Monday, 31 March 2014 11:17

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን የሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎች ለስልጠና ቻይና ተላኩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የቀላል ባቡሩ አስተዳደራዊ መዋቅር በጣሊያኖች እየተጠና ነው
ባለሙያዎቹ በወር 1800 ብር ደሞዝ ይከፈላቸዋል
ኮርፖሬሽኑ ለስልጠናው ወጪ 80 ሚሊዮን ብር መድቧል
አለማየሁ አንበሴ
በቀጣይ ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የታቀደውን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት የሚያንቀሳቅሱ 252 ባለሙያዎች ወደ ቻይና የተላኩ ሲሆን ስልጠናው ከአራት እስከ አስራ አንድ ወራት ይፈጃል ተብሏል።
ባለፈው ማክሰኞ ለገሃር አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው 4ኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ በተሰራው አዲሱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጽ/ቤት ውስጥ በተዘጋጀው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው በኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽንና አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ሣርካ እንደገለፁት የስልጠናውን ሙሉ ወጪ ኮርፖሬሽኑ የሚሸፍን ሲሆን ስልጠናው 80 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡
ስልጠናው በቻይና በባቡር ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ተመራጭ በሆነው ቲያንጂን የባቡር ቴክኒክ ኮሌጅ የሚሰጥ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ ከ23 በላይ በሚሆኑ የስልጠና አይነቶች ተመድበው ይሰለጥናሉ ተብሏል፡፡ ከ252 ሠልጣኞች መካከል 28 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ 16 ያህሉ ሴቶች ለባቡር ሹፍርና (ትሬን ማስተር) ለ11 ወራት የሚሰጠውን ስልጠና የሚከታተሉ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ምልምል ሰልጣኞቹ ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በአውቶመካኒክስ እና በአውቶ ኤሌክትሪሲቲ በዲፕሎማ የተመረቁ ሲሆን ለመነሻ ደሞዝ 1800 ብር ተቆርጦላቸዋል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ በአሁን ሰአት ለአንድ ባቡር ሹፌር እስከ 5ሺህ ዶላር (አንድ መቶ ሺህ ብር ገደማ) እንደሚከፈል መረጃው አለኝ ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ኢትዮጵያዊያኑ ስልጠናቸውን አጠናቀው ሲመለሱና ወደ ስራ ሲሰማሩ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መዋቅር ምን ይሁን? በየባቡር ጣቢያው ስንት ሰራተኞች ይኑሩ? የሰራተኛ ደሞዝ የመሳሰሉትን ጉዳዮች እንዲያጠኑ ኃላፊነት የተሰጣቸው የጣሊያን አማካሪዎች የጥናት ውጤታቸውን ሲያቀርቡ የደሞዝ ክፍያው እንደሚሻሻል ጠቁመዋል፡፡
ሰልጣኞቹን የውጭ ኩባንያዎች ሊያስኮበልሏቸው ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ እንዳለ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ሲመለሱ ለሁለት አመታት እንዲያገለግሉ የሚያስገድድ ውል መፈረማቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የደሞዝ ጭማሪውን እስከ 7 ሺህ ብር በማድረስ ባለሙያዎቹን መያዝ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የራሱን የባቡር ኢንጅነሮችና ባለሙያዎች ሃገር ውስጥ ለማሰልጠን ያቀደ ሲሆን ለዚህም አጋዥ የሆኑ ሲሙሌተር የመሳሰሉ የስልጠና ቁሳቁሶችን ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ ነው ተብሏል፡፡
ወደ ቻይና ለስልጠናው ከተላኩት መካከልም ግምባር ቀደሞቹ አሰልጣኝ ይሆናሉ፡፡ በባቡር ቴክኖሎጂ የደህንነት ጉዳይ ወሳኝ ስለሆነ ወጣቶቹ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ሃገር ሲመለሱ ባቡሩን የሚያቀርበው ኩባንያ ከሚመድባቸው ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ተደርጎ የስራ ብቃታቸው ይገመገማል ብለዋል ኃላፊው፡፡ አክለውም እስካሁን የቀላል ባቡር ትራንስፖርቱን የትኛው አካል ይምራው የሚለው ውሳኔ ላይ ባይደረስም የመጀመሪያዎቹን ሁለት ወይም ሶስት ዓመታት የአስተዳደሩን ጉዳይ መንግስት ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በሁለቱ የጉዞ አቅጣጫዎች ላይ በድምሩ 41 ባቡሮች ለአገልግሎት የሚመደቡ ሲሆን በሁለት ባቡሮች መካከል ያለው የጉዞ ሰአት ልዩነት 6 ደቂቃ ነው፡፡ አንድ ተሳፋሪ የመጀመሪያው ባቡር ቢያመልጠው ሁለተኛውን ለመጠበቅ አንድ ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ይበቃዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲጀመር በቀን ለ18 ሰአት በሶስት ፈረቃ አገልግሎቱ የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጥላሁን፤ በእያንዳንዱ ባቡር ላይ ሁለት ሾፌሮች እና ሁለት ተቆጣጣሪዎች ይመደባሉ፣ በየ6 ሰዓት ልዩነትም ይፈራረቃሉ ብለዋል፡፡
252 ምልምል ሰልጣኞች ከሚሰለጥኑባቸው 23 ያህል መስኮች ጥቂቶቹን መርጠን እንደሚከተለው በሠንጠረዥ አቅርበናል፡፡
ቀሪዎቹ ደግሞ ስዊች ማን፣ ትራክ ዎርክ እና ብሪጅ ኢንጅነሪንግ፣ ያርድ ኮንትሮል፣ ሬልዌይ ኢንጅነሪንግና ትሬን ፕላነር እንዲሁም በሰርቬይ እና በስታትስቲክስ እንደሚሰለጥኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2424 times