Saturday, 15 February 2014 12:25

ደንበኞች በቅድመ-ክፍያ የመብራት አገልግሎት አሰጣጥ ተማረዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“በሁሉም ማዕከላት አገልግሎቱ ያለእንከን እየተሰጠ ነው”

በአዲስ አበባ ተግባራዊ በተደረገው የቅድመ ክፍያ የመብራት አገልግሎት አሰጣጥ ደንበኞች መማረራቸውን እየገለፁ ሲሆን መብራት ሃይል በበኩሉ፤ በሁሉም ማዕከላት አገልግሎቱ ያለእንከን እየተሰጠ ነው ብሏል፡፡
ካዛንቺስ በሚገኘው የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ማዕከል፣በክፍያ አሰባሰብ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ ያገኘናቸው አንዳንድ ተገልጋዮች፤ ክፍያው የሚሰበሰበው በአንድ ሠራተኛ ብቻ በመሆኑ ወረፋ በመጠበቅ የስራ ጊዜያቸውን እያባከኑ እንደሆነ በምሬት ገልፀዋል፡፡ ረጅም ወረፋ ሲጠብቁ ቆይተው  የምሣ ሰአት አሊያም የስራ መውጫ ደርሷል እየተባሉ ወደ ቤታቸው የሚመለሱ በርካታ ደንበኞች እንዳሉ የታዘበ አንድ ወጣት የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ደንበኛ፤ እሱም ራሱ በተመሳሳይ ምክንያት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ወደ ማዕከሉ መመላለሱን ገልጿል።
ከሃያት አካባቢ የአገልግሎት ካርዳቸውን ለማስሞላት ካዛንቺስ ድረስ መምጣታቸውን የገለፁት አንድ ጎልማሳ በበኩላቸው፤ ድርጀቱ በከተማዋ አንድ ማዕከል ብቻ በመክፈቱ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ተገልጋዮች ለእንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል። የአገልግሎቱ መጀመር በተለይ የመብራት አጠቃቀምን በዘመናዊ መልኩ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የሚገልፁት ደንበኞች፤ መብራት ሃይል በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ማዕከላትን በስፋት በመክፈት፣ አገልግሎቱን በተደራጀ የሰው ሃይል በመስጠት ደንበኞችን ከእንግልትና ከምሬት መገላገል ይችላል  ብለዋል፡፡
የደንበኞችን ቅሬታና በአጠቃላይ አገልግሎቱን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን የውጭና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ፤አገልግሎቱ ከሁለት አመት በፊት እንደተጀመረና የደንበኞችን ወጪና ጊዜ ለመቆጠብ ታስቦ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ በከተማዋ አገልግሎቱን የሚሰጡ 29 ማዕከላት እንዳሉ፣ ሁሉም አገልግሎቱን በተቀላጠፈ መልኩ ለ174ሺ35 ደንበኞች ያህል እየሰጡ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ ያሉት 3 ማዕከላት እና በቢሾፍቱ ያሉት 2 ማዕከላት፣ በአጠቃላይ ለ26ሺ39 ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡ የቢል ህትመት ወጪን እንዲሁም የቆጣሪ አንባቢንና የገንዘብ ሰብሳቢን ድካም በማስቀረት ረገድ አዎንታዊ ሚና እንዳለው የሚነገርለት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ አገልግሎት ተግባራዊ በተደረጉባቸው ሶስቱ ከተሞች ለ200ሺ104 ደንበኞች አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነም አክለው  ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ አንድ የአገልግሎት ማዕከል ብቻ በመኖሩ ተቸግረናል የሚለውን የደንበኞች ቅሬታ አስመልክቶ  የተጠየቁት አቶ ምስክር ሲመልሱ “ካዛንቺስና ሜክሲኮ ያሉት እንደ ዋና ማዕከል እሁድን ጨምሮ አገልግሎት የሚሰጥባቸው እንጂ ብቸኛ ማዕከላት አይደሉም፤ በከተማዋ ያሉት 29 ማዕከላት በቂ ሙያተኛ ተመድቦላቸው አገልግሎቱን በተቀላጠፈ መልኩ እየሰጡ ነው” ብለዋል፡፡ በቅርቡም የሃይል ብክነትን  ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሌሎች ዘመናዊ ቆጣሪዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መስሪያ ቤቱ እቅድ መያዙን አቶ ምስክር ጠቁመዋል፡፡  

Read 2326 times