Saturday, 15 March 2014 12:00

IVF… ብዙ ሚሊዮን ልጆች እንዲፈጠሩ አስችሎአል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(2 votes)

           በኢትዮጵያ ከ10-15% የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ መውለድ እንዳልቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢችሉ ወደህክምናው ከዚያም ባለፈ ወደየእምነታቸው በማዘንበል የሚያምኑትን መለመናቸው አይቀርም፡፡ ጠበብት ይህንን ችግር ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ሳይንሳዊ ውጤቶችን ለህዝብ በማቅረብ አገልግሎት ላይ እያዋሉ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ IVF ነው፡፡ ዶ/ር እስክንድር ከበደ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ኮሌጅ የማህጸን እና ጽንስ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ስለ In Vitro Fertilization ለተጠየቁት ጥያቄዎች እንደሚከተለው መልስ ሰጥተዋል፡፡
ጥ/    የIVF  ህክምና በምን መንገድ የሚሰጥ ነው?
መ/    IVF ህክምና እርግዝናን ከማህጸን ውጭ በላቦራቶሪ ውስጥ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡ አሰራሩም የሴትየዋን እንቁላልና የሰውየውን የዘር ፍሬ በመውሰድ እና በማዳቀል በቲዩብ ውስጥ በማዋሀድ እርግዝናው እንዲፈጠር የሚያስችል  ሳይንሳዊ ሕክምና ነው፡፡ የቆይታ ጊዜው እንደላቦራቶሪው የሚለያይ ሲሆን የማዳቀል ስራው ከተሰራ ሶስተኛ ቀን እስከ አምስተኛው ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ስለሚዋሀድ ወደ ሴትየዋ ማህጸን ገብቶ እድገቱን እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡  
ጥ/    የIVF ሕክምና ለእነማን ያስፈልጋል?
መ/    IVF ህክምና የሚሰጠው፡-
የማህጸን ቱቦ በተለያየ ምክንያት ለተዘጋባቸው ሴቶች፣
እንቁላል ከአቃፊዋ ወጥታ ከወንድ የዘር ፍሬ ተገናኝታ ወደ ማህጸን የምትገባው በቱቦው አማካኝነት ሲሆን ቱቦው በተለያየ ችግር ምክንያት ከተዘጋ እርግዝና እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡
እንቁላልን የሚያመነጨው ክፍል በስነስርአት እንቁላልን ያለማመንጨት፣
የሚወጣው እንቁላል ቁጥር እየቀነሰ መሔድና ጥራቱም በዚያው ልክ መቀነስ ካሳየ፣
የሴት ማህጸን ምንም እንቁላል የማያመርት ከሆነ፣
በተለያዩ ምክንያቶች የወንድ የዘር ፍሬ ቁጥር በጣም አናሳ ከሆነ... ወዘተ ናቸው፡፡
ጥ/    የሴትየዋ ማህጸን ምንም እንቁላል የማያመርት ከሆነ እንቁላል ከየት መጥቶ ይዳቀላል?
መ/    ሴትየዋ ማህጸንዋ እንቁላል የማያመነጭ ከሆነ የሚወሰደው እርምጃ ተመሳሳይ ሴት መፈለግ ነው፡፡ ከሴትየዋ ዘመዶች ወይንም አቅራቢያ ካሉ ሰዎች ወይንም ከሌላ ጋ በባህርይ በመልክ እና በተለያዩ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች በተቻለ መጠን የምትመስል ሴት ተፈልጋ እንቁላልዋ ይወሰዳል፡፡ ከዚያም ከዚያች እንቁላል ማምረት ከማትችለው ሴት ባል የዘር ፍሬ ጋር ተቀላቅሎ በላቦራቶሪ ውስጥ ከተዋሀደ በሁዋላ ማርገዝ ወደማትችለው ሴት ማህጸን እንዲገባ ተደርጎ ልጅ እንዲወልዱ ይደረጋል፡፡ ስለዚህም IVF ሊሰራላቸው የሚገባቸው ሰዎች እንደዚህ ያለ እርግዝናን የሚከለክል ከባድ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡
ጥ/     ማህጸን ጽንስ አይቋጥርም ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/    በመጀመሪያ ልጅ አለመውለድ ወይንም ኢንፈርቲሊቲ የሚባለውን ስንመለከት አንዲት   ሴትና ወንድ ለአንድ አመት ያህል አብረው እየኖሩ    እርግዝና ካልተፈጠረ ልጅ መውለድ አለመቻል የሚለውን ያመለክታል፡፡ ከዚህ ጊዜ ቆይታ በሁዋላ ሁኔታው ለምን እንደተከሰተ ለማወቅ ሲባል የህክምና ምርመራ ይደረጋል፡፡
ጥ/    ማርገዝ መቻልንና አለመቻልን ለማወቅ አንድ አመት ያህል መቆየት ግድ ነውን?
መ/    በእርግጥ ውሳኔው በእድሜ ደረጃ ተለያይቶ የሚሰጥ ነው፡፡ ለምሳሌ እድሜያቸው ከ30/አመት በታች የሆናቸው ሴቶች ማርገዝ አለማርገዛቸውን ለማወቅ አንድ አመት ያህል  መቆየት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን እድሜያቸው ከ35/አመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ማርገዝ አልቻልንም ብለው ወደሕክምና ሊመጡ የሚገባቸው በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም እድሜያቸው ከፍ እያለ ስለሆነ እና እርግዝናውን እስኪመጣ ሊታገሱበት የሚችሉበት ብዙ ጊዜ ስለማይኖራቸው ቶሎ ሕክምናውን እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡
ጥ/    እርግዝናን በሚመለከት የተፈጥሮ ህግ ምን ይመስላል?
መ/    የተፈጥሮውን ህግ ስንመለከት አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት አብረው መኖር በጀመሩ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ20-25% የሚሆኑት ሴቶች ያረግዛሉ፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት አንድ አመት ያህል አብረው ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ከ80-90% ያህሉ ሴቶች ብቻ ያረግዛሉ፡፡ ስለዚህም ከዚህ በላይ እርግዝናው ይከሰት ይሆናል ብሎ መቆየቱ አስፈላጊ ስላልሆነ እንደእድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት ድረስ ሳያረግዙ ቆይታ ካደረጉ በሁዋላ እርግዝናው ካልተከሰተ ሕክምናው እንዲጀመር ግድ ይላል፡፡
ጥ/    አንዲት ሴትና አንድ ወንድ እንደተገናኙ የማይረገዝበት ምክንያት ምንድነው?
መ/    አንዳንድ ጊዜ የጊዜ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት እንቁላልዋ የምትወጣው በወር አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ከተፈለፈለች በሁዋላ ቆይታዋ ለ24/ሰአት ያህል ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን የወንድ ዘር በየጊዜው የሚፈጠር ቢሆንም ጽንስ ለማፍራት ግን የወንድ የዘር ፍሬ የሴቷን እንቁላል ማግኘት ግድ ይሆንበታል፡፡ ስለዚህም የሴትዋ እንቁላል ከመውጣትዋ በፊት 12/ሰአት ከወጣች በሁዋላም እስከ 48 ሰአት ድረስ ባለው ጊዜ ወንድና ሴት ካልተገናኙ ጽንስ አይፈጠርም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ምንም እንኩዋን በትክክለኛው ጊዜ ግንኙነት ቢያደርጉም በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ከጤንነት፣ ከተፈጥሮ ሁኔታዎች፣ ከአኑዋኑዋር ባህርይ ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ እርግዝናው ላይከሰት የሚችልባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡
ጥ/    በሕክምናው ዘርፍ ምን ይመከራል?
መ/    በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጥ የምክር አገልግሎት አለ፡፡ ለምሳሌ.. አንድ ባልና ሚስት በስራ ወይንም በተለያዩ ምክንያቶች አብረው የማይኖሩ ከሆነ እና በሚኖራቸው የተዛባ ግንኙነት ምክንያት እርግዝና ባይከሰት ልጅ ያለመውለድ ችግር አለ ተብሎ ሊደመደም አይችልም፡፡ ስለዚህ የሚቻል ከሆነ ባልና ሚስቱ አብረው መኖር አለባቸው፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ እንደባለሙያዎች ምክር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ድረስ ግንኙነት ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እርግዝና ሊከሰት አይችልም፡፡  
ጥ/    እርግዝና እንዳይከሰት የወንድና የሴት ድርሻ ምን ያህል ነው?
መ/    26% የሚሆነው እርግዝና የማይከሰተው በወንድ ምክንያት ሲሆን በሴት ምክንያት ደግሞ ወደ 37% ይሆናል፡፡ በሁለቱም ምክንያት ወደ 30% ሲሆን እንዲሁም ምንም ምክንያት ሊገለጽለት በማይችል ሁኔታ ወደ 28% የሚሆነው ለእርግዝና አለመከሰት ምክንያት ነው፡፡ በህክምናው ዘርፍ የሚሰጡ የተለያዩ ሕክምናዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ... እንቁላል ቶሎ ቶሎ እንዲወጣ የሚያደርግ መድሐኒት አለ፡፡ እንዲሁም ለወንዶችም የሚሰጥ መድሀኒት አለ፡፡ ሁለቱም ተሞክረው የማርገዝ ሁኔታው ሊሳካ ካልቻለ የመጨረሻው እርምጃ IVF የሚባለው ሕክምና ነው፡፡
ጥ/       IVF ሕክምናው በአለም እውን ከሆነ ምን ያህል ጊዜ ሆነው?
መ/    IVF ሕክምና በአለም ላይ ወደ 20 አመት የሆነው ሲሆን በአሁኑ ጊዜም በብዙ ሀገራት የህክምና ማእከላቱ ተቋቁመው መውለድ ለማይችሉ ጥንዶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም ያለንበት ወቅት ተስፋን የሚያጨልም ሳይሆን ብዙዎች በዚህ ዘዴ ልጅ እያገኙ በመሆኑ የሚወለዱት ልጆችም ቁጥር ወደ በርካታ ሚሊዮኖች ደርሶአል፡፡
ጥ/    በላቦራቶሪ የሚፈጠሩ ልጆች እና በማህጸን የሚፈጠሩ ልጆች የጤንነት ወይንም ተፈጥሮአዊ ልዩነት አይኖራቸውም?
መ/    ምንም አይነት ልዩነት የላቸውም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በላቦራቶሪ የሚፈጠሩት ልጆች በቲዩብ ውስጥ ቆይታ የሚያደርጉት ውህደቱ እስኪፈጠር ድረስ ከአምስት ቀን ያልበለጠ ጊዜ ነው፡፡ በማህጸን የሚፈጠረውም ቢሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከውህደት ያለፈ ምንም ተግባር የለውም። የሴትየዋ እንቁላል መቼ እንደምትወጣ ታውቆ ሁኔታውን ምቹ የሚያደርጉ የህክምና ሂደቶች ከተጠናቀቁ በሁዋላ ልክ እንቁላልዋ ስትወጣ ተወስዳ የወንድየው የዘር ፍሬም እንዲሁ ተወስዶ በቲዩብ እንዲቀላቀሉ ከመደረጉ በስተቀር ሂደቱ በማህጸን ውስጥ ያለው አይት ነው፡፡ ስለዚህም የዘር አፈጣጠሩ ያው ከእናት እና አባቱ ስለሆነ ያንኑ ጠብቆ ይወለዳል፡፡
ጥ/    IVF ሕክምናው በኢትዮጵያ ይሰጣል?
መ/    IVF ሕክምናው በኢትዮጵያ አይሰጥም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ሀገራት በመሰጠት ላይ ሲሆን በቅርባችን በሱዳን ካርቱም 11/የሚሆኑ ማእከላት አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ ሕክምናው የሚሰጥ ሲሆን በህንድ አገር ግን በስፋት የሚሰጥ በመሆኑ ዋጋውም ከሌሎች አገሮች በተሻለ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኤሽያ ውስጥ ሕክምናው ይሰጣል፡፡ በኢትዮጵያ እስከአሁን ሕክምናው ካልተጀመረበት ምክንያቶች አንዱ ሕጉ መስተካከል ስላለበት ነው፡፡ መቼ እንደሚጸድቅ ባይታወቅም ጉዳዩ ግን ከፓርላማ መድረሱን ይነገራል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከ10-15% የሚሆኑ ባለትዳሮች ልጅ ያለመውለድ ችግር እንዳለባቸው የሚታወቅ ሲሆን ህጉ ጸድቆ ይፋ ከተደረገ ሕክምናው ይጀመራል የሚል ተስፋ አለ፡፡   

Read 4556 times