Saturday, 15 March 2014 12:50

ኢህአዴግ ሰልፍ የማይጠራን እኮ ኑሮአችንን ሰልፍ ስላደረገው ነው!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የታክሲ---የዳቦ---የውሃ---የግብር---የቦሎ---ረዣዥም ሠልፎች----

  • የማሌዢያው አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ አልወደቀም ተባለ!
  • “መሬት የግል ይሁን” የዘመኑ “መሬት ላራሹ” ነው እንዴ?


       እኔ የምላችሁ … “አንድነት” ፓርቲ ባለፈው ሳምንት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የተሰኘውን ቁጥር 2 ንቅናቄ መጀመሩን ሰምታችሁልኛል?! አይዟችሁ … ብትሰሙም ችግር የለውም፡፡ ይሄኛው “ሽብር” ምናምን የሚል ነገር የለውም (“መሬት የግል ይሁን” ማለት ሽብር ነው እንዴ?) እናላችሁ … የአሁኑ አጀንዳዬ መሬት ነው ብሏል፤ ፓርቲው፡፡ አዎ! መሬት የግል ይሁን እያለ ነው- አንድነት፡፡ (ማን ነበር “ድርሻዬን” እያለ ያቀነቀነው?) እንደምታውቁት … ባለፈው ዓመት ፓርቲው ያደረገው ንቅናቄ፣ ለእኔ ቢጤ “አንድ ለእናቱ” ትንሽ ያስቦካ ነበር፡፡ በሚሊዮኖች ድምፅ “የፀረ-ሽብር አዋጁን አሰርዛለሁ” አይደል ያለው፤ አንድነት፡፡ ኢህአዴግ ያኔ በልቡ “On my dead body!” (ሞቻታለኋ!) ያለ አይመስላችሁም?
 እውነት ግን ፓርቲው 1ሚ. ፊርማ አሰባስቧል ማለት ነው? ለነገሩ አንድነት ፓርቲ 1ሚ. ደጋፊ ያጣል ማለት ዘበት ነው፡፡ ፓርቲው ምንም አልተንቀሳቀሰም ቢባል እንኳ ኢህአዴግ አለለት! ከምሬ እኮ ነው … አውራው ፓርቲ በየሰበቡ የሚያስቀይማቸው ሰዎች፤ አንድም ባህርማዶ አሊያም እንደ አንድነት ያሉ ተቃዋሚዎችን መቀላቀላቸው አይቀርም (ጠላት በማብዛት ኢህአዴግ አቻ የለውም!) እኔ የምላችሁ … የኢህአዴግ አባላት ቁጥር ስንት ሆነ?  ወይስ እንደ ኢኮኖሚ ዕድገቱ አሁንም እየገሰገሰ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ … ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የምትሰለፍበት ጊዜ ትንሽ ቀረብ ሳይል አይቀርም (30 እና 40 ዓመት አይፈጅም ማለቴ ነው!) አንድ ወዳጄ ደስ ይለዋል ብዬ ይሄን የምስራች ብነግረው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “እሰይ፤ ኢህአዴግ ተጨማሪ 30 እና 40 ዓመት ስልጣን አያስፈልገውም!” ብሎኝ ቁጭ አለ! እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … ስለ ስልጣን ቀን ተሌት የሚያስበው ሥልጣን ላይ የተቀመጠ  ብቻ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ለካስ እንደ እኔ ወዳጅ ያለውም ስለ ስልጣን ያስባል፡፡ (“ወንበሩ እንደሆነ አንድ ነው” ያሉት የቀድሞው መሪ ትዝ አሉኝ!)
ወደ አንድነት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ንቅናቄ ቁጥር 2 ልመልሳችሁ፡፡ እንዳልኳችሁ … የአሁኗ ጥያቄ ወይም ንቅናቄ በመሬት ዙሪያ የምታጠነጥን ናት፡፡ በሌላ አነጋገር “የየግላችን መሬት ይሰጠን!” የምትል ቀጭን ጥያቄ፣ ወይም ትግል ናት፡፡ (የዘመኑ “መሬት ላራሹ”!) በእርግጥ “መሬት የግል ይሁን” የሚለው ጥያቄ፣ የኒዮሊበራሊዝም ጠረን እንዳለው ከሩቅ ያስታውቃል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት መፈልፈያም ሳይሆን አይቀርም (በግምት ነው!) እናም ለኢህአዴግ አይመቸው ይሆናል (ሁሌ አይደላም አሉ!) ሌላው መካድ የሌለብን ግን ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የገበሬ .. የጭቁን ህዝብ .. የአርሶአደር-- ፓርቲ ነው፤ ከስር መሰረቱ ማለቴ ነው፡፡ (አሁንማ ኪራይ ሰብሳቢዎች ተደባለቁበት!) እናላችሁ … ኢህአዴግ መሬት የግል እንዳይሆን የሚፈልገው አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የጥንት የጠዋቱ የአልባንያ ፅንፈኛ ኮሙኒዝም ትዝ ብሎት ሳይሆን ቆሜለታለሁ ለሚለው አርሶ አደር አስቦ ነው። “መሬት የመንግሥት ይሁን ያልኩት ገበሬው እንዳይሸጠው ብዬ ነው” ይላል-ኢህአዴግ (ገበሬ “ዱርዬ” መሰለው እንዴ?) አንድነት ፓርቲ ይሄኔ ምን ይላል መሰላችሁ? (“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል!”) “መሬት በመንግሥት እጅ ይሁን ያልኩት ገበሬው ስለሚሸጠው ነው ይበል እንጂ አሁን እሱ እራሱ ለውጭ ባለሃብቶች እየቸበቸበው ነው” ሲል ይተቻል አንድነት - አውራ ፓርቲውን፡፡
እዚህ ጋ ግን አንድነት ያላስተዋለው ጉዳይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ መጀመርያውኑም ገበሬውን መሬት ከመሸጥ ለመከላከል ሞከረ እንጂ እኔ ራሴ “መሬት አልሸጥም! ሃራም ነው!” አላለም እኮ! በነገራችሁ ላይ በአሁኑ የአንድነት የመሬት ጥያቄ ወይም ንቅናቄ ላይ አንዳንድ ኢህአዴጎች ቢሳተፉ እንዳይገርማችሁ፡፡ (የመሬት ሱስ እንደሃሺሽ ነው!) ለምን መሰላችሁ? ነገርዬዋ እኮ የድርሻ ጥያቄ ናት! ስንቱ የኢህአዴግ ሹማምንት በ“መሬት ወረራ” ዘብጥያ መውረዱንም እንዳትዘነጉብኝ፡፡ (የባለሥልጣናት ሃብት በኢንተርኔት ሊለቀቅ ነው የተባለው እውነት ይሆን?) እናላችሁ ---- “ሲሶም ብትሆንም የግሉን  መሬት ቢያገኝ የሚጠላ የለም፡፡” ይላሉ የኒዮሊበራል ተንታኞች አሉ፡፡ (የመንግሥትም ሆኖ እኮ አልማሩትም!) እኔ የምለው--- መሬት “የመንግሥትና የህዝብ ነው” የተባለው ተቀየረ እንዴ? (መንግሥት ሳይጠቀልለው አልቀረም!) እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ---- የ60ዎቹ ተማሪዎች የ“መሬት ላራሹ” ጥያቄ ሲያነሱ “መሬት የህዝብና የመንግሥት ይሁን” ማለታቸው ነበር እንዴ? (ታዲያ ኢህአዴግ ከየት አመጣው?)
ይሄን ሁሉ ስለፈልፍ መሬት አቅሌን አስቶኝ እንዳይመስላችሁ፡፡ የነገው የአንድነት ንቅናቄ ላይ ይገኛል ብላችሁም እንዳትጠብቁ፡፡ ወዳጆቼ፤ እኔ ሰፊ የጋዜጣ አምድ እንጂ ሰፊ መሬት ፈላጊ አይደለሁም (መሬት ላይ ይፃፋል እንዴ?) እናላችሁ … የመሬት ጉዳይ ሆኖብኝ ዝም ብዬ ብለፈልፍም ላነሳ የፈለግሁት ጉዳይ ግን ሌላ ነበር (“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አሉ!)
ምን መሰላችሁ የፈለግሁት? ተማፅዕኖ ነዉ - ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ!! (ተማፅኖቱን ያለማንገራገር ይቀበሉ ዘንድ እማፀናቸዋለሁ!) እናላችሁ----የፈለገ አፈናና ወከባ ቢደርስባቸው፣ የፈለገ ቢታሰሩና መብታቸው ቢጣስ … ሌላ መንገድ ይፈልጉ እንጂ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይጠሩን (የድጋፍም ቢሆን ማለቴ ነው!) በክፋት እኮ አይደለም!! ችግር ስላለ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ አንድነት ፓርቲ በዚህ በሁለተኛ ንቅናቄው፣ ህዝባዊ ስብሰባ እንጂ ሰልፍ ባለመጥራቱ በግሌም እንደ ህዝብም አድንቄዋለሁ (“የልብ አውቃ” አሉ!) “መንግሥት ስብሰባውን ለማደናቀፍ ከሞከረ ግን ወደ ሰላማዊ ሰልፍ እቀይረዋለሁ” ማለቱን ግን አልወደድኩለትም፡፡ እናም ሌላ አማራጭ ቢያስብ ደስ ይለኛል፡፡
ከምሬ ነው----“የእድገት ምስቅልቅሉ” እስኪያልፍልን ድረስ… የተቃውሞ ሰልፍ (የድጋፍም ቢሆን!) እንዳትጠሩን--- አደራ እላችኋለሁ! መቼም እስካሁንም ምክንያቴ ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይኸውላችሁ … ሰልፍ አትጥሩን የምለው በሌላ ሳይሆን ኑሮአችን ራሱ ሰልፍ ስለሆነብን ነው፡፡ ለታክሲ መሰለፍ ከጀመርን ስንት ዓመት ሆነን? (ያውም ጠዋት ማታ!) የዳቦ ሰልፍስ? ብጫ ጀሪካል እየያዙ በየሰፈሩ  ለውሃ መሰለፉስ? (“የቦቴ ውሃ” የተባለው እንደ ኔትዎርኩ ጠፋ እንዴ?) የመብራት ቅድመ ክፍያ ካርድም የሚገዛው በብር ብቻ አይደለም - በሰልፍም ነው!! በነገራችሁ ላይ ---- ኢህአዴግ ስራውን ስለሚያውቅ ሰልፍ መጥራት ትቷል! እንዴ ----- ኑሮአችንን ሰልፍ አድርጎታል እኮ!! ባይገርማችሁ----የመጪው ዓመት ምርጫ ካሁኑ ስጋት ሆኖብኛል (ምርጫም እኮ በሰልፍ ነው!)
እኔ የምለው … እንዲህ መሰለፋችን ካልቀረ ግን ለምን ይሄን የሰልፍ ገድላችንን ጊነስ ቡክ ላይ አናስመዘግበውም?! (ፈረንጅ እኮ እንግዳ ነገር ይወዳል!) እርግጠኛ ነኝ ---- ለተከታታይ ዓመታት እንደኛ የተሰለፈ የዓለም ህዝብ የለም፡፡ እናም ከዓለም አንደኝነቱን የሚቀናቀነን አይኖርም፡፡ (ይሄን ለማስመዝገብም ወረፋ አለው እንዴ!!)
 የሰሞኗን ምርጥ ኩምክና ነግሬአችሁ ልሰናበት፡፡ ይሄ የገባበት ያልታወቀው 200 ተሳፋሪዎችን የያዘ  የማሌዢያ አውሮፕላን ነው የቀልዱ ምንጭ፡፡ እናላችሁ … “አውሮፕላኑ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አልወደቀም!” እየተባለ በእርግጠኝነት ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ “እንዴት ተረጋገጠ?” አትሉም
 “ወደ አውሮፕላን ተሳፋሪዎቹ ሞባይል ሲደወል ይጠራል!”
 አያችሁልኝ ---- ኢትዮጵያ ውስጥ ቢወድቅ ኖሮ አይጠራም ነበር ለማለት እኮ ነው!! (አይ ቴሌና ኔትወርክ!)
አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን “ቴሌ በዝባዥ ነው!” መባሉ ቆጭቷቸው ነው መሰለኝ “ቴሌ አትራፊ እንጂ በዝባዥ አይደለም!” የሚል ማስተባበያ እንደሰጡ ሰማሁ፡፡ ግን  “አገልግሎት ሳይሰጥ ገንዘብ የሚወስድ ምን ይባላል?” (አትራፊ ሊሆን አይችልም!)

Read 5320 times