Monday, 31 March 2014 11:22

የምክር ቤቱ የንግድ ስራ ስልጠና አካዳሚ ተከፈተ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአፍሪካ ቀንድ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአሜሪካ የንግድ ምክርቤት አካል ከሆነው አለማቀፍ የግል ንግድ ተቋማት ማዕከል (CIPE) ጋር በመተባበር ያቋቋመውና በአፍሪካ ቀንድ በአይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት የንግድ ስራ ስልጠና አካዳሚ ባለፈው ማክሰኞ ተመርቆ ተከፈተ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን በአካዳሚው የምረቃ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ የንግድ ስራ የልህቀት ማዕከል በመሆን እንዲያገለግል ታስቦ በአዲስ አበባ የተገነባው የዚህ የንግድ ስራ ስልጠና አካዳሚ መከፈት፣ በአገሪቱ የግል ዘርፍ ላይ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው፡፡
በአገሪቱ ያለው የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ ከተለምዷዊ አስተሳሰቦችና አሰራሮች መላቀቅና በዘመናዊ የንግድ ስራ ንድፈ ሃሳቦችና አሰራሮች መመራት እንደሚኖርበት የገለጹት ወ/ሮ ሙሉ፣ አካዳሚው ለንግዱ ማህበረሰብ አባላትና ለሚመለከታቸው ድርጅቶች ሰራተኞች ተገቢውን ስልጠና በመስጠት፣ የግሉን ዘርፍ አቅም በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የስልጠና ማዕከሉ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትንና  የአባል ድርጅቶችን የአመራርና የአስተዳደር ክህሎት የማጠናከርና ተቋማዊ አቅምን የመገንባት አላማ ያለው ነው፡፡ በንግዱ ዘርፍ በተሰማሩ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት፣ ትብብርና፣ ጥምረት ለማሳደግም ይሰራል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ከፍተኛ የህግ ባለሙያው ፕሮፌሰር ሞሃመድ ሃቢብ በበኩላቸው፣ መሰል አለማቀፍ ትብብር መፍጠር፣ ወቅቱን የጠበቀ የንግድ ስራ እውቀትን በማሰራጨት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ አካዳሚው መቋቋሙ በአገሪቱ ያለውን የግሉን ዘርፍ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃና እድገቱን እንደሚያፋጥን  ተናግረዋል፡፡
የልህቀት ማዕከሉ መገንባቱና ተገቢውን ስልጠና መስጠቱ፣ የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ ልማትና እድገት ላይ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና እንዲጫወት የሚያስችል መነሳሳት እንደሚፈጥርም አክለው ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በተከናወነው የአካዳሚው የምረቃ ስነስርዓት ላይ የመንግስት ተወካዮች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የአለማቀፍ የልማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ከ60 አመታት በላይ የአገሪቱን የንግድ ማህበረሰብ ማገዝ የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ተነግሯል፡፡

Read 2532 times