Saturday, 15 February 2014 12:27

በደህንነት ኃላፊው ላይ የቀረበውን የክስ ማሻሻያ ጠበቆች ተቃወሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

            በቀድሞው የሃገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ አቶ ወልደሥላሴ ወ/ሚካኤልና የቅርብ ዘመዶቻቸው ላይ የቀረበውን የሙስና ክስ፣አቃቤ ህግ እንደገና አሻሽሎ ያቀረበ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው፤ ማሻሻያው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት የቀረበ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
ቀደም ሲል አቃቤ ህግ፣ በደህንነት ኃላፊውና በክሱ በተካተቱት ወንድምና እህታቸው እንዲሁም የቅርብ ወዳጃቸው ላይ ባቀረበው ክስ፣ የአቶ ወ/ሥላሴ ሃብት ወደ ሌሎች ተከሳሾች ተላለፈ የተባለበት መንገድ ግልፅ አይደለም በሚል ጉዳዩ ተብራርቶ እንዲቀርብ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ባለፈው ሰኞ  አቃቤ ህግ ማሻሻያውን ለጽ/ቤቱ በፅሁፍ አቅርቧል፡፡
ማሻሻያውን የተመለከቱት የተከሳሽ ጠበቆችም፣ ማሻሻያው በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት የቀረበ አይደለም፣ ግልፅ ባለመሆኑ ለመከላከል ያስቸግራል የሚል ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም የጠበቆቹን ቅሬታ ከተቀበለ በኋላ  አጣርቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለየካቲት 13 ቀን 2006 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በቀድሞው የደህንነት መስሪያቤት ኃላፊ አቶ ወ/ሥላሴና የመከላከያ ሰራዊት ባልደረባ በነበረው ወንድማቸው አቶ ዘርአይ ወ/ሚካኤል እንዲሁም በእህታቸው ወ/ት ትርሐስ ወ/ሚካኤልና በቅርብ ጓደኛቸው አቶ ዳሪ ከበደ ስም የመኖሪያ ቦታን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችንና በአጠቃላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ይዞ መገኘት በሚል መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡    



Read 3516 times