቅያኖሱ በተቃርኖ የተሞላ ነው” ብዙ አይነት ከሰል አለ… የድንጋይ ከሰል፣ የእንጨት ከሰል፣ የመተሃራ ከሰል፣ የሺሻ ከሰል፣ የሟክ ከሰል ወ.ዘ.ተ. (ወሳኙን ዘርዝሬ ተውኩት)… እና ደግሞ… ይሄኛው ከሰል፡፡ እኔ የማወራው ስለዚህኛው ከሰል ነው፡፡ ‘አያዎ ከሰል’ ብዬ ስለሰየምኩት - የተቃርኖ ከሰል፡፡ “ውቅያኖሱ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው!” አለች አሜሪካዊቷ የስነ - ምህዳር ተመራማሪ ራቼል ካርሰን፡፡ ሴትዮዋ ይሄን ያለችው፣ ለአመታት በአካባቢ ጥበቃ መስክ ያደረገችውን ጥናት መነሻ በማድረግ፣ በውሃ አካላት ውስጥ ስላለው ህይወት በAtlantic Monthly መጽሄት ላይ በከተበችው ጽሁፏ ነው፡፡ ራቼል ካርሰን፤ ከውሃው ውስጥ አለም ያየችውን ብታይ ነው እንግዲህ ይህን ማለቷ፡፡ እኔም የውቅያኖሱን በተቃርኖ መሞላት ለመመስከር፣ እንደ ራቼል ካርሰን በአካባቢ ጥበቃ መስክ ጥናት ማድረግ ግድ አይለኝም፡፡ በአካባቢ ጥበቃ መስክ ከሚሰራ የአንድ ሎካል NGO ሰራተኞች ጋር መዋል ይበቃኛል፡፡ ከእነሱ ጋር ዋልኩ… ዋልኩና ያየሁትን አየሁ… አየሁናም እንዲህ አልኩ… “እርግጥ ነው!... ውቅያኖሱ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው!” ይሄን ያልኩት ከ‘አያዎ ከሰል’ በመነሳት ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም…. በረሃማነትን ለመከላከል ከሚሰራው NGO ጋር ወደ ወለጋ፣ ነቀምት ሄድኩ - ለዘገባ፡፡

እርግጥም ድርጅቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከደን ጭፍጨፋ እንዲታቀብ በማድረግ በኩል ሰፊ ስራ ሰርቷል፡፡ ነዋሪዎች ዛፍ መቁረጥ እየተው ነው፡፡ ችግኝ መትከል እያዘወተሩ ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን አንዳንድ የግንዛቤ ለውጥ ያላመጡ ዛፍ ነቃዮችና ከሰል አክሳዮች አሉ፡፡ ለእነዚህኞቹ የደን ቀበኞች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፣ NGOው የ3 ቀናት አውደጥናት ያካሄደው፡፡ በደን ሽፋን መቀነስና በበረሃማነት መስፋፋት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደረገ፡፡ በጊምቢ አካባቢ በደን ጥበቃ ረገድ የተከናወኑ መልካም ተሞክሮዎች ቀረቡ፡፡ ከሰል ከማክሰል ህገ ወጥ ድርጊታቸው ታቅበው፣ በመደራጀት ምድጃ ማምረት የጀመሩ 7 ሰዎች ልምዳቸውን አጋሩ፡፡ የ NGOው የደን እንክብካቤ ኤክስፐርት፤የከሰል ማክሰልንና የበረሃማነትን ግንኙነት የሚያሳይ፣ የመፍትሄ ሃሳብ የሚሰነዝር 33 ገጽ የዳሰሳ ጥናት በፓዎር ፖይንት አቀረቡ፡፡ በጥናቱ ዙሪያ ውይይት ተደረገ፡፡

ቀጣይ የድርጊት መርሃግብር ተቀረጸ፡፡ ብዙ ነገር ተደረገ… አውደ ጥናቱ በስኬታማ ሁኔታ ተጠናቀቀና በመጣንባት አነስተኛ አውቶብስ ተሳፍረን ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመርን፡፡ መንገድ ላይ በ NGOው ሶስት ሰራተኞች መካከል ውዝግብ ተፈጠረ፡፡ የውዝግቡ ሰበብ ከላይ የጠቀስኩት ‘አያዎ ከሰል’ ነው፡፡ “እንግዲህ ተስማሙ!... ጊቤ በረሃ ኬላ ላይ ያሉት ጠባቂዎች፣ ከ 1 ከሰል በላይ አያሳልፉም!...” አለ ሾፌሩ ቢጨንቀው፡፡ “ለቤት አከራዪ ሁለት ኩንታል ከሰል አመጣልዎታለሁ ብያቸዋለሁ… እኔ ነኝ የምጭነው” አለ አንደኛው፡፡ “ለቤት አከራዪ ትላለህ እንዴ!?... እኔ‘ኮ ለሚስቴ ቃል ገብቼላታለሁ!...” ብሎ ተሟገተ ሌላኛው፡፡ “ለሾፌሩ ገና ከአዲሳባ ሳንነሳ ነው፣ 2 ከሰል እንደምጭን የነገርኩት!... ከፈለጋችሁ ጠይቁት!” ብላ ምስክር ጠራች 3ኛዋ፡፡ ጭቅጭቁ ቀጠለ… እኔ በግርምት የሚሆነውን አያለሁ… የሶስት ቀኑን አውደጥናትና የአሁኑን ውዝግብ አሰላስላለሁ… “አያዎ NGO!!!… አያዎ ከሰል!!!...” እላለሁ፡፡ በነጋታው ዜና እሰራለሁ… “በረሃማነትን ለመከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ” የሚል ርዕስ ያለው ዜና!! “ውቅያኖሱ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው!”

Read 3825 times