Saturday, 22 March 2014 12:40

የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ቅጥር ዘግይቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

          የዋልያዎቹን  ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተከተለው የአሰራር ሂደት ከዓለም አቀፍ ልምዶች አንፃር እንደዘገየ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በብዙ የዓለም አገራት የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኞች ቅጥር ቢያንስ በ4 ቢበዛ በ5 ሳምንታት ውስጥ የሚፈፀም ቢሆንም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚሆን ዋና አሰልጣኝ አፈላልጎ ለመቅጠር እስካሁን 8 ሳምንታት ቢያልፉም ሂደቱ አልተጠናቀቀም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለዋና አሰልጣኙ ቅጥር  ካወጣው ማስታወቂያ  በኋላ ለሁለት ሳምንት   ምዝገባ ተካሂዶ ከመላው ዓለም 27 አሰልጣኞች ያመለከቱ ሲሆን የስም ዝርዝራቸውና ዜግነታቸው ከሳምንት በፊት ታውቋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በመስፈርቶቹ 27ቱን አሰልጣኞች በማወዳደር ሲሰራ 1 ሳምንት ያለፈው ሲሆን የመጨረሻ እጩዎችን  ማንነትና ብዛታቸውን አልገለፀም፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚረከበው አዲሱ አሰልጣኝ መቼ  እንደሚታወቅ ፤  የቅጥሩ  ውል እንዴት እና መቼ እንደሚፈፀም፤ ለምን ያህል ግዜ በሃላፊነቱ እንደሚቆይ፤ ምን ያህል ወርሃዊ ደሞዝ እንደሚከፈለውና ፌደሬሽኑ ክፍያውን እንዴት ሊከፍል እንዳሰበም በይፋ የታወቀ ነገር የለም፡፡
የፌደሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ከሳምንት በፊት ለመገናኛ ብዙሃናት በላከው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ፍላጎት ያሳዩ አሰልጣኞች ከመላው ዓለም ከሚገኙ 15 አገራት የተሰባሰቡ ናቸው ፡፡  ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከቤልጅዬም፣ከቱርክ፣ ከቦስኒያ፣ ከስፔን እና ከቡልጋርያ ከእያንዳንዳቸው አንድ አሰልጣኝ፤ ከጣሊያን፣ከኢትዮጵያ፣ ከስዊድን፣ ከሆላንድ፣ ከሰርቢያ፣ ከፖርቱጋል፣ ከብራዚል እና ከሮማኒያ ከእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት አሰልጣኞች እንዲሁም ከአርጀንቲና ሶስት አሰልጣኞች አመልክተዋል፡፡ እነዚህ አመልካች 27  አሰልጣኞች  በቅጥሩ ለመወዳደር ለፌደሬሽኑ ያስገቡት የስራ ልምድ እና ብቃትን በዝርዝር ባይገለፅም በእግር ኳስ ዙርያ መረጃ በሚገኝባቸው ድረገፆች ስለ ስራ ታሪካቸው ብዙ እውቅና ያላቸው ገሚሱ ናቸው፡፡  ስለ አሰልጣኞቹ መረጃ ማግኘት የተቻለው አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ከመስራታቸው በተያያዘ፤ አንዳንዶቹ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ስላላቸው የስራ ልምድ በተለያዩ ድረገፆች ግለታሪካቸው ተፅፎ በመገኘቱ ነው፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ክለቦችን በማሰልጠን ልምድ ኖሯቸው ለዋናው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ማመልከቻ ያስገቡት የደደደቢት አሰልጣኝ የነበሩት የቱርኩ ሜሜት ታይፉን እና አሁን የመብራት ኃይል ክለብ አሰልጣኝ ሆነው የሚሰሩት የቡልጋርያው ሎርዳን ስቶይኮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን አሰልጥነው የሚያውቁት እና በድጋሚ ቡድኑን ለመረከብ ያመለከቱት ደግሞ የጣሊያኑ ዲያጎ ጋርዚያቶ እና የቤልጅዬሙ ቶም ሴንትፌይት ናቸው፡፡ ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌይት ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ቅጥር ሳይፈፀምላቸው ለሙከራ እንዳሰለጠኑ የሚታወስ ሲሆን አሁን ብሄራዊ ቡድኑን ለመረከብ ከሁሉም ቀድመው ፍላጎታቸውን በሱፕር ስፖርት በመግለፅ የሚጠቀሱ ሆነዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት መግለጫ  እንዳመለከተው የቅጥር ማመልከቻቸውን ካቀረቡት 27 እጩ አሰልጣኞች መካከል ኢትዮጵያዊያን የሆኑት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ከ3 የውድድር ዘመናት  በፊት በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አሰልጣኝነት  የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው እና አሁን በሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሼንዲ በረዳት አሰልጣኝነት በመስራት ላይ የሚገኘው ውበቱ አባተ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ አስቀድሞ በስኮትላንዳዊው ኢፌም ኦኑራ የዋና አሰልጣኝነት ዘመን  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የፉትቦል ዲያሬክተር ሆኖ የሰራውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የአሰልጣኝነት ትምህርት የተከታተለው ዮሃንስ ተሰማ ናቸው፡፡  በአውሮፓ ታዋቂ ክለቦች ተሰልፈው ውጤታማ ከመሆን አልፈው በአውሮፓ፣ በአፍሪካና፣ በእስያ የሚገኙ ብሔራዊና ወጣት ቡድኖችን እንዲሁም ክለቦችን በማሰልጠን ለሻምፒዮንነት ክብር የበቁ ሙያተኞች  እንዳመለከቱ የገለፀው የፌደሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ፤ ብሄራዊ ቡድኑን ተረክቦ ለውጤት ለማብቃት ያላቸውን ፍላጎት በተለያያ መንገድ መግለፃቸው የሚያበረታታ ነው ብሏል፡፡ ከእጩ አሰልጣኞቹ መካከል ከ30 ዓመታት በላይ የማሰልጠን ልምድ ያላቸው፤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ እንደሚገኙበት የተገለፀ ሲሆን የጥቂቶቹ የትምህርት ዝግጅት በዲፕሎማ ከመወሰኑ በስተቀር አብዛኞቹ ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ ያላቸው፤ በአውሮፓው እግር ኳስ ማህበር የመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኝነት ብቃት ማረጋገጫ የያዙና የፕሮፌሰርና የኢንስትራክተርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሙያተኞች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡  
የእግር ኳስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን  ባለፈው 2 ዓመት ከ6 ወር በዋና አሰልጣኝነት የመሩትን ሰውነት ቢሻው  በተሻለ ለመተካትና ለውጥ ለመፍጠር በሚል ካሰናበተ ሁለት ወር ቢሆነውም በምትክነት ለመቀጠር ማመልከቻ ካስገቡት 27 አሰልጣኞች በስራ ልምዳቸው አለመሻላቸውን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ፤ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ለሚደረገው የመጨረሻ ማጣርያ ምእራፍ ለመገባት ከበቁ 10 የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ለመሆን የበቃ፤ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን ውድድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈ፤ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከዓመቱ ምርጥ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በሃላፊነት ለመረከብ ካመለከቱት 27ቱ አሰልጣኞች መካከል ስፖርት አድማስ የተወሰኑትን ለማስተዋወቅ ከዚህ በታች ያለውን አጭር መግለጫ አቅርቧል፡፡ እነዚህን አስር 10 አሰልጣኞች ለስፖርት አፍቃሪው ማስተዋወቅ የተቻለው ስለባለሙያዎቹ የሚገልፁ በቂ መረጃዎችን በተለያዩ ድረገፆች  በማፈላለግ ማግኘት ስለተቻለ ነው፡፡


ፋቢዮ ሎፔዝ የ50 ዓመት ጣሊያናዊ ናቸው። በትልልቆቹ የጣሊያን ሴሪኤ ክለቦች አትላንታና ፌዬሬንቲና በአማካሪነት አገልግለዋል፡፡ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለ6 የውድድር ዘመናት ከ6 በላይ የዝቅተኛ ሊግ ክለቦችን ያሰለጠኑ ሲሆን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ብዙም ልምድ የላቸውም፡፡


ሃንስ ሚሸል እድሜያቸው 49  ሲሆን በዜግነታቸው ጀርመናዊ ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ግብ ጠባቂ ነበሩ፡፡ ከ2001 እ.ኤ.አ ጀምሮ ወደ ማሰልጠን ስራ ገብተዋል፡፡ በአሰልጣኝነት ስራ ዘመናቸው በቻይና ሀ-20 ቡድን ረዳት አሰልጣኝ፣ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለ3 ዓመት በሩዋንዳ  እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዲያሬክተር፣ በ2011 የፊልፒንስ ሀ-25 ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ አድገው ባለፉት 3 ዓመታት ደግሞ የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ በስፖርት ሳይንስና በማኔጅመንት ባችለር ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በታላላቆቹ የዓለማችን ክለቦች ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል፣ ካይዘስላውተርን፤ ሪቨር ፕሌት ሌሎችም  በአሰልጣኝነት የስራ ልምምድ በመስራት አስደናቂ ልምድ አላቸው፡፡ዲያጐ ጋርዚያቶ በትውልድ ፈረንሳዊ ቢሆኑም በዜግነት ጣሊያናዊ ናቸው፡፡ አሁን የ64 ዓመት አዛውንት የሆኑት እኝህ አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመናቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ ከ1984 እ.ኤ.አ ጀምሮ በአሰልጣኝነት ማገልገል ሲጀምሩ የፈረንሳይ ዝቅተኛ ሊግ ክለቦችን ሲያሰለጥኑ ቆይተው ትልቁን ኃላፊነት የተረከቡት በ2001 እ.ኤ.አ ላይ የኢትዮጵያ ሀ 20 ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሲመደቡ ነበር። በዚሁ ጊዜም የኢትዮጵያን ወጣት ቡድን በአርጀንቲና ለተደረገው 14ኛው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ እንዲሳተፍ አብቅተዋል። የኢትዮጵያ ሀ-20 ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ከለቀቁ በኋላ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በክለብ ደረጃ ሲሰሩ ቆይተው በ2007 እ.ኤ.አ ላይ የቶጐ ብሔራዊ ቡድን ተረክበው ነበር፡፡ በቶጎ አሰልጣኝነት የቆዩት ግን ለ2 ወራት የስራ ጊዜ ነበር፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ትልቅ ውጤት በማስመዝገብ የተደነቁ ሲሆን ለሁለት ጊዜያት ያሰለጠኑትን የዲ ሪፖብሊክ ኮንጎውን ቲፒ ማዜምቤ  በ2009 እ.ኤ.አ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ እንዲያሸንፍ አድርገዋል፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮትጵያ ተመልሰው በነበረ ጊዜ ዋና ብሔራዊ ቡድኑን በሃላፊነት ቢይዙም በአወዛጋቢ ሁኔታዎች ቢይዙም ከ2 ወራት በኋላ ተሰናብተዋል፡፡ኤርኒስት ብራንድተስ የ58 ዓመቱ ሆላንዳዊ በተጨዋችነት ዘመናቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ በሆላንድ ብሔራዊ ቡድን ከ1977 -85 እኤአ በመጫወት ልምድ ከማግኘታቸውም በላይ በ1978 እ.ኤ.አ ላይ አርጀንቲና ባስተናገደችው ዓለም ዋንጫ ለመጫወት የበቁ ናቸው፡፡ ከ1993 እ.ኤ.አ ወዲህ በአሰልጣኝነት ማገልገል የጀመሩ ሲሆን በተለይ በትልቁ የሆላንድ ክለብ ፒኤስቪ አይንድሆቨን በረዳት አሰልጣኝነት ለ9 ዓመታት ሰርተዋል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የተወሰነ የስራ ልምድ ያላቸው ሲሆን ለ2 ዓመታት የሩዋንዳውን ክለብ ኤፒአር ካሰለጠኑ በኋላ ባለፈው ዓመት ደግሞ የታንዛኒያው ክለብ ያንግ አፍሪካንስ አሰልጥነው ነበር፡፡


ዞራን ፍሊፖቪች የ69 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ከሚጠቀስ ታሪካቸው ከ1970-78 በዩጎዝላቪያ ብሄራዊ ቡድን የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ሆነው ማሳለፋቸው ነው። በአሰልጣኝነት ስራ የጀመሩት በ1988 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሲሆን ለ2 ዓመት የፖርቱጋሊ ትልቅ ክለብ ቤነፊካ አሰልጣኝ ሆነው ከመስራታቸው በላይ በ1999 እኤአ በጣሊያኑ ክለብ ሳምፕዶርያም አገልግለዋል።  ከዚያም ተጫውተው ወዳሳለፉበት ታዋቂው ክለብ ስታር ቤልግሬድ በመመለስ ለ3 ዓመት በአሰልጣኝነት አገልግለው በ2007 እ.ኤ.አ  የሞንቴኔግሮ ቡድንን በመምራት  ለ2 ዓመት አገልገለው ከዚያ ወዲህ  ስራፈት ናቸው፡፡

ጐራን ስቴቫኖቪች የ47 ዓመቱ ሰርቢያዊ በተጨዋችነት ዘመናቸው የአማካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ ከ1983 ጀምሮ ለስምንት አታመት ለፓርቴዝያን ቤልግሬድ የተጫወቱ ሲሆን በ1985 እ.ኤ.አ የዩጐዝላቪያ ብሔራዊ ቡድን አባል ነበሩ፡፡ ከ2001 እ.ኤ.አ ወዲህ በአሰልጣኝነት መስራት ጀምረው ከ2003-2006 እ.ኤ.አ የሰርቢያና ሞንቴኔግሮ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ካገለገሉ በኋላ በ2009 እ.ኤ.አ ላይ በቀድሞ ክለባቸው ፓርቴዝያን ቤልግሬድ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ተቀጥረዋል፡፡ በ2013 ደግሞ በዚሁ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአፍሪካ ልምድ ያላቸው ሲሆን በ2011 እ.ኤ.አ ላይ የጋና ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን በደቡብ አፍሪካ በተደረገው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈዋል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የቻይና ሱፕር ሊግ ክለብ በሃላፊነት ተረከበው የነበረ ቢሆንም ክለቡ ወደ ዝቅተኛ ሊግ በመውረዱ ተሰናብተው ያለፉትን ወራት ያለ ስራ ቆይተዋል፡፡


ስቴፈን ኮንስታንቲን የ51 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ከ1994 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለአሰልጣኝነት እየሰሩ ናቸው፡፡ 4 ብሔራዊ ቡድኖችን ለማሰልጠን ከሌሎቹ አመልካቾች የላቀ ልምድ ያላቸው ሲሆን  በ1999 እ.ኤ.አ ለሁለት ዓመት ኔፓልን፣ ከ2003 ጀምሮ ለ3 ዓመታት ህንድን፣ ከ2007 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ማላዊን እንዲሁም በ2011 የሱዳን ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት መርተዋል፡፡ በአሰልጣኝነት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሮፌሽናል ፍቃድ ያላቸው ሲሆን በስነልቦና እና በአካል ብቃት ስልጠና ምርጥ ተብለው ሁለት ጊዜ የተሸለሙ፤ በምግብ ሳይንስ ዲፕሎማ ያላቸው እና የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ተብለው በፊፋ እውቅና ያላቸው ኢንስትራክተር ናቸው፡፡

Read 1269 times