Print this page
Saturday, 10 December 2011 09:25

ዕጣ - ፈንታችን - በእጃችን ወይም “ኩሉ ይሤኒ ለእመ ንሤኒ ንህነ”

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

[ተራኪው]፡ በድንገት ያገኘኋቸው እና ከዚያ ወዲህ አይቻቸው የማላውቃቸው አንድ ሰው የማይረሳ ቁም ነገር አጫወቱኝ፡፡ ዛሬ “አባ ኮነግ “ ይረሱኝ ይሆናል፡፡ እኔ ግን እስከ ዛሬ አስታውሳቸዋለሁ፡፡ አዎ፤ ለብዙ ዓመታት ሳስታውሳቸው ኖሬአለሁ፡፡ ይኸው ዛሬም ማስታወሻቸውን ቋሚ ለማድረግ ጨዋታቸውን በፅሁፍ ማስፈር ይዣለሁ፡፡ ሌላው - ሌላው የጨዋታ ዘርፍ እና መነሳንስ ሲቀር፤ የጨዋታቸው አቢይ መልዕክት “ዕጣ-ፈንታችን በእጃችን “ የሚል ኃይለ ቃል ነው፡፡

አባ ኮንግ፤ “ዕጣ-ፈንታችን በእጃችን “ ሲሉ፤ የሰው ልጅ በዕጣ-ፈንታ ልጓም ታስሮ የሚቀር አይደለም ማለታቸው ነው፡፡ “እያንዳንዱ ሰው፤ ዕጣ - ፈንታውን መፍጠር ወይም መቀየር ይችላል “ የሚሉት አባ ኮንግ፤ ዕጣ-ፈንታን የመወሰን ጥበብ እና ብልሃትን አስተምረውኛል፡፡ በትምህርታቸውም፤ ዕጣ-ፈንታን ከመወሰን ጀርባ ያሉ መርሆዎችን አመልክተውኛል፡፡ አባ፤ ዕጣ-ፈንታ የለም አይሉም፡፡ አለ፡፡ ግን ይቀየራል፡፡ 
“ዕጣ-ፈንታ፤ አንድም ነባር መልኩን ይዞ እስከ ዕድሜ ፍፃሜ ይዘልቃል፡፡ አንድም ነባር መልኩን ቀይሮ የተሻለ ደረጃ ይይዛል፡፡ አንድም፤ ነባር መልኩን ቀይሮ ያሽቆለቁላል፡፡ ታዲያ በሦስቱም ጎዳና ለሚታየው ለውጥ፤ እኛ ወሣኝ ድርሻ አለን፡፡ ይህንንም የራሳቸውን ገጠመኝ አስረጅ አድርገው በማንሳት አጫውተውኛል፡፡ ይህንም መሠረት በማድረግ ዕጣ-ፈንታን ለመቀየር የሚያግዝ ሙከራ፣ ልምድ እና ጥበብን አመልክተውኛል፡፡ አባ ኮንግ፤ “የሰው ልጅ በልደት ዕጣ-ፈንታው ተወስኖ መቅረት የለበትም፡፡ ይልቅስ፤ ከክፋት በመራቅ እና አብዝቶ ደግነትን ማድረግ አለበት፡፡ ዕጣ-ፈንታችን በዚህ የሚወሰን ነው “ በማለት፤ የአንድ ልጃቸውን ወይም ተማሪያቸውን ገጠመኝ በማንሳት፤ የእርሳቸው አስተማሪ የነበሩ የአንድ ሊቅን ታሪክ እያወሱ አጫውተውኛል፡፡ እንደርሳቸው ቃል፤ “ብዙ ጥቅም የሌለው ትንሽ ደግነት፤ ብዙ ጉዳት የሌለው ትንሽ የክፋት ሥራ የለም፡፡ “ ስለዚህ፤ ብዙ የማይጠቅም ብሎ ደግ ሥራን መተው፤ ብዙም የማይጎዳ ብሎ ክፉን ሥራ መስራት አይገባም፡፡ የደግነት ብዛት፤ የልደት ዕጣ-ፈንታን ይለውጠዋል፡፡ “ከክፋት ተግባር ፈፅሞ መራቅ እና ትንሽ - ትልቅ ሳይሉ የደግነት ሥራን ሁሉ መስራት፤ ሊመጣ ያለን መከራ ያርቃል፡፡ መልካም ዕድልንም ይስባል፡፡ ዕጣ- ፈንታን ከመቀየር ጀርባ ያለው ምስጢር ይኸው ነው፡፡
[ሊያዎፋን]፡ አባቴ በልጅነቴ ነው የሞተው፡፡ እናቴም “ጥበበ-ህይወትን “ ከመማር ይልቅ ህክምናን ማጥናት እንደሚኖርብኝ አጥብቃ ትመክረኝ ነበር፡፡ እናቴ እንዲህ አለችኝ፡-
[እናት]፡ ህክምናን ብታጠና ከራስህ ተርፈህ ሌሎችን መርዳት ትችላለህ፡፡ የአንድ ሙያ ባለቤት መሆን፤ ምን ሰርቼ እበላለሁ ከሚል ጭንቀት ያወጣሃል፡፡ በህክምና አገልግሎት ዝናን ያተረፈ ትልቅ ሰው ለመሆን ትበቃለህ፡፡ አባትህ ዘወትር ለአንተ ይመኝ የነበረው ይህን ነበር፡፡
[ሊያዎፋን]፡ አንድ ቀን “ደብረ ርህራሄ ወ ቤተ - ደመና “ ከተባለ ገዳም ሄጄ፤ አንድ ሽማግሌ አገኘሁ፡፡ ሽማግሌው ፂማቸው የተንዠረገገ እና ግርማ ሞገስ የተላበሱ ከመሆናቸው የተነሳ፤ ልክ እንዳየኋቸው የበቁ ሊቅ መሆናቸውን ገምቼ፤ የአክብሮት ሰላምታ አቀረብኩላቸው፡፡ ሽማግሌውም እንዲህ አሉኝ፡-
[>¥Gl@W]፡ ልጄ፤ አንተ ወደፊት ትልቅ የመንግስት ባለስልጣን የምትሆን ነህ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት፤ የቻይና መንግስት ሹማምንቱን ለመመልመል የሚሰጠውን ፈተና ትወስዳለህ፡፡ ያንንም በአንደኛነት ትወጣዋለህ፡፡ ታዲያ ለዚህ ፈተና የማታጠናው ለምን ነው?
[ሊያዎፋን]: እኔም አንዲህ ስል መለስኩላቸው፤ እናቴ የ “ጥበበ-ህይወት “ ትምህርት መማሩን ትቼ፤ የህክምና ትምህርት እንድከታተል ምክር ሰጥታኛለች፡፡ ከዚያም፤ ስማቸው ማን እንደ ሆነ፤ የት እንደ ተወለዱ እና የትስ እንደሚኖሩ ጠየኳቸው፡፡ ጥያቄዬንም ሲመልሱ፡-
[>¥Gl@W]፡ ስሜ ኮንግ ይባላል፡፡ የመጣሁትም ከዮናን አውራጃ ነው፡፡ ሻዎ ከተባሉ እና የትንበያ ጥበብን በደንብ ከተካኑ አንድ ሊቅ ዘንድ ተምሪያለሁ፡፡ እናም ይሄን ጥበብ ለአንተ ማስተላለፍ ይኖርብኛል፡፡
[ሊያዎፋን]፡ ከዚያ በኋላ ሽማግሌውን ወደ ቤት ይዣቸው ሄድኩ፡፡ ከእናቴ ጋርም አስተዋወቅኳቸው፡፡ ስለ ሰውየው ማንነት የነገርኳት እናቴም፤ ሽማግሌውን በአክብሮት ተቀብሎ ማስተናገድ ተገቢ መሆኑን ከነገረችኝ በኋላ የሚከተለውን አለችኝ፡-
[እናት]፡ ሚስተር ኮንግ የወደፊቱን ነገር የመተንበይ ብቃት ያላቸው ሰው ከሆኑ ስላለፈውም ነገር በቂ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ ጥያቄ በማቅረብ፤ ሰውዬው እውነተኛ መምህር መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን፡፡
[ሊያዎፋን]: ሽማግሌው ኮንግ ቃላቸው የማይታበል እና ትናንሽ ነገሮችን እንኳን የማይስቱ ሊቅ መሆናቸውን አረጋገጥን፡፡ የሳቸውን ምክር ተከትዬ እንደገና “ጥበበ-ህይወት “ን ለመማር ወሰንኩ፡፡ ይህንኑ ሃሳቤንም የአክስቴ ልጅ ለሆነው ለሽንቼን አማከርኩት፡፡ እርሱም እንዲህ አለኝ፡-
[የአክስቴ ልጅ]: “ወንድሜ ሆይ፤ መምህር ሃይ-ጉ ዩ የተባሉ እና ዮ-ፉ ሼንግ በተባሉ የታወቁ መምህር እግር ተተክተው የሚያስተምሩ ሊቅ አሉ፡፡ በዚያ እየኖርክ ትምህርትህን መከታተል ስለምትችል ወደዚያው ብወስድህ ሳይሻል አይቀርም፡፡
[ሊያዎፋን]: እንግዲህ የመምህር ዩ ተማሪ ለመሆን የበቃሁት በዚህ አኳኋን ነበር፡፡ ሆኖም ሽማግሌው ኮንግ ስለ እኔ በትንቢት የተናገሩት ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ እናም እንዲህ አሉኝ፡-
ኮንግ፡ አንተ በብሔራዊው ፈተና የ14ኛ ደረጃን ታገኛለህ፡፡ በክፍለ ሀገራዊው ፈተናም 71ኛ ትወጣለህ፡፡ በአውራጃዊው ፈተና ደግሞ 9ኛ ደረጃን ታገኛለህ፡፡
[ሊያዎፋን]፡ በቀጣዩ ዓመት በሦስቱም ደረጃ የተሰጠውን ፈተና ወስጄ ያገኘሁት ውጤት ሽማግሌው እንደ ተነበዩት ነበር፡፡ ታዲያ ሽማግሌው ኮንግ፤ ስለ ጠቅላላ ህይወቴም የተናገሩት ትንቢት ነበር፡፡ እንዲህም አሉ፡-
[ኮንግ]፡ እንዲህ ያለውን ፈተና፤ በእንዲህ ያለው ዓመት ወስደህ፤ እንዲህ ያለ ደረጃ ታገኛለህ፡፡ በእንዲህ ያለው ዓመት፤ የመንግስት ሠራተኛ ሆነህ ትቀጠራለህ፡፡ ደግሞ በእንዲህ ያለው ዓመት፤ ሹመት ሽልማት ታገኛለህ፡፡ በመጨረሻም ስዜችዋን በተባለ አውራጃ፤ በአስተዳዳሪነት ትሾማለህ፡፡ በዚህ ስልጣን ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ካገለገልክ በኋላ፤ ሥራውን በገዛ ፈቃድህ በመልቀቅ ወደ ትውልድ ቀዬህ ትመለሳለህ፡፡ እናም በተወለድህ በ53 ዓመትህ፤ ነሐሴ 14 ቀን ከጠዋቱ በ1 ሰዓት ከዚህ ዓለም በሞት ትለያለህ፡፡ አንድም ልጅ ሳታፈራ መሞትህም ያሳዝናል፡፡
[ሊያዎፋን] ሽማግሌው የተናገሩኝን ሁሉ በጽሁፍ መዝግቤ ስለያዝኩ ቃላቸውን ልቅም አድርጌ አስታውሳለሁ፡፡ እርሳቸውን ካገኘሁበት ዕለት ወዲህ በምወስዳቸው ፈተናዎች ሁሉ የማገኘው ውጤት ሽማግሌው ኮንግ ከተነበዩት ዝንፍ ያለ አልነበረም፡፡ እንደ ሽማግሌው ኮንግ ትንቢት፤ እኔ ያሉትን ሹመት የማገኘው 91 ኪሎ ገብስ እና 5 ቁና ሩዝ ደመወዝ እየተሰፈረልኝ ካገለገልኩ በኋላ ነበር፡፡ ሆኖም፤ የትምህርት አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን በሆኑት ሚስተር ቱ ጥቆማ ለሹመት የታጨሁት፤ 71 ኪሎ ሩዝ እየተሰፈረልኝ ከሰራሁ በኋ ነበር፡፡ ያኔ በልቤ የሽማግሌው ኮንግን ትንበያ መጠራጠር ጀመርኩ፡፡
[ሊያዎፋን]፡ የሆነ ሆኖ፤ ትንቢታቸው በመጨረሻው የማይታበል መሆኑ ታየ፡፡ ምክንያቱም፤ የሚስተር ቱ የበላይ አለቃ የሆኑት ሚስተር ያንግ የእኔን የሹመት ሃሳብ ውድቅ አደረጉት፡፡ ብዙ ዓመታት አልፎ፤ ሚስተር ቺዩ -ሚን ያንግ፤ ድንገት ወረቀት ሲያገላብጡ ሳለ የቆየ የፈተና ውጤቴን እስካዩ ድረስ የሹመት ሀሳብ ተነስቶ አያውቅም ነበር፡፡ እርሳቸውም የፈተና ውጤቴን አይተው በመገረም፡-
[ሊያዎፋን]፡ እነዚህ አምስት ፅሁፎች፤ ለንጉሱ የተላኩ ድንቅ ሪፖርቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ እፁብ ድንቅ የሆነ ችሎታ ያለውን ታላቅ መምህር እንዴት እዚህ ቀብረን እናስቀራለን?
[ሊያዎፋን]፡ ሚስተር ያንግ፤ በእርሳቸው ሥር ለሚሰጠው “የአፄ ተማሪ “ ለተሰኘ የፈተና መርሃ ግብር እጩ ሆኜ እንድቀርብ የሚያሳስብ የትዕዛዝ ደብዳቤ በአስተዳዳሪው እንዲፃፍልኝ አደረጉ፡፡ ያን አስገራሚ ሹመት ካገኘሁ በኋላ፤ ሽማግሌው ኮንግ እንዳሉት፤ 91 ኪሎ ገብስ እና 5 ኪሎ ሩዝ ደመወዝ ይሰፈርልኝ ጀመረ፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ፤ በትንቢት የተነገረው ሹመት፣ ማዕረግ ወይም ሀብት ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚመጣ ፍፁም አመንኩ፡፡ ሌላው ቀርቶ፤ የሰው ልጅ የዕድሜ ዘመን እንኳን አስቀድሞ የተወሰነ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ሁሉንም ነገር “ምን ይፈጠር ይሆን? “ የሚል ጉጉት በራቀው ስሜት መመልከት ጀመርኩ፡፡ ጥቅም እና ትርፍ ለማግኘት ብሎ መጣጣርን እርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡
[ሊያዎፋን]፡ በ “አፄው ተማሪ “ መርሃ ግብር ከተመረጥኩ በኋላ፤ በቤጂንግ ዩኒቨርስቲ የመማር ዕድል አገኘሁ፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል በሀገሪቱ መዲና ባለው የቤጂንግ ዩኒቨርስቲ በቆየሁበት ጊዜ፤ ተመስጦ የማድረግ ፍላጎቴ እየበረታ መጣ፡፡ እናም አንዳችም ሀሳብ በህሊናዬ ሽው ሳይል ረጅም ሰዓታትን በፀጥታ አሳልፋለሁ፡፡ መፅሃፍ የማንበብ ፍላጎቴም ጨርሶ ጠፋ፡፡ ጥናቱንም እርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡ ወደ ብሔራዊው ዩኒቨርስቲ ከመምጣቴ በፊት ናንኪንግ በተባለ ግዛት በሚገኘው ቲያ የተባለ ተራራ ላይ የሚኖሩትን “አብርሆት የተቀዳጁ “ እና ዩን - ጉ የተባሉ አንድ የዜን መምህርን ለመጎብኘት ሄጄ ነበር፡፡ ከእኒሁ መምህር ፊት ለፊት በመቀመጥ፤ ተመስጦ ይዤ ሦስት ሌሊት እና ሦስት መዐልት እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር በተመስጦ አዳራሹ ቆየሁ፡፡ ከዚያም መምህር ዩን - ጉ እንዲህ አሉኝ፡-
[መምህር ዩን-ጉ]፡ ተራ - ተርታ ሰዎች፤ ብፅዕናን የማያገኙት ብዙ የባዛኝ እና ከንቱ ሀሳብ በአዕምሮአቸው ስለሚመላስ ነው፡፡ እኔ እና አንተ በተመስጦ ሦስት ቀናትን ስናሳልፍ፤ በአዕምሮህ አንድም ባዛኝ ሀሳብ ሲመላለስ አላየሁም፡፡ ለመሆኑ፤ ይህ የሆነው እንዴት ነው?
[ሊያዎፋን]፡ እኔም መለስኩላቸው፤ “ሚስተር ኮንግ የሚባሉ አንድ ሰው፤ በህይወት ዘመኔ የሚገጥመኝን ነገር ሁሉ በደንብ አድርገው ተንብየው ነግረውኛል፡፡ የዕድሜዬ ርዝመት፣ ሞቴ ህይወቴ፣ ሹመቴ፣ ውድቀቴ ሁሉ አስቀድሞ የተወሰነ እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ፤ በህይወቴ ምን ይገጥመኝ ይሆን በማለት መጨነቅ ወይም መመኘት ፋይዳ የለውም፡፡ እንዲያ ማድረግ ለእኔ አስፈላጊ አይደለም፡፡ በአዕምሮዬ አንድም ባዛኝ ሀሳብ ሲመላለስ ያላዩት በዚህ የተነሳ ነው፡፡ “ መምህር ዩን-ጉ ሣቅ ብለው እንዲህ አሉ፡-
[መምህር ዩን-ጉ]፡ እኔማ ታላቅ ችሎታን የታደለህ ሰው መስለኸኝ ነበረ፡፡ ሆኖም አሁን፤ ከብዙሃኑ የማትለይ ተራ - ተርታ ሰው መሆንህን አወቅሁ፡፡
[ሊያዎፋን]፡ እርሳቸው በተናገሩት ነገር ፍፁም ግራ ተጋባሁ፡፡ ነገሩን እንዲያብራሩልኝም ጠየቅኋቸው፡፡ እርሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፡-
[መምህር ዩን-ጉ]፡ የተራ ተርታው ሰው አዕምሮ ሁሌም በባዛኝ እና ምናባዊ ሃሳቦች የተመላ ነው፡፡ ስለዚህ ህይወታቸው፤ ከይን - ያንግ ዑደት እና ከዕጣ ፈንታ ግዝት አይወጣም፡፡ መቼም፤ ዕጣ-ፈንታ የሚባል ነገር የለም አልልም፡፡ ሆኖም፤ በልደት ዕጣ-ፈንታ ታስረው የሚቀሩት ተራ ተርታ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም፤ ታላቅ ደግነት ማድረግን የተለማመዱ ሰዎች በዕጣ-ፈንታ ገመድ ታስረው አይቀሩም፡፡ ምክንያቱም፤ ከደግ ሥራቸው የሚያዘምሩት ፅድቅ ታላቅ በመሆኑ፤ የዚሁ በጎ ምግባራቸው አዝመራ አስቀድሞ የተፃፈ የልደት ዕጣ-ፈንታቸውን በመለወጥ ከፍ ካለ ደረጃ ይወስደዋል፡፡ በበጎ ምግባራቸው ያከማቹት የበጎ ሥራ ፍሬ ዕጣ-ፈንታቸውን ከስቃይ ወደ ደስታ፤ ከድህነት ወደ ብልፅግና፤ ከአጭር ዕድሜ ወደ የዕድሜ ባለጸጋነት ይለውጠዋል፡፡ እንዲሁ፤ የበዛ ክፋት የሚያደርጉ ሰዎችም በልደት ዕጣ - ፈንታቸው አይወሰኑም፡፡ ሰው፤ የሚፈፅመው ክፉ ተግባር በበዛ እና በከፋ ጊዜ፤ ገና ሲወለድ የተሰጠውን ዕድል፣ ሀብት እና ጸጋ ይነጠቃል፡፡ ህይወቱም ከጥሩ ወደ መጥፎ ይለወጣል፡፡ አንተም ያለፉትን 20 ዓመታት መምህር ኮንግ በተነበዩት የህይወት ጎዳና ህይወትን መጥተሃል፡፡ በልደት የተሰጠህን የመጀመሪያ ዕጣ-ፈንታህን የሚለውጥ የደግነት ሥራን አልሰራህም፡፡ ይልቅስ የዕጣ-ፈንታህ እስረኛ ሆነህ ዘልቀሃል፡፡ ታዲያ አንተ ተራ ተርታ ሟች ፍጡር ያልተባልክ፤ ማን ይባል?
[ሊያዎፋን]፡ ድንግጥ አልኩ፡፡ ከዚያም ለመምህር ዩን-ጉ ጥያቄ ማቅረብ ቀጠልኩ፡፡ መምህር ሆይ፤ አሁን እርስዎ የሚሉኝ፤ አንድ ሰው ሲወለድ የተሰጠውን ዕጣ- ፈንታውን መለወጥ ይችላል ነው? ሲወለድ ከተሰጠው ዕጣ-ፈንታ ማምለጥ ይችላል ነው? መምህሩም እንዲህ ሲሉ መለሱ፡-
[መምህር ዩን- ጉ]፡ ዕጣ-ፈንታ ፈጣሪዎች እኛው ራሳችን ነን፡፡ በህይወት የሚገጥመን መልካም ዕድል ወይም መጥፎ ዕድል የኛው ሥራ ነው፡፡ መጥፎ ሥራ በሰራሁ ጊዜ፤ ውድቀት ተከትሎ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ለበጎ ሥራ በተጋሁ ጊዜም፤ መልካም ዕድል መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ጥንታዊ የጥበብ መዝገቦች ላይ የምናገኘው እውነት ይሄ ነው፡፡ በቡዲስቶች መፅሃፍ እንደ ተፃፈው፤ አንድ ሰው ሃብትን፣ ማዕረግን፣ ልጅን፣ ረጅም ዕድሜን ከተመኘ እና አጥብቆ ካሻ፤ ያሻውን ሊያገኝ ይችላል፡፡ ይሄን ለማግኘት፤ በጎ ሥራን መስራት ነው፡፡ የዕጣ-ፈንታን እስር፤ ደግነት ይፈተዋል፡፡ የጥበብ መፃሕፍት በሀሰት መመስከር ወይም መዋሸት ታላቅ ሀጢአት መሆኑን ይናገራሉና ራሳቸው ሀሰትን አይናገሩም፡፡ ስለዚህ፤ በጎ ሥራ ዕጣ-ፈንታን መቀየሩን በፍፁም እርግጠኛ መሆን እንችላለን፡፡ ታላላቅ መምራን እኛን ለማታለል የሚነሱበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
[ሊያዎፋን]፡ “ማንም ሰው የተመኘውን ነገር ያገኛል “ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ስለዚህ ለመምህሩ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ሜኒሲየስ፤ “ሰው የፈለግነው ነገር ሁሉ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ፍለጋውንም ማድረግ ያለበት ውስጥ እንጂ ውጪ አይደለም፡፡ “ ብሏል፡፡ ውስጣዊ ፍለጋ፤ የልብ ንፅህናን፣ ደግነትን፣ ግብረ-ገባዊነትን የሚጠቅስ ቃል ነው፡፡ እነኝህ የጠቀሳቸው ነገሮች ልንጥርላቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ታዲያ ውጫዊ የሆኑትን ሀብት፣ ዝና እና ክብርን ፈልገን የምናገኛቸው የት-እንዴት ነው? ሃብት፣ ዝና እና ከብር የመሳሰሉትን ነገሮች፤ ሰዎች የሚሰጡን ነገሮች አይደሉም? መምህሩ እንዲህ ሲሉ መለሱ፡-
[መምህር ዩን-ጉ]: ሜኒሲየስ፤ የተናገረው እውነት ነው፡፡ አንተ ግን በስህተት ተረጎምከው፡፡ የዜን ስድተኛው ፓትርያርክ ሁይ-ኔንግ፤ “የፅድቅም ሆነ የኩነኔ ማሣ የሚገኘው ከልባችን ውስጥ ነው “ ሲሉ አስተምረዋል፡፡ ከልባችን ውስጥ ስንፈልግ መልካም ዕድልም ሆነ አበሳ በዚያ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ውጭው የውስጥ ነፀብራቅ ብቻ ነው፡፡ እናም በውስጣዊ ፍለጋ የምናገኘው፤ የልብ ንፅህናን፣ ደግነትን፣ ግብረ-ገባዊነትን ብቻ ሳይሆን ሃብት፣ ዝና እና ክብርንም ጭምር ነው፡፡ አንድ ሰው ልቡን ሳይመረምር እና ሳያይ ሀብትን፣ ዝናን፣ መልካም ዕድልን እና ረጅም ዕድሜን ዓይኑን ጨፍኖ በውጭ ሊያገኛቸው ቢዳክር፤ ፍለጋው ከንቱ ነው፡፡
[ፀሐፊው]፡ ግዕዝ ይህን ሀሳብ በአጭር ቃል፤ “ኩሉ ይሤኒ ለእመ ንሤኒ ንህነ “ ይለዋል፡፡ ትርጉም “በስለሺ “ ብዬ፤ “እኛ ጥሩዎች በሆንን ጊዜ፣ ሁሉ ጥሩ ይሆናል፡፡”

 

Read 3337 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:32