Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 December 2011 09:45

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ህፃናት በማይደርሱበት ሥፍራ ይቀመጥ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት እንዳያነቡት ይመከራል!”
“…አጥሮች ላይ፣ ግንቦች ላይ፣ ቆርቆሮዎች ላይ፣ ጣውላዎች ላይ፣ በሚንቦገቦግ ደማቴ ቀለም “ህዝባዊ መንግስት በአስቸኳይ” “ኢህአፓ ያቸንፋል” እየተባለ የተፃፈውን አንብቤ በቡድኔ ስፋት የኮራሁት እዚህ ነው፡፡ ከሚሊዮን ዓመታት በፊት በሴኖዞይክ ዘመን ከተፈጠረው የሀገሬ አፈር ገነው የሚያበሩ መፈክሮች ያየሁት እዚህ መንገድ ላይ ነው… ለእኛ ለሰዎቹ ብቻ ነው የሻሪ ሻሪ ህግ የሚሰራው መሰል፡፡

ቤዛዊትን በቀትር ታክሲ ስትጠብቅ እዚህ መንገድ ዳር በጥይት ደረቷን መታናት፡፡ ሊመሽ ሲል ከሞተችበት ተነስታ ቤቷ ገብታ ለሃያ ቀናት ተኛች… (ገፅ-36 “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ”) ከአንጋፋው የአገራችን ልቦለድ ደራሲ አዳም ረታ የቅርብ ጊዜ መፅሃፍ የተቀነጨበውንና ለመግቢያዬ የተጠቀምኩበትን ፅሁፍ ስትመለከቱ ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት እንዳያነቡት የሚለውን ማሳሰቢያ ለምን እንዳሰፈርኩ ትረዱኛላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ፅሁፉ እንደምታዩት በ”ቴረሩ” በደርግ ዘመን የነበረውን ሽብርና የእርስ በርስ መጨራረስ ታሪክ በጨረፍታ የሚያስታውስ ነው፡፡ በእርግጥ የገዛ ራሳችን ታሪክ ነው - አሳዛኝ ቢሆንም፡፡ የራሳችን ቢሆንም ግን ለአቅመ አዳምና ሄዋን ላልደረሱ ህፃናት ምንም አይጠቅምም፤ ንፁህ አዕምሮና ልባቸውን ከመመረዝ በቀር፡፡ ለዚህም ነው የዕድሜ ገደቡን ያስቀመጥኩት፡፡ እንጂ አንዳንዶች ሊያሙኝ እንደሚከጅሉት ከኢቴቪ “አኬልዳማ” የተሰኘ ዶኩመንታሪ ፊልም ላይ ኮርጄ አይደለም፡፡  
ለነገሩ መልካም እስከሆነ ድረስ ብኮርጅም ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ እንኳን እኔ መንግስት ከየአገሩ መንግስታት ይኮርጅ የለም እንዴ! (ክፉ ክፉውን ሆነ እንጂ) እኔ የምለው ግን ራሱ ኢቴቪ በሽብር ተጠረጠሩ ግለሰቦች ዙሪያ ያዘጋጀው “ፕሮፓጋንዳ-ቀመስ” ፊልም ላይ የዕድሜ ገደብ ያስቀመጠው ከማን ኮርጆ ነው? (“ፕሮፓጋንዳ - ቀመስ” ያሉት ባለሙያዎች ናቸው)
አሁን ይህቺን በመጠየቄ ደግሞ አንዳንድ ወገኖች ኢቴቪን በተመልካቾቹ ለማሳጣት ወይም ትዝብት ላይ ለመጣል አስቤና አልሜ ያደረኩት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ኢቴቪ ግን የተመልካች ትዝብት ብርቁ እንዳልሆነ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ የዕለት ተዕለት ቀለቡ እኮ ነው! ሳላስበው ሽሙጥ ውስጥ ገባሁ አይደል! ደግነቱ የዕድሜ ገደብ ስላስቀመጥኩ ህፃናት አያነቡትም፡፡ እውነት ግን ኢቴቪ “አኬልዳማ”ን ሲያሳይ ህፃናት እንዳይመለከቱት ይመከራል ያለው ማን መክሮት ነው? ለምን መሰላችሁ የምጠይቀው? እስከዛሬ ብዙ ለህፃናት መታየት የሌለባቸው ነገሮች ያለገደብ በኢቴቪ ሲቀርቡ በመታዘቤ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን ኮርጆም ይሁን ተመክሮ እንኳን ነቃልን! ኢቴቪ ማወቅ ያለበት አንድ ቁም ነገር ግን አለ፡፡ ይኸውም ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ማየት የለባቸውም ተብሎ መከልከል ያለበት “አኬልዳማ” ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ግን ከኢቴቪ ውስጥ ህፃናት ሊያዩት የሚችሉት የድርጅቱን ህንፃ ብቻ ይመስለኛል (እሱም ቢሆን ለህፃናት አዕምሮ መነቃቃት የሚፈጥር ዘመናዊ ህንፃ አይደለም)
ለፖለቲካ ወጌ መግቢያ ያደረኩትን ፅሁፍ ደባብሼ አለፍኩት አይደል … የደራሲ አዳም ረታ ሥራዎችን አፍቃሪ የሆንን ሁሉ እንደምናውቀው ድርሰቶቹ ሁሉ ውብና ድንቅ ናቸው፡፡ የቃላት ውበት… የአፃፃፍ ቴክኒክ … የአገላለፅ ብቃት… ባጠቃላይ የተባ ብዕር የታደለ ብርቅዬ ፀሃፊያችን ነው፡፡ ክፋቱ ግን እኔ የቀነጨብኩት ፖለቲካዊ ቀመስ የሆነውን ክፍል ስለሆነ ለህፃናት አይሆንም - ከ13 ዓመት በታች ለሆኑ! ደራሲው አስፈሪ ወይም አሰቃቂ ፖለቲካዊ ድርሰቶች የመፍጠር ልዩ ተሰጥኦ ስላለው እንዳይመስላችሁ! የአገራችን ፖለቲካ ይኸው ስለሆነ ነው፡፡ እንደውም ሳያለዝበው የቀረ አይመስለኝም፡፡
የእኛ አገር ፖለቲካ እኮ ትላንትም ዛሬም የመድሃኒት ፓኬቶችና ብልቃጦች ላይ ተፅፎ እንደምናየው “Keep away from children” (ህፃናት በማይደርሱበት አካባቢ ራቅ ተደርጐ ይቀመጥ) የሚል ማስጠንቀቂያ (ማሳሰቢያ) የሚያስፈልገው ነው፡፡
ኢትዮጵያችን ብዙ ምጡቅ ጭንቅላት ያላቸው፣ የተማሩ የተመራመሩ፣ ታላላቅ ሰዎች የተፈጠሩባት ድንቅ አገር መሆኗን የሚወዱንም የሚጠሉንም አይክዱትም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አርቆ አስተዋይ፣ ለነገው ትውልድ የሚያስብና የሚጨነቅ ሰው አገራችን አልታደለችም፡፡ ዝም ብዬ ራሳችንን ለማሳነስ አይደለም እንዲህ የምለው፡፡ እውነት ስለሆነ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የኢትዮጵያን ፖለቲካ አጠቃላይ ሁኔታ እንዳይሰሙ (በእውንም፤ በህልምም፤ በቲቪም፤ በራዲዮም) የመከላከል ሙከራ ተደርጐ አያውቅም፡፡ ምናልባት ራስ ወዳድነት የሚያጠቃቸው ይሆናሉ እንጂ ከኤሌክትሪክ የበለጠ አስፈሪ የሆነው ፖለቲካችንን ህፃናት እንዳይጠጉት መጠነኛ የመከላከል ጥረት እንኳን ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ራሳቸዉ ፖለቲከኞቹስ? ገበናቸውን ያውቁት የለም እንዴ? እነሱ እንኳን ይሄን ማሰቢያ ጊዜም የላቸውም፡፡ ቀን ተሌት በስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ስለሆኑ፡፡
ለመሆኑ “አኬልዳማ” በሚል የሰየመው ዶክመንታሪ ፊልም ላይ የእድሜ ገደብ ያስቀመጠው ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያችን እስከ ዛሬ የት ነበር? ለምሳሌ ህወሃት ከደርግ ጋር የተፋለመበትን የጦርነት አውድማ የሚያሳዩ ፊልሞች ዝም ብሎ ሲለቅ የከረመው የህፃናት ካርቱን ፊልሞች መስለውት ነው? ወይስ “ቶም ኤንድ ጄሪ” ፊልም? ምናልባት እኮ አንዳንድ ካድሬዎች “ህፃናቱ ልብ ውስጥ የጀግንነትና የቆራጥነት ስሜት ለማስረፅ የጦርነት ፊልሞቹ የማይናቀ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ” የሚል ወፈፌ ሃሳብ አቅርበው ይሆናል፡፡ የሆኖ ሆኖ ኢቴቪ ዘግይቶም ቢሆን በ”አኬልዳማ” ፊልም መንቃቱ የሚያበረታታ ቢሆንም ትንሽ ቆይቶ ደሞ ይዘነጋዋል የሚል ክፉ ስጋት አደረብኝ፡፡ አዎ … ሌላ ተመሳሳይ አሰቃቂ ፖለቲካዊ ትእይንት ሲያቀርብ በስራ ብዛት የእድሜ ገደቡን ሊዘነጋው ይችላል፡፡ እስቲ አስቡት … “አኬልዳማ ቁ.2” ሲለቀቅ ማሳሰቢያውን ቢዘነጋውስ (ትዝብት አይሆንም?) ይሄ ሃሳብ ሲያስጨንቀኝ ነው የዛሬውን አዲስ ፕሮፖዛል ለማርቀቅ የተነሳሁት፡፡
ሃላፊነት የሚሰማውና ከዛሬው የተሻለ መልካም ትውልድ ለመፍጠር የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ (ኢህአዴግም፣ ተቃዋሚም፣ ዲያስፖራም፣ መሃል ሰፋሪም) በጋራ የሚቀበሉትና የሚደግፉት እንደሚሆን የተማመንኩበት የዛሬ ፕሮፖዛሌ ርእስ ምን ይላል መሰላችሁ? “ማንኛውም የአገር ውስጥ ፖለቲካዊ ክስተቶችን ከ13 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት እንዳይመለከቱት” መቼም ይሄን እገዳ እንደመብት ጥሰት የሚቆጥር አለ ብዬ አላስብም፡፡ እናም ፕሮፖዛሉ እንደሚለው የአገራችን የፖለቲካ ድባብ አስፈሪና ከጦርነት ብዙም የተሻለ ስላልሆነ ህፃናት የማይደርሱበት ስፍራ መቀመጥ አለበት ይላል፡፡ ህፃናት የፓርቲዎችን የምርጫ ክርክር (debates) እንኳን ማየትና መስማት እንደሌለባቸው የሚጠቁመው ፕሮፖዛሌ፤ ፓርቲዎች የሚያወጡት (የሚለቁት) መግለጫም ህፃናት ባሉበት አካባቢ እንዳይነበብ ወይም እንዳይነገር ይጠቁምና በየመግለጫዎቹ ላይ “Keep out of reach of children” የሚል ማሳሰቢያ እንዲሰፍርበት አበክሮ ይገልፃል፡፡ ይሄን ማሳሰቢያ ሳያሰፍር ማናቸውንም መግለጫዎች የበተነ የፖለቲካ ፓርቲ ግን በፀረ-ሽብር ህጉ ተጠያቂ ይሆናል - ይላል ፕሮፖዛሌ፡፡ ቅጣቱ ከበድ ያለ ቢመስልም የነገውን ትውልድ አዕምሮ ከመበረዝ የበለጠ አሸባሪነት እንደሌለ ፕሮፖዛሌ ያስገነዝባል፡፡
እንደሰለጠኑት አገራት ቢሆንማ ህፃናት ከፓርቲዎች ክርክር ብዙ ትምህርት ይቀስሙ ነበር፡፡ ክፋቱ ግን የእኛ አገር የምርጫ ክርክር ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት የሰለጠነ ውይይት ሳይሆን የጦርነት ዕንቢልታ የሚነፋበት የማስፈራሪያና የፉከራ መድረክ ነው፡፡ እስቲ በ97ቱ ምርጫ የሰማናቸውን የስድብ ታፔላዎች እናስታውሳቸው፡፡ “ነፍጠኞች፣ ኢንተርሃሞይ፣ የባዕድ ቅጥረኞች፣ ገንጣይ፣ ከፋፋይ፣ የሻዕቢያ ቅጥረኛ” ወዘተ የመሳሰሉ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አሁን ከዚህ ህፃናት ምን ይማራሉ? ከስድብና ከጥላቻ በቀር፡፡ ፕሮፖዛሌ የፖለቲካ መግለጫና የፖለቲከኞች ንግግር ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የባለስልጣናት ወይም የፖለቲከኞችና የካድሬዎች ንግግር፣ ጋዜጣዊ መግለጫና ኢንተርቪው ህፃናቱ እንዳያዩና እንዳይሰሙ ይመክራል፡፡ ቢያንስ ነፍስ እስኪያውቁ ድረስ፡፡
ህፃናቱ ጨቅላ አዕምሮአቸው በመልካምና በጐ ሃሳቦችና እሴቶች ታንፆ ማደግ አለባቸው የሚለው ፕሮፖዛሌ፤ አይነታቸው የበዛ የወንጀል ሪፖርቶች የሚያቀርበውን የኢቴቪ የፖሊስ ፕሮግራም ባይመለከቱም ይመረጣል ይላል፡፡ በተለይ በሴቶች ላይ እንደሚፈፀሙት የአሲድ ጥቃት ያሉ አሰቃቂና አስከፊ ወንጀሎች ከ13 ዓመት በታች ላሉ ህፃናት መከልከል እንዳለበት አበክሮ ያሳስባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ታፔላ በመሆን የሚያገለግሉ “የሻዕቢያ ነጭ ለባሽ”፣ “ኪራይ ሰብሳቢ”፣ “ጨለምተኛ”፣ “ደርግ ናፋቂ”፣ “ፀረ-ልማት” ወዘተ ቃላት በህፃናቱ ፊት እንዳይነገሩ ያስጠነቅቃል - አፍራሽ እንጂ ገንቢ ፋይዳ ስለሌላቸው፡፡ ከመሬት ጋር በተገናኘ በሙስና ተጠርጥረው በክስ ላይ የሚገኙም ሆነ ጥፋታቸው ተረጋግጦ ቅጣት የተበየነባቸው ባለስልጣናትን የዝርፊያና የስርቆት ገድል የሚተርኩ ፕሮግራሞችንም ህፃናቱ መመልከት የለባቸውም የሚለው ፕሮፖዛሉ፤ የዘመናችን ሙሰኞች ፈፀሙት ወይም ዘረፉት እየተባለ ያለው የህዝብ ሃብት መጠን የህፃናት አዕምሮ ሊያመዛዝነው የሚችለው ስላልሆነ ከዚህ አይነቱ ፕሮግራም እንዲርቁ ይጠይቃል፡፡ ለነገሩ እንኳንስ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው የኢቴቪ ፕሮግራሞች ቀርቶ የልጆች ክ/ጊዜ ተብሎ በኢቴቪ ሲቀርብ የምናውቀው ተረት ሁሉ በጭራቅና በ”አያ ጅቦ” የተሞላ (አስፈሪ) እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን አይደለም እንዴ?
አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ከኢቴቪ ፕሮግራሞች የትኛውን ማየት እንዳለባቸው ለመወሰን እንደሚቸገሩ የሚያወሳው አዲሱ ፕሮፖዛል፤ ቢቻል ቢቻል ህፃናቱ 18 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ኢቴቪን ባይመለከቱ ይጠቀማሉ እንጂ ምንም የሚጐዱት ነገር የለም ይላል፡፡
ኢቴቪን የሚያስቀይም ፕሮፖዛል ቢሆንም ለአዲሱ ትውልድ ሲል ይሄን መስዋዕትነት ቢከፍል ለአገር ታላቅ ውለታ እንደዋለ ይቆጠርለታል፡፡ ሌላው አማራጭ ደግሞ “ኢቴቪ -የህፃናት” ጣቢያ መክፈት ነው፡፡ በዚህ ጣቢያ ግን ተደራጁ የሚል ፕሮፖጋንዳ ማስተላለፍ አይፈቀድም!!

 

Read 4375 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:50