Saturday, 15 March 2014 12:42

“እኛም አንድ ሰሞን ‘ሽቅብ’ ወጥተን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ጸሀዩዋ በጾም መዳከማችንን አይታ ነው እንዴ እንዲህ ጉልበቷን ሰብስባ የመጣችው! “ጠበሰችን…” ማለት ብቻ አይገልጸውም፡፡
ይቺን አሪፍ የሆነች የጥንት ስንኝ ስሙኝማ…
በቅሎ ከመንገድ ጠፍታኝ፣
ኮርቻ ይዤ ስታዩኝ፣
እስቲ ሁላችሁም አስታውሱ፣
መርገፍ አለና እንዳትረሱ፡፡
እናላችሁ… ‘መርገፍ መኖሩ’ እየተረሳ ዘላለማዊ የሆንን የሚመስለን ሰዎች እየበዛን ይመስላል፡፡ ‘ከአንድ እንጀራ ለማታልፍ ሆድ’… አለ አይደል… ማን አለብኝነታችን፣ እብሪታችን፣ ምድር በሺህ ዓመት ሊዝ ለግላችን የተሰጠችን ይመስል የጎረስነውን ጉንጭ ሙሉ በቅጡ እንኳን ገና ሳናኝክ የሌላውን ነጥቀን ለመጉረስ የምንሞክር…ምን አለፋችሁ፣ ነገርዬው ሁሉ እየተበላሸ ነው፡፡
የምር ግን ራሳቸውን ‘ልዩ ፍጡራን’፣ ሌላውን ‘ድምር ህዝብ’ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ማየት እየተለመደ ነው፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም በተግባር “አምስት መቶ አንሞላም…” እንዳሉት ‘ፊውዳሏ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሴትዮ ሚያደርጋቸው እየፈሉ ነው። (እግረ መንገዴን…ድሮ ወገን፣ ስልጣን፣ ገንዘብ ስላላቸው የተቀረውን  የሚንቁ፣ ‘ፊውዳል’ ምናምን ይባሉ ነበር፡፡ “አንተ ደግሞ እንደ ፊውዳል አታስብ…” ምናምን ይባል ነበር፡፡ ጥያቄ አለን…የዘንድሮዎቹስ ምን ይባላሉ! ልክ ነዋ…‘መርገፍ መኖሩ’ እውን ሲሆን የመድረክ ‘ዲስኩራችንን’ ምን ብለን እንደምናሳምር ማወቅ አለብና!
ቀን ወጣልኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፣
እንደ ዛሬ ሳይሆን፣
እኛም አንድ ሰሞን ‘ሽቅብ’ ወጥተን ነበር፡፡
የሚሉ የባቢሎን ግንብ ‘ገንብተው የጨረሱ’ ይመስላቸው የነበሩ መአት መኖራቸውን ማስታወስ አሪፍ ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ‘ፈረንጅ አገር’ ከርማ የመጣች ነች አሉ፡፡ እናላችሁ… የዛች የፈረደባት የሁላችን መሰብሰቢያ የሆነች አገር ፓስፖርትም ይዛለች፡፡ እናላችሁ… እዚቹ ከተማችን ውስጥ አንድ ለፈረንጅ የተጠጋ ድርጅት አለቃ ነች፡፡ ታዲያላችሁ… ይቼ ሴትዮ ሊፍት ውስጥ ስትገባ አንድም ሠራተኛ ሊፍቱ አጠገብ ዝር አይልም፡፡ ስትወጣም፣ ስትወርድም ብቻዋን ነው፡፡
ታዲያላችሁ…አንድ ቀን በድርጅቱ የሚሠራ ሰው ዘመድ ያላት ወይዘሮ እንግዳ ትመጣለች። ስለ መሥሪያ ቤቱ ‘የሊፍት ጉድ’ የምታውቀውም ነገር የላትም፡፡ እናማ… አለቅየዋ ብቻዋን ባለችበት ሊፍት ውስጥ ዘው ትልና አብረው ይወጣሉ፡፡ ላይ ሲደርሱም አለቅየዋ ሆዬ ሴትዮዋ የምትገባበትን ክፍል ታይላችሁና ቢሮዋ ገብታ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተመልሳ ትመጣለች፡፡ ያቺን ሴትዮ፣ ምን አለፋችሁ…የምትይዘው የምትጨብጠው እስክታጣ ድረስ ከፍ ዝቅ አድርጋ… “እኔ የገባሁበት ሊፍት ውስጥ የምትገቢ አንቺ ማነሽ!” አይነት ሙልጭ አድርጋ ሰድባት ትሄዳለች፡፡
ሴትዮዋ ልትጠይቀው የሄደው ሰውም በሁኔታው በጣም ከመናደዱ የተነሳና በራሱም የሚተማመን በመሆኑ፣ በተራው አለቅየዋ ቢሮ ድረስ ሄዶ፣ ለሁለት የአሥር ዓመት ዕቅድ የሚበቃትን ያህል ‘አጠጥቷት’ በዛው የሥራ መልቀቂያውን አስገባ እላችኋለሁ፡፡
ቀን ወጣልኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፣
እንደ ዛሬ ሳይሆን
እኛም አንድ ሰሞን ‘ሽቅብ’ ወጥተን ነበር፡፡
የሚሉ የባቢሎን ግንብ ‘ገንብተው የጨረሱ’ ይመስላቸው የነበሩ መአት መኖራቸውን ማስታወስ አሪፍ ነው፡፡
እናላችሁ… በገባሁበት ሊፍት አይደለም መግባት ዝር ትሉና አይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች እየበዙ ነው፡፡ በመገልገያ ቦታዎች ሌላው እየጠበቀ እያለ እነሱ ቅድሚያ ካልተሰጣቸው… አለ አይደል… “ሰብስበህ ሳይቤሪያ ላክልኝ…!” የማለት አይነት ‘ቡራ ከረዩ’ የሚቃጣቸው አሉላችሁ፡፡ ቢሮ ውስጥ እናያቸዋለን፣ ህክምና ተቋማት ውስጥ እናያቸዋለን፣ ሆቴል ውስጥ እናያቸዋለን፣ ሬስቱራንት ውስጥ እናያቸዋለን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋሟት ውስጥ እናያቸዋለን፣ መዝናኛ ስፍራዎች ላይ እናያቸዋለን…ምን አለፋችሁ እንደየአቅማቸው… “አምስት መቶ አንሞላም…” አይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ማየት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡
እናላችሁ… ሌላ ሌላው ሲገርመን ጭራሽ “ሊፍት ውስጥ አብራችሁን አትግቡ…” የሚሉ ስረ መሠረታቸው እዚቹ የሆኑ ጉዶች ተፈጥረውላችኋል።
ቀን ወጣልኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፣
እንደ ዛሬ ሳይሆን
እኛም አንድ ሰሞን ‘ሽቅብ’ ወጥተን ነበር፡፡
የሚሉ የባቢሎን ግንብ ‘ገንብተው የጨረሱ’ ይመስላቸው የነበሩ መአት መኖራቸውን ማስታወስ አሪፍ ነው፡፡
ስሙኝማ… እዚህ ከተማ ውስጥ በ‘ፈረንጅ ቀመስ’ ድርጅቶች አንዳንድ የውጪ ዜጎች በሀበሻ ልጆች ላይ የሚያሳዩትን ዘረኝነት እንሰማለን። እንደውም ከስድቡና ከማንቋሸሹ አልፎ ሀበሻ ሠራተኞችን እንዲች ብለው የማይጨብጡ እንዳሉ ሁሉ ሰምተናል፡፡ አሁን ጭራሽ… “እንዴት የገባሁበት ሊፍት ውስጥ አብራችሁኝ ትገባላችሁ…” የሚሉ ስረ መሠረታቸው እዚቹ ጦቢያችን የሆኑ… አለ አይደል……‘ዕንቁላል ሻጮች’ (ቂ…ቂ…ቂ…) መጡና አረፉት፡፡
(የ‘ፈረንጅ የሥራ ባልደረቦች’ ያሏችሁ ወዳጆች… ዝም ብሎ “እንትን ኤን.ጂ.ኦ. ነው የምሠራው…” “እንትን ኤምባሲ ስሠራ ስምንት ዓመቴ…” ምናምን ብሎ መሸለሉ ‘ኤክስፓየሪ ዴቱ’ አልፎበታል። ከእነኛ ረጃጅም የግቢ ግንቦች ጀርባ፣ ከእነኛ የውድ ቪላዎች ግድግዳዎች ጀርባ ያለውን ጉድ ስለምንሰማ…አለ አይደል…“አይ ጦቢያ፣ ፈረንጅ ‘አፈሬን ይዘህማ አትሄድም፣ ጫማህን አጥበህ ነው መርከብ ላይ የምትወጣው…’ በተባለባት አገር ዛሬ “ሊፍት አብራችሁኝ አትገቡም” የሚሉ እንቁላል ሻጮችና፣ ሀበሻን ለመጨበጥ እንኳን የሚጠየፉ እንቁላል ገዢዎች (ቂ…ቂ…ቂ…) ፈልተው ስናይ ያሳዝናል፡፡
ቀን ወጣልኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፣
እንደ ዛሬ ሳይሆን፣
እኛም አንድ ሰሞን ‘ሽቅብ’ ወጥተን ነበር፡፡
የሚሉ የባቢሎን ግንብ ‘ገንብተው የጨረሱ’ ይመስላቸው የነበሩ መአት መኖራቸውን ማስታወስ አሪፍ ነው፡፡
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የዕድል ነገር ካነሳን አይቀር የሰው ዕድል ነገር አንዳንዴ አይገርማችሁም! ይቺን ስሙኝማ… አንዱ ‘የተመቸው’ እንበል መኪና መግዛት ይፈልግና ለአንድ ለምታውቁት ሰው “እባከህ ራቫ 4 መግዛት ፈልጌ ደህናዋን አንድ አራት መቶ ሺህ ብር አላገኝም…” ይለዋል፡፡ (እንትና ያቺ ከተማችሁ የዓመት በጀቷ ስንት ነበር ያልከኝ?) እናማ… “እሱ ነገረኝ” ለመባል ‘ዕድሉ’ ካላችሁ…ይኸው የምታውቁት ሰው… “ቆይ እስቲ ስለ መኪና የሚያውቅ አንድ ጓደኛ አለኝ…” ይልና ይደውልላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ… ሌላኛው ሰው…አለ አይደል…“ስማ ጨጓራ አስቸገረኝ፣ ጥሩ ሀኪም የት ነው ያለው?” ሲል የምታውቁትን ሰው ይጠይቀዋል፡፡ የምታውቁት ሰውም… “ቆይ እስቲ አንድ ጨጓራው ሁልጊዜ የሚቆስል ወዳጅ አለኝ…” ብሎ ይደውልላችኋል፡፡ እናማ… ዕድል እንደዚህ ነች… አንዱን ስለ ራቫ 4 መኪና፣ ሌላውን ደግሞ ስለ ጨጓራ በሽታ፡፡
ብቻ…“ሊፍት አብራችሁኝ አትገቡም የሚል እንቁላል ሻጭ ነው…” ከመባልስ ስለ ጨጓራ ቁስል መጠየቁ ይሻላል፡፡
ከጨጓራ ቁስለት ይሰውራችሁማ፡፡ (ምንም እንኳን አሁን፣ አሁን… አለ አይደል… “ከጨጓሯ ቁስለት ይሰውራችሁ…” ከሚል አይነት ምኞት ይልቅ “ጨረቃ ላይ ቢራ ለመጠጣት ያብቃህ…” የሚለው የመሳካት የተሻለ ዕድል ያለው ቢመስልም…ከቁስለት ይሰወራችሁ፡፡
ቀን ወጣልኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፣
እንደ ዛሬ ሳይሆን፣
እኛም አንድ ሰሞን ‘ሽቅብ’ ወጥተን ነበር፡፡
የሚሉ የባቢሎን ግንብ ‘ገንብተው የጨረሱ’ ይመስላቸው የነበሩ መአት መኖራቸውን ማስታወስ አሪፍ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…በ‘ኮሚዋ’ ሩስያ ዘመን ሞስኮ ውስጥ ነው አሉ፡፡ በአንድ የሜይ ዴይ ሰልፍ ላይ አንድ ሽማግሌ አይሁዳዊ “ጓድ ስታሊን፤ ደስተኛ ለነበረው የልጅነት ዕድሜዬ ምስጋና ይግባህ…” የሚል ትልቅ መፈክር ይዘዋል፡፡ ይሄኔ አንድ ካድሬ ቢጤ ነገር ይቀርባቸውና… “ይሄ የያዝከው ምንድነው? በፓርቲያችን ላይ እያሾፍክ ነው እንዴ?” ሲል ያፈጥባቸዋል፡፡ ሰውየውም “እኔ እያሾፍኩ አይደለም፡፡ ጓድ ስታሊንን ለማመስገን ብዬ ነው፣” ይላሉ፡፡
ይሄን ጊዜ ካድሬውም… “በአንተ ልጅነት ዘመን ስታሊን እንዳልተወለደ ሁሉም የሚያወቀው ነው…” ሲል ያፈጥባቸዋል፡፡ አዛውንቱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “እኔም እኮ የማመሰግነው ለዚሁ ነው…” ብለውት እርፍ፡፡
እናማ የሚያማርሩ ነገሮች ሲበዙ…አለ አይደል…ወደ ኋላ ተመልሰን… “ያን ጊዜ እናንተ እንኳን አልኖራችሁ…” አይነት ነገር ለማለት እንገደዳለን፡፡
ቀን ወጣልኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፣
እንደ ዛሬ ሳይሆን
እኛም አንድ ሰሞን ‘ሽቅብ’ ወጥተን ነበር፡፡
የሚሉ የባቢሎን ግንብ ‘ገንብተው የጨረሱ’ ይመስላቸው የነበሩ መአት መኖራቸውን ማስታወስ አሪፍ ነው፡፡
ሰው ሆኖ በመፈጠሩ፣ የዚች አገር ዜጋ በመሆኑ…‘ልዩ’ የሆንን፣ የወርቅ ምንጣፍ ሊነጠፍልን የሚገባን የሚመስለን፣ “እኔ በገባሁበት ሊፍት ውስጥ ሌላ ፍጡር ዝር ማለት…” እንደሌለበት የምናምን… ‘ህልማችን’ ቢበቃ አሪፍ ነው፡፡
ስንነቃ… አለ አይደል…እውነተኛውን ዓለም መቀበል አቅቶን አንደኛውን ‘እንዳይለይልን’ ነዋ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3003 times