Monday, 31 March 2014 11:44

የሴቶችን ድንግልና መገለጫ በቀዶ ጥገና መመለስ (hymenoplasty)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(22 votes)

        ጠያዊው ወንድ ተጠያዊው ደግሞ የተዋልዶ ጉዳዮችን በተመለከተ በዌብ ሳይቱ  (ኢንተርኔት) ምላሽ የሚሰጥ ባለሞያ ነው፡፡ ጥያቄው “ረዥም ጊዜ በቆየንባቸው የፍቅር ጓደኝነት ጊዜ ጓደኛዬ ድንግል እንደሆነች ነበር የምትነግረኝ ሆኖም ጊዜው ደርሶ አልጋ ላይ ስንወድቅ የፍቅር ጓደኛዬ ድንግል አልነበረችም፡፡ ምንም አይነት የደም ምልክትም አልነበረም ጓደኛዬ በተፈጥሮ ድንግል ላትሆን ትችላለች ወይንስ ዋሸችኝ?” መላሹ በተራው ጥያቄውን በጥያቄ ይጠይቃል ጓደኛህን ታምናታለህ ወይንስ አታምናትም? ከጓደኛህ የምትፈልገው ከእሷ አንድ ነገርን ነው ወይንስ ጠቅላላ ማንነቷን? ብሎ ይጀምራል፡፡  
የሴቶችን የድንግልና ጉዳይ አሁንም በብዙ ወንዶች ዘንድ ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ እናስባለን፡፡ “ብር አንባር” አሁንም የክብር፣ የታማኝነት፣ የፍቅር ሰንሰለት ማጥበቂያ፣ መቼም አንደዬ ባህልና ልምዱ የተለያዩ ጉዳዮችን መግለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በአንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት ሴት ልጅ በሰርጓ ቀን ምሽት ባሏ፣ የቧላ ቤተሰቦችና የራሷም ቤተዘመድ እንደሚጠብቃት ድንግል ሆና ካልተገኘችና የዚህም ማረጋገጫ ካልታዬ ባሏ ሊገድላት፣ ከሱ እጅ ከተረፈች ደግሞ ወንድሞቿ ወይም አባቷ ሁሉ ሊገድላት ይችላል፡፡ የክብር መገለጫ፣ ሌላውንም ማስከበሪያና የትዳሩም መሰረት ተደርጎ ይወሰዳልና፡፡ እንዲህ ያለ ግድያ ወንጀል ቢሆንም ገዳዮች በጎሳዋቻቸው ባህል ውስጥ ይሰወራሉ፡፡
በህንድ ሳንሲ በተሰኘ ጎሳ ማህበረሰብ ውስጥ የሴቶች ድንግልና የሚሰጠው ቦታ በጣም የላቀ ነው። አንዲት ሳንሲ ድንግል አለመሆኗ ከታወቀ ቀጥሎ በዱላ ሁሉ የምትገደደው ድንግልናዋን ማን እንደወሰደ እንድታወጣ ነው፡፡ ይህን የፈፀመው ሰው ደግሞ ለወላጆች ካሳ ይከፍላል፡፡ ይህ የሳንሲ ማህበረሰብ የሴት ድንግልና መግለጫ መኖር አለመኖር የሚመረመሩበት የራሣቸው ልማዳዊ ዘዴ አላቸው፡፡ ግምገማውን ለእናንተ ለአንባቢያን ትቼ የምርመራ ልምዱን እንመልከት፡፡
የመጀመሪያው የውሃ ሙከራ የሚሉት ነው፡፡ የድንግልና ምርመራ የሚደረግባት ሴት ልጅ ራሷን ወይም ጭንቅላቷን ሙሉ በሙሉ ውሃ ውስጥ እንድትደፍቅ ትደረጋለች፡፡ ያለ ምንም አየር (ኦክስጅን) አንድ ሰው መቶ እርምጃ ተራምዶ እስቲደርስ መቆየት ከቻለች ሳንሲዎች ልጅቱ ድንግል መሆኗን አረጋገጡ ማለት ነው። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የእሳት ሙከራ የሚሉት ነው። ሙሽራዋ በሠርጓ እለት ከመጀመሪያው ለሊት በፊት ቅጠልና ሊጥ እጇ ላይ አድረጋ የጋለ (ፍም) የመሰለ ብረት ይዛ እንድትጓዝ ትጠየቃለች ብረቱ ቅጠሉንና አልፎ እጇን ካቃጠላት ድንግል አይደለችም ብለው ይወስዳሉ፡፡ እንዚህ ሁለት ሙከራዎች ከድንግልናው ጋር ምን ያያይዛቸዋል ካላችሁ ለሁላችንም እንቆቅልሽ መሆኑ ነው፡፡ መንግስት የዚህን ማህበረሰብ ወግ ጥሶ መግባት አልቻለም፡፡   
በቱርክ ደግሞ የሴቶች የድንግልና መገለጫ መኖር አለመኖር ማረጋገጫ ሙከራ ድርጊቱ ሴት ልጆችን ማማረር ብቻም ሳይሆን ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ሴቶች መኖራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ የአንድ ወቅት ሪፖርቱ ነበር፡፡ ቱርኮች በሰርጋቸው ቀን ሴቷ የድንግልናዋ  መገለጫ ይሆን ዘንድ ቀይ መቀነት ወገቧ ላይ ይደረግላታል ድንግል ከሆነች ማለት ነው፡፡ የድንግልና ምርመራን በተመለከተ በቱርክ በተደረገ ጥናት ተገድጄ ተደፍሬአለሁ የሚል ስሞታ ለምታሰማ ሴት ልጅ ምርመራው ያስፈልጋል የሚሉ ቢበዙም በተጨባጭ ግን የሚደረጉት ምርመራዎች ከልምዶቻቸው ጋር በተያየዘ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት ልጅ ከማግባቷ በፊት ለባሏና ለአካባቢዋ ሰርተፊኬት ማቅረብ አለባት። ያለገባ ሠርተፊኬት እንደሚሰጠው ሁሉ ለድንግልናም እንደዚያው ሠርተፊኬት ይሰጣል፡፡
በአጠቃላይ ምርመራውን ግን በሴቶች ላይ የስነልቦና መታወክ (Psychological trauma) መፍጠሩ አልቀረም ይላል ጥናቱ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ምርመራዎች የሚካሄዱት ከሴቶቹ ፈቃድ ውጭ በመሆኑ ነው፡፡
ወደ አቅራቢያ ደቡብ አፍሪካ ደግም በተለይ በዙሉ ማህበረሰብ የወንዶችም የሴቶች የድንግልና ምርመራ ኤች. አይ. ቪን ከመከላከል ጋር አቆራኝተው ያስቡታል፡፡ ሆኖም ከዚህ በተፃራሪ በዚሁ ማህበረሰብ ውስጥ አንድ የተሳሳተ አስተሣሰብ (myth) እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይኽውም ኤች. አይ. ቪ ኤድስ ያለበት ሰው ድንግል ከሆነች ሴት ጋር ግንኙነት ካደረገ ይፈወሳል በሚል ሌሎች አደጋዎች በተለያዩ ጊዜያት ተከስተዋል፡፡  
በዙሉ የወንዶች የምርመራ አይነት አሁንም ቀደም ሲል በህንድ እንዳየነው እንቆቅልሽ አይነት ነው። ረዥም ሽቦ በሦስት ስንዝር ከመሬት ከፍ ብሎ ግራና ቀኝ እንጨቶች ላይ ይታሰራል፡፡ ታዲያ የድንግልና ምርመራ የሚደረግበት ወንድ ብልቱን በእጁ ሣይዝ ከሽቦው አሻግሮ እንዲሸና ይጠየቃል፡፡ ሽንቱን በቀጥታ መሬት ላይ ከጨረሰ ድንግል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሆኖም ከተፈናጠረና አወራረዱ የተዝረከረከ ከሆነ ሽቦውን ካበላሸው ውጤቱ ተቃራኒ ይሆናል፡፡ ሌላም አለ አሸዋ ላይ በተመሣሣይ ሁኔታ እንዲሸና ይጠየቃል ሽንታቸው አሸዋው አንድ ቦታ ላይ ብቻ ቀዳዳ ከፈጠረ ድንግል ናቸው ብለው ይወሰዳሉ። በአጠቃላይ የድንግልና ምርመራ በዙሉ ማህበረሰብ ፍርሃት እንዲነግስ አድርጓል። በተለይ ተገዶ መደፈር ያውም ህፃናትን በዝቶ የሚታይ ክስተት በመሆኑ። ወደመነሻችን ርዕስ ጉዳይ እንመለስ፣ ድንግልና ምንድን ነው ከተባለ ለሴቶች ብቻ የሚውል ቃል አይደለም፡፡ የሴቶችን የድንግልና መስመር ወይም መረብ (hymen) የሚገልፅም አይደለም፡፡ ምንም አይነት ወሲባዊ ተራክቦ የሌለው ሰው ድንግል ነው፣ ግን ወሲባዊ ግንኙነትስ የግድ የወንድና የሴት ተራክቦን የተለመደውን ብቻ የሚያሳይ ነው?   
የሴቶች የድንግልና መገለጫ (hymen) ስስ የሴቶችን ብልት የውስጥ ክፍል ወይም በር (ሙሉ በሙሉ ባይሆንም) የሚዘጋ መረብ መሰል ሥሥ ሽፋን (tissue) ነው፡፡ ጠንካራ አጥር ወይም ጠንካራ ቆዳ ትግል፣ ኃይል የሚፈልግ አይደለም እንደባለሞያዎቻች ትንተና፡፡ ከግንኙነት ውጭም በተለያዩ ምክንያቶች በቦታው ላይገኝ ይችላል፡፡ በእርግጥም ደግሞ የሴቶች ጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡
በእርግጥ የድንግልና መገለጫ መስመር (hymen) በተፈጥሮ ማንኛዋም ሴት ልጅ ይኖራታል፡፡ ይሁንና በመጀመሪያው የግንኙነት ቀን ጊዜ ህመም ሊኖራትም ላይኖራትም፣ ህመሙ ጠንካራ ወይም ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ የደም ፈሣሽ ሊበዛም፣ ሊያንስም በጣም ትንሽ ሊሆንም ይችላል፡፡ ብቻ በማንኛውም መንገድ ከወንድ ጋር በሚደረግ ወሲባዊ ተራክቦም ይሁን በሌላ አጋጣሚና ሁኔታዎች የድንግልና መገለጫ (hymen) ከፈረሰ በኃላ ራሱን የሚተካበት ወይም መልሶ የሚዘጋበት ወይም እንደሌላ የአካል ክፍል የሚያድግበት ሁኔታ የለም፡፡ ይሁንና ህንዶች ከባህሎቻቸው ጫና የተነሳ በቀዶ ጥገና የነበረውን በነበረበት መመለስ አስፈልጓቸዋል፡፡ አንዲት የዚህ ህክምና ባለሞያ ስትገልፅ በቀዶ ጥገናው የድንግልና መገለጫ የሆነውን (hymen) እንደገና መሥራትና መዝጋት ብቻም ሣይሆን ቀጣይ ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈፀም የደም ፈሣሽ ክስተት ይኖር ዘንድ የድንግልና መገለጫውን ከሌላው የአካል ክፍል ህዋስ (Cells) ጋር የሚያገናኝ ሰንሰለት (membrane) እንዲፈጠር ይደረጋል፡፡ ይህ ቀዶ ጥገና ሁለት ቀናት የሚወስድ ሥራ ሲሆን ቀደም ሲል የገለፅነውን የባህል ጫና ለማቃለል ህንዶች ይጠቀሙበታል፡፡ ሌላ ወግ ይዘን ለሣምንት እንመለሳለን፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡

Read 21213 times