Saturday, 15 February 2014 13:01

‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰሚ ጠፋሳ! የተበላሸ ነገር ሲጠቆም… የመፍትሄ ሀሳብ ሲቀርብ… “ኧረ ቤቶች!” ሲባል እህ ብሎ የሚያዳምጥ፣ “አቤት…” ብሎ በር የሚከፍት ተመናመነብንሳ! እርስ በእርሳችን ያለን አመለካካት ከመዛባቱ የተነሳ ነገራችን ሁሉ.. አለ አይደል… ዶፉን እንኳን እየለቀቀው “ኧረ ዝናቡ ልብሱን አበሰበሰው፣ ወደ ውስጥ አስገቡት…” ሲባል ነገርዬው “ስለ ልብስ መበስበስ አንተ ነሀ የምትነግርኝ!” አይነት ‘ዝምታ’ እግር ተወርች እያሰረን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በቃ፣ “‘ሞዴሊስት’ አይባልም…” “‘ዋይኔ’ ሩኒ አይባልም….” “ኒውዘርላንድ’ አይባልም…” እንዲህ አይባልም፣ እንዲያ አይባልም ቢባል ሰሚ ጆሮ ጠፋ አይደል!… “ምን ይባል፣ ምን አይባል ማነው ለእኔ የሚነግረኝ…” አይነት ‘ዝምታ’ ውጦ ነው፡፡ (አንዳንድ የስፖርት ጋዜጠኞች እኛ በምንከታተለው ቲቪ የሚመጡ ዘጋቢዎች “ዌይን ሩኒ” ሲሉ፣ እናንተ በምትከታተሉት ቲቪ የሚወጡ ዘጋቢዎች “‘ዋይኔ’ ሩኒ…” የሚሉት…እኛን ማጋጫታቸው ነው እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… እንኳን ቁማር ይወዳሉ የሚባሉት… አባቱ ናቸው አጎቱ… አልሰሙን! አሀ…ልክ ነዋ…“እንወራረድ ዌይንዬን ሀበሾች ‘ዋይኔ’ እያሉ ነው የሚያቆላምጡት…” ብለው ሊወራረዱ ይችሉ ነበራ!)
ይሄ ‘ሞዴሊስት’ የሚሉት ነገርማ…ራሳቸው በሞዴሊንግ ኢንደስትሪው ውስጥ ያሉ ሰዎች ሲደጋግሙት ግራ ግብት አይላችሁም! ነው ወይስ ሞዴሊስት ልማታዊ ሞዴል የኒኦ ሊበራሎች ሆኖ ነው! (ምን እናድርግ ዘንድሮ…እንትን ያልናት ሁሉ በልማታዊነትና በኒኦ ሊበራሊስትነት ሚዛን እየተቀመጠች ግራ ገባን! “እኔን ግራ ይግባኝ…” የሚል በሌለበት ዘመን…አለ አይደል… ግራ ከመጋባት ይሰውራችሁ!)
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ “ፌይንት ሠራሁ…” ምን ማለት ነው? ምንም ይሁን ምን ከ‘ሞዴሊስት’ ይሻለኛል፡፡
ደግሞላችሁ…“በጉዳዩ ‘ኢንተረስቲንግ’ ነኝ…” የምትለዋ ትስማማኛለች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…“እህ!” የሚል እየጠፋ፣ ነገርዬው ሁሉ የ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ ነገር ሆነብን!
የምር እኮ… ላይ የሰንበቴ ጌሾ ማስጣት የሚችለው ወንበር ላይ ከሚቀመጡት፣ እታች ከአቧራው ጋር አብረን እየቦነንን ያለነው ሁላችን…“እህ…” ብሎ መስማት ይቅርታ የማይደረግለት ሀጢአት ነገር እያደረግነው ነው፡፡
“እዚህ ቦታ የጎደለ ነገር አለ…” “እዛ ቦታ የተዛባ ነገር አለ…” ሲባል እህ ብሎ ለማዳመጥ ፈቃደኛ አለመሆን ‘ብሔራዊ መለያ’ አይነት ነገር እየሆነ እኮ ነው!
“ኧረ እዚህ ቦታ ውሀ ከጠፋ አምስት ቀኑ፣ ውሀ ጥም ማለቃችን ነው…” ሲባል ማን ሰምቶ!
“ኧረ በሞባይል ከመደዋወል ከቦሌ ጉለሌ የምንፈልገው ሰው ያለበት መሄዱ እየቀለለ ነው…” ብንል ማን ሰምቶ! (ይልቁንም እንደ ልባችን ማግኘት ባቃተን አገልግሎት… ስለ ‘ልዩ ቅናሽ’ ዕድሎች ይነገረናል፡፡)
“ኧረ እዚህ ቦታ ቧንቧ ፈንድቶ መፍሰስ ከጀመረ ሳምንቱ…” ሲባል ማን ሰምቶ!
“ኸረ ከተማዋ ቆሸሻ፣ ለነዋሪም የጤና ቀውስ ለጎብኚም ‘የዕይታ ቀውስ’ እየፈጠረች ነ”ው…” ሲባል ማን ሰምቶ! (ይልቁንም ስለ አፍሪካ ዋና መዲናነቷ፣ እየዘመነችና እያሸበረቀች ስለ መሆኗ እንሰማለን!)
“ኧረ ታክሲው ከፍጥነት በላይ ነው እየበረረ ያለው፣ ሾፌር ረጋ በል…” ሲባል ማን ሰምቶ! (ይልቁንም… አለ አይደል… በቀደም አንድ ፕሮግራም ላይ እንደሰማነው በምሽት መሀል መንገድ ላይ መኪናውን አቁሞ “ከፈለጋችሁ ወረዱ…” አይነት መልስ ነው የምናገኘው፡፡
እናላችሁ…“እህ!” የሚል እየጠፋ፣ ነገርዬው ሁሉ የ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ ነገር ሆነብን!
ሀሳብ አለን… ለዓለም አቀፍ የአእምሮ ንብረት ምናምን ድርጅት ማመልከቻ ይግባልን፡፡ ልክ ነዋ…. እነሱ ጤፊቷን ‘ሊወስዱብን’ ዳር ዳር እያሉ አይደል…እኛም ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ የሚሉት አጠራሮች  በእኛ የአእምሮ ንብረትነት ይመዝገቡልን። በሌላ አገር እንደዚህ ስለመባሉ የምናውቀው ነገር የለማ!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ሰዎች አለቃ ሲሆኑ የሚባሉትን ለመስማት የሚከብዳቸው ለምንድንው? ነው ወይስ እዚህ አገር ብቻ ድምጽ ከ‘ታች ወደ ላይ’ አይጓዝም እንዴ! ልክ ነዋ…ምንም ነገር እዚች አገር ሲገባ ‘ሞዲፋይድ’ ስለሚሆን (ቂ…ቂ…ቂ…) የድምጽ ሞገድ አካሄድም ‘አገሪኛ ተች’ ተሰጥቶት እንደሆነ ብዬ ነው፡፡ ስሙኝማ… “መጠጥ ከድራፍት ወደ ብሉ ሌብል ሲለወጥ የመስሚያ ህዋሳቶችን ይተናኮላል…” ምናምን የሚል ‘ጥናት’ የሰማ ሰው ካለ ሹክ ይበለኝማ! (እንትና ‘ጎልድ ሌብሉ’ ጠርሙሱ ስንት ነበር ያልከኝ? ለምን ይዋሻል… የእንትንን አውራጃ ህዝብ ቁጥር የነገርከኝ መስሎኝ ነበር!)
እኔ የምለው ቴሌ አንዳንዴ ወይ ለመልካም ምኞት መግለጫ  ወይ ጠንቀቅ በሉ ለማለት የሚልካቸውን የጽሁፍ መልእክቶች ልብ ብላችሁልኛል! ይሄ ኬብሉ ምናምን ሲቆራረጥ “በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች የተነሳ…” ምናምን ይባላል፡፡ እኔ የምለው…እነኚህ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ‘የቴሌ እንግሊዘኛ’ ላይም መመላለስ ጀመሩ እንዴ! (ቂ…ቂ…ቂ…) ኧረ እባካችሁ…አታሳጡን! ይቺን እዩልኝማ…
(Please don’t respond to fraud text/SMS falsely sent using +228 & other country code as if you would win a lottery/gift or selected for award. Ethio telecom)
እናላችሁ…እኛ ብዙ ባይገባንም ይሄን የሚያክል ግዙፍ ድርጅት ከዚህች ሻል ያለች የ‘ፈረንጅ አፍ’ መጻፍ አቃተውሳ! ነው… ወይስ ኮንትራቱ ሁሉ ወደ ምሥራቅ ሲሄድ ‘የፈረንጅ አፍ’ም ወደ ምሥራቅ ዘመም ማለት ጀመረች! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…አይገርማችሁም…ለምንድነው “እህ…” ብለን የምንሰማ ቁጥራችን እንደ ኑሯችን ቁልቁል የሆነው!
የተበላሸ ነገረ እየታየ፣ መስመር የለቀቀ ነገረ እየታየ… “ኧረ ይሄን ነገር አንድ በሉት…” ምናምን ሲባል…. ‘ቄሱም መጣፉም’ ጭጭ!  እናላችሁ የሚሰማ እየጠፋ ነው፡፡ አሁንማ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ድፍን አገር ጉድጓድ ምሶ ያደፈጠ ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ… በየቀኑ የምንሰማቸው፣ የምናያቸውና ያየንና የሰማን የሚመስሉን ነገሮች በዝተው አደነዘዙና!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ….ኳስ ተጫዋቾቹ ‘ውራ’ ሆነው የተመለሱበት ቻን ከመሄዳቸው በፊት “ብናሸንፍ ስንት ሽልማት ትሰጡናላችሁ?” ብለው ጠይቀው ነበር የሚሉት ነገር ግርም አላላችሁም! የምር ‘የጉድ ዘመን’ ቢባል አይበዛበትም፡፡
ኮሚክ እኮ ነው… ለአፍሪካ ዋንጫ ዋዜማ እኮ “የተገባልን ገንዘብ አልተሰጠንም…” ምናምን ተብሎ የልምምድ አድማ ነገር ነበር፡፡ ያን ሰሞን እኮ… እኛም የሚዲያ ሰዎች…አለ አይደል… በሌሎች አገሮች ተጫዋቾች የጠላነውና ሲሰቀጥጠን የኖረ የአገርን ጉዳይ በ‘እርግጡን ተናገር’ መደራደር እኛው ዘንድ መጣና አረፈው!… ከማለት ይልቅ “ቶሎ ስጧቸው እንጂ!” አይነት ነገር ውስጥ መግባታችን… የሚታዘበን ቢኖር ኖሮ አስተዛዛቢ ነበር፡፡
“አይ አገር አይ አገር ኢትዮጵያ…” ምናምን የሚል ዘፈን ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ ለዓለም ዋንጫ የደረስንበት መድረሱ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቀ እንደሆነ ሁሉ፣ ባንዲራ ለብሶ አገር ለመወከል ስንት ትበጥሳላችሁ አይነት ነገርም ያየንበት ጊዜ ትዝ አይለንም፡፡ (ይቺ አገር ተጠብቃ እዚሀ ድረስ የዘለቀችልን በሰላም አደባባይም ይሁን በጦር ሜዳ ‘በባንዲራዋ ስር’ አገልግሎት ለመስጠት “መጀመሪያ በሂሳቡ እንስማማ…” በማለት አይደለም፡፡
እናማ…የእግር ኳሳችን ነገር በአሰልጣኞች ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት መዛባቱ፣ በተጫዋቾች ዕድሜ ሽወዳ… ምናምን ብቻ ሳይሆን መስተካካል ያለባቸው ብዙ ነገሮች ያሉ አይመስላችሁም፡፡ (“ሜዳሊያ ብናመጣ ስንት ትበጥሳላችሁ…” ሳይሉን በየኦሎምፒኩ መድረክ፣ በየዓለም ሻምፒዮና አንገታችን ቀና እንዲል የሚያደርጉን አትሌቶቻችን ክብር ምስጋና ይድረሳቸው፡፡)
እናላችሁ…በእግር ኳስም ነገርዬው የሚሰማ አልገኝ እያለ ተቸግረናል፡፡ ከስር በመቶ የሚቆጠሩ የተዋጣላቸውን ተጫዋቾች ኮትኩቶ ስለማምጣትና የዛሬ አምስትና ሰባት ዓመት ከማንኛውም አገር እግር ኳስ ቡድን ጋር የሚስተካካል ቡድን ስለመገንባት ከማሰብ ይልቅ አሁንም የ‘ዕቅዳችን አድማስ’ ከሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ “ኧረ እባካችሁ ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት እከሌ ይምጣ እከሌ ይቅር ከማለት ይልቅ በመላ አገሪቱ ውስጥ በወጣቶች ላይ ሥራ ይሠራ ሲባል…ማን ሰምቶ! ዘፈናችን “ሁልጊዜ አበባዬ…” ነገር ሆነብን፡፡
(በነገራችን ላይ በወከባው ውስጥ ሰምጠው ሳይቀሩ፣ “የአገር ጉዳይ ነው…” በሚል ሽፋን ቀሺሙን “አሪፍ ነው…” ሳይሉ ስለ ረጅም ጊዜ ዕቅድ አስፈላጊነት ሲናገሩ የዘለቁ የሚዲያ ሰዎች መኖራቸው አሪፍ ነው፡፡ በዚሁ ቀጥሉማ!)
እናላችሁ…ነገርዬው ሁሉ የ‘ሞዴሊስት’ እና ‘ዋይኔ’ ሩኒ ነገር ሆነብን!
“መከራው ያላለቀለት በሬ ከሞተ በኋላ ቆዳው ነጋሪት ይጠፈራል” የሚሏት አባባል አለች፡፡ ከዕድለ ቢሱ በሬ ዕጣ ፈንታ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5099 times