Saturday, 15 March 2014 12:23

መዘዘኛው የዩክሬን የፖለቲካ ምስቅልቅል

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(9 votes)

          የበርካታ ሀገራትን ፖለቲካዊና፣ ኢኮኖሚያዊ ውህደት በተመለከተ አለማችን በየትኛውም ክፍሏ ቢሆን ከአውሮፓ ህብረት በተሻለ የተሳካ የሀገራት ውህደት ነው በሚል ልትጠቅሰው የምትችለው ነገር አንድም እንኳ የላትም፡፡ ይህ እውነትም ትክክልም ነገር ነው፡፡
የዛሬ ሀምሳ ሰባት አመት የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት ሮበርት ሹማን ሀሳብ አመንጭነት፣ በስድስት የምዕራብ አውሮፓ አገራት የተመሠረተው የአውሮፓ ህብረት፤ ዛሬ ሀያ ስምንት ሀገራትን በአባልነት አቅፎ ይዟል፡፡ ይህ እድሜ ጠገብ የሀገራት ህብረት፤ የውህደት አድማሱን የማስፋት ብርቱ እንቅስቃሴው ዛሬም ድረስ ለአፍታ እንኳ አልተገታም፡፡ ከዛሬ አራት አመት በፊት የወጠነውን ህብረቱን፤ ወደ ምስራቅ አውሮፓ የማስፋት እቅድ እውን ለማድረግ፣ ባለፈው አመት ሰኔ ላይ ክሮኤሻን ሀያ ስምንተኛ አባል አድርጐ በመቀበል ጀምሯል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አድማሱን ወደ ምስራቅ አውሮፓ በማስፋት ሊቀዳጀው ካሰባቸው ፖለቲካዊ ግቦች አንዱና ዋነኛው በምስራቅ አውሮፓ ራሺያ ያላትን ተጽዕኖ በመግታት፣ በምትኩ የህብረቱን የተጽዕኖ አድማስ ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ግብ መሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ተብለው ለአባልነት በግንባር ቀደም እጩነት ከታሰቡት የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት መካከል ደግሞ ዋነኛዋ ሀገር ዩክሬይን ናት፡፡
በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሶቪየት ህብረት ስትፈራርስና የቀዝቃዛው ጦርነት ፍፃሜውን ሲያገኝ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የራሺያ እጣ ፈንታ የድሮ የገናናነት ታሪኳን ወግ እየጠረቀች በትዝታ መኖር ብቻ ነው በሚል ከአሜሪካ በስተቀር አብዛኞቹ ሀገራት በእርግጠኝነት ገምተው ነበር። አሜሪካ ግን ምንም እንኳ ዋነኛ የርዕዮተዓለም ባላንጣዋ የነበረችው ሶቪየት ህብረት በመፈራረሷ ጓዝ ቀለለልኝ ብላ ደስ ቢላትም፣ የራሺያን ነገር ግን መቼውንም ጊዜ ቢሆን ችላ ብላ ትታው አታውቅም። ለአሜሪካ ራሺያ ማለት የተኛ ድብ ማለት ናት፡፡ መቼ ነቅታ እጅግ ስለታም ጥፍሮቿን እንደምታነሳ ጨርሶ የማትታወቅ፡፡
እናም የራሺያን ነገረ ስራ ሁሉ ነቅቶ መቆጣጠርና፣ የተጽዕኖ አድማሷን እንዳታሰፋ ማድረግ ለአሜሪካ የትናንትም ሆነ የዛሬ የብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ዋናና የቅድሚያ አጀንዳዋ ነው። ለዚህ አጀንዳዋ መሳካት ደግሞ ዩክሬንን ከራሺያ ጉያ መንጠቅ መቻልን የመሰለ ድል የላትም፡፡ ፊቱኑ ጀምሮ ቅጥ ያለው ፍቅር ኖሮአት ከማያውቀው የአውሮፓ ህብረት ጋር በአዲስ ፍቅር መሞዳሞድ ጀምረው፣ አንድ ቦላሌ ለሁለት ካለበስን ብለው፣ አሁን ለያዥ ለገራዥ ያስቸገሩበት ዋናው ምክንያትም ይሄው ነው፡፡
የተኛች ድብ ናት ለተባለችው ራሺያና ለፕሬዚዳንቷ የዩክሬን ጉዳይ መቼውንም ጊዜ ቢሆን የተራ ጉርብትና ጉዳይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ለራሺያ የዩክሬን ጉዳይ የአባት ሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ ቆፍጣናው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቀድሞ ሶቪየት ህብረት አባል ሀገራትን በተለይም ዩክሬንን ማዕከል አድርጐ ያካተተ፣ ዩሮኤሽያቲክ ህብረት ለመመስረት በሙሉ ሀይላቸው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙበት ዋነኛ ምክንያትም የአባት ሀገር ራሺያን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት በማስጠበቅና የተጽዕኖ ምህዳሩን በማስፋት፣ የቀድሞ ክብርና ዝና ለማስመለስ ነው። ስለዚህ ዘመናትን የተሻገረ የታሪክ፣ የባህልና የሰው ለሰው ግንኙነት ጥልቅ ትስስር ያላት ዋነኛ ጐረቤቷና አጋሯ ዩክሬን፤ በአውሮፓ ህብረትና በአሜሪካ ተጠለፈች ማለት ለፕሬዚዳንት ፑቲንና ለሀገራቸው የጦር ሀይል በቁም የመሞት ያህል ነው፡፡
ዩክሬናውያንም ቢሆኑ የወደፊቱንም አለም አቀፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን በተመለከተ ጠረጴዛቸው ላይ የቀረበላቸው ምርጫ፣ ከአውሮፓ ህብረትና ከአሜሪካ ጋር አሊያም ከራሺያ ጋር መግጠም ብቻ መሆኑን በሚገባ ተረድተውት ነበር፡፡ የህይወት መስዋዕትነት እስከ መክፈል ድረስ ሁለት ጐራ ለይተው አምባጓሮ ያስነሱትም ለዚህ ነበር፡፡
ዩክሬናውያን የማታ ማታ ምርጫቸው ከአውሮፓ ህብረትና ከአሜሪካ ጋር መወገን ሆነ፡፡ ቀላል የማይባል የህይወት፣ የአካልና የንብረት መስዋዕትነት በመክፈል አፍቃሬ ራሺያ የነበሩትን ድሎት አፍቃሪና ቅንጡውን ፕሬዚዳንታቸውን ቪክሮ ያኑኮቪችን፣ የስልጣን ወንበራቸውን አስጥለው ነፍሴ አውጭኝ ብለው እንዲፈረጥጡ ማድረግ ቻሉ፡፡
ይህ ታሪካዊ ክስተት ከተፈፀመ በኋላ ዩክሬናውያን “እሰይ ስለቴ ሰመረ!” ብለው ንሴብሆ ያሸበሸቡት፣ “ከእንግዲህ የፖለቲካ ምስቅልቅሉ አበቃ፤ የእኛም የልባችን ሞላ” በሚል ቅን መንፈስ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ያኑኮቪችን በጐዳና ላይ አመጽ ከስልጣናቸው ነቅለው አገር አስጥለው ሲያባርሯቸው ጨርሶ ባልገመቱትና ባልጠበቁት ሁኔታ ዋነኛ ወዳጃቸው የነበሩት ፕሬዚዳንት ፑቲን እጃቸውን አጣጥፎ ማየት የልብ ልብ ተሰምቷቸው ጮቤ እንዲረግጡ አድርጓቸው ነበር፡፡
እናም ታዲያ አሁን በሀገራቸው በዩክሬን የተፈጠረውን እጅግ መዘዘኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምስቅልቅል ይፈጠራል ብለው የገመቱ በጣም እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ራሺያ ግን በእርግጥም የተኛ ድብ ነበረች፡፡ ረጅሙን እንቅልፏን እየለጠጠች ነው ብለው ምድረ ዩክሬናውያን ሁሉ፣ ነገር አለሙን ችላ ባሉበት ሰአት ድንገት ከች ብላ ሱሪያቸውን አስወለቀቻቸው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ዩክሬናውያን ከራሺያ እቅፍ አፈትልከው ሲወጡ ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተለይም ደግሞ ከራሺያ በኩል ለሚመጣባቸው የቅጣት እርምጃ፣ የአውሮፓ ህብረትንና አሜሪካን ያስጥሉናል ወይም ይታደጉናል ብለው በእጅጉ ተስፋ አድርገው ነበር። ይሁን እንጂ ተስፋቸው ተራ ተስፋ ብቻ እንደሆነና የአውሮፓ ህብረትም ሆነ አሜሪካ ከጅብ የማያስጥሉ የአህያ ባል መሆናቸውን የተረዱት እጅግ ዘግይተው ነው፡፡
አንቀላፍተዋል ሲባሉ ከነበሩበት ድንገት ተግ ያሉት ድቡ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ጦር አውርድ እያለ መሬት ሲገርፍ የነበረውን ጦራቸውን በምድረ ዩክሬን ላይ ፈተው በመልቀቅ፣ የዩክሬንን ሉአላዊነት በመድፈር ሲያዋርዷቸውና ይባስ ብሎም የግዛት አንድነቷን የከፋ አደጋ ላይ ሲጥሉት፣ ብዙ የተባለላቸውና እነሱም ብዙ ያሉት የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ እስካሁን ማድረግ የቻሉት ነገር ቢኖር በራሺያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ማስፈራራት ብቻ ነበር፡፡
ሁለቱ ምዕራባውያን አካላት “ራሺያን ልክ ያስገባታል” እያሉ ሲፎክሩበት የነበረው ማዕቀብም የማታ ማታ ሆኖ የተገኘው የስም ማዕቀብ ብቻ ነው። ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የአውሮፓ ህብረት ከለንደን እስከ ፓሪስ፣ ከበርሊን እስከ ብራሰልስ ከወዲያ ወዲህ ሲላጋበትና ሲዳረቅበት የባጀው፣ በውጭ ሀገር የሚገኝ የራሺያ ተቀማጭ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስና በተመረጡ የራሺያ ዜጐች ላይ የጉዞ እገዳ ማዕቀብ ለመጣል ነበር፡፡ ከዚሁም ብሶ አሜሪካ ውሳኔዋን ለማሳወቅ ገና በማቅማማት ላይ ትገኛለች፡፡
ከአውሮፓ ህብረት ሀገራት መካከል ይህን ማዕቀብ በራሺያ ላይ ለመጣል ዋና አጋፋሪ ሆነው “ሲያሽቃብጡ” የነበሩት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ናቸው፡፡ እኒህ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰሞኑን ሲሆኑ የነበረውን በጥሞና ሲከታተል የነበረው ድፍን አለሙ፣ አጃኢብ በማለት መገረሙ አልቀረምር፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት አጋፋሪ መሆናቸው ሳይሆን በሳቸው አጋፋሪነት የተጣለውን ይህን ማዕቀብ፣ እሳቸውና ሀገራቸው እንግሊዝ ከቶ ምኑን ከምን አድርገው ያስፈጽሙት ይሆን የሚለው ነው፡፡ የዚህ ስረ መሠረቱ ደግሞ እንዲህ ነው፡፡
ዛሬ ማንም ቢሆን በግልጽ እንደሚያውቀው፣ የሩሲያውያን ባለሀብቶች ከፍተኛ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ማዕከል ሞስኮ ሳትሆን ለንደን ናት። በአለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ባለጠግነታቸው ለታወቁ ሩሲያውያን ድንቡሎ የማይከፍሉበት የታክስና የግብር ገነት (tax havens) በተለያዩ ከተሞቿና በአስተዳደሯ ስር ባሉ እንደ ጂብራልታር፣ ካይመን ደሴቶችና የእንግሊዝ ቨርጂን ደሴቶች በመሳሰሉ ሀገራት ያዘጋጀችላቸው ራሷ እንግሊዝ ናት፡፡ ከሀምሳ በላይ የሚሆኑ ታላላቅ የራሺያ ኩባንያዎች ንግዳቸውን በዋናነት የሚያካሂዱት በለንደን የአክሲዮን ገበያ ነው፡፡ እንግሊዝ አሉኝ የሉኝም የምትላቸው የፋይናንስና የቢዝነስ አማካሪዎች፣ የባንክ ባለሙያዎች፣ የህግ አማካሪና ጠበቆች እንዲሁም የሄጅ ፈንድ ማናጀሮች ተቀጥረው የሚሰሩት ለሩሲያውያን ባለሀብቶች ሲሆን የሚያንቀሳቅሉስትና የሚያስተዳድሩትም የሩሲያውያንን ከፍተኛ ሀብት ነው፡፡ በአጠቃላይ ዛሬ የእንግሊዝ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆነው ከመንኮታኮት የታደጉት ሩሲያውያን ባለሀብቶችና በእንግሊዝ በስራ ላይ ያዋሉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘባቸው ነው፡፡
እንግዲህ ይህንያፈጠጠ እውነት ተከትሎ የሚመጣው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፡፡ በእውኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን፤ የሩሲያውያንን ሀብት እንዳይንቀሳቀስ በማገድ በዋናነነት ያጋፈሩትን የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ተግባራዊ በማድረግ፣ አይናቸው እያየ በሀገራቸው ኢኮኖሚ ላይ የሞት ፍርድ ይፈርዳሉ ወይስ የፖለቲካ ድራማቸውን ለብቻቸው መተወን ይጀምራሉ? ትንሽ እንታገስና ጉዳቸውን እንይ!


Read 5272 times