Monday, 07 April 2014 15:28

ግብፅ ለህዳሴው ግድብ ቦንድ መግዛት እፈልጋለሁ አለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

       በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን የታላቁን ህዳሴ ግድብ በመቃወም ግንባታውን ለማደናቀፍ የተለያዩ ዘመቻዎችን እያካሄደች ያለችው ግብፅ፤ ግድቡ ሁለቱን ሃገራት የጋራ የሚጠቅም ከሆነ ቦንድ በመግዛት በገንዘብ ለመደገፍ እንደምትፈልግ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማስታወቃቸውን የዜና ምንጮች ገለፁ፡፡
በቤልጅየም ብራሰልስ እየተካሄደ ባለው የአፍረካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ ላይ ለመካፈል የተጓዙት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋህሚ  የህዳሴ ግድብን ለማስቆም ከፍተኛ ዘመቻ ሲያካሂዱ ሰንብተዋል፡፡ ሮያል ኢንስቲትዪት ፎር ኢንተርናሽናል ሪሌሽን በተባለው ተቋም ሃሙስ እለት ባደረጉት ንግግርንና፣ ሃገራቸው የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በገንዘብ ለመደገፍ ማቀዷን አስታውቀው ግድቡ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ግድቡን የማስተዳደር ስልጠን ከሁለቱ ሃገራት በተውጣጣ ኮሚቴ ስር መሆን አለበት፡፡
ቀደም ሲል የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያና የግብፅ የጋር ፕሮጀክትነት እንዲሆን ተመሳሳይ ጥያቄ መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መንግስት ግን ጉዳዩ ከሉአላዊነት ጋር የተያያዘ መሆኑን በማመልከት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡  ግድቡን የጋራ ለማድረግ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ አበክራ እንደምትሰራ የተናገሩት ነቢል ፋህሚ፤ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የግብፅን ጥቅም የሚቀናቀን ጉዳይ ላይ ግን ትዕግስት እንደሌላት ተናግረዋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካትሪን ጋር የመከሩ ሲሆን በጉባኤው ላይም የግድቡ ጉዳይ መነጋገሪያ እንደሆነ ኃላፊዋን መጠየቃቸው ተጠቁሟል፡፡ የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 3ኛ አመት መከበሩን በተመለከተ የግብፅ የሚዲያ ተቋማት በርካታ ዘገባዎች ሲያቀርቡ የሰነበቱ ሲሆን፤ የተለያየ አቋም አስተጋብተዋል፡፡ ግድቡ ሁለቱንም ሃገራት እንደሚጠቅም መሆኑ የሚገልፅ ዘገባ ያሰራጩ የሚዲያ ተቋማት እንዳሉዋሉ፤ ሌሎች ደግሞ ግብፅ ጥቅሟን ለማስከበር በተለይም በ1902 እ.ኤ.አ ሚኒልክ ፈርመውበታል የተባለውን ስምምነት በመጥቀስ በአለማቀፉ ፍ/ቤት ክስ እንድታቀርብ እየመከሩ ነው፡፡
የግብፅ ምሁራንና ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የግድቡ መገንባት ማንኛውም 95 በመቶ ውሃ ፍላጎቷን ከናይል በምታገኘው ሃገራቸው ላይ የውሃ መጠኑን በ20 በመቶ በመቀነስ ጉዳት ያመያል ሲሉ እየተከራከሩ ሲሆን አንዳንድ የኢንጅነሪንግ እውቀት ያላቸው ምሁራኖቿ ግን ከዚህ በተቃራኒው ግድቡ ዓመቱን ሙሉ የውሃ ፍሰት ሳይቀንስ እንዲዘልቅ ይረዳል ሲሉ መከራከሪያ ሲያቀርቡ ተደምጧል፡፡
ግንባታው ከተጀመረ 3 ዓመት የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ 32 በመቶ ስራው የተጠናቀቀ ሲሆን ለግድቡ ግንባታ 11.5 ቢሊዮን ብር ከህብረተሰቡ ቃል የተገባ ሲሆን አጠቃላይ ወጪው 80 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተመልክቷል፡፡  

Read 6034 times