Saturday, 15 February 2014 13:26

የትጋትና የፈጠራ ተምሳሌቷ - ፀጋ ወተት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

         ከጥቂት ወራት በፊት ነው፡፡ እኔና የስራ ባልደረባዬ ምሳ በልተን በካዛንቺስ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በኩል ወደ ቢሮአችን እየሄድን ነበር - በእግራችን፡፡ ሆቴሉ ፊት ለፊት አንዲት አነስተኛ የሸቀጥ ኪዮስክ (ሚኒ ሱፐር ማርኬት) ነገር ተከፍታ አየንና ጐራ አልን፡፡ አንዲት ወጣት ቁጭ ብላለች - ብቻዋን። ቤቷን ከቃኘን በኋላ ባዶ እጃችንን ላለመውጣት የታሸገ ቆሎ አነሳን - ለመግዛት፡፡ ወጣቷ “ሳንዱችና እርጐም አለ” አለችን - ፈገግ ብላ፡፡ ከባልደረባዬ ጋር ተያየንና “እርጐውን እንሞክረው” ተባባልን፡፡ እርጐው መጣልን፡፡
ሁለታችንም ወደድነው፡፡ በተለይ እኔ በእርጐው ተደነቅሁ፡፡ ምክንያቱም ከብዙ ሱፐር ማርኬቶች እርጐ ስገዛ በጣም ነው የሚኮመጥጠኝ። ይሄኛው ግን ጣፋጭ ነው፡፡ በእርጐ ሰበብ ወደ ሚኒ ሱፐር ማርኬቷ መመላለስ ጀመርን፡፡ የቢፍና ቺዝ ሳንዱቹንም ለመድነው፡፡ እንደ እርጐው ንፁህና ጣፋጭ ነው፡፡ ሆድን ያዝ ያደርጋል፡፡ ኪስ አይጐዳም፡፡ አሁን በአብዛኞቹ የስራ ቀናት ምሳ የምንበላው በዚህች ቤት ነው፡፡ ለብዙዎቹ ባልደረቦቻችን ጠቁመናቸውም ተጠቃሚ ሆነዋል። መጀመሪያ ስንጐበኛት ኦና የነበረችው ያቺ ሚኒ ሱፐርማርኬት ዛሬ በእጅጉ ተለውጣለች፡፡ ቤቷ “ፀጋ ወተት” ትባላለች፡፡
ፀጋ ወተት ከጎኑ ካለው ቀበሌ በተከራያት በጣም ጠባብ ክፍል ውስጥ የወተት ተዋጽኦና የተለያዩ ዓይነት ሳንዱቾች  ያቀርባል፡፡ የፀጋ ወተት መስራችና ኃላፊ፣ ወ/ሮ ሰብለወንጌል ዘውዱ፣ ከጧት እስከ ማታ እንግዶቿን ያለዕረፍት ስታስተናግድ ስለምትውል አንዳንድ ጊዜ ለሚያናግሯት ሁሉ መመለስ እንደሚያቅታት ትናገራለች፡፡ ለመሆኑ ሰብለ ምን ብታቀርብ ነው ገበያው እንዲህ የደራላት?
ወ/ሮ ሰብለ፣ በአንድ ማይክሮዌቭና ለብቻዋ የቺዝ፣ የጥጃ፣ የዶሮ፣ የሞርቶዴላ (አሳማ) ሥጋና የቱና ሳንዱዊቾች በማዮኔዝ እያሰናዳች ከእርጎ ጋር ማቅረብ ከጀመረች  ስምንት ወር ሞልቷታል። ብዙ ሰዎች የተለያዩ አማራጮች በማግኘታቸው ደስተኛ እንደሆኑ የምትናገረው ወ/ሮ ሰብለ፤ አንዳንድ ደንበኞች እርጎና ሳንድዊች፣ ሌሎች ደግሞ እንደፍላጎታቸው ሳንድዊች ወይም እርጎ ብቻ እንደሚያዙ ገልጻለች፡፡
ይኼኔ፣ “ለካስ ሰው፣ አማራጭ ካገኘ በደስታ ይቀበላል!” በማለት፣ በሚጥሚጣና በማር የምታቀርበውን እርጎ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ እንደየሰው ፍላጐት በስትሮበሪና በቸኮሌት  ማቅረብ ጀመረች፡፡ የደንበኞቿ ቁጥርም አየጨመረ መጣ፡፡ ገበያው ደራ፣ ገቢዋ አደገ፡፡
ሰብለ ሥራ ስትጀምር፣ ሳንድዊች ሰሪዋ፣ እርጎ አቀባይዋ፣ ሌሎች ሸቀጦች ሻጭዋ፣ ገንዘብ ተቀባይዋ፣ ዕቃ ሰብሳቢዋ እሷው ብቻ ነበረች። ዛሬ ሁለት ማይክሮዌቮች ተጨምረው፣ ዘጠኝ ሰራተኞች ተቀጥረው በሁለት ፈረቃ 24 ሰዓት እየሰሩ ነው። አሁን የእሷ ሥራ በአብዛኛው ገንዘብ መቀበል፣ የጎደሉ ነገሮችን እያዩ ማሟላት፣ … በአጠቃላይ ድርጅቱን በበላይነት መምራት ነው፡፡
የካዛንቺሷ በቅርቡ ሥራ ትጀምር እንጂ፤ ፀጋ ወተት ከተቋቋመ አምስት ዓመት ሲሆነው ድርጅቱን በበላይነት የሚመሩት የወ/ሮ ሰብለወንጌል አክስት ወ/ሮ ሂሩት ዮሐንስ ናቸው። የወተት ላሞች ስላላቸው ለምን እንደቺዝ ያሉ የወተት ተዋፅኦዎችን እያዘጋጀን አናቀርብም በሚል ወተት፣ እርጎ፣ አይብ፣ … ማቅረብ ጀመሩ። የካዛንቺሱ ዓይነት የወተት ተዋጽኦ መሸጫ በ22 አካባቢ ከፍተው ነበረ። ገበያ ስላልነበረው ዘጉት። በካዛንቺሱ መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ወተት፣ እርጎ፣ አይብ፣ … ሲሸጡ ከቆዩ በኋላ ወተት ማቀናበሪያ (ፓስቸራይዝድ ማድረጊያ) መሳሪያ ገዝተው ይኸኛውን ኪዮስክ እንደከፈቱ ሰብለ ገልፃለች፡፡
ለመሆኑ የደንበኞች አስተያየት ምንድን ነው? ስል ጠየቅዟት - ሰብለን፡፡
ሆድ የማይጎረብጥ፣ በቀላሉ የሚፈጭ ለጤና የተስማማ ምግብ ስለሆነ ደንበኞች በጣም ወደውታል፤ በጣም ነው የሚያደንቁት፡፡ ሦስት አራት ጊዜ የሚመጣ ሰው አለ፡፡ እዚህ ቤት በቀን ቁርስ፣ ምሳ፣ መክሰስና እራት የሚበላ ሰው አለ። አሁን ገበያ በደንብ ስላለው፣  በሁለት ፈረቃ 24 ሰዓት ነው የምንሰራው፡፡ የሌሊት ተረኞች ሲገቡ፣ ቀን የዋሉት ይወጣሉ፡፡ ጧት ደግሞ የቀኖቹ ሲገቡ፣ ያደሩት ይወጣሉ፡፡ እንደዚህ ነው የምንሰራው፡፡
በስንት ብር ካፒታል ጀመርሽ?
በ50 ሺ ብር ነው
አሁን ገቢው እንዴት ነው?
በጣም ጥሩ ነው፡፡ ዋጋው ርካሽ ስለሆነ ብዙ ትርፍ የለውም እንጂ ከወጪ ቀሪ በቀን እስከ 7 ሺ ብር ይገኛል፡፡
ዋጋችሁ እንዴት ነው?
በጣም ርካሽ ነው፡፡ ይኼው ዓመት ሊሞላን ነው፤ ዋጋ እንኳን አልጨመርንም፡፡ ሰው ጥራት ያለው ነገር በርካሽ ዋጋ ስለሚፈልግ በጀመርንበት ነው እየሸጥን ያለው፡፡ እርጎ በሚጥሚጣ 8 ብር፣ በማር 10 ብር፣ በስትሮበሪና በቸኮላት 15 ብር ነው፡፡ ይኼ በፊትም የነበረ ዋጋ ነው፡፡
ለመሆኑ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው እዚህ የሚጠቀሙት?
ልጆቻቸውን ይዘው የሚመጡ ቤተሰቦች አሉ፡፡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ ጎልማሶች፣  ወንደላጤዎች፣ የቢሮ ሴቶችም ወጣ ብለው መጥተው ምሳቸውን በልተው ይመለሳሉ፡፡ አረጋውያን ወንዶችና ሴቶችም እርጐአቸውን ጠጥተው ይሄዳሉ፡፡ “እስካሁን የት ነበርሽ?” የሚሉኝ ብዙ ናቸው፡፡
ቤቷ ጠባብ ተጠቃሚው ብዙ ነው፡፡ እንዴት ነው የሚስተናገዱት?
ቤቷ ጠባብ ከመሆኗ የተነሳ ከሰራተኛ ጋር በጣት ከሚቆጠር ጥቂት ሰው በስተቀር ማስተናገድ አትችልም፡፡ ውጭ በረንዳ ላይ እንዳይቀመጡ ደግሞ ተከልክሏል፡፡ ስለዚህ ጊዜያዊ መፍትሔ ብዬ ቁጥር አዘጋጅቻለሁ፡፡ አንድ ሰው እርጎ ሲይዝ ወዲያው ይሰጠዋል፡፡ ሳንድዊች ሲያዝ ደግሞ ቅደም ተከተሉ ተሳስቶ ቅሬታ እንዳይፈጠርና ሁሉም እንደአመጣጡ እንዲስተናገድ፣ የተራውን ቁጥር ጽፌ ቲኬት እሰጠዋለሁ፡፡ ተራው እስኪደርስ ውጭ ሲጠብቅ ይቆይና ቁጥሩ ሲጠራ ተቀብሎ፣ በቁሙ በልቶ የተጠቀመበትን ፕላስቲክ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ወርውሮ ይሄዳል፡፡ መኪና ውስጥ ሆነው አዘው የሚበሉና አስጠቅልለው ወደ ቤት የሚወስዱም (ቴክ አዌይ) አሉ፡፡ ሌሊት ጭምር አራት አምስት ጊዜ የሚመጡ አሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተው  በጣም እንደወደዱት ነው፡፡ ዝግጅታችንን ስለወደዱልን በጣም እናመሰግናለን። ወደፊትም የሰውን ፍላጎት እያየን ጥራት ያለው ነገር ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡
ከወተት ተዋጽኦ ውጭ በመደርደሪያዎቹ ላይ ብዙ የሱፐርማርኬት ሸቀጦች ይታያሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የእናንተ ምርቶች ናቸው?
አይደሉም፡፡ እኔ እዚህ ውስጥ የምሰራው ብቻዬን አይደለም፡፡ አብረውኝ የሚሰሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አንድ ቀን አንዲት ልጅ ሙልሙል ዳቦ ይዛ መጣችና “እኔ እንደዚህ ዓይነት ነገር እሰራለሁ፡፡ ይህን ለናሙና ቅመሺውና ጥሩ ከሆነ እዚህ ላስቀምጥና ይሞከር” አለች፡፡ አንድ ሰው ሳንድዊች ያዝና ወረፋ ሲጠብቅ፤ ይርበዋል ወይም የሚቸኩል፣… ሊሆን ይችላል፤ ይኼኔ ያንን ሙልሙል በእርጐ በልቶ ሊሄድ ይችላል፤ ብዬ አሰብኩና ተቀበልኳት፡፡ እውነትም በጣም እየተወደደ ነው፡፡ ያቺም ልጅ ተጠቀመች፣ እኔም ተጠቀምኩ፡፡ አብሮ ሊሄድ የሚችል ነገር እዚህ ማቅረብ ለሰውም ጠቀሜታ አለው፡፡
ሙልሙል ብቻ አይደለም እኔ ጋ እየተሸጠ ያለው፤ ብዙ ነገር አለ፡፡ ማር፣ ማዮኔዝ፣ ስትሮበሪ፣ ቸኮላት፣ ..የሚያቀርቡልኝ ልጆች አሉ፡፡ ሽሮ በርበሬ፣ ኩኪሶች፣ ቋንጣ፣ ቆሎ፣ቺፕስ፣ የለውዝ ቅቤ ... የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ ጋ ያለውን አይተው፣ ከእኔ ንግድ ጋር የሚሄድ ነገር ሲያመጡ፣ እውነትም ይሸጣል፡፡ ሁለታችንም እንጠቀማለን። እንግዲህ እኔ የምሰራው ለብቻዬ ሳይሆን ለሌሎችም የሥራ ዕድል ፈጠርኩ ማለት ነው፡፡
ከአንቺ ምርት ውጭ ያሉት ነገሮች ምንድናቸው?    
ዓሣ፣ የፈረንጅና የአበሻ ዶሮ፣ እንቁላል፣ .. የእኔ ምርቶች ደግሞ ቅቤ፣ የፀጉርና የገበታ፣ አይብ አለ፡፡ አንድ ሰው በዓመት በዓል ጊዜ ወደ እኔ ሱቅ ቢመጣ የተለያዩ ነገሮች ፍለጋ በየቦታው ሳይንከራተት ከአንድ ቦታ ያገኛል፡፡ ይህም ድካምና ወጪ ይቀንስለታል፡፡ እኛ ቤት ያለው ነገር ርካሽና አቅምን ያገናዘበ ነው፡፡ ለምሳሌ የእኛ የፀጉር ቅቤ፣ ንፁህና ጥራቱ የተጠበቀ ስለሆነ ለምግብ ሊሆን ይችላል፡፡ አቅም የሌለው ሰው አንድ ኪሎ በ150 ብር መግዛት ካልቻለ፣ የፀጉሩን 200 ግራም ቅቤ በ30 ብር ገዝቶ አንጥሮ መጠቀም ይችላል፡፡
የእናንተ ዕቃዎች ዋጋቸው ምን ያህል ነው?
የምግብ ቅቤ አንድ ኪሎ 150 ብር ነው፡፡ አይብ ግማሽ ኪሎ ከ 20 ብር ጀምሮ አለ፡፡ የአበሻ ሙሉ ዶሮ 80 ብር፣ የተገነጠለ 90 ብር፣ የፈረንጅ እንደኪሎው 115 ብር፣ ዕንቁላል ደግሞ 2.50 ብር ይሸጣል፡፡
ይህን ሥራ ከጀመርሽ በኋላ ያጋጠመሽ ችግር አለ?
ሥራው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ሰውም ለምዶታል ወዶታል፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የመስሪያ ቦታ ጥበት አለብኝ፡፡ ቦታው በቅርቡ ለልማት ይፈርሳል ስለተባለ ቀበሌው ሌላ ሰፋ ያለ ቤት እንዲሰጠኝ አልጠየቅሁም። ሌላው ችግር መብራት ነው። ደንበኞቼን ቶሎ ቶሎ ለማስተናገድ ሁለት ተጨማሪ ማይክሮዌቭ ብገዛም፣ መብራት በየጊዜው ስለሚጠፋና ስለሚቆራረጥ በስራዬ ላይ እንቅፋት ሆኖብኛል፡፡ ለመብራት ኃይል ሳመለክት “ይስተካከላል” ከማለት በስተቀር ሲያስተካክሉ አላየሁም፡፡
የወደፊት እቅድሽ ምንድነው?
ይህን ሥራ ሰው በጣም ስለወደደልኝ ከዚህ ይበልጥ ማስፋፋት ነው እቅዴ፡፡ እኔ ወጣት ነኝ። መንግሥት፣ ደንበኞቼን ወረፋ ሳይጠብቁና ሳይጨናነቁ የማስተናግድበት ሰፋ ያለ ቦታ ቢሰጠኝ ከዚህ በላይ በመስራት ደንበኞቼን የማስደሰት እቅድ አለኝ፡፡  
በሚኒ ሱፐር ማርኬት ቁርስ ሲመገቡ ያገኘኋቸው ወ/ሮ አልጋነሽ የ69 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ስለምግቡና ስለቤቱ አስተያታቸውን ጠየቅኋቸው፡-  
ምግቡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ልጅቱን በጣም ነው የማደንቃት፤ ጎበዝ ናት፡፡ ሠራተኞቹም ጎበዞች ናቸው፣ እንግዳ በደንብ ያስተናግዳሉ፡፡ እሷ በተለይ በፈገግታ ነው የምታስተናግደው፤ ምንም እንከን የማይገኝባት ሴት ናት፡፡ በርቺ ነው የምለው፡፡  
ወ/ሮ ሰብለ ፀጉር መስራት በጣም ያስደስታታል። በ1993 ዓ.ም 12ኛ ክፍል እንደጨረሰች የፀጉር ሥራ ሙያ ካልተማርኩ ብላ ማሰልጠኛ ት/ቤት ገብታ ከ10 ወር በኋላ ተመረቀች፡፡ ጥሩ ችሎታ ስለነበራት ት/ቤቱ አስቀርቷት እዚያው ማሰልጠን ጀመረች። ከዚያም ለ10 ወራት ካስተማረች በኋላ ሁል ጊዜ አንድ አይነት ማስተማር ሰለቻትና ተወችው፡፡
ከማሰልጠኛው እንደለቀቀች የኬንያውያን ፀጉር ቤት ተቀጥራ መስራት ጀመረች፡፡ የፀጉር ሥራ ብዙ ጊዜ መቆም ስለሚጠይቅ እግሯን ያማት ጀመር፡፡ ኬንያውያኑም ወደ አገራቸው ሲሄዱ ማቋረጥ አለ፡፡ ስለዚህ የፀጉር ስራውን ተወችው፡፡ ንግድም ሞክራ ነበር፡፡ የልብስ ሱቅ ከፍታ ስላልሆነላት ተወችው። በመጨረሻ ከቤተሰብ ጋር እየሰራሁ ላግዛቸው በማለት 22 አካባቢ በነበረው ፀጋ ወተት ሰራች። ያ ሲዘጋ የካዛንችሱን ፀጋ ወተት ከፍታ መስራት ጀመረች፡፡

Read 3852 times