Print this page
Monday, 31 March 2014 11:12

የኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ልጅ በእንግሊዝ መነጋገሪያ ሆኗል

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(16 votes)

ዴቪድ ካሜሮንን ጨምሮ 19 የእንግሊዝ ጠ/ ሚኒስትሮች የተማሩበት ታዋቂ ኮሌጅ ይገባል “ፖለቲከኛ ለመሆን የግድ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የለብኝም!…” - ልጁ
“ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን አንጸባራቂ ኮከብ እንደሚሆን አምናለሁ!” - መምህሩ

በአገረ እንግሊዝ ያጡ የነጡ ድሆች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች አንዷ ናት - ኒውሃም፡፡
እዚህ ግባ የሚባል ገቢ የሌላቸውና ከመንግስት በሚያገኙት ድጎማ ከእጅ ወደአፍ ኑሮን የሚገፉ ድሃ ዜጎችና ስደተኞች የከተሙባት የምስራቅ ለንደኗ ኒውሃም፣ ከሰሞኑ የበርካታ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን የዜና ርዕስ ሆናለች፡፡
የድሆች መንደር ኒውሃም፣ በአንድ ልጇ ስሟ ተደጋግሞ ተጠራ። ነገ ከነገ ወዲያ የኒውሃምና የድሃ ነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን፣ የመላ እንግሊዝ ተስፋ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት የተሰጠው ይህ ልጅ፣ ይስሃቅ አይሪስ ይባላል፡፡ ይስሃቅ አሁን፣ የመንግስት ተረጂ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወላጆቹ የአቶ አባተ እና የወ/ሮ በቀለች ብቻ ሳይሆን የኒውሃም ብሎም የእንግሊዝ ልጅ ነው፡፡ ከሰሞኑ ስለይስሃቅ የተሰማው ወሬ፣ ለወላጆቹ ብቻ አይደለም የምስራችነቱ - ለመላ ኒውሃም ነዋሪዎች ጭምር እንጂ፡፡  
“የኒውሃሙ ይስሃቅ፣ የኤተን ኮሌጅ ተማሪ ሊሆን ነው!” ሲሉ ዘገቡ፣ እነ ቢቢሲና ዘ ጋርዲያን፡፡
ከኒውሃም ድሆች መካከል የሚኖረው ይስሃቅ፣ የሞላላቸው የእንግሊዝ ባለጸጎችና ታላላቅ የአገሪቱ መሪዎች ተመርጠው ወደሚገቡበት ቅጽር ግቢ ይገባ ዘንድ ተጠራ፡፡ በመንግስት ድጎማ ከሚተዳደር እዚህ ግባ የማባይል ተራ ትምህርት ቤት ወጥቶ፣ በአገረ እንግሊዝ ዝናቸው ከናኘ ኮሌጆች አንዱ ወደሆነው ታዋቂው ኤተን ኮሌጅ ሊገባ ነው፡፡
“ታዲያ ኮሌጅ መግባት አዲስ ነገር ነው እንዴ!?... የልጁ ኮሌጅ መግባት ዜናነቱ ምን ላይ ነው!?” የሚል ጥያቄ የሚሰነዝር አንባቢ፣ እሱ ልጁንም ኤተንንም በቅጡ የማያውቅ ሊሆን ይችላልና አይፈረድበትም።
ልጁ ይስሃቅ ነው፡፡ ከኒውሃም ድሆች መካከል በመንግስት ድጎማ ኑሯቸውን የሚገፉ የስደተኛ ኢትዮጵያውያን ወላጆች የአብራክ ክፋይ። በመንግስት ድጎማ በሚተዳደር እዚህ ግባ የማባይል የማህበረሰብ ትምህርት ቤት የሚማር ያልተመቸው ብላቴና፡፡ ግማሽ ያህሉ ተማሪዎች፣ ከመንግስት የሚሰፈርላቸውን የእለት ቀለብ እየተመገቡ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ቀለም ሲቆጥር የሚውል ያልደላው ተማሪ፡፡
ኮሌጁ ደግሞ ኤተን ነው፡፡ ኤተን ዝም ብሎ ኮሌጅ አይደለም። እንኳን በመንግስት ድጎማ ለሚተዳደሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን፣ ለሞላላቸው እንግሊዛውያን ወላጆችም ልጅን ከፍሎ ለማስተማር የሚያዳግት ውድ ኮሌጅ፡፡ የተመረጡ ተማሪዎች የሚገቡበት፣ የላቁ ተመራቂዎች የሚወጡበት ዝነኛ ግቢ ነው - ኤተን፡፡ እንግሊዝ የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትሯን ዴቪድ ካሜሮንን ጨምሮ፣ 19 ጠቅላይ ሚኒስትሮቿን ያገኘችው ከዚህ የተከበረ የልሂቃን አጸድ ውስጥ ነው፡፡
የድሃው ልጅ ይስሃቅ፣ በመንግስት ድጎማ ከሚተዳደር እዚህ ግባ የማባይል ተራ ትምህርት ቤት ወጥቶ፣ በአገረ እንግሊዝ ዝናቸው ከናኘ ኮሌጆች አንዱ ወደሆነው ታዋቂው ኤተን ኮሌጅ የመግባት ዕድል ማግኘቱ ነው፣ ነገርዬውን የእነ ዘጋርዲያን ትልቅ ወሬ ያደረገው፡፡
አንድ ዕለት…
ተማሪው ይስሃቅና የፎሬስት ጌት ትምህርት ቤት መምህሩ ሲሞን ኢሊየት፣ ያችን የለመዷትን የምሳ ሰዓት ወግ ጀመሩ፡፡ ይስሃቅና መምህር ሲሞን በኢራቅ ስላለው ጦርነት ማውራት ከጀመሩ አንድ ወር ያህል ሆኗቸዋል፡፡ መምህሩ የተማሪያቸውን ዝንባሌ ተረድተዋል፡፡ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደሚመስጡት ልብ ብለዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአለማቀፋዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያነሳላቸው ጥያቄዎች፣ በውስጡ ያለውን እምቅ ስሜት ፍንትው አድርጎ አሳይቷቸዋል፡፡ ከፎሬስት ጌት የተሻለ ትምህርት ቢያገኝ፣ ጥሩ ፖለቲከኛ እንደሚወጣው ተሰምቷቸዋል፡፡ ለዚህ ነው መምህሩ ለተማሪያቸው አንዲት ሃሳብ የሰነዘሩለት፡፡
“እኔ እምልህ ይስሃቅ፣ ለምን ግን ለኤተን ኮሌጅ አመልክተህ ነጻ የትምህርት እድል ለማግኘት አትሞክርም?” ነበር ያሉት መምህሩ። እውነቱን ለመናገር ይስሃቅ፣ እስከዚያች ቅጽበት ድረስ ኤተን ስለሚባለው ኮሌጅ እምብዛም የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ይስሃቅ መምህሩ ያቀረቡለትን ሃሳብ እንደዋዛ ችላ ብሎ አላለፈውም፡፡ ስለ ጉዳዩ ያማከራቸው አባቱ አቶ አባተ “በርታ” ሲሉ አበረታቱት፡፡
ይስሃቅ እንደተባለው በረታ፡፡ የነጻ የትምህርት እድል ማመልከቻውን ወደ ኤተን ሰደደ፡፡ ይህ እድለኛ ብላቴና፣ ለታዋቂው ኤተን ኮሌጅ ያስገባው ማመልከቻ ተቀባይነት አግኝቶ ለቃለ መጠይቅ ተጠራ፡፡ ከትምህርት ቤቱ መልማይ ባለሙያዎች ጋር ተገናኘ፡፡ በተደረጉለት ተደጋጋሚ ቃለ መጠይቆች የመዛኞቹን ቀልብ መግዛት የቻለው ይህ ተማሪ፣ በስተመጨረሻም ያንን የተከበረ ግቢ አልፎ ይገባ ዘንድ ተመረጠ፡፡ በኮሌጁ የሁለት አመታት ነጻ የትምህርት እድል ተሰጠው፡፡
አሁን የዚህ ታላቅ ግቢ በር ከባለጸጋ ላልተወለደው ብላቴናም ወለል ብሎ ተከፍቷል፡፡ የስደተኞቹ ኢትዮጵያውያን ወላጆች የአቶ አባተ እና የወ/ሮ በቀለች የአብራክ ክፋይ የሆነው ይስሃቅ፣ ከሰሞኑ 76ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ የሚገመት ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ኤተን ለማምራት ጓዙን እየሸከፈ ነው፡፡
መስከረም ላይ ይስሃቅ ከዚያች የድሆች መኖሪያ መንደር ከኒውሃም ወጥቶ የቴምስን ወንዝ ተሻግሮ ተጓዥ ነው - ወደ ኤተን ኮሌጅ ቅጽር ግቢ፡፡ ኤ ሌቭል በተባለው ደረጃ የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የሂሳብ፣ የፍልስፍናና የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን መከታተል ወደሚጀምርበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም፡፡
ለይስሃቅ ነገ እንደ ትናንት አይሆንም፡፡
የአገሪቱ መንግስት ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት እድል ተጠቃሚነት በሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ በሚተዳደረው የፎሬስት ጌት የማህበረሰብ ትምህርት ቤት ነበር፣ ትምህርቱን ሲከታተል የኖረው፡፡ እንደማንኛውም የኒውሃም ነዋሪ ልጆች፣ እዚህ ግባ የማይባል ትምህርት ነበር የሚማረው - ከክፍል ጓደኞቹ ከእነ ኢርፋንና አሌክሲስ ጋር፡፡
ይስሃቅ አይሪስ አሁን አርቆ ማየት ጀምሯል፡፡ ከፊት ለፊቱ አንድ ሰፊ መንገድ ይታየዋል - ወደ ኤተን ኮሌጅ የሚያመራ፣ ከዚያም ወደ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚያቀና፡፡ የነገ ህልሙ ይሄን መንገድ ተከትሎ መጓዝና ተገቢውን ትምህርት ተከታትሎ ሲጨርስ በፖለቲካው መስክ መሰማራት ነው፡፡
“በኤተን ኮሌጅ ለሁለት አመታት የሚሰጠኝን ትምህርት ካጠናቀቅኩ በኋላ፣ ወደ ኒውሃም ከመመለሴና በፖለቲካው መስክ ከመሰማራቴና ምናልባትም በገለልተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩነት ከመወዳደሬ በፊት፣ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ፖለቲካ ወይም ታሪክ ማጥናት እፈልጋለሁ፡፡ ለእኔ የሌበር ፓርቲ ፖለቲከኞችና ወግ አጥባቂዎች ላይ ላዩን ሲታዩ ለየቅል ይምሰሉ እንጂ፣ ጀርባቸው ሲፈተሸ አንድ ናቸው፡፡ ኦክስፎርድ የምገባው ፖለቲካ ተምሬ ለመውጣትና እንደማንኛውም ፖለቲከኛ የተለመደውን ስራ ለመስራት አይደለም፡፡ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ነው የምፈልገው፡፡” ብሏል ይስሃቅ፡፡
የይስሃቅ የትምህርት ዕድል፣ ህይወቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንደሚያመራትና የሆነ ጊዜ ላይ ስማቸው ከሚጠራ ታላላቅ እንግሊዛውያን አንዱ እንደሚያደርገው ብዙዎች ግምታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ትልቅ ተስፋ እንደሚጠብቀውም ይተነብያሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ፣ በ1440 ከተመሰረተው ከዚህ ታዋቂ ኮሌጅ ተመርቀው የሚወጡ ብዙዎች በተሰማሩበት የሙያ መስክ እውቅና ማግኘታቸው  ነው፡፡
“በምኖርበት የኒውሃም ማህበረሰብ ውስጥ፣ አደንዛዥ እጾችና የወንጀል ድርጊቶች ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው የሚገኙት፡፡ ወላጆቼ ከመንግስት በሚደረግላቸው ድጋፍና ጥቅማጥቅሞች ነው የሚኖሩት። ይሄም ሆኖ ግን፣ ድህነቱ እንዳለ ሆኖ ኒውሃምን እንደቤቴ ነው የማያት። ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ተከታትዬ ከጨረስኩ በኋላ፣ ተመልሼ ወደ ኒውሃም እመጣለሁ፡፡ ከዚያም ቀሪ ህይወቴን የኒውሃምን የኑሮ  ሁኔታ በማሻሻል ስራ ላይ ተሰማርቼ እገፋለሁ፡፡” ይላል ይስሃቅ ስለወደፊት እቅዱ ሲናገር፡፡
ይስሃቅ ያገኘው የትምህርት ዕድል ለወላጆቹ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል፡፡
“አባቴ በህይወት ዘመኑ ተሳክተው ማየት የሚፈልጋቸው ሁለት ህልሞች እንዳሉት ይናገር ነበር፡፡ የመጀመሪያው ወደ እንግሊዝ መምጣት ነበር፡፡ ሁለተኛው ህልሙ ደግሞ፣ ልጁ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተማሩበት ኮሌጅ ሲማር ማየት ነበር፡፡ አሁን ሁለቱም ህልሞቹ እውን ሆነውለታል” ብሏል- ይስሃቅ፡፡
እርግጥም አቶ አባተ ሁለት ህልሞች ነበሯቸው፡፡ የ17 አመት ወጣት ሆነው ነው ከአገራቸው ኢትዮጵያ በመነሳት ውጣ ውረድ የበዛበትን የስደት ጎዳና ተከትለው ጉዞ የጀመሩት፡፡ ካይሮ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ነጻ የትምህርት እድል ለማግኘት ደጋግመው ሞክረው፣ በሶስተኛው ተሳክቶላቸው ግብጽ የገቡት አባቱ፣ ህልማቸው የእንግሊዝን ምድር መርገጥ ነበር፡፡ ይህ ህልማቸው እውን ከሆነ ከሃያ አመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ የጤናቸው ጉዳይ አላሰራ ብሏቸው እስካቋረጡበት ጊዜ ድረስ፣ በእንክብካቤ ሰጪነት ተቀጥረው ሲሰሩ ነው የኖሩት፡፡ ሁለተኛው ህልማቸው ደግሞ፣ እዚያው እንግሊዝ ከገቡ በኋላ ካገኟት የትዳር አጋራቸው ከወ/ሮ በቀለች የወለዱት ልጃቸው ይስሃቅ፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተማሩበት ትምህርት ቤት ሲማር ማየት ነበር - ከሰሞኑም ይሄው ህልማቸው እውን ሆነ፡፡
“ለኤተን ኮሌጅ የነጻ የትምህርት ዕድል ማመልከቻ ሊያስገባ ማሰቡን ሲያማክረኝ በደስታ ነበር የተቀበልኩት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ እንዳሰበው ኮሌጁ ማመልከቻውን ተቀብሎ የትምህርት ዕድል ባይሰጠው፣ ልጄ ይከፋብኝ ይሆን ብዬ መስጋቴ አልቀረም” ብለዋል አባትዬው በወቅቱ ስለነበረው ነገር ለዘጋርዲያን ሲናገሩ፡፡ እናቱ ወ/ሮ በቀለች በበኩላቸው፣ ይስሃቅ ልዩ ተሰጥኦ የታደለ ብስል ልጅ ነው ሲሉ ይመሰክሩለታል፡፡
ይስሃቅ ግን እናቱ እንዳሉት እርግጥም የተለየ ብቃት የታደለና ተጋንኖ የሚነገርለት ልጅ አለመሆኑን ነው የሚናገረው፡፡ “እውነቱን ለመናገር፣ የላቀ አእምሮ አለው ተብሎ ያን ያህል ተጋንኖ የሚወራልኝ ሰው አይደለሁም፡፡ በትምህርቴም መካከለኛ ውጤት ነበር የማመጣው። ያም ሆኖ ግን ለንባብ የተለየ ፍቅር አለኝ፡፡ በተለይ መምህሬ ስለ ኤተን ኮሌጅ ከነገሩኝ በኋላ ደግሞ፣ ልቦለድ ያልሆኑና በታሪክ፣ በወቅታዊ ጉዳዮችና በፖለቲካ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሃፍትን ማንበብ ጀምሬያለሁ” በማለት፡፡
“አንዳንድ ጋዜጦች፣ ‘በመንግስት ድጎማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ልጅ፣ ወደ ኤተን ሊገባ ነው’ የሚል ዘገባ አሰራጭተዋል፡፡ እኔ እንደማስበው ግን፣ ወደዚህ ኮሌጅ የመግባት ዕድል ያገኘሁት በድጎማ የሚኖሩ ስደተኛ ወላጆች ልጅ ከመሆኔ ጋር ተያይዞ በተደረገልኝ ልዩ ድጋፍ ወይም ቅድሚያ በማግኘት  አይደለም፡፡ ኮሌጁ ባደረገልኝ ቃለ መጠይቆችና በተሰጡኝ ፈተናዎች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ በመቻሌ እንጂ!” ብሏል ይስሃቅ ስኬቱ በጥረት እንጂ በችሮታ የተገኘ አለመሆኑን ሲናገር፡፡
ከዚህ ቀደም የተከታተለው ትምህርት እምብዛም ጥራት ያለው አለመሆኑ፣ በኤተን ኮሌጅ ከሚገጥሙት የላቁ  ተማሪዎች ጋር ተወዳድሮ ውጤታማ እንዳይሆን እክል ይፈጥርበት እንደሆን የተጠየቀው ይስሃቅ፣ በፍጹም ሲል ነበር ምላሹን የሰጠው፡፡
“በእነሱና በእኔ መካከል ያለው ብቸኛ ልዩነት ያደግንበት ማህበረሰብ በውስጣችን የራስ መተማመን ስሜት በማስረጽ ረገድ የሚከተለው አካሄድ ነው፡፡ እነሱ ገና ከልጅነታቸው ጀምረው የፈለጉትን ነገር የማሳካት ብቃት እንዳላቸው እየተነገራቸው ነው ያደጉት፡፡ ወደኤተን ሲገቡም ስኬታማ ሆነው እንደሚወጡ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የላቸውም፡፡ እኔ ባደግሁባት ኒውሃም ግን እንዲህ አይነት አስተዳደግ የለም፡፡ ስኬታማ የመሆን ብቃት እንዳለህ ሳይነገርህና በራስ የመተማመን ስሜት ሳታጎለብት ነው የምታድገው፡፡ እኔን ለዚህ ደረጃ ያበቃኝ መምህሬ ሲሞን ኢሊየት ያደረጉልኝ ማበረታታትና ድጋፍ ነው” ብሏል ይስሃቅ፡፡  
ጋዜጠኞቹ እንዳሉት፣ እርግጥም በኤተን ኮሌጅ ለመማር ከሌሎች የተሻሉ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎች ከእሱ የላቁና ለውድድር የሚያዳግቱ አለመሆናቸውን፣ ለማረጋገጥ ጊዜ እንዳልፈጀበት ነው ይስሃቅ የሚናገረው፡፡
“በኤተን ኮሌጅ ለቃለመጠይቅ በተገኘሁበት ወቅት ያጋጠሙኝ ተማሪዎች፣ ከእኔ የተለዩና የላቀ አእምሮ ያላቸው እንዳልሆኑ ተረድቻለሁ፡፡ ስንገኛኝ ያቀረቡልኝ የመጀመሪያው ጥያቄ፣ የየትኛው እግር ኳስ ክለብ ደጋፊ ነህ የሚል ነበር፡፡ እኔ የማስበው የነበረው ስለፖለቲካ ወይም ስለሌላ አለማቀፋዊ ጉዳይ ይጠይቁኛል ብዬ ነበር” ብሏል ይስሃቅ፡፡
የኒውሃሙ ተማሪ በመጪው መስከረም ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ ዊንድሶር ውስጥ ወደሚገኘው ኤተን ኮሌጅ ያመራል፡፡ ከማህበረሰብ ትምህርት ቤት ወጥቶ፣ ከአዲሱ የኤተን ኮሌጅ ማህበረሰብ ጋር ይቀላቀላል፡፡ ይስሃቅ ከቤተሰቡ የሚነጥለው ቀጣዩ ጉዞ ይከብደው እንደሆን ተጠይቆ ነበር፡፡
“ከቤተሰቦቼ ተነጥዬ ወደ ኤተን መግባቴ ከእኔ ይልቅ ለቤተሰቦቼ ነው አስቸጋሪ የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ከእነሱ ተነጥዬ የምሄደው ወደ ዊንድሶር ነው፡፡ ዊንድሶር ደግሞ አሁን ከምኖርባት ኒውሃም ያነሰ ግርግርና ጩኸት ያለባት አካባቢ ናት፡፡ ትልቅ እድል ነው ያጋጠመኝ፡፡ እርግጥ ነው፣ የምሄደው ከቀድሞው ፍጹም የተለየ ነገር ወዳለበት አካባቢ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ካደግሁበት ኒውሃምም ሆነ ከተማርኩበት ፎሬስት ጌት ትምህርት ቤት ማህበረሰብ የተለየ ከሆነው የኤተን ማህበረሰብ ጋር ነው የምቀላቀለው፡፡ ቢሆንም አይከብደኝም ብዬ አስባለሁ” በማለት መልሷል ይስሃቅ፡፡
መምህሩ ሲሞን ኢሊየትም ቢሆኑ ተማሪያቸው በኤተን ኮሌጅ የሚገጥመውን አዲስ አኗኗር ተላምዶ አላማውን በማሳካት ውጤታማ እንደሚሆን ጥርጥር የላቸውም፡፡
“ይስሃቅ አሁንም ቢሆን፣ ወጣት ተማሪዎች የእሱን ፈለግ ተከትለው እንዲጓዙ ያነሳሳ ተማሪ ነው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን አንጸባራቂ ኮከብ እንደሚሆን አምናለሁ!” ብለዋል የቀለም አባቱ ኢሊየት፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ህልም አለህ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝሮለት ነበር የዘጋርዲያኑ ዘጋቢ ለይስሃቅ፡፡
“ፖለቲከኛ ለመሆን የግድ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የለብኝም… ከታች ወዳለው ህዝብ ወርዶ ማህበረሰቡን የሚለውጡ ስራዎችን የሚሰራ ፖለቲከኛ ልሆን እችላለሁ!” ሲል መልሷል፡፡
ጋዜጠኛው ሌላ ጥያቄ ይዞ ወደ አባትዬው ፊቱን አዞረ፡፡
“በርካታ ጠቅላይ ሚንስትሮችን ወዳፈራው ኤተን የሚጓዘው ልጅዎ፣ አንድ ቀን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ብቅ ይላል ብለው ያስባሉ?” ሲልም ጠየቀ፡፡
“ማን ያውቃል!?...” አባትዬው ፈገግ ብለው መለሱ፡፡

Read 5974 times