Saturday, 15 February 2014 12:44

ከቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ጋር - በመኖርያ ቤታቸው ውስጥ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(14 votes)

አቶ ግርማ እና የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት ሁለተኛ ክስ ቀርቦባቸዋል
የተከሰስንበትን ጉዳይ በግል ጠበቃ ቀጥረን እየተከራከርን ነው
ግቢው ደን ስለሌለው እንጂ ከቤተመንግስት አይለይም
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ደሞዛቸው ስንት ነበር? ጡረታቸውስ?

የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ የ12 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ተጠናቆ ከቤተመንግስት ሲወጡ፣የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት ከተከራየላቸው መኖርያ ቤት ጋር በተገናኘ  ውዝግቦች የተፈጠሩ ሲሆን ሁለት ክሶችም ተመስርቶባቸዋል - በእሳቸውና በፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት ላይ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ወደ መኖርያ ቤታቸው ያመራሁትም በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ላነጋግራቸው አስቤ  ነው፡፡ በወር 400 ሺ ብር ገደማ ኪራይ የሚከፈልበት ባለ 3 ፎቅ መኖርያ ቤታቸው  በኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳና፣ ከአክሱም ሆቴል በስተጀርባ ነው፡፡
መኖርያ ቤታቸው በር ላይ ስደርስ የተቀበሉኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት ነበሩ፡፡ ጉዳዬን አስረድቼ  ቀጠሮ መያዜ ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ቅጥር ግቢው እንድዘልቅ ተፈቀደልኝ፡፡ በስተግራ በኩል ቀልብ በሚማርከው መናፈሻ ላይ ዓይኖቼን እያንከራተትኩ ነበር ወደ ዋናው መኖርያ ቤት መግቢያ በር ያመራሁት፡፡
ኮሪደሩ በቀጥታ ወደ እንግዳ መቀበያውና የመመገቢያ ክፍሉ ያደርሳል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የአቶ ግርማን ልጅ መናንና በጥናት ላይ የነበሩ ሁለት ልጆቿን አገኘን፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላም ምቾት በሚሰጥና በሚደላ የቆዳ ሶፋ ላይ አረፍ እንድንል ተጋበዝን፡፡ ቀና ስል ግድግዳው ላይ ትልቅ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን ተሰቅሎ  ተመለከትኩ፡፡ ዓይኖቼ ቀጥሎ ያነጣጠሩት በቀድሞው ፕሬዚዳንት  ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ቤተሰቦቻቸው ፎቶግራፎች ላይ ነበር፡፡ ፎቶዎቹም ግድግዳው ላይ ነው የተሰቀሉት፡፡ ለጥቂት ደቂቃ ከተቀመጥኩ በኋላ ከሚደላው ሶፋ ላይ ለመነሳት ተገደድኩ፡፡ ሜሮን በተባለችው  የመኖርያ ቤቱ አስተናጋጅ አማካኝነት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢሮ ወደሚገኝበት ሁለተኛ ፎቅ ለመሄድ፣ የዳን ቴክኖ ክራፍት ሥሪት በሆነው አሳንሰር (ሊፍት) ውስጥ ገባን፡፡ አሳንሰሩ ከ1ኛ ፎቅ እስከ 3ኛ ፎቅ ድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡  
  ገና ወደ ቢሮው እንደዘለቅሁ ዓይኔ ያረፈው ጠረጴዛው ላይ ወዳሉት የወረቀቶች ክምር ነበር፡፡ “አቶ ግርማ አሁንም ይሰራሉ ማለት ነው?” - ስል ራሴን ጠየቅሁኝ፡፡ በዊል ቼር ላይ የተቀመጡት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ትንሽዬ ሬድዮ ከፍተው እያዳመጡ ነበር፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ዓይን መግለጫ ወግ ስናወጋ ቆየንና ወደ ቁምነገራችን ገባን፡፡ መቅረፀ ድምፄን አውጥቼ ቃለመጠይቁን ጀመርኩ፡፡
ከ12 ዓመታት የቤተመንግስት ኑሮ በኋላ በግለሰብ የኪራይ ቤት ውስጥ መኖር ምን ይመስላል?እንዴት ነው  ቤቱ ተስማማዎት?
በጣም ደስ የሚል ቦታ ነው፤ደን ስለሌለው ነው እንጂ ከቤተመንግስት አይለይም፡፡ ቤተመንግስት በደን የተሞላ ነው፡፡
በዚህ ቤትና ቀድመው ሊከራዩት በነበረው ቤት ዙሪያ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የዘለቁ  ውዝግቦች ተፈጥረዋል፡፡  የውዝግቦቹ መንስኤ ምንድነው ?
እኔ እዚህ ውዝግቡ ውስጥ የለሁበትም፡፡ ማን እንደተከራየውና እንዴት እንደተከራዩት አላውቅም።  የሆኖ ሆኖ የፅ/ቤቱ ሃላፊ ትመስለኛለች፡፡  መጀመሪያ የተከራየችው  ቤት የሚመቸን አልሆነም፤ ቤተሰቦቼም  ይሄኛውን መረጡ፡፡ በዚህ ስንስማማ የበፊቱን  ውል አቋርጠው እዚህ ገባን፡፡ በዚህ የተነሳ  ነው ውዝግቡ የተፈጠረው፡፡
ውዝግቦቹ  ፍርድ ቤት ከመድረሳቸው በፊት እርስዎ መፍትሄ ለማበጀት አልሞከሩም?
ይሄ የአስተዳደር ጉዳይ ስለሆነና  የፅ/ቤቱን  ሃላፊን ስለሚመለከት፤ እዛ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ገብቼ ይህንን አድርጉ፣ ይህንን አታድርጉ አላልኩም።
የፕሬዚዳንት ፅ/ቤቱ ቤቱን ሲከራይ ያውቁ ነበር?
ቤት ሲፈልጉ እንደነበርና እንደምንከራይም አውቃለሁ፡፡ እንደውም ከፈረንሳይ በላይ እንጦጦ አካባቢ ተገኝቶ ነበር፤ ይሄኛው ቤት ሶስተኛ ነው፡፡ ልጄ ይሄን አይታው ይሻላል ብላ ተመረጠ፡፡
እርስዎስ --- መርጠውት ነበር?
እኔ እንደውም አዲስ አበባ የመኖር ሃሳብ አልነበረኝም፤ አገሬ እኖራለሁ ብዬ ነበረ፡፡
ከሥልጣን የተሰናበቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች መኖሪያ ቤትን  በተመለከተ ህጉ ከአራት እስከ አምስት መኝታ ክፍሎች ያሉት በማለት ያስቀምጣል፤ ይሄ ቤት ግን ከሃያ በላይ ክፍሎች አሉት፡፡ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ህጉ ይሄንን ያህል ክፍል ይከራያል የሚል አይመስለኝም፤እንደሚበቃው መጠን ነው የሚለው፤ ቤተሰቤ ሃያ ቢሆን የሚበቃኝ ሃያ ክፍል ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ገደብ ያለው ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኛ በዚህ ቤት ውስጥ ሰራተኞችን ጨምሮ ከአስር በላይ ሆነን ነው የምንኖረው፡፡
ይሄን ቤት ያከራየው የኮሚሽን ሠራተኛ የአገልግሎት ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ክስ ሲመሰርት፣ የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት የጠበቃ ባለሙያ የለኝም በሚል ፍትህ ሚኒስቴር ወክሎ እንዲከራከርለት  ጠይቋል፡፡ እርስዎ ፕሬዚዳንት ሳሉም ፅ/ቤቱ የህግ ባለሙያ አልነበረውም ማለት ነው?
ይህን ያወቅሁት አሁን ነው፡፡ በፊት ጠበቃ የሚያስፈልገው ነገር ነበር ወይ? አላውቅም። ለቤቱ  ጉዳይ ጠበቃ የሚያሳፈልገው ከሆነም ለእለቱ የሚሆን አንድ ጠበቃ መቅጠር የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ የሆነ ሆኖ መንግስት ሲከሰስ የሚመልስበት መንገድ ስላለው ሊሆን ይችላል ወደ ፍትህ ሚኒስቴር የላከው፡፡ ቤቱን ካገናኘን የኮሚሽን ሰራተኛ ጋር የተዋዋለችው ልጄ ናት። ክሱም ለእኛ በግል ስለሆነና  ፅ/ቤቱ አይወክልም ስለተባልን፣በግላችን ጠበቃ ቀጥረን እየተከራከርን ነው፤ፍርድ ቤቱም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት አብዛኛው ስራ ከህግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንዴት የህግ ባለሙያ የለውም?
አዋጅ ማፅደቅ፣ ለታራሚ ምህረት መስጠት ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች ነበሩ፤ ጠበቆች ግን አይደሉም፡፡
በሥልጣን ዘመንዎ በየአመቱ ስንት እስረኞች ምህረት ይደረግላቸው ነበር?
 ምህረት እንደጠየቁትና ይገባቸዋል እንደተባሉት አይነት ነው፤ አምስት ሺህ ስድስት ሺህ ይደርሳሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ሳሉ ደሞዝዎ ስንት ነበር? አሁንስ ጡረታዎ?
ደሞዜን መናገር አስፈላጊ ከሆነ ዘጠኝ ሺህ ብር ነበር፤ አሁንም አልተቀነሰም፡፡
ከፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ በኋላ ምን እየሰሩ ነው?
አሁን ምንም የምሰራው የመንግስት ስራ የለም። በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ቼር ኢትዮጵያ ከሚባል በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር ሽምጥ ሸለቆ ውስጥ የጠፉትን ደኖች መልሶ ለማልማት እየተጋን ነው፡፡
አሜሪካ ውስጥ ፕሬዚዳንቶች ከስልጣን ከወረዱም በኋላ በፕሬዚዳንትነት ስያሜያቸው ነው የሚጠሩት፡፡ ፕሬዚዳንት ክሊንተን --- ፕሬዚዳንት ቡሽ -- እየተባሉ፡፡ እርስዎስ?
ያው ነው፤ እኔ “የቀድሞው” የሚለውን ጨምሬበታለሁ እንጂ፡፡
ከወዳጅ ዘመድዎ ጋር ያለዎት ግንኙነት ቤተመንግስት በነበሩ ጊዜና አሁን ምን ይመስላል?
ምንም ልዩነት የለውም፤ ዘመድ ወዳጅ የሆነ በፊትም አለ፤አሁንም አለ፡፡
በስልጣን ላይ ሳሉ ቁጭ ብድግ ሲል ከርሞ፣ ከወረዱ በኋላ ፊቱን ያዞረና የታዘቡት ሰው አለ?
እንዲህ አይነት ሰው እኔ ጋ መጥቶ አያውቅም፣ድሮ የሚመጣ አሁንም ይመጣል፡፡ የሚጠይቁኝን እኔ ማድረግ ከቻልኩ አደርጋለሁ፤ ካልቻልኩ ደግሞ ለሚችል ሰው እንዲያደርጉላቸው እነግራለሁ፡፡
ቃለመጠይቁን እንዳጠናቀቅሁ መኖርያ ቤታቸውን መጎብኘት እችል እንደሆነ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ጠየቅኋቸው፡፡ እሳቸውም “በደስታ” አሉና ወደ ቢሮአቸው ያመጣችኝን ሜሮንን  መደቡልኝ፡፡  ከሜሮን ጋር ጉብኝቴን ጀመርኩ - ከምድር ቤት፡፡
በምድር ቤቱ  ስድስት የሰራተኞች ማደሪያ ክፍሎች፣ አንድ ጌጣጌጦችና ፎቶዎችን የያዘ ሰፊ ክፍል፣ አንድ በዘመናዊ የስፖርት መሳሪያዎች የተደራጀ ጂም፣ አንድ ስቲም ባዝና የምግብ ማብሰያ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡
ከዋናው የመኖርያ ቤቱ ህንፃ  በስተኋላ ስድስት የፌደራል ፖሊስ አባላት የማረፊያ ክፍሎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ክፍሎች ትይዩ ደግሞ ትልቅ የመዋኛ ገንዳ ይገኛል፡፡
በውጪ በኩል የሚያስወጣውን ደረጃ ይዘን ወደ አንደኛ ፎቅ ወጣን፡፡ በዚህ ፎቅ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መኝታ ክፍልና የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ናቸው ያሉት፡፡ ወደ ሁለተኛ ፎቅ ወጣን- የፕሬዚዳንቱ ቢሮ ያለበት ማለት ነው፡፡ ከቢሮው ሌላ የአቶ ግርማ ልጆችና ባለቤታቸው መኝታ ክፍሎች እንዲሁም የእንግዶች ማረፊያን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ክፍሎች ይዟል፡፡
በመጨረሻም የቤቱ አናት (ቴራስ) ላይ ወጣን። አዲስ አበባ ቁልጭ ብላ ነው የምትታየው፡፡ ዘመናዊ ባር የተዘጋጀለት ቴራሱ፤ ለትላልቅ ድግሶችና ፕሮግራሞች የሚሆን ዘና ያለ ቦታ  አለው፡፡
የአቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ መኖርያ ቤትን የሚጠብቁ እዚያው ነዋሪ የሆኑ አምስት የፌደራል ፖሊስ አባላት ያሉ ሲሆን ስድስት ተመላላሽና ቋሚ የፅዳትና የምግብ ዝግጅት ሰራተኞችም እንዳሉ ከሜሮን ማብራርያ ለመረዳት ችያለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን በመላላክ የምታገለግል አንዲት ሠራተኛም አለች፡፡ ከእነአጃቢያቸው ጭምር አራት መኪኖችም ተመድቦላቸዋል - የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፡፡

Read 7644 times