Monday, 17 February 2014 09:10

ስለት

Written by 
Rate this item
(12 votes)

…ሰናይት ይሏታል፡፡ እኔ ሰኒ እላታለሁ፡፡ ከተዋወቅን ያለፈው ሰኔ ሚካኤል 3ኛ አመታችንን ደፈንን፡፡ ዝም ብሎ መተዋወቅ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከመላመዳችን የተነሳ ፊቷን አይቼ ምን እንደምታስብ መገመት ሳይሆን ማወቅ ጀምሬያለሁ፡፡
እወዳታለሁ፡፡
እሷም “እወድሃለሁ” ትለኛለች፡፡
3ኛ አመታችንን ባከበርን ማግስት እድል እጇን ዘረጋችላት፡፡ ስትዘረጋላት “ልጨብጣት ወይ?” ብላ አማከረችኝ፡፡ “ምን ይጠየቃል ጨብጫት እንጂ” አልኳት፡፡ “እንዴት እንዲህ ትለኛለህ? ያንተ እጅ እያለ ባትወደኝ ነው እንጂ…” ብላ አኮረፈችኝ፡፡
ቶሎ ታኮርፋለች፡፡ ጥቃቅን ነገሮች ሁሉ ያስኮርፏታል፡፡ ብስክስክ ናት፡፡ እኔም አመሏን ለምጀዋለሁ፡፡ እሷም አልፎ አልፎ ቱግ የምለውን ነገር ታውቅልኛለች፡፡ መቻቻል ማለት ይሄ አይደል…ቢሆንም ይሄ አመሏ አንዳንዴ ትዕግስቴን ይፈታተነኛል፡፡
ከሰኒ ጋር የት ተገናኘን?
ቡና ቤት! (ለማንም ግን አይነገርም፤ ምስጢር ነው፤ በተለይ በተለይ ቤተሰብ እንዳይሰማ!)
ስንላመድ ከቡና ቤት አውጥቼ መጀመሪያ ወደ ልቧ፣ ኋላም ወደ ቤቴ አስገባኋት፡፡ ስትረጋጋ ቤተሰቤን ልጠይቅ አለችኝ ፈቀድኩላት፡፡ ያኔ እግረ መንገዷን ከእድል ጋር ተገናኘች፡፡
ታድያስ የእድሏ በር የተከፈተው በኔ ምክንያት አይደለምን? በሩን ባልከፍተው ቁልፉን ያቀበልሁ እኔ አይደለሁምን?
ውጭ ሀገር መሰደድ እንደ ሎተሪ በሚታይባት ሀገር ውስጥ ከዚህ የበለጠ ምን ጥሩ እድል አለ ጃል? አለ እንዴ? የለም እኮ!!
መሄድ የለብሽም ብላት በጄ እንደማትል ልቦናዬ እያወቀው፣ አፌን ለምን አበላሻለሁ ብዬ “ይቅናሽ” ብላት በአትወደኝም ተተረጐመብኝና በለመድኩት ኩርፊያ ገረፈችኝ፡፡
ውጭ ሀገር ለመሄድ 1…2 …ማለት ተጀመረ፡፡ ግን “ፕሮሰሱ” እንደታሰበው እንደጥንቸል ሊሮጥ አልቻለም፡፡
አንድ ቀን ይሄን “ውጭ” የሚለውን ልቧን ወደ ውስጥ ለመሳብ በማሰብ፣ ሻይ ቡና ልበልሽ ብዬ አንድ እኔ ነኝ ያለ ካፍቴሪያ ውስጥ ቋጠርኳት፡፡ አንድ ሁለት እያልን ጨዋታችንን አደራነው፡፡ ልክ እንደጥንቱ…ከወትሮው ልማዳችን በሹካ መጐራረሱን ብቻ ትተን…ልክ እንደ ጥንቱ በደንብ አወጋን፡፡  
ምንጭ፡- (ባለ “ሚኒስከርቷ” የሥነግጥምና የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ)

Read 6292 times