Saturday, 15 March 2014 12:56

ድንበር አልባው የአፋር ማህበረሰብ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በኤርትራውያን ታጣቂዎች የተጠለፉትን ጀርመናውያን ያስመለሱ የአፋር  ሽማግሌዎች ምን ይላሉ?

         ከሁለት አመት በፊት ነው ድርጊቱ የተፈፀመው። በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አንዱ ወደ ሆነው ኢርታአሌ ይጓዙ የነበሩ ጀርመናውያን ቱሪስቶች ከኤርትራ ድንበር አቋርጠው በመጡ ታጣቂዎች ሲጠለፉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ተገደሉ፡፡ ከመካከላቸው ማምለጥ የቻለው አንድ ኢትዮጵያዊ፣ በአቅራቢያ ወደ ምትገኘው የአፍዴራ ቀበሌ ኩሩርዋድ መንደር በመምጣት የተፈጠረውን ሁኔታ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተናገረ፡፡ የመንደሯ ሽማግሌዎችም በኤርትራ ከሚገኙ የአፋር ባላባቶች ጋር በመደራደር፣ ጀርመናውያኑ በህይወት እንዲመለሱ አደረጉ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲም ባለፈው ሳምንት የመንደሯ ሽማግሌዎች ጀርመናውያኑን በማስመለስ ላደረጉት ውለታ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ከትግራይ ደጋማ አካባቢዎች በመነሳት በአለት ውስጥ ለውስጥ ይሄድ የነበረን የዝናብ ውሀ አቅጣጫ በማስቀየር፣ ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲሰጥ ያሰራውን ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ኢዝሎር ሲሩስ በተገኙበት አስረክቧል፡፡
በኤርትራ ታጣቂዎች ተወስደው የነበሩትን ጀርመናውያን በማስመለስ ትልቅ ሚና የተጫወቱት ጊልሳ ያኢድ እና ሳልህ ኡስማን ሁኔታውን አስመልክቶ የተናገሩትን እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበነዋል፡፡
ቱሪስቶች ኢርታአሌን ለማየት ሲሄዱ ከአፍዴራ የሚያጅቧቸው ሁለት ሚሊሺያዎች እና አንደ መንገድ መሪ ይመደባል፡፡ ከኤርትራ የመጡት ሽፍቶች ሁለቱን ጀርመናውያን ጠልፈው ሲወስዱ ሁለት ኢትዮጵያውያንን ገድለው ነው፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ስላመለጠ ሁኔታውን መጥቶ ነገረን። በአፋር ባህል እኛን ብሎ የመጣ ሰው፣ እኛ መሬት ላይ መግደል ወይም ሲገደል ማየት ትልቅ ነውር ነው፡፡ ቱሪስቶቹ ምንም አይነት መሳሪያ አልያዙም። የውሀ ጥማቸውን ለመቁረጥ የላስቲክ ውሀ ብቻ ነበር የያዙት፡፡ ድርጊቱን እንደ ሰማን የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይል፣ ፖሊስ እንዲሁም  ሴቶች እና ህፃናት ሳይቀሩ ወደ ስፍራው ሶስት ቀን ተጉዘን ደረስን፡፡ ቦታው ከፍተኛ የውሀ እጥረት ያለበት ስለሆነ ግመሎቻችንን ውሀ ጭነን ነበር የሄድነው። ሴቶቹ እና ህፃናቱ ምግብና  ውሀ ለማቅረብ ነው ተከትለውን የመጡት፡፡ የሄድነው እጅግ ተቆጥተን ነበር፡፡ ብንሞትም እንሙት እንጂ እኛን ብለው የመጡ የውጪ ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውና ሚሊሺያዎቹንም መግደላቸው እጅግ አስቆጭቶናል። አርታአሌን  በቁጥጥር ስር ካዋልን በኋላ የተወሰኑት የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን ጭነው ወደ አፍዴራ ሲመለሱ፣ እኛ በባህላዊው የአፋር የመረጃ መቀባበያ ዘዴ “ዳጉ” መሰረት መረጃ ማሰባሰብ ጀመርን፡፡ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የሚኖረው አፋር  በጎሳ የተሳሰረ ነው፡፡ ማንም የታጠቀ ሀይል ይሁን ሽፍታ ከጎሳው ባላባቶች ትእዛዝ አይወጣም፡፡  አስራ ሁለቱ  የባላባት ልጆች ተሰባስበው መከሩ፡፡ ከአገር ውጪ ያሉ የባላባት ልጆችም የታገቱትን ሰዎች እንዲያስለቅቁ ጥሪ ቀርቦ መላላኩ ተጀመረ፡፡ ኤርትራ ለሚገኙት ባላባቶች ሰዎቻችን ለምን ተገደሉ? ተጠልፈው የተወሰዱት በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንዲነግሩንና አሳልፈው እንዲሰጡን ጠየቅናቸው፡፡ ባላባቶቹም በጥያቄያችን መሰረት የተጠለፉት ሰዎች እንዲመለሱ ተነጋገሩ። የባላባት ትእዛዝ የማያከብር ማንኛውም አፋር፣ የአፋር ዘር ያለበት ቦታ ላይ መኖር አይችልም። ታጣቂዎቹም ቢሆኑ የባላባቶችን ትእዛዝ ከጣሱ ማረፊያ ስለማይኖራቸው፣ የጠለፏቸውን ሰዎች ለመመለስ በተደረገው ድርድር ተስማሙ፡፡ የመንግስት አካላት በህገ መንግስት ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎችን እንደሚያከብሩ ሁሉ ሽፍቶችም ቢሆኑ የጎሳ ስርአቱንና ውሳኔውን ያከብራሉ፡፡  እኛም ድንበሩን ተሻግረን የተጠለፉትን ሰዎች ለመረከብ ኤርትራ ገባን፡፡ በኤርትራ ከሚኖሩ የአፋር ጎሳዎች አንዱ የሆነው የዳሂሜና ጎሳ ልጅ ሰዎቹን ይዞልን መጣ፡፡  እኛም ለሁለቱ አንዳንድ ግመል ሰጥተን፣ ውሀ የጫነችላቸውን አንድ ግመል አስከትለን ወደ መንደራችን ስንወስዳቸው፣ አጠገባቸው የነበሩት ሰዎች በጭካኔ ተገድለው፣ እነሱ በህይወት መመለሳቸው ደስታና ግራ መጋባት ውስጥ ከተታቸው፡፡ ደስታቸው ግን ወሰን አልነበረው፡፡
በኤርትራ ያሉ ታጣቂዎች እኛ ከቱሪስቶቹ በምናገኘው ጥቅም ደስተኞች ባለመሆናቸው በጣም እናዝናለን፡፡ እኛ ግን ማንም ቢሆን በኛ መሬት እንግዳ ሆኖ እስከመጣ ድረስ የደህንነቱን ጉዳይ በሀላፊነት መውሰድ ባህላዊ ግዴታችን ነው። ፈረንጆቹ እሳቱን ለመጎብኘት  ሲመጡ የግመል ኪራይ፣የአጃቢ፣ የመንገድ መሪ --- እየተባለ ስለሚከፈለን ብዙ ጥቅሞችን እናገኛለን፡፡ ከዛን ቀን በኋላም  ለቱሪስቶቹ የበለጠ ጥበቃ ማድረግ ጀመርን። አሁን በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከአስር በላይ የጎብኚ  ቡድን  ይሄዳል፡፡  ሁሉም በሰላም ደርሶ እየተመለሰ ነው። ከሁለት አመት በፊት ጠለፋውን የፈፀሙት ሰዎች ስላልተያዙም ልዩ የፀጥታ  ሀይል እስከአሁን ጠለፋው የተደረገበት ቦታ ላይ ይገኛል፡፡


Read 5121 times