Saturday, 22 February 2014 13:22

ደደቢት በሻምፒዮንስ ሊግ ከአምናው የኮንፌደሬሽን ካፕ ሻምፒዮን ሴፋክሲዬን ተገናኘ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

           በ2014 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የአምናው የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ደደቢት ወደ አንደኛ ዙር ማጣርያ ማለፉን አረጋገጠ፡፡ በሌላ በኩል በ2014 የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ  ቅድመ ማጣሪያ በሁለቱም ጨዋታ የተሸነፈው መከላከያ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል። ባለፈው ሰሞን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ  ደደቢት ከሜዳው ውጭ በዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም 2ለ0 ቢሸነፍም፤ በአጠቃላይ የደርሶ መልስ ውጤት 3ለ2 አሸንፏል።  በኮንፌደሬሽን ካፕ ቅድመ መጣርያ የመልስ ጨዋታ ሊዮፓርድስን በሜዳው ያስተናገደው የአምናው የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን መከላከያ 2ለ0 ተሸንፎ በአጠቃላይ ውጤት 4ለ0 ተረትቶ ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ አንደኛ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ኢትዮጵያን የወከለው ደደቢት የሚገናኘው  ከቱኒዚያው ክለብ ሲኤስ ሴፋክሲዬን ጋር ነው፡፡ ደደቢት ከቱኒዚያው ክለብ ጋር የደርሶ መልስ ትንቅንቁን ከሳምንት በኋላ በሜዳው ይጀምራል፡፡  
መከላከያ ትኩረቱን ወደ ሊጉ ይመልሳል
በ2014 የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ የቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎች ወደ አንደኛ ዙር ለመግባት 11 ክለቦች እድል ነበራቸው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የጥሎ ማለፍ አሸናፊ የነበረው መከላከያ ከታላቁ የኬንያ ክለብ ጋር በመደልደሉ ቅድመ ማጣርያውን ማለፍ አልቻለም፡፡ መከላከያ ትኩረቱን ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ በመመለስ ለዋንጫ ተፎካካሪ እንደሚሆን ተገምቷል። መከላከያ ከዘንድሮ በፊት በአፍሪካ ደረጃ በሁለት የውድድር ዘመናት የተሳትፎ ልምድ ነበረው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ድሮ “ካፕዊነርስ ካፕ” ተብሎ በሚጠራው የጥሎ ማለፍ ዋንጫ በ1976 እኤአ ተሳትፏል፡፡ በወቅቱም እስከ ሩብ ፍፃሜ ለመጓዝ በቅቶ ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ ደግሞ በኮንፌደሬሽን ካፕ ሲሳተፍ ቅድመ ማጣርያውን አልፎ ነበር፡፡ ከዚያ በመጀመርያው ዙር ክለብ በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል፡፡
ደደቢት 3 ኬኤምኬኤም 2
በ2014 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሳምንት በፊት በቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎች 14 ክለቦች ወደ አንደኛ ዙር ማጣርያ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ አምና የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፈው ደደቢት በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር በአጭር ጊዜ ስኬታማ በመሆን ከመደነቁም በላይ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ባለው አስተዋፅኦም የተለየ ነው፡፡ በ2011 እና በ2012 እኤአ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ደደቢት ለዚህ ውጤቱ በሁለት የውድድር ዘመን የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ካፕን ለመሳተፍ ልምድ አለው፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትየጵያን ሲወክል ግን ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ማጣርያ የደደቢት ተጋጣሚ የሆነው የቱኒዚያው ክለብ ሴፋክስዬን በስኬት እና በምርጥነት ከአፍሪካ 5 ታላላቅ ክለቦች ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ የቱኒዚያ ፕሪሚዬር ሊግን ለ8 ጊዜ ያሸነፈው ሴፋክስዬን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለት ጊዜ በነበረው ተሳትፎ በ2006 ኤአ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘበት ውጤት ከፍተኛው ነበር፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፕ ደግሞ በ2007፤ በ2008 እና በ2013 እኤአ ለሶስት ጊዜያት ዋንጫውን በማንሳት እና በ2008 እና 20009 እኤአ በካፍ ሱፕር ካፕ ሁለተኛ ደረጃን አከታትሎ አስመዝግቧል፡፡
በቱኒዚያዊው አሰልጣኝ ሃመዲ ዳው የሚመራው ሴፋክሴዬን በተጨዋቾች ስብስቡ የካሜሮን፤ የጋና፤ የአይቬሪኮስት፤ የጋቦንና የሞሮኮ ተጨዋቾችን ያካተተ ሲሆን አጠቃላይ 26 ተጨዋቾች የሚገኙበት ስብስቡ በትራንስፈርማርኬት የዝውውር ገበያ ስሌት 8 ሚሊዮን 750ሺ ዩሮ የተተመነ ነው፡፡ 3152 የተመዘገቡ አባላት ያሉት ሴፋክሴዬን በሜዳነት የሚጠቀመወ 12ሺ ተመልካች የሚያስተናግደውን ስታዴ ታሌብ ማሃሪ ስታድዬምን    ነው፡፡

Read 1895 times