Saturday, 10 December 2011 09:33

እጅጋየሁ ጠላ ቤት

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(1 Vote)

በሰቆጣ ዳገት በብርብር ፀሃይ እቱ ጥላ ይዤ ልከተልሽ ወይ”
የተከበራችሁ አንባብያን፡-
የዛሬ ጽሑፋችን ያየሁትም የተሳተፍኩበትም ታሪክ ስለሆነ፣ የሰዎቹን ስም ለውጫለሁ፣ ማንም ለይቶ እንዳያውቃቸው ለመጠንቀቅ፡፡ ታሪካቸው ፈጣሪያቸው እንደፃፈው፣ ምንም “ሳይሻሻል” ቢነገር፣ በምናብ እነሱን ሆነን፣ ለአጭር ሰአት ራሳችንን ረስተን፣ ድራማውን እንኖረዋለን ብዬ አምናለሁ (የመዝናናት አንድ መልክ)

በደርጉ ዘመን እንገኛለን፡፡ ወይዘሮ እጅጋየሁ ጠላና አረቄ ቤት አላት፣ በመጠነኛ ዋጋ የምታቀርበው ምግብም ባለሙያ እንደሰራችው ያስታውቃል፡፡ 
ውፍረት የሚያምርባት፣ ረዘም ያለች፣ ፈገግታዋ የሚያዝናና፡፡ ጥቁር ስለምትለብስ እና እሸቴ የሚባል የአስራ ሁለት አመት ልጅ ስላላት፣ ባልዋ በደጉ ዘመን በሞቀ ትዳር ስትኖር ያስገቡትን ቴሌፎን ወደዚህኛው ቤቷ ይዛው መጥታለች፡፡
የምመገበውም የምዝናናውም እጅጋየሁ ቤት ነው፡ከሷ ጋር እንስማማለን፣ እሸቴን ቀልደኛ ስለሆነ እወደዋለሁ፣ ጮካ አራዳ ስለሆነ ደሞ ያስደንቀኛል፡፡ ትምህርቱን ማጥናትና የቤት ስራ መስራቱን ሲጠይቀኝ ስለማግዘው፣ ከናቱ ጋር በመጠኑ እንዋደዳለን፡፡
አንዳንድ ምሽት እየመጣ የእጅጋየሁን ጠላ እያጣጣመ የሚያደንቅላት፣ አመነሸዋ የሚባል ጐልማሳ አለ፡፡ ምናልባት አርባ አመት ይሆነዋል፣ ረዘም ያለ ደንዳና፣ ግርማ ሞገስ ያለው፡፡ ፈገግ ሲል፣ ፊቱ ከነፍንጭት ጥርሱ ወደ ሀያዎቹ አመታት ያለ ጐረምሳ ያስመስለዋል፡፡ እጅጋየሁን እንደሚፈልጋት ያስታውቃል፡፡ ከእሸቴ ጋር ደሞ ሽርክ ሆነዋል፡፡ አንዴ “ምላጭ” ይለዋል፣ ሌላ ጊዜ “ቅመም”፡፡ ብቻ ያሞጋግሰዋል እንጂ አያቆላምጠውም፡፡
ከአመነሸዋ ጋር በእጅጋየሁና በእሸቱ በኩል ስለተዋወቅን፣ እና ኮከባችን ስለተገጣጠመ፣ ባጭር ጊዜ እየተግባባን ሄድን፡፡
ገበያ ባልበዛ ሰአት እጅጋየሁ፣ አመነሸዋ፣ እኔ ሆነን ከምግብ ቤቱ በመጋረጃ ወደተከለለው መኝታ ቤትዋ ገብተን እንጫወታለን፡፡ ተፈላልገዋል ግልጽ ነው፡፡
ሁለቱም የተጉለት ልጆች በመሆናቸው ደሞ ብዙ የሚያወጉበት የሚያግባባቸው ርእሰ ጉዳይ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስለገጠመኛቸው ወይም ስለሰሙት የሰዎች ታሪክ ሲወያዩ ሙሉ ልቤን ወስደውት በጆሮዬ እሳተፋለሁ፡፡
አመነሸዋ በተፈጥሮ አስተዋይነቱ Sociologist ነው፡፡ ለናሙና ያህል አንድ ቀን ያጫወተን እነሆ፡-
ማንም ከተማ ብትሆን በመጀመሪያ አንዲት ቤት ነበረች፡፡ ሁለት ሶስት እያለች መንደር ትሆናለች፡፡ እያደገች ትሄዳለች፡፡ ማንም ሳያውቅባት ቀስ በቀስ ከተማ መሆን ይዳዳታል፡፡ አንድ ጥርጊያ መንገድ፣ አንድ ጋሪ፣ አንድ የአረብ ሱቅ (ወይም ዛሬ ዛሬ ከሆነ የጉራጌ ሱቅ) ከነሻይ ቤቱ ይኖራታል፡፡ አንድ ጋሪ ወይ አንድ ሱቅ ከጨመረች፣ ከዛሬ ነገ ከተማ ሆንኩ ትላለች፡፡
ብቸኛዋ ሱቅ ውስጥ አህመድ የተጣጠፉ እግሮቹ ላይ ቁጭ ብሎ ጫት እየቃመ ነው፡፡
“የአሊ እናት” ብሎ ይጣራል
“አቤት” ትላለች ሚስቱ
“አንድ ሻሂ” ብሎ ከጮኸ በኋላ፣ በትንሽዬ ድምጽ “ኩስ ኡምሽ” ይላታል፡፡
ብቸኝነቱ ከራሱ ጋር ያናግረዋል…ከዚህ ከታሪካችን ጋር ግንኙነት በሌለው ምክንያት ለሶስት ሳምንት ያህል ከእጅጋየሁ ቤት ቀርቼ ነበር፡፡ ዛሬ ረፋድ ላይ ብቅ ስል፣ ፆመ ነነዌ የሚፈታበት ቀን ሆኖ፣ አመነሸዋ ከአጥሩ እንጨት ላይ በሚስማር ላይ የተንጠለጠለ በግ እየበለተ ነው፡፡ እጅጌውን ሰብስቦ ሽርጥ ታጥቋል፡፡ እሸቴ ብልቱን እየተቀበለ ሳፋ ውስጥ ያስቀምጠዋል፡፡
“ቅመም” አለው “አረቂዬን አቀብለኝማ” አቀበለው፣ ጨለጣት “ሌላ ቅዳልኝ” ትንሽ ቆይቶ አንድ ገጠር ሽማግሌ ድምጽ በጣም ጮሆ “በእንተ ስማ ለማርያም!” ተዘከሩኝ ፃድቃኖቼ” ብሎ ሲለምን፡-
“ምን ያስጮሆታል” አላቸው፣ መበለቱን እየቀጠለ “እንደ ጨዋ ሰው ቀስ ብለው አይለምኑም”
“አዬ ጌታዬ፣ ችግሬን አውቀህልኝ ቢሆን ኖሮ ግን ባልነቀፍከኝ ነበር”
“እና ችግርዎ ምንድነው?”
“ላስታ ነው አገሬ፡፡ ገና በልጅነት ጀምረን ገደል ለገደል ዝንጀሮ ስናባርር ሩቅ ለሩቅ እየተጯጯህን ነው፡፡ እዚያ ነው መጮህ የለመደብኝ”
“ለምንድነው ምታባርሩት”
“እህላችንን እየበላብን፣ እያጠፋብን ፍዳችንን ስለሚያሳየን ነዋ! እንደ ዝንጀሮ ማን ጠላት አለ?”
“ዝንጀሮ ሸሽተው ነው ወዲህ የፈለሱት?”
“እንኳን ከዝንጀሮ ከባለስልጣን ሰው አልሸሽም፡ ደፋር ስለሆንኩ ነበር ወደዚህ የላኩኝ፡፡ መንግስት አድሀርያን ከሚባሉ ግፈኞች የተነጠቀ መሬት ሊሰጠን ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ልከታተልና ላስፈጽም ነበር የመጣሁት፡፡ እየተመላለስኩ ብሞክርም የሚያናግረኝ መንግስት አጣሁ፡፡ የነበረችኝን ገንዘብ ጨረስኩ፡፡ ልመና መጣ”
“እንዴት ነው የመጣው?”
“ልመና ሲጀመር ይከብዳል፡፡ ትልቅ አለት ተሸክሞ በገደል ሽቅብ እንደመውጣት ይከብዳል፡፡ ሲዘከሩህ አይናቸው አያይህም፡፡ ሰው አይደለህማ በነሱ ቤት!፡፡ ግን እንዳይለመድ የለም፣ ልመናንም ትለምደዋለህ፡ ቀስ እያለ የእለት እንጀራህን የምታገኝበት እለታዊ ስራ ይሆናል፡፡ ያውም ሰኞ ሰንበት ሳይል ያስሰራሀል፡፡
እየዞርክ ካልለመንክ ምን ትሰራለህ? መለመን ግምኛ የሚያስገድድ ሱስ ነው፡፡
ይኸውና ሚስቴና ልጆቼ ሁልጊዜ ይናፍቁኛል፡፡ ግን አገሬ ገብቼ እንዴት ልለምን እችላለሁ? ካልለመንኩስ እንዴት ይሆንልኛል?”
“አባባ” አለቻቸው እጅጋየሁ “እንግዲህ ሰው ሲመጣ ምግብ እኔ አቀርባለሁ፣ እርስዎ አረቄ ጠላውን እየቀዱ ሂሳብ ይቀበሉልኝ”
“እሺ ምን ከፋኝ? አንዳንድ ሰዎች “በእንተ ስማ ለማርያም” ብዬ ሳምባርቅባቸው
“ተው ስምዋን አታንቀልቅለው” ይሉኛል
“ታድያ እንዴት ላድርጋት? እሷ በየሰው ደጃፍ እያንቀለቀለችኝ አይደለምን?
አሁን አሁንማ ሌሊትም በህልሜ ስለመ ብርሃን ስል ነው ማድረው፡፡ ጐረቤቶች ረበሽከን እያሉኝ ነው፡፡ ምን ላድርግ? ልጇን ይዛ ነው ምትመጣብኝ፡፡ በመብረቅ ነጐድጓዱ ክርር እርር የሚያደርግ ሃያል”
ይኸው አስራ አንድ አመት እዚህ ሲኖሩ፤ ጩኸታቸው ያው ነው እንጂ የሚናገሩት ቃላት ግን የሰቆጣም ያዲሳበባም እየሆነ ሄዷል፡፡
በነገራችን ላይ፣ ከዚህ በፊት አመነሸዋ አገራቸው መግቢያ ገንዘብ ሊሰጣቸውና ወደዚያ የሚጓዝ ሰው ፈልጎ ሊያቆራኛቸው መወሰኑን ነገራቸው፡፡
“አንተስ እውነተኛ ክርስቲያን ነህ፡፡ እኔን ግን ያዲሳባ ውሀና የልመና በረከት ይበልጥብኛል፡፡ እዚሁ መቅረቴ አልቀረም”
“እና ገንዘብዎትን ተቀብለው ሊሸውዱኝ ይችሉ አልነበረም?”
“ምን ሊያደርግልኝ? ልመናዬ ካንተ የበለጥኩ ሀብታም አድርጎኛል፡፡ ቤት መስራት እንኳን በቻልኩ ነበር፣ ልመናዬ በለጠብኝ እንጂ፡፡ ሚስቴንና ልጆቼን አስካደኝ! ከዳሁዋቸው፡፡ ዋ! “በሰቆጣ ዳገት በብርብር ፀሀይ” ሲሉ እሱ እንደለመዱት ይቀበላቸውና “እቱ ጥላ ይዤ ልከተልሽ ወይ?” ብሎ ይደመድመዋል …
… ስለ ፆም ነነዌ ስናወራ ቆይተን፣ አመነሸዋ “አንተ ምላጭ” አለው “አሳ ነባሪው እንደ ዮናስ ቢውጥህ ኖሮ፣ ያንን ሶስት ቀን እንዴት ትችለው ነበር?”
“ቆንጆ አሳዎች እያመጣ እያበላኝ፣ ስለ አሳ ነባሪ ኑሮ እጠይቀው ነበር”
“ምን ብለህ?”
“ሚስት አለህ ወይ? በልጅነትህ እኔን ታክል ነበር ወይ?”
“እሱን ተወውና፣ ይልቅ እንደኚህ ለማኝ የማይለቅ ሱስ አይቻለሁ፡፡ ያውም የኚህ አባባ ሰው አይጐዳም፡፡ የማማ ኤልሳቤጥ ሱስ ግን መርዝ ነው፡፡ እሳቸውን ምንም ሳይጠቅም ሌላ ሰውን ይሰብራል”
“ኤልሳቤጥ እንኳ በጣም ቆንጅዬ ስም ነው” አልኳት፣ በጨዋታው ለመሳተፍ ያህል
“ኧረ መልካቸውን ብታዩት፣ ጋሼ! በስድሳ አመታቸው እንኳ ውበታቸው ከማንም ኰረዳ እኩል ይሆናል፡፡ ድምፃቸው ደሞ ሙዚቃ ነው፡፡ አቤት ማማር! አቤት ክፋት!”
“እንግዲህ አታንጠልጥይን፡፡ ቁም ነገሩ ምንድን ነው?”
“ቁም ነገሩማ እንዲህ ነው ይኸውላችሁ፡፡ የልጃቸው ባል የተረፈው ሀብታም ነው፡፡ ለማማ ኤልሳቤጥና ድሀ ቤተሰባቸው ምን የመሰለ ቤት አሰርቶላቸው ጐረቤቱ ሆኑ፡፡ ሰውየው ደግ ይሁን እንጂ ሚስቱን ማሪቱን በምክንያትም በሰበብም በጥፊ ያጮላታል፡፡ ደግነቱ አንድ ጥፊ ብቻ ነው፡፡
“ሰውየው ብዙ ጊዜ ጓደኛው ቤት ያመሻል፡ ጓደኝየውም እነሱ ቤት ያመሻል፡፡ ተናኘ የምትባል ሚስቱም ከማሪቱ ጋር በቂ ይግባባሉ፡፡ በዚህ መሀል ነው እንግዲህ እማማ ኤልሳቤጥ ከይሲ መንፈስ የመጣባቸው፡፡ ማሪቱን የገዛ ልጃቸውን ከባሏ ጋር ሊያፈራርሷት ተነሱ፡፡
“አንቺ ሞኝ በግ! ይሏታል” “ባልሽ’ኮ ተናኘን ወሽሟታል፡፡ መወሸሙንስ ተይው፣ ወንድ ሲባል ውሻ ነው፡ ግን እንዴት ቢንቅሽ ነው ውሽማውን ቤትሽ ድረስ እያመጣ ”’ሚያሽኰረምማት?!”
ማሪቱ እናቷን አመነች፡፡ ቤት ደርሶ መኝታ ቤት ሲገባ፣ የገዛ ሽጉጡን ከትራሱ ስር አወጣችና አነጣጥራ ተኰሰችበት፡
ሳተችው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ባልዋ ተለወጠ፡፡ ጥፊና ስድብ ቀረ ተረሳ፡፡ ሲገባም ሲወጣም “ማርዬ!” እያለ መሳለም ሆነ፣ እንደ ታቦት”
በጣም ተገርመን በሀሳብ ተውጠን በፀጥታ ቆየን …
… ታቦት ሲነሳ ጊዜ፣ ጋሼ፣ ይህን ጠቦት ያረድኩት ቅዱስ ገብርኤል ስለቴን ስለሰማልኝ ነው፡፡ ለራሴ ደስታ! ለሊቀ መላኩ ደሞ ለሚመጣው ታህሳስ ወደ ቁሉቤ እወርዳለሁ፡፡ እና እዚያ በሶስት መቶ ብር መቋሚያዎች ገዝቼ፣ አቅማቸው ለደከመ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች አንድ አንድ አድላቸዋለሁ”
“ድንቅ ስለት ነው!” አልኩት “ገብርኤል ራሱ መሆን አለበት እንዲህ የተቀደሰ ሀሳብ ያሳደረብህ” (ይህን ያህል ሳሞግሰው አረቄው ምን ያህል እንደወሰደኝ ታወቀኝ፡፡ ከዚህም የባሰ መስከሬ የታወቀኝ “ምን አርግልኝ ብለህ ነበር የተሳልከው?” ያልኩት ጊዜ ነበር (በግል እንኳ ለመጠየቅ የሚከብድ ጉዳይ!)
እሱም እንደኔው ሰክሮ ስለነበረ፣ መጥቶ በጆሮዬ “የሷን ፍቅር ሰጠኝ” ብሎኝ የአራጅ ስራው ስለተፈፀሙ እጁን ሊታጠብ ወጣ፡፡
በነጋታው ገና መጠጣት ሳንጀምር ስናወራ “አንዲት ሴት እሺ ማሰኘት ለኔ ቀላል ነበር” አለኝ “እቺን ግን እንደፈለገችኝ እያወቅኩም እንኳ ፈራሁዋት፣ ድንግል ልጃገረድ እንደመፍራት”
“እና እንዴት ሆንክ?”
“አድፍጬ ጊዜዬን አስተካክዬ፣ ማንም በሌለበት ሰአት በጉልበት ደፈርኳት”
“እና አላኮረፈችህም?”
“እሷም እስክደፍራት እየጠበቀች ነበር፡፡ አለችኝ እየሳቀች”
ግራ እንደገባኝ አይቶ “ባህላችን ነው’ኮ” አለኝ፡ “<አስገድዶኝ ነው” ለማለት መቻል አለባት፡፡ እንደዚህ እንደከተማ “ላውጣሽ” ብሎ መስማማት አይታሰብም፡፡”
ብዙም ጊዜ ሳይቆይ፣ አንድ ቀን አመነሸዋ የአስራ ስምንት አመት ጐረምሳ ልጁን ይዞ መጥቶ “የክርስትና ስሙ ጥበበ ስላሴ ነው፣ የቤት ስሙ ግን ጥበቡ ነው፡፡” ብሎ አስተዋወቀን፡፡ እንደ አባቱ መልከ መልካምም ጨዋታም ነው፡፡ በኋላ እንደተገነዘብኩት፣ እዚህ ሁልጊዜ የሚመጣው አባቱን ለመጠበቅና ሲመሽ ወደ ቤቱ ለመውሰድ ነው፣ የመጠጥ ነገር የማያስተማምን በመሆኑ፡፡
ምናልባት ሶስት ሳምንት ካለፈ በኋላ፣ ወደ ስምንት ሰአት ላይ፣ እጅጋየሁ ከቤቱ ውጪ ድንጋዩ ርብራብ ላይ ፣ ሳፋ ውስጥ አንሶላዎች ታጥብ ነበር፡፡ ከሳፋው በላይ አጎምብሳ ልብሱን እያሸች ወፍራም ዳሌዋ ሲተራመስ፣ በቅንዝር እየነዘርኩ ፈዝዤ አይኔን ተክዬ ቀረሁ፡፡
“ና’ስቲ ያንን ጫፍ ያዝ እንጭመቀው” ስትለው ተቀብሎዋት ሊጨምቅ ተንጠራራ፡፡ በቅንዝር ተገትሮ ይታያል፡፡ ስታሰጣም እንደዚያው ተከተልናት፡፡
እኔስ ካንድ ሩብ ሰአት በኋላ ቅንዝሬን እረሳዋለሁ፣ እሱ ግን በዚህ እድሜው የተቀጣጠለው እሳት ጤና አይሰጠውም፡ አሳዘነኝ፡፡
“ጓድ ጥበቡ፣ ና ወጣ ብለን እንዘዋወር” ብዬ ወሰድኩት፡፡
አስር ብር በግድ እያስጨበጥኩት “እኔም እንዳንተ ጐረምሳ ስለነበርኩ ሁኔታህ ይታወቀኛል፡፡ አንዷ ቆንጆ ጋ ደርሰህ ስትመለስ እንገናኛለን”
ቃል ሳይናገር ሄደ፡፡
ሌላ ጊዜ ብቻችንን ስንሆን ላረጋጋው ሞከርኩ “ለብቻህ አስብበት፡፡ አንተም ያባትህን ሴት አልተመኘሀትም፣ እኔም የጓደኛዬ ሚስት አልቀሰቀሰችኝም፡፡ ሁለታችንም ወንድ ነን፣ ሁለታችንንም የሴት ገላ ቀሰቀሰን፣ በቃ! በኋላ ነው እሷ ምናችን እንደሆነች የታወቀን፡፡ እምልህ ይታይሀል፣ አይደለም?”
“ይታየኛል፡፡ አንተ ጥሩ ሰው እንደሆንክም ይታየኛል፡ባለ ውለታህ ነኝ፣ ብድር መላሽ ያርገኝ” (ያባቱ ልጅ! ብዬ አሰብኩ)…
…ቀጣዩ የታሪካችን ምዕራፍ ሲያስገርመኝና በትውስታ ሲመላለስ ይኖራል፡፡
ማታ እጅጋየሁ ቤት ስመጣ ከፍቷት ወይም ተረብሻ አገኘሁዋት፡፡ “አመነሸዋ በስልክ ጓደኛህ ሞተ ብለውት ወደ ነገሌ ቦረና ሄደ፡፡ እንዳትቀብሩት አላቸው”
“ለምን?” ብዬ ቸኩዬ ጠየቅኳት
“ቀድሜህ የሞትኩ እንደሆነ፣ እትብቴ የተቀበረበት መንደር ወስደህ እንድትቀብረኝ አደራ ብሎኛል”
“አይቻልማ!” አልኩት “ያን ሁሉ መንገድ ተጉዘህ እስክትደርስ፣ ከዚያ ደሞ ወደ መንደሩ እስክታደርሰው፣ መበስበስ ይጀምራል”
“ዘዴ አይጠፋም፣ ብሎኝ ሄደ” አለችኝ፡፡
ከተመለሰ በኋላ የሰራውን ሲነግረን “የእብደት ነው? ወይስ ጓደኝነት ይህን ያህል ጥልቀት ሊኖረውም ይችላል?” እያልኩ ስደነቅ ነበር፡፡
ለታሪካችን አንባብያን ለማስታወስ ያህል፣ ደርጉና ኢህአፓ ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር እያሉ ሲከታከቱ “ነፃ እርምጃ” የተወሰደባቸው ወጣቶች ሬሳ በየመንገዱ እናገኝ ነበር “ቀይ ሽብር ይፋፋም!” ተብሎ ተለጥፎባቸው፡፡ በዚህ ላይ ከሻዕቢያና ከወያኔ ጋር ጦርነቱ አገሪቱን ወጥሮ ይዟታል፡፡
ማንም ጐረምሳ ውሎ መግባቱ ሁልጊዜ ጥያቄ ላይ ነበር፡ እንደዚህ አገር ቀውጢ በሆነችበት ወቅት ነበር አመነሸዋ ገድል-እብደቱን የፈፀመው፡፡
መጀመርያ እሱ ከዚህ ቀደም ቁም ነገር ሰርቶለት የሚያውቅ ያንዳንድ ቀን ወዳጁ አለ፣ የቄራ መኪና ነጂ ነው፡ እሱጋ ሄዶ ጉዳዩን ገልጦ ነገረውና መላ አቀረበለት፡፡
“በሽጉጥ አስፈራርቼ ላስገድድህና፣ አንተ ሲዳሞ ሶረና ወስደኸኝ፣ አስከሬኑን ተጉለት መንደሩ አድርሰኸኝ ወደ ስራህ ትመለሳለህ፡፡ እና ትከሰኛለህ፣ ጥፋቴን አምናለሁ፣ ለዘለአለም የማልረሳው ውለታ ዋልክልኝ ማለት ይሆናል፡፡”
አሳመነውና አብረው ሄዱ፡፡ ሬሳውን ጠቅልለው ቄራ መኪናው ውስጥ አስገቡት፡፡ ዋናው ጥረታቸው በተቻለ መጠን ሽታውን ለመቀነስ ነበር፡፡ ጓደኛው ሲነዳ አመነሸዋ ሬሳውን መንጠቆ ላይ በእግሮቹ ቁልቁል ሰቀለው፣ እንደ ታረደ በግ፡፡ እና ሆድ እቃውን በቢላ ዘክዝኮ፣ ፈርሱንም፣ አንጀቱንም ወለሉ ላይ ዘረገፈው፡፡
ከዚያ አስከሬኑን አውርዶ ጠቅልሎ እጥግ አስቀመጠው፡እና ትቶት በሩን ዘግቶ ወደ ጋቢና ሄደ፡ጉዞው ረዥም፣ ዝምታ የበዛበት፣ ፍርሀት የተሞላ ነበር፡፡ ታቦታቸው ሰማእቱ ጊዮርጊስ በአምበላይ ፈረሱ ያጀባቸው ያህል ነበር፡፡ ምንም ሳያጋጥማቸው፣ ማንም ሳይጠይቃቸው ወደ አቀዱት መንደር ደረሱ……አመነሸዋ ጓደኛውን ቀብሮ እርሙን አውጥቶ ተመለሰ፡፡ ቀስ በቀስ የሲዳሞ ቦረና ጉዞው እንደተረት፣ እንደ ህልም እየሆነ ሄደ፡፡
እሸቴና ጥበቡ የተንኮል ጭምር ሽርኮች ሆኑ፡፡ ጥበቡ ጥናቱንና የቤት ስራውን ይከታተላል፡፡ እጅጋየሁና አመነሸዋም ፍቅራቸው እየለመለመ ሄደ፡፡
ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ተፋፍመው አብቅተው እንደ መቀዝቀዝ ብለዋል፡፡ የደርጉ ፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ እየሰለቸን መጣ…
…ቀጣዩ የታሪካችን ምዕራፍ እስከመቼም ሊገባኝ የማይችል ምስጢር ነው፡፡ ኧረ ያስፈራኛል! ባጭሩ ተናዝዤ ልገላገለው እንጂ፣ ምርጫዬስ ዝምታ ነበር፡፡
እኔ፣ እጅጋየሁ፣ እሸቴ እየተጫወትን ነበር ስልኩ የተደወለው፡፡ እሸቴ ሄዶ ተመልሶ “ላንተ ነው” አለኝ
“ጋሼ” አለኝ አመነሸዋ “ልጄ ጥበቡ ድንገት ሞተ፡፡ ቀስ አርገህ ለእጅጋየሁ ንገራት”
ተመልሼ ነገርኩዋቸው፡፡ እሷ እንባዋ በፀጥታ መፍሰስ ጀመረ፡፡ እሸቴ “ምላጭ” ቤቱን ስለሚያውቀው አብረን ሄድን፡
አመነሸዋ እንባ አልወረደውም፣ ፊቱ ያስታውቃል፡ፍዝዝ ብሎ በህልም ያለ ይመስላል፡፡ “እግዜር ቢገድልብኝ እንኳ እንደምንም በቻልኩት ነበር” አለኝ “ልጄ ግን በገዛ ራሱ ታንቆ ስናገኘው እንዴት ልቻለው?” ራሱን እየነቀነቀ “እኮ እንዴት? አልችለውም፡፡ ቀብሬው፣ እርሜን አውጥቼ እጠፋለሁ”
“ወዴት መጥፋት ይቻላል?”
“ወደ አንዱ ገዳም ወይም ወደ አንዱ ዋሻ፡፡ እሱ ፈጣሪ እንዳዘዘልኝ፡፡”
እጅጋየሁን መጥቼ እንዳልሰናበትሽ ባታይኝ ይመረጣል ብለህ አስረዳልኝ”
እኔና እሸቴ ተሰናብተነው ወደ እጅጋየሁ ተመለስን፡፡…
…ስለዚህ ታሪካችን ብዙ ጊዜ አስባለሁ፡፡ እና ሽማግሌው ለማኝ “በሰቆጣ ዳገት በብርብር ፀሀይ እቱ ጥላ ይዤ ልከተልሽ ወይ?” ብለው እየዘፈኑ፣ አመነሸዋ እጅጋየሁን ጥላ ይዞ ሲከተላት ይታየኛል…

 

br /

Read 6702 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 12:57