Print this page
Tuesday, 04 March 2014 11:33

“...ገንፎውን በሆስፒታል ማገንፋት...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

“... ስሜ ምሳዬ ጸጋዬ ነው፡፡ ሕመሜም የማህጸን መውጣት ነው፡፡ እኔ የምኖረው በዚሁ በአለም ከተማ ውስጥ ቢሆንም ሐኪሙን ለማግኘት በቀጠሮ ቆይቻለሁ፡፡ ምክንያቱም እንደእኔው የታመሙ ብዙዎች ስላሉና ደግሞም በድንገተኛ ለሚመጡት ቅድሚያ ስለሚሰጥ ነው፡፡ በማህጸኔ በኩል ወደውጭ  እንደፊኛ ተወጥሮ በጣም ያመኛል፡፡ ይደማልም፡፡ ሽንቴን ስሸናም በግድ የምጥ ያህል ተሰቃይቼ ነው፡፡ ይኼው ...አሁን እድል ቀንቶኝ ኦፕራሲዮን ልሆን አልጋ ይዣለሁ፡፡ እንግዲህ እግዚሐር ይርዳኝ...”
    በአለም ከተማ እናት ሆስፒታል ታካሚ
ባለፈው እትም በመርሐቤቴ አለም ከተማ እናት ሆስፒታል ተገኝተን ያለውን እንቅስቃሴ ለአንባቢ ማለታችን ይታወሳል፡፡ በዚህ እትም ከሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አየለ ተሾመ እና ከአስተዳዳሪው አቶ ደነቀ አየለ እንዲሁም ከታካሚዎች ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንድታነቡት ጋብዘናችሁዋል፡፡ በቅድሚያ መልስ የሰጡት አቶ ደነቀ ናቸው፡፡
ጥ/    ሆስፒታሉ በሕክምና እቃ አቅርቦት እና በሙያተኞች ምን ያህል የተሟላ ነው?
መ/    እስከአሁን ከተተገበሩት ዋና ዋና ስራዎች መካከል ከሆስፒታሉ እቃ ማሟላት ጀምሮ ሙያተኞችንም በበቂ በማሰማራት በኩል በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ሆስፒሉ ቀደም ሲል ከአንድ እና ቢበዛ ከሁለት የማይበልጡ ጠቅላላ ሐኪሞች የሚመደቡበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከአምስት እስከ ሰባት ሐኪም ድረስ በሆስፒታሉ ይመደባሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሆስፒታሉ አቅም በላይ አንድ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ተመድበው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ በቋሚ የተመደቡት ባለሙያ ቀደም ሲልም የነበሩ ቢሆንም በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አማካኝነት እንደገና ለስድስት ወር በቅጥር ተመድበው ሌሎች ባለሙያዎችንም ያሰለጠኑ ሲሆን የኮንትራት ስራው ካለቀ  በሁዋላ በፌደራል ጤና ጥበቃና በክልልሉ ጤና ቢሮ አማካኝነት ተፈቅዶ በዚሁ እንዲሰሩ መደረጋቸው በአካባቢው ላሉ ታካሚዎች በተለይም ለእናቶች ጤና ትልቅ እገዛ አድርጎአል። በዚህም ምክንያት ማንኛውም አገልግሎት በሆስፒታላችን እየተሰጠ ሲሆን ወደሌሎች ሆስፒታሎች ሪፈር መደረግም በተለይም በእናቶች በኩል ቀርቶአል ማለት ያስችላል፡፡
ጥ/    እናቶች ወደ ሆስፒታል መጥተው የመውለዳቸው እንዲሁም የእርግዝና ክትትል የማድረጋቸው ልምድ ምን ያህል ነው?
መ/    ህብረተሰቡ ባጠቃላይ ወደሆስፒታል የመምጣት ልምዱ ተሻሽሎአል፡፡ የታካሚዎች ፍሰትን ሚመለከት ለምሳሌ ...ከ15/አስራ አምስት ሺህ አካባቢ የማይበልጥ የነበረው በአሁን ጊዜ እስከ 40/አርባ ሺህ እና ከዚያ በላይ ደርሶአል፡፡ የወላዶችን ሁኔታ ስናይ በአመት ውስጥ ከሁለት መቶ የማይበልጡ እናቶች ይወልዱ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በተቋማችን በሰለጠነ የሰው ኃይል እስከ ስድስት መቶ እናቶች ይወልዳሉ፡፡ በየዘርፉ ያለው አገልግሎትም እንዲሁ ቁጥሩ የጨመረ ሲሆን በተለይም በእናቶችና ሕጻናት ጤንነት በኩል በርካቶች ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡
ጥ/    እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስተማር ምን የተወሰደ እርምጃ አለ?
መ/    በሆስፒታሉ ከሚሰጠው አገልግሎት ጎን ለጎን ከሰኞ እስከ አርብ የባለሙያዎች የመወያያ መድረክ አለ፡፡ እናቶችንም በተመለከተ በየጠዋቱ ለየክፍሎች ማለትም ለወረዳ ወይንም ለየጤና ጣብያዎች ሊሆን ይችላል... ግብረመልስ ይሰጣል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ሆስፒታሉ ከወረዳ ከሚመለከታቸው አካላት፣ ከጤና ጣብያ ኃላፊዎች፣ ከሆስፒታል ቦርድ አካላት ጋር በመተባበር ሆስፒታሉ ጤና ጣብያዎችን የሚደግፍበትን ስልት አጠናክሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ለእነዚህ የጤና ተቋማት ድጋፍ ይሰጣል ሲባልም ካሉት የስራ ዘርፎች እናቶችንና ሕጻናትን በሚመለከት ሰፋ ያለ ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም አሰራር በተለይም እናቶችን በሚመለከት ያሉትን ሶስት መዘግየቶች ...እናቶች ከቤታቸው ሳይወጡ እንዲሁም በመንገድ ምክንያት እና በህክምና ተቋም ከመጡ በሁዋላ የሚፈጠረውን መዘግየት ለማስቀረት ያላሰለሰ ጥረት በመደረግ ላይ በመሆኑ በውጤቱም ሰፊ ልዩነት እየታየ ነው፡፡ ስለዚህም እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በጤና ተቋም እንዲወልዱ ለማድረግ ከሆስፒታሉ ጀምሮ በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር በሚኖረን የመረጃ ልውውጥ መሰረት ዛሬ በሆስፒታሉ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር በአመት እስከ ስድስት መቶ ሊደርስ ችሎአል፡፡  
---------///---------
የወላዶችን ክፍል ተዟዙረን ስናይ አንዲት ወላድ አገኘን፡፡ እርስዋ ግን ልታናግረን አልቻለችም፡፡ ትፈራለች፡፡ እንዲያውም በነጠላዋ ሽፍን አለች፡፡ እናትየው እና ሌሎች ቤተሰቦች ከአልጋዋ አጠገብ ቆመዋል፡፡ እናትየውን ጠየቅናቸው፡፡  
“...ስሟ እናቴ ነው፡፡ የወለደችው የመድኃኔአለም እለት ማክሰኞ ነው፡፡ እኔም እናትዋ ነኝ፡፡ ምጥ ይዞአት ትንሸ በቤት ቆይታ ነበር፡፡ በሁዋላም የማይቻል ሲሆን ስናመጣት የልጁ አቀማመጥም ትክክል አይደለም ብለው በኦፕራሲዮን አገላገሉአት... ይኼው አሁን ድካም ነው እንጂ ሴት ልጅዋን አቅፋለች፡፡ እኛም ደስ ብሎናል፡፡”
ጥ/    እርስዎ የት ነበር የሚወልዱት?
መ/    አረግ... እኔማ በቤቴ ነዋ፡፡
ጥ/    አዋላጅ ነበረ ወይንስ እራስዎ ይወልዱ ነበር?
መ/    አዋላጅም ነበሩ፡፡ እሳቸው ካልተገኙና ለጊዜው ምጥ ከመጣ እራሴም እወልደው ነበር፡፡ በእርግጥ እትብት ማተብ ላይ ለሰው እንጂ ለእራሴ ሲሆን እቸገራለሁ፡፡ ነገር ግን አጠገቤ ላሉት እንዲህ አድርጉ እንዲህ አድርጉ ብዬ እናገራለሁ። እንዲህ እንደዛሬው ብድግ ብሎ ወደሆስፒታል መምጣት የት አለ? በጊዜው ሆስፒታሉም እጅግም ነው... እኛም አናውቀውም።
ጥ/    የትኛው ይሻላል? የአሁኑ ነው ወይንስ የድሮው?
መ/    አረግ... ምን ተገናኝቶ... ያኔ በእኛ ጊዜ እኮ ቤት ይቁጠረወ ነው እንጂ... ስንትዋ በየቤትዋ ቀርታለች... እንዲያው የቀናን ሴቶች ወልደናል እንጂ መውለድስ በእኛ ጊዜ አበሳ ነበር። አሁን ምን ችግር አለ እንዲያውም ምጥ ሲጀምር በቤት ማቆየት ደግ አይደለም፡፡   
----------///--------
በአለም ከተማ እናት ሆሰስፒታል በዘንድሮው ውድድር ከአሸናፊዎች ተርታ ተመድቦ የአንድ ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆኖአል፡፡ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር አየለ ተሾመ  እናት ሆስፒል ለተሸላሚነት የበቃበትን ምክንያት እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡
ጥ/    በአለም ከተማ እናት ሆስፒታል በፌደራል ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን ያበቃው የስራ እንቅስቃሴ ምንድነው?
መ/    መሸለሙ ሁለት ነገርን ይመለከታል፡፡
አንደኛው አጠቃላይ የሆስፒታሉን አገልግሎት የሚመለከት ነው፡፡ ይህም ሆስፒታሎች የተገልጋዩን እርካታ ለማምጣት አነስተኛ መስፈርት መሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች የሪፎርም ትግበራ የሚባል በ2002/ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረ አሰራር ያላቸው ሲሆን ያንን ማስተግበር ይጠበቃል፡፡ አላማውም ቅልጥፍና፣ ጥራት እና ስነምግባር ያለው አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የእናቶችና የህጻናት ጤና ነው፡፡ የእናቶችና የህጻናትን ጤንነት በሚመለከት በአለም አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን የምእተ አመት ግብ ለማሳካት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ሲሆን ለዚህም ስኬት የህክምና ተቋማት ከተቋም ውጭ በመሄድ ህብረተሰቡ ድረስ በመድረስ አገልግሎቱን ማቅረብ እንዲሁም ህብረተሰቡም በሰለጠነ የሰው ኃይልና በጤና ተቋም መገልገልን እንዲያውቅ ለማስቻል ጥረት መደረግ ስላለበት ይህ ለውድድሩ ሌላው መስፈርት ነው። በሆስፒታል ዙሪያ ያሉትን ጤና ጣቢያዎች እና የቅብብሎሽ ስርአቱን በማጠናከር እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን በመደገፍ ጭምር የተሸለ ለውጥ ማምጣት ይጠበቃል፡፡ ስለዚህም በአካባቢያችን ባለው ባህላዊ ተጽእኖ ምክንያት ብዙ ሴቶች ወደጤና ተቋም መጥተው የማይወልዱ የነበረ ሲሆን አሁን ግን መልኩን በመለወጡ እና ተጠቃሚው በመብዛቱ እንዲሁም የጤና ተቋማቱም አሰራር ተደራሽ በመሆኑ ሁለተኛው ለሽልማት የበቃበት ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ አሰራር መሳካት ምስክሩ ደግሞ ህብረተሰቡ እራሱ ነው፡፡ ይህንንም ከፌደራል በኤክስፐርቶች ደረጃ የተቋቋመ የባለሙያዎች ቡድን በሁሉም ሆስፒታሎች ተዟዙሮ መሬት ላይ የደረሰውን አሰራር ማለትም ከዶክመንት በመመርመር እና ከህብረተሰቡ መልስ በማግኘት በተጨማሪም በራሱ መስፈርት በመመዘን ለውጤት የሚበቁትን ይለያል። በዚህ መሰረት በአለም ከተማ እናት ሆስፒታል ተሸላሚ ሆኖአል፡፡
ጥ/    እናቶች ወደ ሆስፒታል የማይመጡባቸው ባህላዊ ነገሮች ምንድናቸው?
መ/    ምንም እንኩዋን እየቀነሰ ቢመጣም አንዲት ሴት ምጥ ሲቆይባት ጥይት ይተኮሳል፡፡ ይህም ድምጹን ስትሰማ በድንጋጤ ትወልዳለች በሚል ነው፡፡ እንዲሁም ባልየው ቀበቶውን ሲፈታ ምጡ ይቀላል ብለው ያስባሉ፡፡ ምጥ ሲይዛት ሆድዋን በቅቤ ማሸት የአንግዴ ልጅ ሲቆይ ሆድዋን በቁና ማሸት የመሳሰሉት ልምዶች አሁንም አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዲት ሴት ስትወልድ ወዲያውኑ ገንፎ አገንፍቶ ወላድዋን ጨለማ ውስጥ በማድረግ ገንፎ መስጠት እና ተሰብስቦ ቡና እየጠጡ ገንፎ መብላት ባህል ስለሆነ በጤና ተቋም ሲወልዱ ግን ይህ ባለመደረጉ ትልቅ ነገር እንደቀረ ይቆጥሩታል፡፡ በዚህም ሳቢያ አሁን ገንፎውን በሆስፒታል ማገንፋት እና የቡና ስነስርአቱን ማድረግ እንዲችሉ ማብሰያውም ሁሉም ግብአት ተዘጋጅቶአል። ስለዚህ እናቶች ሲወልዱ ቤተሰቦቻቸው ያንን አዘጋጅተው መቅመስ የሚችሉበትን አሰራር አመቻችተናል፡፡ የተቀሩትን ባህላዊ ልማዶችም እንዲተውና ወደጤና ተቋም በመምጣት አገልግሎት እንዲያገኙም ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ነን፡፡


Read 2111 times