Saturday, 22 February 2014 12:18

ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ 180 የሳኡዲ ተመላሾችን በነፃ ሊያስተምር ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እስካሁን ለ3ሺ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል

ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቅርቡ ከሳኡዲ ለተመለሱ 180 ያህል ኢትዮጵያዊያን ነፃ የትምህርት እድል መስጠቱን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው መስራችና ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብነት ግርማይ፣ በዩኒቨርሲቲው ሾላ ካምፓስ ከትላንት በስቲያ የትምህርት እድሉ የተሰጣቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካይ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና ጋዜጠኞች በተገኙበት በሰጡት መግለጫ፤ ዩኒቨርስቲያቸው ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ለተመለመሉና ከፍለው መማር ለማይችሉ 3ሺህ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል መስጠቱን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴርን መስፈርት ላሟሉ የሳኡዲ ተመላሾች ተመሳሳይ እድል መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሀዋሳና በባህርዳር በአጠቃላይ ስድስት ካምፓሶች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ ካምፓስ 30 ተማሪዎች ገብተው እንዲማሩ መወሰኑ ተገልጿል፡፡
ተማሪዎቹን አስተምሮ ለማስመረቅ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ የጠቆሙት ዶ/ር አብነት፤ ከሌቭል አንድ እስከ ዲግሪ ድረስ እንዲማሩ እድሉ መመቻቸቱን ገልፀዋል፡፡ የትምህርት አሰጣጡንና አጠቃላይ የዩኒቨርስቲውን ድባብ  በተመለከተ ተማሪዎቹ ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ የሚፈልጉትን የትምህርት አይነት፣ የት መማር እንደሚሹና የሚማሩበትን ሰዓት መምረጥ እንደሚችሉ ዶ/ር አብነት ተናግረዋል። “ትምህርታችሁን ጀምራችሁ እስክታጠናቅቁ ድረስ ራሳችሁን፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁንና  የከተማ አስተዳደሩን የሚያስከብር ስርዓት እንድትከተሉ እጠይቃለሁ” ሲሉም ለተማሪዎቹ ምክርና ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካይ በበኩላቸው፤ቢሯቸው ተማሪዎቹንና የትምህርት አቀባበል ሁኔታቸውን እንደሚከታተል ገልፀው፣ ለሁሉም መልካም እድል ተመኝተውላቸዋል፡፡ እድሉ የተሰጣቸው ተማሪዎችም ነፃ የትምህርት እድሉን በማግኘታቸው ከተማ አስተዳደሩንና ዩኒቨርሲቲውን አመስግነው ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል ቃል ገብተዋል፡፡   


Read 1973 times