Saturday, 15 March 2014 12:18

ታካሚዎችን ነገሬ የማይሉ ደንታ ቢስ ሃኪሞች!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

“ሃኪም ልሁን ባይ” ታካሚዎችም አሉ


ሙያዊ ሥነ-ምግባራቸውን አክብረው፣ ለታካሚዎቻቸው ተገቢውን ጊዜና ትኩረት ሰጥተው፣ የህክምና እርዳታ የሚያደርጉ ሀኪሞች እንዳሉ ሁሉ፣ ህመምተኛውን አስቀምጠው ለረዥም ሰዓት ሞባይል ስልክ የሚያወሩ፣ መፅሃፍ የሚያገላብጡ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ሰፋ ያለ ጨዋታ የሚያደርጉና ህመምተኛው በክፍሉ ውስጥ መቀመጡን ሁሉ የሚዘነጉ አንዳንድ  ባለሙያዎችም አሉ፡

             እየተመላለሰ ከሚያሰቃያት የጨጓራ ህመሟ በላይ የሚያስጨንቃት ለህመሟ ማስታገሻ ፍለጋ የሃኪሞችን በር ደጅ መጥናቱ ነው፡፡ በሽታዋ ተከታታይ ህክምና የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ የተለያዩ የህክምና ተቋማትን ተመላልሳባቸዋለች። ለጤናዋ መፍትሄ ፍለጋ በሄደችባቸው የጤና ተቋማት ያስተዋለቻቸው ጉዳዮች ግን ተስፋ አስቆራጭ ሆነውባታል፡፡ በየህክምና ተቋሙ ካጋጠሟት የጤና ባለሙያዎች መካከል አብዛኛዎቹ የሙያ ሥነ-ምግባራቸውን የሚፃረር ተግባር ሲፈፅሙ ታዝባለች፡፡ ስለችግሯና ስለህመም ስሜቷ ለሃኪሞች በዝርዝር መናገር ብትፈልግም ጆሮውን ሰጥቶ፣ የምትናገረውን ከልቡ የሚያዳምጣት ባለሙያ አለማግኘቷ ከበሽታዋ በላይ አሳምሟታል፡፡ ችግሩ በመንግስት የህክምና ተቋማት ብቻ ሳይሆን ረጅም ቀጠሮ ሰጥተውና ውድ ዋጋ አስከፍለው የህክምና አገልግሎት በሚሰጡ የግል ተቋማት ውስጥ መከሰቱ ደግሞ ይበልጥ ግራ አጋባት፡፡
 “ይህንን ሁሉ ገንዘብ ከፍዬና ብዙ ወረፋ ጠብቄ የመጣሁት ከሃኪሜ ጋር ስለበሽታዬ በግልፅ ለመነጋገር፣ ህመሜን  በአግባቡ አስረድቼ፣ተገቢ ህክምናና ፈውስ ለማግኘት ቢሆንም ለእኔ የተረፈኝ ግን ተጨማሪ በሽታ ሸምቶ መመለስ ነው፡፡ አንዳንዱ ሐኪምማ ጭራሽ ቀና ብሎ ሊያይሽ እንኳን አይፈልግም፡፡ የሆነ ነገር ወረቀት ላይ ጫር ጫር ያደርግና ላብራቶሪ ሂጂ ብሎ ያሰናብትሻል፡፡ ታካሚው ከሐኪሙ ጋር በደንብ የመነጋገር፣ እንዲሁም ለበሽታው ስለሚታዘዝለት መድኃኒትና ስለሚሰጠው ምርመራ ዓይነት የመጠየቅና የማወቅ መብት እንዳለው እንኳን ፈፅሞ አያስቡም፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ ግን ምን ታደርጊዋለሽ? ጤና እስካልሆንሽ ድረስ ከእነሱ እጅ አትወጪም፡፡”
በቤተል ሆስፒታል ህክምናዋን ለመከታተል መጥታ ያገኘኋት፣ የአርባ ሁለት ዓመቷ ወ/ሮ ሰላም ሙሉጌታ የሰጠችኝ አስተያየት ነበር፡፡ ለዚህ ዘገባ መረጃዎችን ለማሰባሰብ በተዘዋወርኩባቸው ጋንዲ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ጳውሎስ፣ ቤተል፣ ኮሪያና ቤተዛታ ሆስፒታሎች ውስጥ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት መጥተው ያገኘኋቸው ታካሚዎችም በአብዛኛው ወ/ሮ ሰላም በሰጡት አስተያየት ይስማማሉ፡፡ ሀኪሞቻቸው በቂ ጊዜ ሰጥተው እንደማያዳምጧቸውና ለጥቄያዎቻቸው ተገቢና አጥጋቢ ምላሽ እንደማይሰጧቸው የተናገሩት ታካሚዎች፤ በተለይ “ለምን? እንዴት?” እያለ ጥያቄ የሚያበዛባቸውን ታካሚ እንደማይወዱ ይናገራሉ፡፡ ችግሩ ከባድ የስራ ጫና አለባቸው በሚባሉት የመንግስት የጤና ተቋማት ውስጥ በስፋት የሚታይ ቢሆንም ከፍተኛ ክፍያ እያስከፈሉ፣ ረጅም ቀጠሮ አስጠብቀው አገልግሎት በሚሰጡ የግል ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችም ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ህሙማኑ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የሙያ ሥነ-ምግባቸውን አክብረው ለታካሚዎቻቸው ተገቢውን አክብሮትና ጊዜ እንዲሁም ሙያዊ እርዳታ የሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡
የህክምና ባለሙያዎች የታካሚያቸውን ጤንነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ የሚሆነው በሃኪምና ታካሚ መካከል መልካም ግንኙነትና መግባባት ሲኖር ነው፡፡ ታካሚዎች የሚሰማቸውን ስሜት ለሀኪማቸው በዝርዝርና በግልፅ ማስረዳታቸው ውጤታማ ህክምና ለመስጠት እንደሚያግዝ ይታወቃል፡፡ ታካሚው ህመሙን ለሃኪሙ በዝርዝር በማስረዳቱ የሚያገኘው ስነ-ልቦናዊ እፎይታም ቀላል አይደለም፡፡ በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ህክምናቸውን ለመከታተል መጥተው ያገኘኋቸው አንዲት እናት፤ “የሀኪሞችን ደጃፍ መርገጥ አጥብቄ እጠላ ነበር፡፡ ከልጆቼ ጋር ሁሌም የሚያጋጨኝ ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ የረዥም ጊዜ የስኳርና የደም ግፊት ታማሚ በመሆኔ ብዙ ሃኪሞች ፊት በተደጋጋሚ ቀርቤአለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ የህሙማንን የስቃይ ስሜት መስማትና ማየት የሰለቻቸው ናቸው፡፡ ሊያዳምጡኝ ፍቃደኛ አይደሉም፡፡ በዚህ ምክንያትም የባሰ ተናድጄና ታምሜ ነው የምመለሰው፡፡ በዚህ ሃኪም ቤት ያገኘሁት ዶ/ር ግን የተለየ ሆኖብኛል፡፡ አክብሮቱ፣ እርጋታውና በጥሞና ማዳመጡ ሁሉ አስገርሞኛል፡፡ ለካ እንዲህም አይነት አለ ነው ያስባለኝ፡፡ ከቤቴ ታምሜ ብመጣ እንኳን እሱ ጋ ገብቼ ስወጣ ቀለል ይለኛል፡፡ ምንም ባያደርግልኝ በሚገባ አዳምጦኝ አይዞሽ ሲለኝ፣ በሽታዬ ቀለል ሲለኝ ይታወቀኛል፡፡” ብለዋል፡፡
ሙያዊ ሥነ-ምግባራቸውን አክብረው፣ ለታካሚዎቻቸው ተገቢውን ጊዜና ትኩረት ሰጥተው፣ የህክምና እርዳታ የሚያደርጉ ሀኪሞች እንዳሉ ሁሉ፣ ህመምተኛውን አስቀምጠው ለረዥም ሰዓት ሞባይል ስልክ የሚያወሩ፣ መፅሃፍ የሚያገላብጡ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ሰፋ ያለ ጨዋታ የሚያደርጉና ህመምተኛው በክፍሉ ውስጥ መቀመጡን ሁሉ የሚዘነጉ አንዳንድ  ባለሙያዎችም አሉ፡፡ ህመምተኛው ከተለያየ የአኗኗር ሁኔታና የትምህርት ደረጃ የሚመጣ በመሆኑ እንደ የአመጣጡና እንደ የሁኔታው መቀበልና ማስተናገድ ከማንኛውም የህክምና ባለሙያ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
በእርግጥ ከታካሚዎችም ችግር አይጠፋም፡፡ “ሀኪም ልሁን ባይ” ታካሚዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ታካሚዎች የሃኪሙን ውድ ጊዜና ጉልበት አለአግባብ ከማባከናቸውም ባሻገር፣ ከሀኪሙ ጋር አላስፈላጊ እሰጣ አገባ ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሚታዘዝላቸውን ምርመራና ህክምና በአግባቡ ለመፈፀም ፍቃደኛ አይሆኑም፡፡ አብዛኛዎቹ የዚህ ዓይነት ባህርይ ያላቸው ታካሚዎች ሐኪማቸው የህመማቸውን ምክንያት ለማወቅ ማድረግ የሚፈልገውን ምርመራ እንዳያደርግ ይከላከላሉ፡፡ ለምሳሌ ሐኪሙ የደም ምርመራ አዞላቸው ከሆነ እኔ የሚያመኝ ሆዴን ነው የሠገራ እንጂ የደም ምርመራ ምን ያደርግልኛል ብለው ሙግት ይገጥማሉ። ሀኪሙ መድኀኒት በሚያዝበት ጊዜ እሱ ቶሎ አያሽለኝም ለእኔ የሚሻለኝ ይኸኛው ዓይነት ነው ብለው ይከራከራሉ ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ማከሙ ለጤና ባለሙያው ትልቅ ፈተና እንደሆነ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ሰለሞን ግሩም ይናገራሉ፡፡ የሃኪም ታካሚ መልካም ግንኙነት ለተሳካና ውጤታማ ለሆነ ህክምና ወሳኝነት እንዳለው የሚናገሩት ዶ/ሩ፤ ታካሚው ስለህመም ስሜቱ፣ ቀደም ሲል ይወስዳቸው ስለነበሩ መድኃኒቶች፣ መድኃኒቶቹ ስለአስገኙለት ለውጥ፣ ህመሙ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ እንደሆነው---- በዝርዝር ለሀኪሙ መናገሩ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ታካሚው ከሃኪሙ ጋር የሚያደርገው ቀና ግንኙነትና ግልፅ ውይይት ለባለሙያው ውጤታማ ህክምና ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ በተጨማሪ ታካሚው ህመሙን በዝርዝር በማስረዳቱ የሚያገኘው ስነ-ልቦናዊ ህክምና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ በሃኪምና ታካሚው መካከል የተሳካ ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል ከፍተኛ የስራ ጫና፣ የጊዜ እጥረትና የሃኪሙ የግል ባህርይ ጥቂቶቹ እንደሆኑ ዶ/ሩ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በማስወገድ በሃኪምና ታካሚ መካከል ያለውን ግንኙነት የሰመረ ለማድረግ ሁለቱም ወገኖች ኃላፊነት አለባቸው የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን፤ ሃኪሙ ለህመምተኛው በቂ ጊዜና ልዩ ትኩረት መስጠት እንዲሁም ታካሚው ስሜቱን በግልፅና በዝርዘር እንዲያስረዳው መፍቀድ አለበት ብለዋል፡፡ ሐኪሙ ምንም እንኳን የበዛ የስራ ጫና ቢኖርበትም ለታካሚው በቂ ጊዜ በመስጠት ስለህክምናውና የምርመራ ዓይነቶች፣ ስለሚያዝለት መድኃኒት ምንነትና አወሳሰድ እንዲሁም ስለ ጎንዮሽ ጉዳቱ በአግባቡ የማሳወቅና የማስረዳት ሙያዊ ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ታካሚው በበኩሉ፤ የሃኪሙን የስራ ጊዜ ያለአግባብ ላለማባከን ጥንቃቄ ማድረግ፣ ሃኪሙ ዘንድ ከመቅረቡ በፊት ስለህመም ስሜቱ፣ ለሃኪሙ መንገር ወይንም ሃኪሙን መጠየቅ ስለሚፈልገው ጉዳይ ቀደም ብሎ ማሰብና መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ይሄ  ሁለቱም ወገኖች የተቃና ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረግ ስኬታማ የህክምና ውጤት ይፈጥራል ብለዋል - ዶ/ሩ፡፡
አንድ ሃኪም በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በሚደርስበት አገር፣ የህክምና ባለሙዎች እጅግ የበዛ የስራ ጫና ቢኖርባቸውም ሙያቸው ከሰው ህይወት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ፣ ሙያው የሚጠይቀውን ልዩ ትኩረት ለህመምተኛው በመስጠት፣ቃለ መሃላ የፈፀሙበትን ጉዳይ አክብረው ሊተገብሩ ሰሩ ይገባል፡፡ ታካሚውም አላስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች የሃኪሙንና የሌሎች ታካሚዎችን ጊዜ ከማባከን መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለስኬታማ ህክምና የሁለቱም ወገኖች የጋራ ትብብር ወሳኝ ነው፡፡    

Read 1834 times