Saturday, 22 February 2014 13:23

ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር ከሳምንት በኋላ ይጀመራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

        የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ከ17 ዓመት በታች የታዳጊ ውድድር ከሳምንት በኋላ ይጀምራል፡፡ የታዳጊዎችን ውድድርን በጥራት ለመምራት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በውድድሩ ተሳታፊ በሚሆኑ ክለቦች ላይ አስፈላጊውን  የእድሜ ማጣራት በማከናወን ከሞላ ጎደል ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ  ለማወቅ ተችሏል፡፡ በውድድሩ ከ17 ዓመት በታች ቡድናቸውን የሚያሳትፉ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው የተዘጋጀውን የእድሜ ማረጋገጫ ምርመራ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የህክምና ኮሚቴ የግምባር ፍተሻ እና በቴክኒክ ኮሚቴው ተጨማሪ ማረጋገጫ መሰረት አከናውነዋል፡፡  ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድሩ የካቲት 22 እንደሚጀመር የገለፀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተሳታፊ ክለቦች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ ያስተላለፈ ሲሆን ዘንድሮ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ብዛት 9 እንደሆኑና ውድድድራቸውን በደቡብ እና በማዕከላዊ ዞኖች በመከፋፈል እንደሚያደርጉ አስታውቋል፡፡ በማዕከላዊ ዞን  ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ኢትዮጵያ ቡና፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ደደቢት፤ መብራት ሃይልና ሙገር ሲምንቶ ሲመደቡ፤ በደቡብ ዞን ደግሞ አርባምንጭ ፤ ሲዳማ ቡና እና ሃዋሳ ከነማ ይገኛሉ፡፡
ከ17 ዓመት በታች ውድድሩ የተዘጋጀው በታዳጊዎች ላይ በመስራት የአገሪቱን እግር ኳስ እድገት በጠንካራ መሰረት ላይ ለመጣል ያስችላል ተብሎ ነው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተተኪ ተጨዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን ለማፍራት እንደሚንቀሳቀስ  ስፖርት አድማስ ያነጋገራቸው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የውድድር ዋና ስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ተድላ ዳኛቸው ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ  የታዳጊዎችን ውድድር ለማካሄድ በፌደሬሽን በኩል እንቅስቃሴው ከተጀመረ ቢቆይም ተግባራዊነቱ አልተሳካም ነበር፡፡ በቀድሞ የፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ የሴቶች እግር ኳስ  ቡድኖችን ከማቋቋም ባሻገር የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች የታዳጊ ቡድኖች እንዲኖራቸውና ውድድር እንዲያካሂዱ ከስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተድላ ዳኛቸው፤ አሁን ያለው አዲስ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም በወጣቶች ላይ መስራት ለእግር ኳሱ እድገት ወሳኝ አቅጣጫ ነው በማለት የታዳጊዎች ውድድሩን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ይገልፃሉ፡፡
የእድሜ ማረጋገጫ ምርመራዎች
አንድ ክለብ የሀ 17 ቡድን ሲመሰርት ማሟላት ያለበት መስፈርቶች በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በኩል ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመርያው የተጨዋቾች የእድሜ ገደብን ማሟላትና ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ክለቦች በዘመናዊ የህክምና ምርመራ በማከናወን በሚያቀርቡት ማስረጃ ብቻ ሳይሆን በፌዴሬሽኑ የህክምና ኮሚቴ በኩል በግምባር የተጨዋቾችን ተክለሰውነት በተለያዩ ዘዴዎች በመፈተሽ በሚካሄድ  ምርመራ  መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ አቶ ተድላ ዳኛቸው እንደሚያስረዱት ክለቦች በየትኛውም ዘመናዊ የህክምና ተቋም የኤምአርአይ ምርመራቸውን ካከናወኑ በኋላ የፌደሬሽኑ  የቴክኒክ እና የህክምና ኮሚቴዎችን ተጨማሪ ማረጋገጫ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ እንደ አቶ ተድላ ዳኛቸው ገለፃ ከኤምአርአይ ምርመራው ሌላ ኮሚቴዎቹ  በተለያዩ መንገዶች የተጨዋቾችን እድሜ ለማጣራት የሰሩት አንዳንድ የማጭበርበር ሁኔታዎችን ለማስቀረትነው፡፡ በዚህም መሰረት የህክምና ኮሚቴው የእያንዳንዱን ክለብ ተጨዋቾች  ወደ ስታድዬም ጠርቶ በአጠቃላይ ተክለሰውነታቸውን ገምግሟል፡፡ ማንኛውም ተጨዋች በሁሉም  ምርመራዎች የእድሜው ትክክለኛነት ካላረጋገጠ መጫወት አይችልም፡፡ ከ17 ዓመት በታች በተዘጋጀው የታዳጊዎች ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦች በስብስባቸው የሚይዟቸው ተጨዋቾች እድሜያቸው 15 እና 16 ዓመት  መሆን ሲገባው ይህን የእድሜ ገደብ በሟሟላት እስከ 25 ተጨዋቾች ያስመዘግባሉ፡፡  ክለቦች ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የያዟቸውን ተጨዋቾች እድሜ በሁሉም ምርመራዎች እንዲያረጋግጡ በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ እስከ የካቲት 15  የተሰጠው ቀነ ገደብ ዛሬ ያልቃል፡፡ ከዛሬ በፊት ብዙዎቹ ክለቦች የምርመራ ሂደቱን እንዳጠናቀቁ የሚናገሩት አቶ ተድላ፤ አንዳንድ ክለቦች ቢዘገዩም  በአስቸኳይ አስፈላጊውን መመርያ ተከትለው እንዲሰሩ በማበረታት ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የማጣራት ሂደቱን እንዲጨርሱ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ በማዕከላዊ ዞን ካሉት ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ደደቢት፤ መከላከያ፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሉንም መስፈርቶች በሟሟላት እና በማረጋገጥ  የውድድሩን መጀመር በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ አርባምንጭ ከነማ እና ሃዋሳ ከነማ ግን ትንሽ ቢዘገዩም በቀጣይ ሳምንት የምርመራውን ሂደት እንደሚጨርሱ ተስፋ ተደርጓል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከምንጊዜውም በላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለውን የእድሜ ማጭበርበር ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም መያዙን የገለፁት የውድድር ዋና የስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ተድላ ዳኛቸው፤ የተጨዋቾች መረጃ  በትክክለኛ መንገድ  ተሰርቶ በዘመናዊ የመረጃ ክምችት  መቀመጥ  ስላለበት የምርመራ ሂደቶችን በትኩረት መከናወናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ከታዳጊዎች ውድድሩ ጋር በተያያዘ የተጨዋቾች ምዝገባ የተከናወነው አለም አቀፍ መመርያን በመከተል ነው፡፡ በዚህ መሰረትም በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አሰራር በትክክለኛ ምርመራዎች እድሜው ተረጋግጦ የተመዘገበ ተጨዋች ወደፊት እድሜውን ሊጨምር ወይንም ሊቀንስ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የውድድሩ አካሄድ እና ጠቀሜታዎች
ከ17 ዓመት በታች የሚካሄደው የታዳጊዎች ውድድር በአንድ ዙር እንደሚደረግ የተናገሩት የውድድር ዋና የስራ ሂደት ሃላፊው፤ የየክለቦቹ ተጨዋቾች ተማሪዎች እንደመሆናቸው ከውድድሩ በተያያዘ ትምህርታቸውን እንዳያስተጓጉልባቸው በሳምንት አንዴ ጨዋታዎችን ለማካሄድ እንደተወሰነና ታዳጊዎቹ በየስታድዬሞቹ በቂ ተመልካች እንዲያገኙ  ከተለያዩ የፕሪሚዬር ሊግና ሌሎች ውድድሮች ጋር ጎን ለጎን በማካሄድ  የፉክክር መንፈሱን ለማሟሟቅ መታሰቡን ገልፀዋል፡፡ በታዳጊዎች ውድድሩ ለሚያሸንፍ ክለብ ልዩ ዋንጫ መዘጋጀቱ እንደማይቀር የጠቀሱት የውድድር ዋና የስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ተድላ ዳኛቸው፤ በታዳጊ ደረጃ የሚደረግ ውድድርን በተለያየ የማበረታቻ ድጋፎች ማስኬድ መሰረታዊ ጥቅም ስለሚኖረው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በዚህ ረገድ ትኩረት እንደሚሰጥ አስባለሁ ብለዋል፡፡
የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በታዳጊዎች ውድድር በመሳተፋቸው በርካታ ጥቅሞችን እንደሚያገኙ የውድድር ዋና የስራ ሂደት ሃላፊው ያስገነዝባሉ፡፡ የመጀመርያው  ጥቅም ውድድሩ ለዋና ቡድናቸው በቂ እና ብቁ ተተኪ ተጨዋቾችን የሚያሳድጉበት እድል ለክለቦች ይፈጠርላቸዋል፡፡ ዋና ቡድናቸውን ለማጠናከር ብቻ ሳይሆን ክለቦች በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡበትንም ሁኔታ የሚያስቀርና ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ክለቦች ወጣት ተጨዋቾችን በዝውውር ገበያ በማቅረብ ገቢ ሊያገኙበት ይችላሉ፡፡ ከክለቦች ተጠቃሚነት ባሻገር ከፍተኛው ውጤት ክለቦች ለብሄራዊ ቡድን ወጣት እና ተተኪ ተጨዋቾችን በየጊዜው እንዲያፈሩ የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡  በ2015 እኤአ ኒጀር ላይ በሚደረገው የአፍሪካ የሀ-17 ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ አያይዘው ያነሱት አቶ ተድላ ዳኛቸው፤  በዚህ አህጉራዊ ሻምፒዮና ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሀ 17 ብሄራዊ ቡድን የሚበቁ ተጨዋቾችን ለማግኘት ውድድሩ አመቺ መድረክ ይሆናል ብለዋል፡፡
በውድድሩ  ክለቦች በዋናነት በስልጠና ወጥ አሰራር እንዲኖራቸው ይደረጋል ያሉት  አቶ ተድላ ዳኛቸው፤  በየክለቡ ታዳጊዎችን የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ብቃታቸው እንደሚመዘን ወጥ የሆነ የስልጠና መመርያ ተከትለው እንዲሰሩ እና እንዲወዳደሩ ጥረት እንደሚደረግ አስገንዝበው፤ ለዚህም  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዲፓርትመንት የስልጠና ማንዋል በመስራትና አሰልጣኞች ብቃታቸውን የሚያሳድጉባቸው ሴሚናሮች በማዘጋጀት እንደሚንቀሳቀስ በመግለፅም ታዳጊዎች  በወጥ  የስልጠና ሂደት በማለፍ ለብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሲደርሱ በተመሳሳይ ብቃት እና አቋም እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል፡፡
በክለቦች ህጋዊነት ሰርተፍኬት ያለው ወቅታዊ ሁኔታ
ከ17 ዓመት በታች በሚደረገው የታዳጊዎች ውድድር ላይ ክለቦች ቡድኖችን በማቋቋም መሳተፋቸው በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንን የሚጠየቀውን የአንድ እግር ኳስ ክለብ መመዘኛ ለሟሟላት ወሳኝ መሆኑን የሚገልፁት የውድድር ዋና የስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ተድላ ዳኛቸው፤  የክለቦች ህጋዊነት ሰርተፍኬትን በየደረጃው በማግኘት በአህጉራዊ ውድድሮች ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን  ያስረዳሉ፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በወጣ መመርያ መሰረት አንድ ክለብ በውድድር ሲሳተፍ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶች አሉ፡፡ እነዚህን መስፈርቶች የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ያወጣው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በሚያዘጋጃቸው አህጉራዊ ውድድሮች ለክለቦች የመሳተፍ ፍቃድ የሚሰጠው ተገቢውን መስፈርት አሟልተው የክለቦች ህጋዊነት ሰርተፍኬት ያገኙትን ብቻ  ነው፡፡  ክለቦች ይሄው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን መመርያ ተገልጾላቸው የተቀመጡትን መመዘኛ መስፈርቶች እንዲያሟሉ ከተነገራቸው ሶስተ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከመስፈርቶቹ መካከል በቅድሚያ ክለቦች በአደረጃጀታቸው በወጣቶች ላይ የተመሰረት መዋቅር  እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፤ ይህም የእግር ኳሱን ወጥ እድገት ለመቀጠል ወሳኝ ስለሆነ ነው፡፡
ክለቦች በታዳጊዎች እና በወጣቶች ስልጠና ሊያሰሯቸው የሚችሏቸው ብቁ አሰልጣኞች እንዲኖሯቸው ይጠየቃል፡፡ አንድ በፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ክለብ ክለብ የተሟላ ዕህፈት ቤት፤ በቂ የፋይናንሻል አቅም ፤ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ፤ የተሟላ የባለሙያዎች አደረጃጀት ሊኖረው ይገባል፡፡ በእነዚህ መስፈርቶች መሰረት ክለቦች  በሶስት  ደረጃዎች በኤ፤ ቢ እና ሲ በመመዘን የህጋዊነት ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል፡፡ የህጋዊነት ሰርተፍኬቱን ለመስጠት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የክለቦች አደረጃጀት፤ አቅም አቅም በግንባር እንዲገመግም ሃላፊነት እንደተሰጠው አቶ ተድላ ዳኛቸው ሲናገሩ፤ ለዚህም ተብሎ ሁለት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ከአዲሱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጋር በመተዋወቅ በቅርቡ ስራቸውን ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ በክለቦች ህጋዊነት ሰርተፍኬት አሰጣጥ ላይ የሚሰሩት ኮሚቴዎች አንደኛው ቅደመ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን ሌላኛው የይግባኝ ሰሚ  ነው፡፡ ቅድመ ውሳኔ የሚሰጠው ኮሚቴ በመጀመርያ ውሳኔ ሰጭነቱ ክለቡ ምን አሟልታል በሚል በቂ ግምገማ እና ክትትል በማድረግ የየክለቡን የፍቃድ ደረጃ የሚወስን ይሆናል፡፡ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ደግሞ ክለቦች በቅድመ ውሳኔ ሰጪ ኮሚቴው በተሰጣቸው  ደረጃ ላይ ቅሬታ ካላቸው ይግባኝ ብለው የተሰጣቸውን ምዘና ሊያስተካክሉ የሚችሉበት ነው፡፡
አንዳንድ ሁኔታዎችን በመገንዘብ ለመረዳት እንደሚቻለው በክለቦች ህጋዊነት ሰርተፍኬት መመዘኛ ብዙዎቹ  የኢትዮጵያ ክለቦች በሲ ደረጃ ሲሆኑ በቢ ደረጃ ያሉ ጥቂት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እግር ኳስ በኤ ደረጃ ሰርተፍኬት የሚያገኝ ክለብ የለም፡፡ በክለቦች ህጋዊነት ሰርተፍኬት እንዲሰጥ መመርያ ያስፈለገው አንድ ክለብ በአህጉራዊ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ለመሳተፍ ማሟሟላት  የሚገባው ደረጃዎች ስላሉ ነው፡፡ ክለቦች በዚህ መመርያ መሰረት ሊያሟሉ የሚገባቸውን መስፈርቶች እንዲያሟሉ በፊፋ በኩል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በተደጋጋሚ ቢሰጡም ብዙም እየተራመዱ አይደለም፡፡  የፐሪሚዬር ሊግ  ክለቦች አስቀድመው የሴቶች ቡድን በማቋቋም ተንቀሳቀሰው አሁን ውድድር እየተደረገ ውጤቱን በማየት ላይ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሀ 17 ቡድኖች መያዛቸው አንዱ ርምጃ ሲሆን አንዳንድ ክለቦች የቴክኒክ ዲያሬክተር መቅጠራቸው፤ በማርኬቲንግ ባለሙያ መስራትም መጀመራቸውም እንደለውጥ የሚታይ ቢሆንም ገና ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

Read 2023 times