Saturday, 15 February 2014 13:22

በፒያኖ ፍቅር የወደቀው ወጣት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(9 votes)

       ወጣት ይስሃቅ ካሣሁን ይባላል፡፡ ፒያኖ የመጫወት ፍላጐት ያደረበት ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር፡፡ ጊዜው 2002 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ በገርጂ የኮርያ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው የ “ጉድ ኒውስ ቸርች” አዳራሽ ፒያኖ የሚማሩ ልጆችን ሲመለከት ነው ፍላጐቱ የተቀሰቀሰበት፡፡ እሱም እንደነዚያ ልጆች ፒያኖ የመማር ዕድል ቢያገኝ ተመኘ፡፡ ግን እድል አልቀናውም፡፡ ስለዚህም በምሳ ሰዓት ሰው ጭር ሲል ወደ አዳራሹ ተደብቆ እየገባ፣ በፈቃዱ የፒያኖውን ቁልፎች መነካካት ጀመረ፡፡ የቤተክርስቲያኑ የጥበቃ ሠራተኞች ግን አላስደርስ እያሉ መከራውን አበሉት፡፡ በተደጋጋሚ አግኝተው እንዳባረሩትም ይስሃቅ ያስታውሳል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ አዳራሹን ይቆልፉበት ነበር፡፡ ክልከላው ቢያይልበትም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ የአዳራሹ በር ሲቆለፍበት  በመስኮት ሁሉ እየገባ ፒያኖ ይለማመድ እንደነበር ይናገራል፡፡
አንድ ዓመት ያህል እንዲህ ካሳለፈ በኋላ የታዳጊውን የፒያኖ ፍቅር ያስተዋሉት የቤ/ክርስቲያኑ ኃላፊ፤ ሌላ አዳራሽ ውስጥ ባለ ፒያኖ እንዲለማመድ ፈቀዱለት፡፡ ይሄኔ ይስሃቅ በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ስራዬ ብሎ ፒያኖ ማጥናት የጀመረው፡፡ “በቀን ለ10 ሰዓታት ቁጭ ብዬ ፒያኖ እለማመድ ነበር” ይላል ወጣቱ የፒያኖ ተጫዋች። መጀመሪያ ላይ ከኢንተርኔት ሙዚቃዎችን እየገለበጠ ነበር የሚለማመደው፡፡ ታዋቂና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን ለማወቅና ለማጥናትም ብዙ እንደጣረ ይናገራል፡፡ ከዚያም ትኩረቱን ወደ አገርኛ የፒያኖ ሙዚቃዎች በማድረግ በተለይ የእማሆይ ፅጌ ማርያም ዜማዎችን ይሞካክር ጀመር፡፡ አሁንም ድረስ በእማሆይ ሥራዎች እንደሚመሰጥ ገልጿል፡፡
ቤተክርስትያኑ ውስጥ የዕውቅ ሙዚቀኞችን ስራዎች ሲጫወት ያዳመጡ ሰዎች “ለምን የራስህን ሙዚቃ አትሰራም?” እያሉ ሲገፋፉት ሞራልና መነቃቃት እንዳገኘ የሚናገረው ይስሃቅ፤ በ2003 ዓ.ም “Hope and Reload” የተሰኘውን የመጀመርያ ሙዚቃውን እንዳቀናበረ ይገልጻል። በእርግጥ ሙዚቃውን ለመድረስ ከፈጀበት ጊዜ ይልቅ ሥራውን በቪድዮ ለመቅረፅ የበለጠ ጊዜ እንደወሰደበት አልሸሸገም፡፡ የ11 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውን “Hope and Reload” ለመቅረፅ 3 ወር ፈጅቶበታል፡፡ ቀረፃው እንደተጠናቀቀም በዩቲውብ ድረገጽ ላይ ለተመልካቾች ዕይታ አበቃው፡፡
በዩቲውብ የተለቀቀው አዲስ ስራው ያልጠበቀው ምላሽ ያስገኘለት ሲሆን “ሊንክ” ተደርጐ ከ20 በላይ ድረገፆች ላይ ሊሰራጭለት እንደቻለ ይናገራል፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ፈፅሞ ያልገመታቸው ዝነኛ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሥራውን አድምጠው የማበረታቻ አስተያየት ሰጥተውታል፡፡ በያኒ የሙዚቃ ቪድዮ ላይ የትንፋሽ መሳሪያ የሚጫወተውና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሙዚቃ መምህር የሆነው ኪላኒ ተጠቃሽ ነው፡፡ የይስሃቅን ሙዚቃ አስመልክቶ በኦፊሴላዊ ድረገፁ ባሰፈረው አስተያየት “ድንቅ የሙዚቃ ሥራህን ስላሰማኸን አመሰግንሃለሁ፡፡ ለማደግና ሥራህን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ በምታደርገው ጥረት ሁሉ መልካሙን እመኝልሃለሁ” በማለት አድንቆታል። ሌላው ዝነኛ አሜሪካዊ ሙዚቀኛና የትሩግሩቭ ሪከርድስ ባለቤት ቶማስ ዶንከር በበኩሉ፤“እንዲያ ነው እንጂ! በጣም ውብ ሥራ ነው፡፡ ዋው! በጣም ተደምሜበታለሁ” ሲል አወድሶታል፡፡ ከማይክል ቦልተንና ከአሜሪካዊው ራፐር አይስኪውብ ጋር የሚሰራው ሳክስፎኒስቱ ስኮት ማዮ በሰጠው አስተያየት፤“ድንቅ ነው! በሙዚቃህ ውስጥ ውብ ስሜት ይንፀባረቃል፤እባክህ ሙዚቃ መድረስህን ቀጥልበት፡፡ የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ነህ” በማለት አበረታቶታል፡፡ ታዋቂው አሜሪካዊ ፒያኒስትና አክተር ኒክ ሮልፍ በበኩሉ፤ “ወንድሜ፤እኔ የምመክርህ እየሰራህ ያለውን  እንድትቀጥልበት ነው፤ አዲስ ነገር እየፈጠርክ ነው” ሲል አድንቆ ፅፎለታል፡፡  
በአንድ ወቅት ከታዋቂው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ጋር የመገናኘት ዕድል ገጥሞት እንደነበር የሚናገረው ይስሃቅ፤ ግርማ ይፍራሸዋ የሰራውን ሙዚቃ በትዕግስትና በትኩረት ካዳመጠለት በኋላ፣ የማበረታቻ ምክር እንደለገሰው ጠቁሞ ባለውለታው እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ወጣቱ የፒያኖ ተጫዋች ይስሃቅ ካሣሁን ገና የቀለም ትምህርቱን አላጠናቀቀም፡፡ በቦሌ ቃለህይወት የፕሪፓራቶሪ ተማሪ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርት ተሰጥኦውንና ችሎታውን የማሳደግ እቅድ እንዳለው ይናገራል፡፡ በተለይ በውጭ አገር ለመማር የስኮላርሺፕ ዕድል ቢያገኝ ምኞቱ ነው፡፡ እስከዛው ግን እየተደበቀ ይገባበት በነበረውና ፒያኖ መጫወት በተለማመደበት ኮርያ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው “ጉድ ኒውስ ቸርች” የሙዚቃ ዳይሬክተር ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአንድ አልበም በላይ የሚሆኑ ሙዚቃዎችን እንደሰራ የሚናገረው ይስሃቅ፤ የራሱ ኦርጋን ፒያኖ ቢያገኝ ሙዚቃ የሚያቀነባብርበት ስቱዲዮ የመክፈት ሃሳብ እንዳለው ገልጿል፡፡ እስካሁን የሰራቸውን የሙዚቃ ስብስቦችም በአንድ አልበም የማውጣት ሃሳብ አለው፡፡ በእስካሁን ትጋቱ ከቀጠለ የስኬት ማማ ላይ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡


Read 3202 times