Saturday, 15 February 2014 12:22

የፌስቡክ መስራችና ባለቤቱ ‘የ2013 ለጋስ አሜሪካውያን’ ተባሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጊዜው ቢከፋም ለጋሾች እጃቸው አልታጠፈም
50 በጎ አድራጊዎች 7.7 ቢሊዮን ዶላር ለግሰዋል
ከሴቶች ለጋሾች ይልቅ ወንድ ለጋሾች በርክተዋል

በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2013 ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ገንዘባቸውን ከለገሱ አሜሪካውያን መካከል፣ የፌስቡክ መስራቹ  ማርክ ዙከርበርግና ባለቤቱ ፒሪሲላ ቻን ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ክሮኒክል ኦፍ ፌላንትሮፒ የተባለው ተቋም ይፋ አደረገ፡፡
ጥንዶቹ የአመቱን የወደር የለሽ የቸርነት ክብር የተጎናጸፉት፣ ሲሊከን ቫሊ ፋውንዴሽን ለተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት 990 ሚሊዮን  ዶላር ዋጋ ያለው የፌስቡክ የአክሲዮን ድርሻ በመለገሳቸው ነው፡፡ ይህ በአመቱ በአሜሪካ ምድር የተሰጠ ከፍተኛ ልግስና፣ ፋውንዴሽኑን ከአገሪቱ ታላላቅ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተርታ ያሰልፈዋል ተብሏል፡፡
ዙከርበርግና ሚስቱ በአመቱ የአገሪቱ 50 አባ መስጠቶች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት አሜሪካውያን በእድሜ ለጋዎቹ ሲሆኑ በሰላሳ አመት እድሜ ላይ የሚገኙት ጥንዶቹ፣ ባለፉት ሁለት አመታትም ለዚሁ የበጎ አድራጎት ድርጅት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአክሲዮን ድርሻ በልግስና አበርክተዋል።
ጥንዶቹ የለገሱት ገንዘብ በትምህርትና በጤና ዘርፎች ለሚከናወኑ ስራዎች ይውላል ተብሏል፡፡
ክሮኒክል ኦፍ ፌላንትሮፒ የአመቱ ለጋስ ብሎ በሁለተኛነት ያስቀመጣቸው፣ ቴክሳስ ኢነርጂ የተባለው ኩባንያ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ ጆርጅ ሚሼል ናቸው፡፡ ባለፈው ሃምሌ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት እኒህ ባለጠጋ፣ቤተሰባቸው ለበጎ አድራጎት ድርጅት እንዲሰጥላቸው አደራ ብለው በሄዱት 750 ሚሊዮን  ዶላር ነው ለዚህ ክብር የበቁት፡፡
ከናይኪ ኩባንያ መስራቾች አንዱ የሆኑት ፊል ናይት እና ባለቤታቸው ፔኔሎፔም፣ ለኦሪገን ሄልዝ ኤንድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ፋውንዴሽን የካንሰር ምርምር እንዲውል መዥረጥ አድርገው በሰጡት 500 ሚሊዮን  ዶላር ከአገሪቱ የአመቱ ቀዳሚ ለጋሶች ሶስተኛ ሆነዋል፡፡ የአሜሪካን የወደር የለሽ ቸሮች ዝርዝር በቀዳሚነት ሲመሩ የቆዩት የማይክሮ ሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስና ባለቤታቸው ሚሊንዳ ጌትስ፣ በ2013 ክብራቸውን ማስጠበቅ ባይችሉም በአመቱ ከ181 ሚሊዮን  ዶላር በላይ ለግሰዋል ተብሏል፡፡ ጥንዶቹ በ2004 ለበጎ አድራጎት ተግባር ለመስጠት ቃል የገቡትን 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን  ዶላር ቀስበቀስ መክፈል መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡
በክሮኒክል ኦፍ ፌላንትሮፒ የ2013 ወደር የለሽ ለጋሶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት 50 አሜሪካውያን፣ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች በድምሩ 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ሰጥተዋል - በ2014፡፡
በአመቱ 296 ሚሊዬን ዶላር በመስጠት በለጋሾች ዝርዝር ውስጥ የአምስተኛነትን ደረጃ የያዙት ጆን አርኖልድ እና ባለቤቱ ላውራ፣ ድጋፍ የሚሹ ወገኖቻቸውን ብቻም ሳይሆን መንግስታቸውንም በመርዳት የሚታወቁ ጥንዶች ናቸው፡፡ ባልና ሚስቱ ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ መንግስት መዘጋቱን ተከትሎ በተከሰተ የአቅም ማጣት ችግር ላይ ፈጥነው ደርሰዋል፡፡ መንግስት በወቅቱ ትምህርት ቤቶቻቸው ተዘግተው ቤት ሊውሉ የነበሩ 7ሺህ ያህል አሜሪካውያን ህጻናትን ትምህርት ማስቀጠል የቻለው፣ እነዚህ ጥንዶች ባበደሩት 10 ሚሊዮን  ዶላር ነው፡፡
በአመቱ የለጋሾች ዝርዝር ውስጥ ዙከርበርግን ጨምሮ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎች አምስት ታዋቂ ግለሰቦችም ተካተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢቤይ መስራች ፔሪ ኦሚድያር፣ የጎግል መስራች ሰርጌይ ብሪንና ከማይክሮሶፍት መስራቾች አንዱ የሆኑት ፖል አለንና ሚስቶቻቸው ይጠቀሳሉ።
ወንዶች በሚበዙበት በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ለጋሾች፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተንገራገጨ ባለበት ወቅት ሳይሰስቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለበጎ አድራጎት ስራ መለገሳቸው ያስደንቃቸዋል ተብሏል፡፡
ለጋሾቹ በአመቱ ከሰጡት ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያህሉን የወሰዱት የእርዳታ ድርጅቶች፣ ሆስፒታሎችና ኮሌጆች ሲሆኑ፤ የተቀረውም በህክምና ምርምር፣ ሰብአዊ አገልግሎቶች፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በህጻናትና ወጣቶች ወዘተ ዙሪያ ለሚሰሩ ድርጅቶችና ተቋማት እንደሚውል ተነግሯል፡፡


Read 2227 times