Saturday, 22 February 2014 12:26

“የአብዮተኛው ትውልድ” ኪሳራ በስንት ይሰላል?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አብዮቱ ሲመነዘር፡ በሚሊዮኖች ረሃብና ሞት፣ በሚሊዮኖች ችጋርና ጉስቁልና የታጨቀ ነው።
መልኩ ሲታይ፡ በርካታ መቶ ሺ ዜጎች ያለቁበት ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብርና የጦርነት እሳት ነው።
“አብዮተኛው ትውልድ”፣ ስለ አብዮቱ 40ኛ አመት የሚናገርበት አንደት ማጣቱ አይገርምም።

ልክ የዛሬ አርባ አመት፣ የነዳጅ ዋጋ ላይ የአስር ሳንቲም ጭማሪ እንደተደረገ ነው አገሪቱ በቀውስ የተናጠችው - በየካቲት ወር አጋማሽ 1966 ዓ.ም። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተዘወተረ ከመጣው ሰልፍ ጋር፤ የተማሪዎችና የአስተማሪዎች ረብሻ፣ የሰራተኞች አድማና የወታደሮች አመፅ ታክሎበት፣ አገር ምድሩ በተደበላለቀ ስሜት ተቀጣጠለ። ከከተሜነትና ከዘመናዊ ትምህርት፣ ከካቢኔና ከፓርላማ አሰራር፣ እንዲሁም ከመደበኛ የጦር ሃይል አደረጃጀት ጋር ገና መተዋወቅ የጀመረችው አገር፣ መላ ቅጡ ጠፋባት። ሁለት ወር አልቆየም። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው ስልጣን ለቀቀ። ለወታደሮች ደሞዝ ተጨመረ። ግን አገሬው አልተረጋጋም።
መንግስት መውጪያ መግቢያ ጠፋበት። ለአስተማሪዎችና ለሌሎች ሰራተኞች ሁሉ በአንዴ ደሞዝ የመጨመር አቅም የለም። የነዳጅ ዋጋ መደጎምም የማይሞከር ሆኗል። በመላው አለም ዋጋው አልቀመስ ብሏላ። በርካታ የአረብ አገራት በእስራኤል ላይ በከፈቱት ድንገተኛ ጦርነት ሳቢያ፣ ከጥቅምት እና ጥር 1966 ዓ.ም፣ በአለም ገበያ 3 ዶላር በበርሜል የነበረው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከሶስት እጥፍ በላይ ንሯል - ከ10 ዶላር በላይ አልፏል። ኢትዮጵያ ውስጥ በቀድሞ ዋጋው መቀጠል አለበት ከተባለ፤ መንግስት ለሰራተኞችና ለወታደሮች የሚከፍለው ደሞዝ ያጣል። አጣብቂኝ ውስጥ ነው የገባው።
በዚያ ላይ፣ ከነዳጅ ዋጋ ንረት በተጨማሪ፣ በከፍተኛ ድርቅ ሳቢያ የእህል እጥረትና የዋጋ ንረት ተከስቷል። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔ ቢሰየምም፣ ተደራርበው የመጡትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ምትሃት አልነበረውም። ለዚህም ይመስላል፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር “ትንሽ ፋታ” ለማግኘት የተጣጣሩት።  በዚህ መሃል፤ በደሞዝና በጥቅማጥቅም ጥያቄ ዙሪያ ወታደሮችን ለማስተባበር ከየአካባቢው ግንኙነት የፈጠሩ የበታች መኮንኖች፣ ሳይታሰብ በአለቆቻቸውና በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉልበት እያገኙ መጥተዋል። ለዚህም አንዱ ምክንያት፤ እንደየእለቱ ስሜትና አዝማሚያ፣ “ያኛው ሚኒስትር ጉቦኛ ነው፤ ያኛው ባለስልጣን ዘራፊ ነው፤ ይያዝልን፤ ይታሰርልን” የሚሉ የተለያዩ ጩኸቶች መራገባቸው ነው። አንድ ጉበኛ ወይም አንድ አጭበርባሪ ባለስልጣን ቢታሰር፤ ቅንጣት መፍትሄ እንደማያስገኝ ግን ግልፅ ነው። እናም፤ የአገሪቱ ቀውስና ትርምስ ሳይረግብ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔያቸው በአምስት ወር ውስጥ ከስልጣን ወረዱ።
የቀውሱ አቅጣጫና መጨረሻ፣ ወዴት ወዴት ይሆን ብሎ የሚጨነቅ ብዙ ነው። “አቅጣጫውን እኔ አውቃለሁ፤ እኔ ዘንድ ሁነኛ መፍትሄ ይገኛል” የሚል አንጋፋና አዋቂ ሰው ግን አልነበረም። በእርግጥ፤ በቡድን “እኛ እናቃለን፤ መፍትሄውም በእጃችን ነው” እያሉ ነጋ ጠባ መፈክር የሚያስተጋቡና የሚጮሁ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን፣ የአዋቂነት አልያም የአንጋፋነት ደረጃ ላይ የደረሱ አይደሉም። ብዙዎቹ ገና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው፤ ጥቂቶቹ ደግሞ አዳዲስ ምሩቃንና ወጣት ምሁራን። እነዚህ ናቸው “አብዮተኞቹ”። ከሌላው ሕዝብ በቁጥር ሲነፃፀሩ፤ እጅግ በጣም ጥቂት ቢሆኑም፤ አንድ በመቶ ያህል እንኳ ባይሆኑም፤ ከሌላው ሁሉ የላቀ ሃይል አግንተዋል። ሌላው ሁሉ ግራ ተጋብቶ ሲደናበር፤ “የአገሪቱን ችግር ተንትነው የሚያውቁበት መመኪያ፤ መፍትሄ የሚያበጁበት መሳሪያና የወደፊቱን ጉዞ የሚመሩበት አቅጣጫ” መያዛቸውን እየተናገሩ ማን ይስተካከላቸዋል? መመኪያቸው የማርክስ የሌኒን መፅሃፍ ነው። መሳሪያቸው፤ “አብዮታዊ እርምጃ” ነው። ጉዟቸው ደግሞ ሶሻሊዝም።
በአብዮተኞቹ አስተሳሰብ፣ “ከሁሉም የከፋው ሃጥያት፣ የግል አእምሮውን መጠቀም፤ ለራስ ሕይወትና ለራስ ኑሮ ማሰብ ነው” ... ራስወዳድና ግለኝነት እጅግ ወራዳ ፀረሕዝብነት ነው በማለት ያወግዙታል። “ከሁሉም የከፋው ወንጀል ደግም፣ የራስን ሕይወት ማሻሻልና የንብረት ባለቤት መሆን ነው” ... ቡርዧ ወይም ንዑስ ቡርዧ እያሉ ያንቋሽሹታል። “ከሁሉም የከፋ በደል ደግሞ፤ የሥራ እድል መፍጠርና ሰራተኞችን መቅጠር ነው” ... በዝባዥ ወይም ጨቋኝ ተብሎ ይኮነናል። በማርክስና በሌኒን መፃህፍት ውስጥ ተደጋግመው የሰፈሩ እነዚህ ሃሳቦች ናቸው የአብዮተኛው ትውልድ መመኪያና አለኝታ። የግለሰብ ነፃነትን እያወገዙ፣ የንብረት ባለቤትን እያንቋሸሹ፤ የነፃ ገበያ ስርዓትንና ብልፅግናን እየኮነኑ ጥዋት ማታ አብዮተኞቹ መፈክር ሲያሰሙ፤ በአጠቃላይ የስልጣኔ አስተሳሰቦችን እያንኳሰሱ ሲጮሁ፤ በልበሙሉነት የሚሞግታቸውም ሆነ የሚመክታቸው አልተገኘም። ገና በጭላንጭል ይታዩ የነበሩ የስልጣኔ አስተሳሰቦች ከነአካቴው ተዳፍነው፤ የአፈና፣ የዝርፊያና የግድያ ሃሳቦች እንደ አዲስ ነገሱ። ከዚያማ መንገዱ ጨርቅ ሆነላቸው፤ መፈክሮቻቸው በቀላሉ ወደ ተግባር ይሸጋገራሉ። ማውገዝ፣ ማንቋሸሽና መኮነን በቂ አይደለማ። “መርገጥ፣ መጨፍለቅ፣ መደምሰስ” የሚሉ የአብዮታዊ እርምጃዎች ተከትለው ይመጣሉ። ደግሞም አልዘገየም።
በየካቲት አጋማሽ “በግብታዊነት የፈነዳው አብዮት”፣ አመት ሳይሞላው ነው፤ ከሃሳብ ወደ ተግባር መሸጋገር የጀመረው። 120 የበታች መኮንኖች የተሰባሰቡበት ኮሚቴ፤ መስከረም ላይ ንጉሡን ከስልጣን ሲያስወግድ ባወጣው አዋጅ፤ መቃወም ወንጀል ነው ብሎ አወጀ። ሁሉም ሰው ከራሱ በፊት አገርን ማስቀደም እንዳለበት ሲያስረዳም፤ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን መርህ የሚቃወም፣ ለመቃወም የሚያስብ ወይም የሚያሳስብ... ወዬለት ሲል ዛተ። የራሴን ሃሳብ መግለፅ መብቴ ነው ብሎ መሟገት አይቻልም - ራስ ወዳድነትና ግለኝነት ተወግዟላ። ለማንኛውም የደርግ ዛቻ በባዶ አልነበረም። በእስር የቆዩ 59 የቀድሞ ባለስልጣናት፤ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡና ሳይከራከሩ እንዲገደሉ ህዳር ወር ላይ ተወሰነ - በአንድ የደርግ አባላት ስብሰባ። የየካቲቱ አብዮት አመት ሲሞላው፣ የደርግ የስልጣን ዘመን ገና መንፈቅ እንዘለቀ፤ ሌላ አዋጅ መጣ።   
በአብዮታዊ እርምጃ፤ ባንኮች፣ ፋብሪካዎች፣ የቢዝነስ ድርጅቶች ተወረሱ። መሬት ሁሉ የመንግስት ነው ተባለ። ከ500 ካሬ ሜትር በላይ መሬት፣ ከአንድ መኖሪያ ቤት በላይ ግንባታና ሕንፃ ሁሉ ተወሰደ። ማከራየት ወንጀል ሆነ። ሰራተኛ መቅጠር ተከለከለ። አብዮተኛው ትውልድ መመኪያና አለኝታ አድርጎ የዘመረላቸውን መፈክሮች ሁሉ፤ በላይ በላዩ ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ጊዜ አልፈጁም። መቃወም ብቻ ሳይሆን ለመቃወም ማሰብ አይቻልም የሚል የአፈና አዋጅ፤ ፋብሪካ መፍከትም ሆነ ሰራተኛ መቅጠር አይቻልም ብሎ ንብረትን የሚወርስ የዝርፊያ አዋጅ፤ ያለ ፍርድ እንዳሻው ማሰርና መረሸን የሚችል የግድያ ስልጣን ... ምን ቀረ? የግል ሃሳብን፣ የግል ንብረትን፣ የግል ሕይወትን ... በአጠቃላይ የግል ነፃነትን ገና ሳይፈጠር በእንጭጩ ለማጥፋት የሚያስፈልጉ የአብዮተኞቹ ሃሳቦችና መፈክሮች በሙሉ ሳይውሉ ሳያድሩ በደርግ ተግባራዊ ሆነዋል። አብዮተኞቹ ተሳክቶላቸዋል።
ሶስተኛው ደረጃ በራሱ ጊዜ የሚመጣ ውጤት ነው - የሃሳብና የተግባር ውጤት። የማያቋርጥ የአፈና፣ የዝርፊያና የግድያ ስርዓት። ማለትም የሶሻሊዝም ጉዞ። እዚህ ላይም፣ አብዮተኞቹ ምንም የጎደላቸው ነገር የለም - የተመኙትን ውጤት አግኝተዋል። ከንጉሡ ዘመን ጋር እያነፃፀርን ልናየው እንችላለን።
“እንደተመኘኋት አገኘኋት” - የአብዮተኞቹ ጉዞ
እንደምታውቁት፣ የአፈና፣ የዝርፊያና የግድያ ስርዓት ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ከአፈና ጋርም ነው መሃይምነትና ኋላቀርነት የሚንሰራፉት። ከዝርፊያ ጋር ደግሞ ድህነትና ረሃብ ይበረታሉ። ከግድያ ጋርም ሽብርና ጦርነት ይበራከታሉ። ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ ትታወቃለች። በንጉሡ ዘመንም እንዲሁ፣ አፈናው፣ ዝርፊያውና ግድያው ለአገሪቱ የሚያንስ አልነበረም። በእርግጥ፤ በዚያን ዘመን አንዳንድ የነፃነት ጭላንጭሎች እየተፈጠሩ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከ1950ዎቹ ጀምሮ አፄ ኃይለስላሴ በተገኙበት ይዘጋጁ የነበሩ አመታዊ የግጥም ውድድሮችን መጥቀስ ይቻላል። ተማሪዎች በየአመቱ በሚያቀርቧቸው ግጥሞች፤ መንግስት ላይ ትችቶች ይሰነዝሩ እንደነበር አብዮተኞቹ አይክዱትም። የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የሚዘጋጁት ጋዜጣ ላይም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መረር ያሉ የተቃውሞ ፅሁፎች ታትመዋል። እንዲያም ሆኖ፣ የንጉሱ መንግስት፣ የሃሳብ ነፃነትን ያከብር ነበር ማለት አይደለም። ንጉሱ ከዩኒቨርስቲው አመታዊ የግጥም ውድድሮች ርቀው ጠፉ። የዩኒቨርስቲው ጋዜጣ ላይም እገዳ እንዲጣል አስደርገዋል። በአጭሩ፣ ንጉሡ የሃሳብ ነፃነትን በማስከበር የሚወደሱ አይደሉም።
አሳዛኙ ነገር፤ እጅግ የባሰ የአፈና ስርዓትን ጎትቶ የሚያመጣ አብዮት መፈጠሩ ነው። ስልጣን የያዘው ደርግ እና ከጎኑ የተሰለፉ አብዮተኞች፣ እንዲሁም ስልጣን ለመንጠቅ በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉ አብዮተኛ ድርጅቶች ሁሉ፤ እንደየአቅማቸው የቻሉትን ያህል የአፈና ስርዓት ዘርግተዋል። ተቃውሞና ትችት መተንፈስ ጨርሶ ተከለከለ። ስልጣን የያዘ አብዮተኛ፣ “ተቃወምከኝ፣ ትችት ሰነዘርክ” ብሎ ካሰበ፤ “ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ” እያለ አፋፍሶ ያስራል፤ ይገድላል። ስልጣን ያልያዘ አብዮተኛም ቢሆን፣ አድፍጦ ይገድላል፤ ካልሆነለትም ስም የማጥፋት ዘመቻ ያፋፍማል። ይህም ብቻ አይደለም። በቃ፤ ለመቃወምና ለመተቸት ማሰብ ወይም ማሳሰብ፣ የአገር ክህደት ወንጀል ነው ተባለ። ምን ይሄ ብቻ?
በየመንደሩ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች በቀበሌና በከፍተኛ፤ አልያም በፆታና በእድሜ፣ በስራ ቦታና በሙያ አይነት... የመሰባሰብ ግዴታ መሰባሰብ፣ የሴቶች ማህበር፣ የወጣቶች ማህበር፣ የወዛደሮችና የመምህራን ማህበር ... ወዘተ የማህበር አባል የመሆን ግዴታ፣ እናም ፓርቲንና መንግስትን የማወደስ የግዴታ ሸክም ተጫነባቸው። ቢያንስ ቢያንስ በንጉሱ ዘመን፣ ተቃውሞና ትችት የመሰንዘር ብዙ ነፃነት ባይኖር እንኳ፤ አፍን ይዞ ዝም ማለት ይቻል ነበር። ከአብዮቱ በኋላ ግን፣ ለፓርቲና ለመንግስት እየሰገዱ ውዳሴ የመዘመር ግዴታ መጣ። አይን ያወጣ ዘመናዊ አፈና ብለን ልንሰይመው እንችላለን።
ያው፤ አፈና በሚኖርበት ዘመንና ቦታ ሁሉ፣ በዚያው መጠን ወከባ፣ እስርና ግድያ ይኖራል። በእርግጥ፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን፣ በቀጥታ ንጉሡን መተቸትና መቃወም ከባድ ቢሆንም፣ በጥቅሉ ጥንታዊውን የፊውዳል ሥርዓት መተቸት እንደ ወንጀል አይቆጠርም ነበር። ሃዲስ አለማዬህን ድርሰቶች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። እንዲያም ሆኖ፣ የመመረረ ተቃውሞ የሚሰነዝሩና የሚቀሰቅሱ ሰዎች በንጉሡ ዘመን መታሰራቸውና አንዳንዶችም መገደላቸው አልቀረም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከዋናዎቹ የሶሻሊዝም አቀንቃኞች መካከል በገናናነት ስሙ የሚነሳው ጥላሁን ግዛው፣ በንጉሡ መንግስት ነው የተገደለው። ስም እየጠቀሱ፣ እገሌና እገሊት ብለው እየቆጠሩ፣ በንጉሡ ዘመን እነማን እንደተገደሉ የሚዘረዝሩልን የታሪክ ሰዎችን የምናጣ አይመስለኝም። ችግሩ ምን መሰላችሁ? የ66ቱ አብዮት ይህንን ሁሉ ታሪክ ገለባበጠው። ከአብዮቱ በኋላ፤ የሚታሰሩና የሚገደሉ ሰዎችን በስምና በቁጥር ለመዘርዘር መሞከር ከንቱ ሆነ። እንዲያውም ያልታሰሩትን መቁጠር ነበር የሚሻለው። እንደተራ ነገር፣ ከየቤቱና ከየጎዳናው በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን እያፋፈሱ በየቀበሌ ማጎር፤ ከዚያም እንደዘበት በረድፍ መረሸን... የአገራችን የሶሻሊዝም አብዮተኞች ያስመዘገቡት ውጤት፣ ከሌሎች አገራት ሶሻሊዝም አብዮተኞች የተለየ አይደለም። የጅምላ እስርና የጅምላ ግድያ፣ ሽብርና ጦርነት ነው ውጤቱ።
የአብዮተኞቹ ውጤት ግን ከዚህም የላቀ ነው። ራስወዳድነትን በማውገዝ የሰዎችን የብልፅግና ፍላጎት ለመስበር ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ግለኝነትን በመኮነን የንብረት ባለቤትነትን ለማጥፋት ያለ እረፍት ዘምተዋል። ዘመቻቸው ያለ ውጤት አልቀረም። በእርግጥ ቀድሞውንም ያን ያህል ንብረትና ብልፅግና አልነበረም። ነገር ግን፤ በአብዮተኞቹ ዘመቻ የብልፅግና ተስፋ ተዳፍኖ፣ የንብረት ምልክት ጠፍቶ፤ የአገሬው ሕዝብ ከቀድሞ በባሰ ድህነትና ችጋር ለከፋ ስቃይ ተዳርጓል።
በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር፤ በስልጣን ሽሚያና በጦርነት ከተፈጠረው እልቂት ያልተናነሰ ጥፋት የተከሰተውም በድህነት ምክንያት ነው። በ77ቱ ድርቅ፣ ወደ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በረሃብ እንደሞቱ በወቅቱ ተዘግቧል። የውጪ ለጋሾች ተሯርጠው ደራሽ እርዳታ ባያቀርቡ ኖሮ፤ በ81 እባ በ82 ዓ.ም እንዲሁም በ92 ዓ.ም ሚሊዮኖች በረሃብ ያልቁ ነበር። ታዲያ፤ የያኔዎቹ አብዮተኞች፣ አሁን በየካቲት ወር ወይም ዘንድሮ በ2006 ዓ.ም ስለ አብዮቱ አርባኛ አመት፣ አንዳች ቁምነገር ለመናገር የሚያስችል አንደበት ማጣታቸው ይገርማል?   

Read 2043 times