Print this page
Saturday, 22 March 2014 12:04

እየተናጠ ባለው ዓለም ምን እንደሚጠብቅን ማን ያውቃል?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

4 የጥንቃቄ ምክሮች - ለመንግስትና ለኢህአዴግ

       አለማችን፣ ከዳር ዳር እየተናጠች ግራ ግብት ብሏታል። የነ ግብፅ እና ሶሪያ እልባት ሳያገኝ፤ ውዥንብር የበዛበት የዩክሬን ትርምስ ተጨመረበት። የዘመናችንን ቀውስ ፍንትው አድርጎ በሚያሳየው የዩክሬን ትርምስ ውስጥ፣ ዋናዎቹ ተዋናዮች አንጋፋ ፖለቲከኞችና ትልልቅ ፓርቲዎች አይደሉም። በሃይማኖትና በቋንቋ ዩክሬንን ለሁለት መሰንጠቅ የጀመሩት ሁለት ነውጠኛ ቡድኖች፤ ከጥቂት ወራት በፊት እንኳን በአለም ደረጃ እዚያው ዩክሬንና ራሺያ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተደማጭነትና ታዋቂነት አልነበራቸውም። “ናሽናል ሶሻሊዝም” በተሰኘው የፋሺዝም ቅኝት እንደ ሞሶሎኒና እንደ ሂትለር “ከራስህ በፊት ለእናት አገርህ” እያሉ የሚዘምሩት ሁለቱ ቡድኖች፤ “አገር ትቅደም። ለአገር መስዋዕት ሁኑ፡፡ የሚል መፈክር ያስተጋባሉ። አንደኛው ቡድን፣ “ለራሺያ መስዋዕት ሁኑ” ሲል፤ ሌላኛው ደግሞ “ለዩክሬን መስዋዕት ሁኑ” እያለ ዘረኝነትንና የሃይማኖት ጥላቻን በጭፍን ስሜት  እያራገቡ በርካታ አመታትን አስቆጥረዋል - ድጋፍ ባያስገኝላቸውም።
እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ፣ የዩክሬንን አመፅ የመራው የ42 አመቱ ዲሚትሮ ያሮሽ፣ ከመምህራን ኮሌጅ የተመረቀ ከመሆኑ በቀር ያን ያህልም የሚታወቅ ታሪክ የለውም። ከአመታት በፊት በያሮሽ የተመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ፣ ቀኝ ዘርፍ በሚል ስያሜ ያቋቋመው ነውጠኛ ቡድን የፓርላማ ወንበር የላቸውም። ፓርቲው በምርጫ ቢወዳደርም አልተሳካለትም። አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል። ያሮሽ የአገሪቱ የፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ከመሆኑም በላይ፤ የቡድኑ አባላት የዩክሬን አለኝታና የቁርጥ ቀን ልጆች ስለሆኑ ትጥቅ አይፈቱም ብሏል - በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት እንደማለት ነው።
በብዛት የራሺያ ቋንቋ የሚናገሩ ሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎችን የያዘችው ክሬሚያ፣ ከዩክሬን እንድትገነጠልና ወደ ራሺያ እንድትጠቃለል አመፅ ያካሄደው ሁለተኛው ቡድንም ተመሳሳይ ነው። በክሬሚያ ምክር ቤት ውስጥ ከ3 ወንበር በላይ ይዞ እንደማያውቅና ባለፈው ምርጫ ያገኘው ድምፅ አራት በመቶ ገደማ ብቻ እንደሆነ የታይም መፅሄት ዘገባ ገልጿል። የቡድኑ መሪ ሰርጌ አክስዮኖቭ ከታዋቂ የክሬሚያ ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ የሚጠቀስ አልነበረም። ታዋቂ ለመሆን ስላልሞከረ አይደለም። ክሬሚያ ከዩክሬን እንድትገነጠል የሕግ ረቂቅ ለምክርቤቱ በማቅረብ ዝና ለማትረፍ በተደጋጋሚ ሞክሯል - ለበርካታ አመታት። ግን ከቁም ነገር የቆጠረው ሰው አልነበረም። በቅርቡ ነው፤ ሌላ መላ የፈጠረው።
ካለፈው ጥር ወር ወዲህ፣ ከየቦታው ወጣቶችን እየመለመለ ማሰባሰብ የጀመረው አክስዮኖቭ፣  ወደ ጠረፍ አካባቢ እየወሰደ ታጣቂ ቡድን ሲያደረጅ ከርሟል። ብዙም አልቆየም። ከሁለት ወራት በኋላ ዩክሬን ስትቃወስ፣ አክስዮኖቭ ለታጣቂዎቹ የዘመቻ ትዕዛዝ አስተላለፈ። እናም ስራቸውን ሰሩ። የክሬሚያ ምክር ቤትን ወረሩትና ሁለት የአዋጅ ረቂቆች ቀረቡ። አዳራሹን ከሞሉት ሰዎች መካከል፣ የትኞቹ የምክር ቤት አባል እንደሆኑ፣ የትኞቹ ደግሞ የታጣቂ ቡድን አባል እንደሆኑ የሚታወቀው፤ መሳሪያ በመታጠቅና ባለመታጠቅ ብቻ ነው። አዋጅ ለማፅደቅ ድምፅ የሰጡት የትኞቹ እንደሆኑ ግን አይታወቅም። በአንደኛው አዋጅ፣ ክሬሚያ ከዩክሬን እንድትገነጠል በህዝብ ለማስወሰን ምርጫ ይካሄዳል ተባለ። በሁለተኛው አዋጅ ደግሞ፣ የ32 አመቱ አክስዮኖቭ፣ የክሬሚያ ፕሬዚዳንት ሆኖ ስልጣን ያዘ። ፓርቲው በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉት ወንበሮች ሶስት ብቻ ቢሆኑም፤ በሺ የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን ስላሰማራ፣ ከፍተኛውን ስልጣን ተቆጣጠረ። በዚህ ምክንያት የሚሰነዘሩበትን ትችቶች በማጣጣል፣ “በወቅቱ ግርግር ስለነበር ምንም ማድረግ አይቻልም” የሚለው አክስዮኖቭ፤ “ሃላፊነት የሚወስድ ሰው ጠፋ። ስለዚህ ለአገሬ መስዋዕት ለመሆን ታሪካዊ ሃላፊነት ተረከብኩ” ብሏል።
የዘር እና የሃይማኖት ልዩነትን የሚያራግቡት ሁለቱ ቡድኖች፣ ከተወሸቁበት ጉራንጉር ወጥተው እንዲህ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ገናና ለመሆን የበቁት ታጣቂ ቡድን በማደራጀታቸው አይደለም። ከሌሎች ፓርቲዎች ያን ያህል የተለየ የፖለቲካ አቋም ስላላቸውም አይደለም። አንጋፋዎቹና ትልልቆቹ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ “የናሽናል ሶሻሊዝም” አስተሳሰብን የሚከተሉ ናቸው። የዩክሬን ገዢ ፓርቲ ምን ተብሎ እንደሚጠራ ማየት ትችላላችሁ - “አባት አገር” ይባላል። የራሺያ ገዢ ፓርቲ ደግሞ “አንዲት ራሺያ” ይሰኛል። “ብሄረተኝነት” ወይም “አገራዊነት” የሚባለው የፋሺዝም ቅኝት፣ “እያንዳንዱ ሰው፣ ከራሱ ጥቅምና ከራሱ ሕይወት በፊት፤ ከግል መብቱና ከነፃነቱ በፊት ለአገሩ፣ ለብሔሩ፣ ለጎሳው ቅድሚያ መስጠትና መስዋዕት መሆን አለበት” የሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚህ የተለየ አዝማሚያ አላቸው የሚባሉት ሌሎቹ ፓርቲዎች፤ በአብዛኛው የሶሻሊዝምና የኮሙኒዝም እንጥፍጣፊዎች ናቸው - “እያንዳንዱ ሰው ከራሱ ሕይወትና ከግል ነፃነቱ በፊት፤ ለድሆች፣ ለጭቁኖችና ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠትና መስዋዕት መሆን አለበት” የሚለውን ሃሳብ ያዘወትራሉ።
“ናሽናሊስቶቹ” እና “ሶሻሊስቶቹ” ያን ያህልም በሃሳብና በስሜት የሚራራቁ አይደሉም። ሁለቱም በጋራ፣ “የግለሰብ ነፃነትና መብት” የሚባለውን ነገር ይጠላሉ። አንደኛው ወገን፤ “ለአገር ወይም ለብሔር ብሔረሰብ ጥቅም ቅድሚያ እሰጣለሁ” በሚል መፈክር፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ “ለጭቁን ሕዝብና ለድሆች ጥቅም ቅድሚያ እንሰጣለሁ” በሚል ሰበብ፤ የሰውን መብትና ነፃነት መርገጥ እንደሚቻል ያምናሉ። ይህ ብቻ አይደለም ተመሳሳይነታቸው። የትኛውን ሰበብና መፈክር ያዘወትራሉ ብለን ልንለያቸው ካልሞከርን በስተቀር፤ አንዱ የሌላኛውን መፈክር ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም። ዘረኝነትንና ብሔረተኝነትን በማራገብ የሚታወቁት ሂትለርና ሞሶሎኒ፣ ለሰፊው ሕዝብና ለድሆች በአለኝታነት የምንቆም ሶሻሊስቶች ነን ይሉ አልነበር? በሰፊው ሕዝብና በድሆች ስም የሚምሉ የሚገዘቱ የዩጎዝላቪያ ሶሻሊስቶችም በተራቸው፤ ዘረኝነትንና ብሄረተኝነትን በማጦዝ አገሪቱን ሰነጣጥቀው በደም አጨቅይተዋታል። የእያንዳንዱን ግለሰብ መብትና ነፃነት ለማክበር ፍላጎት የሌላቸው እነዚሁ ቅኝቶች፤ “የሕዝባዊነት አስተሳሰብ ተከታይ” (collectivist) የሚል የጋራ ስያሜ ሊሰጣቸው ይችላል። በራሺያም ሆነ በዩክሬን፣ ትልልቆቹና አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች የዚህ አስተሳሰብ ምርኮኞች ናቸው - እያንዳንዱ ሰው፤ ምንም አይነት ነፃነት የሌለው የሕዝብ ሎሌ ወይም አገልጋይ ባርያ መሆን ይገባዋል ብለው የሚያምኑ። እያንዳንዱ ሰው የሕዝብ ሎሌ መሆን አለበት ሲባል፤ በሌላ አነጋገር የመንግስት ሎሌ፤ እናም የገዢው ፓርቲ ሎሌ ይሆናል እንደማለት ነው።
እንደዚያም ሆኖ፤ በሃሳብ ደረጃ “ሕዝባዊነት”ን የሚሰብኩ የዘመናችን ብዙ ፓርቲዎች፤ በተግባር የምኞታቸውን ያህል መሄድ አይችሉም፤ እንደ ሞሶሎኒና ሂትለር ወይም እንደ ሌኒንና ስታሊን፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ የፋሺዝም ወይም የሶሻሊዝም ስርዓት ለማስፈን አይደፍሩም። ለምን? ሕዝባዊነት፣ በ20ኛው ክፍለዘመን ምን ያህል እልቂትና ስቃይ፣ ምን ያህል ድህነትና ረሃብ እንዳስከተለ ስለሚታወቅ፤ አብዛኛውን ወጣትና ምሁር የመማረክ ወይም የማነሳሳት ሃያልነቱ ሞቷል። ስለዚህ፤ የዩክሬን ትልልቅ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሕዝባዊነትን የሚሰብኩ አብዛኞቹ የዘመናችን ፓርቲዎች፣ በሙሉ ልብ ሃሳባቸውን ተንትነው ቢያቀርቡ ሆ ብሎ የሚከተላቸው አያገኙም፤ ሃሳባቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉትም በግማሽ ልብ ነው። የአስተሳሰባቸውን ያህል የሰውን ምርትና ንብረት በጠራራ ፀሐይ ባይወርሱም፤ መንግስት እለት በእለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ እየገባ በአላስፈላጊ ቁጥጥሮችና ገደቦች የሰዎችን ኑሮ እንዲያናጋ ያደርጋሉ፡፡ በተለያዩ የቀረጥና የታክስ አይነቶች የሰውን ኪስ ያራቁታሉ። የስብከታቸውን ያህል ጭልጥ ብለው ባይገቡበትም፣ በመጠኑ ዘረኝነትን ያራግባሉ። በአጭሩ ስብከታቸውና ድርጊታቸው ይለያያል። ቆጠብ ለማለት ይሞክራሉ።
አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ችባ ሆነዋል ቢባል የተጋነነ አይደለም። “የሕዝባዊነት” አስተሳሰባቸውን ተንትነው እንዳያቀርቡ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን የሞተ አስተሳሰብ ነው። በስሜት ደረጃ እያግለበለቡ እንዳይሰብኩም መዘዙን እየፈሩ ቆጠብ ይላሉ። ከትንታኔም ሆነ ከስሜት አንዱንም ሳይሆኑ ይቀራሉ። ሁለቱ መናኛና ነውጠኛ ቡድኖችም ወደ ትንታኔ የመግባት ዝንባሌ የላቸውም። ነገር ግን፤ ጭፍን ስሜት ከማግለብለብ ቆጠብ የማለት ፍላጎት የላቸውም። ጭልጥ ብለው ዘረኝነት ውስጥ ገብተዋል። ጉልበት ያገኙትና ዋነኛ የጥፋት ተዋናይ ለመሆን የበቁትም በዚህ ምክንያት ነው።
በእርግጥ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን “የሕዝባዊነት አስተሳሰብ” ነግሶ ከመሞቱ በፊት፣ ሁለት ዋና ዋና የአስተሳሰብ አይነቶች ነግሰው ሞተዋል። አንደኛው፤ ሊበራሊዝም የሚባለው የስልጣኔ ዘመን አስተሳሰብ ነው። “እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ሕይወትና ንብረት ላይ ብቸኛ አዛዥና ወሳኝ መሆን ስላለበት መብቱና ነፃነቱ ሙሉ ለሙሉ ሊከበርለት ይገባል፤ በሌላ ሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ደግሞ ቅንጣት ስልጣን የለውም። ስለዚህ የማንንም ሰው መብትና ነፃነት ንክች ማድረግ የለበትም። እነካለሁ፤ በሌሎች ሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ፈላጭ ቆራጭ እሆናለሁ የሚል ወንጀለኛ መኖሩ አይቀርም። መንግስት የሚያስፈልገውም በዚህ ምክንያት ነው” ይላል ሊበራሊዝም። በዚህ አስተሳሰብ፤ የመንግስት ስራ፣ ሌላ ሳይሆን የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ማስከበርና ይህንን የሚጥሱ ወንጀለኞችን ልክ ማስገባት ነው። አለመግባባት የፈጠሩ ሰዎችንም መዳኘት።
በአጭሩ፣ የመንግስት ስራ፤ የዳኝነት ወይም የግልግል እንዲሁም የዘበኝነት ወይም የጥበቃ ስራ ነው። እንግዲህ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው። ሰዎች ድምፃቸውን የሚሰጡትና ውሳኔ የሚያስተላልፉት፤ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ለማዘዝ አይደለም። ከራሱ ከሰውዬው በስተቀር፣ ማንም የማዘዝ ስልጣን የለውም። በቁጥር የመብለጥና የማነስ ጉዳይ አይደለም።  ለብቻዬም ብሆን አልያም ሚሊዮኖችን ባስከትል ወይም ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ 99 በመቶ ያህሉ የድጋፍ ድምፅ ቢሰጠኝ ለውጥ የለውም። በሌላ ሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ቅንጣት ስልጣን አይኖረኝም። 99 በመቶም ሆነ 51 በመቶ “ሕዝብ” እና “የሕዝብ ተመራጭ”፣ እንዳሰኘው ሰውን የመግደል አልያም የሰውን ንብረት የመውረስና የመዝረፍ መብት የለውም። እና ታዲያ፣ ሕዝብ በፖለቲካ ምርጫዎች ላይ የሚሳተፈውና ድምፅ የሚሰጠው ለምንድነው? የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት የሚያስከብሩ የመንግስት አካላትን (ማለትም ገላጋዮችና ዘበኞችን) አማርጦ ለመቅጠር ነው ምርጫ የሚካሄደው። ስልጣን አገኘሁ ወይም በቁጥር እበልጣለሁ ብሎ፣ ሰዎችን መጨፍጨፍና መዝረፍ አይቻልም።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን ተስፋፍቶ፣ በ18ኛው ክፍለዘመን ለአሜሪካ ምስረታ ጠንካራ መሰረት ሊሆን የበቃው የ“ሊበራሊዝም” አስተሳሰብ፣ ከሁሉም በላይ ለእያንዳንዱ ሰው መብትና ነፃነት ከፍተኛውን ክብር ይሰጣል። ዲሞክራሲ ደግሞ፣ ይህንን መብትና ነፃነት ለማስከበር የሚያገለግል መሳሪያ ወይም አሰራር ነው። ለዚህም ነው ሊበራል ዲሞክራሲ ብለው የሚጠሩት። “ዲሞክራሲ” በጥሬው ሲሆን ግን፤ 51 በመቶው “ሕዝብ” ወይም “የሕዝብ ተመራጭ” እንዳሰኘው በሰዎች ላይ የሚፈነጭ የ“አምባገነንነት” ዝርያ ይሆናል። ለዚህም ነው፤ ታላቋን የነፃነት አገር አሜሪካን የመሰረቱ ጥበበኛና አስተዋይ ፖለቲከኞች፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ስርዓት በ“ግለሰብ ነፃነት” ላይ እንጂ በ“ዲሞክራሲ” ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ በአፅንኦት ሲናገሩ የነበሩት።  ለዚህም ነው፤ በአሜሪካ የነፃነት መግለጫ፤ ማንኛውም አይነት መንግስት፣ የተመረጠም ይሁን ያልተመረጠ፣ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ንጉሳዊ፣ አገር በቀልም ይሁን መጤ፣ የእያንዳንዱን ሰው መብትና ነፃነት የማያከብር እስከሆነ ድረስ፣ ከስልጣን መወገድ የሚገባው ሕገወጥ መንግስት እንደሆነ በግልፅ የሚያውጀው። በሕገመንግስት ውስጥም እንዲሁ፣ በሕዝብ የሚመረጠው የአገሪቱ ምክር ቤት (ኮንግረስ)፣ የሰዎችን የሃሳብ ነፃነት የሚጥስ፣ በሰዎች ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ፣ ወይም ሃይማኖትን በመንግስት ጉዳይ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ ሕግ የማፅደቅ ስልጣን እንደሌለው በግልፅ ተደንግጓል። በሕዝብ ተመርጬ ስልጣን ይዣለሁ ብሎ እንዳሻው የሰዎችን መብትና ነፃነት መጣስ አይችልም። ሕገመንግስት ያስፈለገውም፤ ይህንን “የሕዝብ” ወይም “የመንግስት” ስልጣን ለመገደብ ነው። በአጭሩ፤ ዋነኛው የፖለቲካ ማጠንጠኛ፣ ዲሞክራሲና ምርጫ አይደሉም - የእያንዳንዱ ሰው መብትና ነፃነትን ማስከበር ነው አስኳሉ። ይሄው ስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በአሜሪካ በስፋት ከከተገበረ በኋላ፤ በርካታ አገራት ቀስ በቀስ እንዲሻሻሉ፣ ከአምባገነንነትና ከእልቂት፣ ከድህነትና ከረሃብ እንዲላቀቁ ረድቷል። አሳዛኙ ነገር፤ እየተጠናከረ ከመሄድ ይልቅ፤ “የራስ ወዳድነት አስተሳሰብ ነው” በሚል እየተንቋሸሸና እየተሸረሸረ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን የበላይነቱን አጥቶ በ“ሕዝባዊነት” አስተሳሰቦች አማካኝነት ተዳክሟል። አብዛኛውን ወጣትና ምሁር የመማረክ ወይም የማነሳሳት ሃያልነቱ ተመናምኗል። እናም፤ ሊበራሊዝምን የሚሰብኩ አብዛኞቹ የዘመናችን ፓርቲዎች በግማሽ ልብ ነው ተግባራዊ የሚያደርጉት። በአብዛኛውም፣ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ሲሉ።
ሶስተኛው ርዕዮተ ዓለም፣ ከሊበራሊዝምና ከሕዝባዊነት በፊት ገናና የነበረ ጥንታዊ ርዕዮተ ዓለም ነው - ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም። ይሄኛው ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብም፤ ዛሬ እንደ ጥንቱ ሃያል አይደለም። ለሺ አመታት አለምን በጦርነትና በድህነት ውስጥ ዘፍቋት የቆየው ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ የበላይነቱን በሊበራሊዝም አስተሳሰብ  ተነጥቆ የስልጣኔ ብርሃን ከደመቀ ወዲህ እንደገና ሃያልነቱን መልሶ የማግኘት እድል አላገኘም።
ከእነዚህ ሶስቱ አስተሳሰቦች ውጭ (ከሃይማኖታዊ፣ ከሊበራሊዝም፣ እና ከሕዝባዊ አስተሳሰብ ውጭ) ሌላ አይነት አስተሳሰብ የለም። ግን ደግሞ ሶስቱ አስተሳሰቦች፣ አብዛኛውን ወጣትና ምሁር የመማረክና የማነሳሳት ሃይልነታቸውን አጥተዋል። እና የአለምና የታሪክ መዘውር የሚሽከረከረው በምንድነው? መድረሻችንስ የት ነው?
ሊታረቁ የማይችሉት ሶስቱ የአስተሳሰብ አቅጣጫዎች ከተዳከሙ፤ በመላው አለም ለዘብተኛነት ሰፍኖ፣ መቻቻል ነግሶ፣ ግጭት በርዶ፣ ሰላምና ብልፅግና ይሰፍናል እያሉ በየዘመኑ ሲናገሩ የነበሩ ምሁራን ጥቂት አይደሉም። ይህንን እንደ ቂልነት የምትቆጥረው ታዋቂዋ ደራሲና ፈላስፋ አየን ራንድ፣ የለዘብተኛነት መንገድ  ስንዝር እንደማያራምድና እንደማያዛልቅ ትገልፃለች። ሊበራሊዝምና አብሮት የሚመጣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ፣ አለምን ከጨለማ አውጥቶ፣ በበሽታና በረሃብ ሲያልቅ፣ በጦርትነትና በግጭት ሲጨፋጨፍ የነበረውን የሰው ልጅ፣ ከድሮው በሶስት እጥፍ የሚበልጥ እድሜ እንዲኖረው፣ በመቶ እጥፍ የላቀ የኑሮ ምቾት እንዲያገኝ ማድረጉን ታስረዳለች። በተቃራኒው፣ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሕዝባዊነት፤ አለምን አጨልመው፣ ምድሪቱን በደም አጨቅይተው፣ የሰውን ልጅ በረሃብ አሰቃይተዋል። ያው፤ ትክክለኛ አስተሳሰብ ወደ ስኬት ሲያደርሰን፣ የተሳሳተ አስተሳሰብ ደግሞ ወደ ጥፋት እያንደረደረ እንጦሮጦስ ያወርደናል።
ጨርሶ ጎልቶ የሚታይ አስተሳሰብ ከሌለስ? ሦስቱ አስተሳሰቦች ሲዳከሙ ውጤቱ ምን ይሆናል? ራንድ እንዲህ ትላለች - ሰዎች ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብ አቅጣጫቸውን ካልቀየሩ በቀር፣ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ባለው አያያዛቸው ከቀጠሉ መጨረሻቸው ጨለማ ነው። ከእንሰሳ ባልተሻለ ጭፍን ስሜት እየተቧደኑ እርስ በርስ መናጨትና መበላላት የበዛበት ዘግናኝ የጨለማ ዘመን ይፈጠራል። ሰዎች አስተሳሰባቸውን ካላስተካከሉ፤ የአለም አዝማሚያ ቀስ በቀስ ወደዚሁ ትርምስ እንደሚያመራ ትናገራለች ራንድ - ከ40 ዓመታት በፊት ባሳተመቻቸው መፃህፍቷ።
የዛሬ 18 ዓመት፣ “Clash of Civilizations” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ የሚታወቁት ሳሙኤል ሃቲንግተን በበኩላቸው፤ ገናናዎቹ የፖለቲካ አስተሳሰቦች መክሰማቸውን በመግለፅ፣ ሰዎች ከኢኮኖሚ ስሌት ጨርሶ ባይለያዩም በጥንታዊ የባህል፣ የቋንቋ፣ የብሄር ብሄረሰብና የሃይማኖት ውርሶች እየተሰባሰቡ መቧደን እንደሚጀምሩ ይገልፃሉ። በሌላ አነጋገር፤ ዋና ዋናዎቹ አስተሳሰቦች፣ ከሃሳብ ትንታኔ ጋር ተራርቀው ወደ ስሜት ደረጃ ይወርዳሉ። የሊበራሊዝም አስተሳሰብ፣ ዋነኛ መሰረተ ሃሳቡ ይጠፋና፣ ከተራ የፖለቲካ ምርጫ እና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ብቻ የተቆራኘ የምኞት ስሜት ይሆናል። እናም፣ ሰዎች አፈና ወይም የኢኮኖሚ ችግር ሲበረታባቸው፤ እና ደግሞ የሌላው አገር ነፃነትና ብልፅግና በሳተላይት ቴሌቪዥንና በኢንተርኔት ሲያዩ፣ በቅሬታ ስሜት ተሞልተው ያምፃሉ። መፍትሄውን ግን አያውቁትም።
የግብፅና የሶሪያ፣ የሴንትራል አፍሪካና የኮንጎ ግጭቶችን ተመልከቱ። አዳሜ፣ አፈናና ችጋር እየመረረው፣ ነፃነትንና ብልፅግናን በመመኘት አደባባይ ይወጣል። መንግስት ይገለበጣል፤ ግን ተመልሶ ያው ነው። ችግር፣ በራሱ ጊዜ መፍትሄ አይወልድም። ያለ ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ በስሜት ብቻ፣ ሁነኛ መፍትሄ አይገኝም። ግብፃውያን ምን ተረፋቸው? መሃመድ ሙርሲን የመሰለ የሃይማኖት አክራሪ ወይም ጄነራል አሲሲን የመሰለ በአገርና በሕዝብ ስም የሚፎክር አምባገነን! ሶሪያውያን ምን ተረፋቸው? በአንድ በኩል፣ በአገርና በሕዝብ ስም መንደሮችን በአውሮፕላን የሚደበድብ መንግስት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሺዓ እና ሱኒ እያሉ ሰውን የሚጨፈጭፉ የሃይማኖት አክራሪዎች! ሌላ ያተረፉት ነገር የለም። ለነገሩ፤ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብም ሆነ ሕዝባዊነት፣ ከስሜት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም። ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለአገሬው ወይም ለአለም ችግሮች፤ ለኢኮኖሚና ለፖለቲካ ቀውሶች መፍትሄ ያመጣል በሚል ትንታኔ ሰዎችን መማረክ በፍፁም አይቻልም፤ መፍትሄ እንደማያመጣ ታይቷልና። ነገር ግን፣ በሃይማኖት ሰበብ የሰዎችን ስሜት ማነሳሳትና በሃይማኖት አቧድኖ ማጋጨት ይቻላል። የሕዝባዊነት አስተሳሰብም እንዲሁ፣ እንደ ሃያኛው ክፍለዘመን በየአገሩ የፋሺዝምና የሶሻሊዝም አብዮት የማካሄድ ጉልበት የለውም። ግን፣ ሰዎችን በዘርና በብሄር ብሄረሰብ፣ በቋንቋና በቀዬ ሰበብ እያነሳሱና እያቧደኑ ማጋጨት ይቻላል። ይሄው ነው እየሆነ ያለው።
21ኛው ክፍለ ዘመን ከ20ኛው ክፍለዘመን በእጅጉ እንደሚለይ የሚገልፁት ሃቲንግተን፤ የብሄር ብሄረሰብና የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ጉዳይ ዋነኛ የፖለቲካ ጉዳይ ይሆናሉ በማለት ያስረዳሉ። ከዚህም በመነሳት ነው፤ በ21ኛው ክፍለዘመን የሃይማኖት አክራሪነት፣ አሸባሪነትና ግጭት እንደሚበራከት የተነበዩት። አልተበራከተም የሚል የለም። በደፈናው፣ የአለምን አዝማሚያ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ በአንድ የተለያዩ አገራት ምን አይነት ፈተና እንደሚጠብቃቸው ሃቲንግተን ተንብየዋል። ለምሳሌ፣ ሱዳን ከሰሜንና ከደቡብ ለሁለት እንደምትገነጠል ተናግረዋል። እንዳሉትም አልቀረም። ሃይማኖትና መንግስት ሊነጣጠሉ ይገባል በሚለው መርህ ለመቶ አመታት በተጓዘችው ቱርክ፣ የሃይማኖት ጉዳይ እንደገና እያቆጠቆጠ አገሪቱን እንደሚረብሻትም ሃቲንግተን ገልፀዋል። ይሄውና ሃይማኖትንና መንግስትን ለማዛመድ በሚፈልግ ፓርቲ አማካኝነት የአገሪቱ ቀውስ ተባብሷል። በአሜሪካና በአውሮፓ ላይ ከሚሰነዘረው የአሸባሪዎች ጥቃት በተጨማሪ፣ “የሱኒ ተከታይ፣ የሺዓ ተከታይ” በሚል ሰበብ ግጭቶች እየተፈጠሩ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስና ሌሎች በርካታ አገራት ችግር ውስጥ እንደሚገቡም ምሁሩ ተንብየዋል። ደግሞም እየሆነ ነው። ከመካከለኛው ምስራቅ የሚወጡ የየእለቱን ዜና በመስማት ማረጋገጥ ይቻላል።
ሁሉንም ለመዘርዘር ያስቸግራል። ግን፣ አንድ ሌላ ትንበያ ልጨምርላችሁ። ዩክሬን፣ ከብሄር ብሄረሰብና ከቋንቋ፣ ከሃይማኖትና ከባህል ጋር በተያያዘ ውዝግብ ለሁለት ልትሰነጠቅ እንደምትችል ሃቲንግተን ሲገልፁ፣ ክሬሚያ እና ምስራቃዊ የዩክሬን አካባቢ ወደ ራሺያ ሊጠቃለሉ እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ። ይህንን ያሉት ከዛሬ 18 አመት በፊት ነው።
በአጠቃላይ፤ ዋና ዋናዎቹ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የተዳከሙበት የዛሬው ዘመን፣ በጭፍን ስሜቶችና በተቀጣጣይ አደጋዎች የተከበበ፤ ብዙዎችን ግራ የሚያጋባ ዘመን ሆኗል።
መናኛ ፖለቲከኞች የሃይማኖትና የብሄር ብሄረሰብን ጉዳይ እያራገቡ ችግር ሲፈጥሩ፤ አለም የሚይዘውና የሚለቀው ጠፍቶበታል። በዩክሬን፣ እዚህ ግባ የማይባሉ ሁለት ቡድኖች አገሬውን ሲቀውጡ፣ የዩክሬን አንጋፋ ፖለቲከኞች ምን አደረጉ? ቀልባቸው የተገፈፈ አጃቢ ከመሆን የዘለለ ነገር አላደረጉም። አለምን መቶ ጊዜ የሚያጠፋ የኒኩሊዬር መሳሪያ የታጠቁት የራሺያ መሪዎችንም እዩዋቸው - በቁራሽ መሬት ነው የሚደነፉት - ቁምነገር ይመስል። መደገፍም ሆነ መቃወም አቅቷት “የሚመለከታቸው ወገኖች በውይይት ችግራቸውን ይፍቱ” ብለው ከሚንተባተቡት የቻይና ገዢዎችም የጠራ ነገር አታገኙም። ሌላው ይቅርና በስልጣኔ ደህና የተራመዱት ምዕራባዊያንስ ምን ፈየዱ? የዩክሬን ቀውስና የራሺያ ድርጊት፣ በአውሮፓ ትልቁ የ21ኛው ክፍለዘመን ቀውስ እንደሆነ የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
ግን፤ የአሜሪካና የአውሮፓ ባለስልጣናት ወዲህና ወዲያ ከመወራጨት ሌላ ምን አደረጉ? ቱ ራራሺያን አደብ ለማስገዛት የሚያስችል የአስተሳሰብ ፅናት ጠፍቶባቸው፤ የሚያደርጉትን ብቻ ሳይሆን የሚናገሩትን አጥተዋል። ከሁለት መልከ ጥፉ (ከራሺያና ከዩክሬን ‘ፋሺሽት’ ቡድኖች) አንዱን መምረጥ የቸገራቸው አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማትም፣ ጥርት ያለ ነገር አልያዙም። በአጠቃላይ፤ ዓለም የሶሪያን እልቂት በሩቁ ከመመልከት ውጭ ምንም ማድረግ እንዳልቻለው ሁሉ፤ በዩክሬን ጉዳይ ላይም እንዲሁ መያዣና መጨበጫ አላገኘለትም። መደናበር ብቻ!
ታዲያ የኢትዮጵያ መንግስትና ኢህአዴግ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ነገሩ ተደበላልቆባቸው ግራ ቢጋቡ ምን ይገርማል? እነሱን በጣም የሚያሳስባቸው፣ መንግስት በሕዝብ አመፅ ይወርዳል መባሉ ነው። ይሄ ተራ ነገር ነው። አሁን አለምን እየናጣት ያለው ቀውስ ጋር ሲነፃፀር፣ የአንድ መንግስት መውደቁና አለመውደቅ ኢምንት ነገር ነው። እጅግ አሳሳቢው ነገር፤ በየጊዜው የሚፈጠሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ አስተሳሰብ አለመኖሩ ነው። ከአመፅ አዙሪት የሚገላግልና ለዘላቂ የስልጣኔ ለውጥ የሚበጅ ጠንካራ አስተሳሰብ በአለማችን አለመኖሩ ነው። ደረጃውና መጠኑ ይለያይ እንጂ፤ በአለማችን የሰፈኑ ስርዓቶች በአብዛኛው በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ መስክ ቅሬታዎችና ችግሮች እየተደራረቡ እንዲከማቹ የሚያደርጉ ናቸው። ቅሬታና ችግር ተከማችቶ ምሬት ሲበዛ፣ አደባባይ ወጥቶ ከመጮህ ውጭ፣ ግልፅና ጤናማ መፍትሄ የለም። የአስተሳሰብ ኦና ሲፈጠር፤ በቦታው በብሄር ብሄረሰብና በቋንቋ፣ እንዲሁም በሃይማኖት ሰበብ የሚራገቡ መርዘኛ ስሜቶችን ለመከላከል የሚያስችል የስልጣኔ አስተሳሰብ የለም። መውጪያ የሌለው የትርምስ አዙሪት ነው የሚሆነው። ይሄ ነው ሊያሳስበን የሚገባው።
ያለ ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ አስተማማኝ መፍትሄ ማግኘት ባይቻልም፤ ለጊዜው ጠንቀቅ ማለት ጥሩ ነው። አንደኛ፤ በዋጋ ንረትና በታክስ ጫና፣ አልያም በአላስፈላጊ የሕግ ገደቦችና የቢሮክራሲ ቁጥጥሮች ኢኮኖሚን ላለማዳከም በእጅጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አለበለዚያ መዘዙን አንችለውም። ሁለተኛ፣ ጓዳና አደባባዩን ካልተቆጣጠርኩ ብሎ ዜጎችን መውጪያ መግቢያ ከማሳጣት፣ እንዲሁም በትንሽ በትልቁ ንትርክና ፍጥጫ ከመፍጠር ቆጠብ ብሎ፤ በፖለቲካውም ሆነ በፍትህ መስኮች ያለ ማቋረጥ የመሻሻል ምልክቶች እንዲታዩ መትጋት ያስፈልጋል። ሶስተኛ፡ የብሔር ብሔረሰብና የቋንቋ ጉዳዮችን ከማራገብ መቆጠብ ነው። አራተኛ፡ የሐይማኖት ጉዳይ ከፖለቲካ ጋር እንዳይቆራኝ በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል።    


Read 4474 times
Administrator

Latest from Administrator