Monday, 31 March 2014 10:57

የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ኃላፊ ከሥልጣናቸው ተነሡ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(3 votes)

የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩት ወ/ሮ አማረች በቃሉ፤ከቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ የቤት ኪራይ ውል አፈፃፀም ጋር በተገናኘ በተፈጠረ የሥራ ዝርክርክነት  ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ ምንጮች ጠቆሙ፡፡
መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፃፈ ደብዳቤ ሃላፊዋ፣ በአሰራር ዝርክርክነት ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ የጠቆሙት ምንጮች፤በዝርክርክነት ተብሎ የተጠቀሰውም የቀድሞ ፕሬዚዳንት የቤት ኪራይ ውል አፈፃፀም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ አማረች ግን ይሄን አይቀበሉም፡፡ ጉዳዩ በኢህአዴግ የተለመደ የስራ ዝውውር እንጂ የአሠራር ዝርክርክነትም ሆነ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጉዳይን የተመለከተ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፤ ከአንድ ወር በፊት በፅ/ቤቱ በተደረገ ግምገማ በጽ/ቤቱ የአመራር፣ የአስተዳደርና  የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዝርክርክነት እንዳለ የተጠቀሰ ሲሆን ወ/ሮ አማረችም በተመሳሳይ ጉዳይ ተገምግመዋል፡፡
ከግምገማው ጋር ግንኙነት እንዳለው ባይታወቅም አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባለፈው ጥር ወር ላይ በፃፉት ደብዳቤ፤ የፅ/ቤቱ ሃላፊ ወ/ሮ አማረች በቃሉ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱላቸው ጠይቀው እንደነበር ምንጮች አስታውሰው፤ ሃላፊዋ ላለፉት ሶስት ወራት በሥራቸው ላይ ቆይተው በዚህ ወር ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ ገልፀዋል፡፡
ከሃላፊነታቸው በተነሱት ወ/ሮ አማረች በቃሉ ምትክም የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩት አቶ ብሩክ ግዛው የተሾሙ ሲሆን ስለአዲሱ ኃላፊነታቸው የጠይቀናቸው አቶ ብሩክ፣መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አሁን የተከራዩትን መኖርያ ቤት አፈላልጎ ያገኘላቸው የኮሚሽን ሰራተኛ፣በውሉ መሰረት ክፍያ አልተፈፀመልኝም በማለት በፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት፣ በፕሬዚዳንቱና በልጃቸው ላይ ክስ መመስረቱ የሚታወቅ ሲሆን መጀመርያ ላይ ቤት ያከራየው ግለሰብም ከፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት የ2.1 ሚ ብር ካሣ እንዲከፈለው የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በማስገባት ቀጣዩ እርምጃ ክስ መመስረት እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ምንጮች እንደሚሉት፤ ይሄ ሁሉ ችግር የተፈጠረው በፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት የአመራርና አስተዳደር እንዝላልነት ሲሆን የሃላፊዋ መነሳትም ከዚህ ጋር በቀጥታ የተገናኘ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

Read 4206 times