Monday, 07 April 2014 15:33

“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው በማያውቀው ነገር ባለቤቱ ማኩረፍ ትጀመራለች፡፡ ምክንያቱን ለማወቅ ቢሞክርም ነገርዬው ጭራሽ እየባሰ ቤት ውስጥ እሱን ማናገር ሁሉ ታቆማለች፡፡ ምን የሚያስቀይማት ነገር እንደሠራ ለማወቅ ቢሞክር አንዲትም ነገር ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ለቅርብ ወዳጆቹ ያማክራቸዋል፡ እነሱም ነገሩን ሲያጣሩ ለካስ የእሱው የቅርብ የሚባል ዘመድ እዚሀ ላይ የማይጻፉ ነገሮች እንደሚያደርግ በጎን ለሚስቱ ሹክ ይላት ነበር። ነገርዬውን ለሚስቱ በደንብ አስረድተዋት እርቅ ወረደ፡፡ ዘመድዬው ለምን እንደዛ ማድረግ እንደፈለገ እስካሁን ሊያወቁ አልቻሉም፡፡
እናላችሁ ዘንድሮ ሉሲፈር በሩቅ ባዳ ሳይሆን በቅርብ ዘመድ በኩል ይመጣባችኋል፡፡
የምር ግን…ሉሲፈር መልኩን እየለዋወጠ መከራችን እያበላን ነው፡፡ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…አለ አይደል… ሉሲፈር ያለገደብ እየፈነጨባት ያለች አገር ብትኖር የእኛዋ ነች፡፡ በስንትና ስንት በኩል ይመጣባችሁ መሰላችሁ!
ሉሲፈር፣ ሚኒስከርት በለበሰች እንትናዬ ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ! በባዶ አንጀት፣ በደከመ ጉልበት ምናምን እንደገና ሚኒስከርት አይተን!
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እንዴት ነው ነገሩ! ለእንትናዬዎቻችን ኮድ ተሰጣቸው እንዴ! አሀ…ወዳጆቼ የነገሩኝን ነዋ! ልክ ነው እንደ መኪና ታርጋ ለእነሱም ‘ኮድ ሁለት’፣ ‘ኮድ ሦስት’ እየተባለ መለያ ይሰጣቸዋል አሉ፡፡ እንግዲህ እኔ የማውቀው ‘ኮድ ሁለት’ የቤት ‘ኮድ ሦስት’ ደግሞ የንግድ ምናምን መሆናቸውን ነው። ጥያቄ አለን…ኮድ አሰጣጡ የሚመነዘረው በቃል በቃል ትርጉም ነው ወይስ በአዛማጅ ትርጉም!
ስሙኝማ…የምር ሳስበው ግን…አለ አይደል… ‘ኮድ ሁለት’ እያነሰ ‘ኮድ ሦስት’ እየበዛ የሄደ ይመስለኛል፡፡ (እነ እንትና… “ይመስለኛል” ማለትን እንኳን ተዉልና!)
ኮድ አሰጣጡ ይስፋፋልንማ… ‘የዕለት’፣ ‘ተላላፊ’ ምናምን የሚባሉ መለያዎችም ይካተቱልን። አያሻሙማ! በዕለቱ ‘ማሳካት’ ካልቻልን ዕድላችን እንደ ቤት ካርታ እንደሚመክን ብናውቅ አሪፍ ነዋ! ቂ..ቂ…ቂ…
‘ተላላፊ’ እስከዚህ ችግር የለበትም፡፡ “ጠዋት ተቀብተሽው የነበረው ሊፕስቲክ ምን አጠበው!” “ጋላክሲ 4 በየትኛው ገንዘብሽ ነው የገዛሽው!” ምናምን ብሎ ንትርክ አይሠራም፡፡ ኮዱ ‘ተላላፊ’ ይላላ! ቂ…ቂ…ቂ…
ሉሲፈር በ‘ቦተሊከኛ’ ተመስሎ ሊመጣ ይችላል። ልክ ነዋ…የዘንድሮ ‘ቦተሊከኛ’ ማጣፊያው ሲያጥረው፣ (“ሊበራልና ኒኦ ሊበራል ምንና ምን ናቸው?” የሚለውን መመለስ ሲያቅተው ማለትም ይቻላል! ቂ…ቂ…ቂ…) በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ወደ ስድብና ወደ “ዋ! ውርድ ከራሴ” አይነት ነገር ይገባል፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ ቦተሊከኛ ሞልቷል፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ድሮ፣ ድሮ ሴራው ሁሉ…አለ አይደል… የኢምፔሪያሊስቶች፣ ፔትሮ ዶላር ያሰከራቸው፣ የትሮትስካይቶች፣ የአምስተኛ ረድፈኞች፣ የፊውዳል ርዝራዦች… ምናምን ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ሴረኞች ወደ ‘ኒኦ ሊበራሊስቶች’ እየተጠቃለሉልን ስለሆነ ተመችቶናል፡፡ ልክ ነዋ…ትንፋሽና ቃላት እንቆጥባለና!  ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞላችሁ…ሉሲፈር በኃይማኖት ሰባኪ ተመስሎ ሊመጣ ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…የመንግሥተ ሰማያትን ቋንቋ በሚያምር አንደበት እያንበለበሉ ስምንት የህይወት ዘመናት እንኳን ቢኖሩ ተናዘው የማይጨርሱት ሀጢአት ተሸክመው… አለ አይደል… “የመንግሥተ ሰማያት ‘ማስተር ኪይ’ በእኛ እጅ ነው…” የሚሉ ‘ኃይማኖተኞች’ መአት ናቸው፡፡ እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የእኛ ህዝብ ነገር ሆኖ ነው እንጂ ኃይማኖትን ለመባረኪያነት ሳይሆን ለመክበሪያነት የሚጠቀሙ፣ በሰማያዊ ቃላት ጀርባ የተሸሸጉ መአት ናቸው፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ ኃይማኖት ሰባኪ ሞልቷል፡፡
ሉሲፈር በሬስቱራንት አስተናጋጅ ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ በዛ ሰሞን አንድ ሬስቱራንት ውስጥ ደስ ሳይለው የታዘዘ አስተናጋጅ ሱሪውን ሳይሆን በስህተት የትራስ ልብሱን ለብሶ የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ ጨርቅ ይህን ያህል ይጨማደዳል! የምር እኮ…አጥቦ አስጥቶ እሲኪደርቅ ከሚወስደው ጊዜ ይልቅ መተኮሱ የበለጠ ጊዜ ይፈጃል! (ባለ ምግብ ቤቶች… የጠረጴዛ ጨርቅ ማሳመር ብቻ አይደለም!)  
ማስቲካ እያኘከች ትእዛዝ የምትወስድ፣ እጁን ኪሱ ከትቶ “ምን ይምጣ!” ብሎ የሚቆጣ፣ ምን ልታዘዝም ምን ይምጣም ሳይል አፍጦ የሚያይ፣ የማታዋን ጠጅ ለማምከኛ የሹሮ ፍትፍት ሳይበላ የመጣ (ቂ…ቂ…ቂ…)…ምን አለፋችሁ… ‘ትራጂያዊ ኮሜዲ’ (የሚባል ነገር አይጠፋም ብዬ ነው!) ምናምን ፊልም ሊሠራባቸው የሚችሉ በየቦታው አሉላችሁ፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ አስተናጋጅ ሞልቷል፡፡
እኔ የምለው የምግብ ቤት ነገር ከተነሳ አይቀር…  የአንዳንዶቻችን አበላል… አለ አይደል… ምን ይመስላል መሰላችሁ… ‘ላስት ሰፐር’ ይመስላል።  እንዴት ነው ነገሩ… ሁለት ጉንጭ ሞልቶም፣ ጮክ ብሎ አውርቶም ይሆናል እንዴ! ‘ቴብል ማነርስ’ የሚባለው ነገር ለ‘ሹካ’ ምግቦች ብቻ ሳይሆን ለቋንጣ ፍርፍርም እንደሚሠራ ግንዛቤ ይግባልንማ!
ሉሲፈር፣ በሚኒባስ ሹፌር ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ በቀደም ከአምባሳደር ወደ አራት ኪሎ የሚወስደው ታክሲ ውስጥ ተቀምጠናል። እናላችሁ…ሁለት ተለቅ ያሉ ሰዎች እየገቡ እያሉ ሹፌሩ መኪናዋን አንቀሳቀሰና ሊወድቁ ተንገዳገደው እንደምንም ገቡ፡፡
ከዛላችሁ… አንደኛው ሰውዬ እንደ ቀልድም አስመስለው “ጥለኸን ነበር እኮ…” አሉት፡፡ እሱዬው ምንም መልስ አልሰጠም፡፡ ጭራሽ ሌላኛው ሰውዬ “አስቆጣነው መሰለኝ” አሉ፡፡ እሱ ሆዬ “ይቅርታ የለ፣ ምን የለ መንገዱን ቀጠለ፡ እናላችሁ በዛ ሰዓት ‘ሰይጣን ያሳሳተው’ ሰው “አይተህ አትነዳም!” ምናምን ቢል የሚፈጠረው ይታያችሁ፡፡ እናላችሁ…በስርአት ሳይነዳ ቀርቶ ላንገዳገደን የሚኒ ባስ ሹፌር ይቅርታ ጠያቂዎች እኛው ልንሆን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሚኒባስ ሾፌሮችና ረዳቶች ባህሪይ… “ስደተኞችን ጭኖ ወደ የመን የሚሄደውን ጀልባ በየት በኩል ብሄድ አገኘዋለሁ?” ለማስባል ምንም አይቀረው። በየዕለቱ የማያቸው ነገሮች… “ይሄ ምስኪን ህዝብ በስንቱ መከራውን ይይ!” የሚያሰኝ ነው፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ ታክሲ ሾፌር ሞልቷል፡፡
ሉሲፈር ስልጣኔ አናታቸው ላይ በወጣ ወላጆች ተመስሎ ይመጣል፡፡ የምር አሥራ ሦስቷን ሳይደፍኑ ሁሉንም ነገር የሚለምዱ ልጆች…ዋናዎቹ ችግር ፈጣሪዎች ገንዘብ ሁሉ ነገር የሚመስላቸው ወላጆቻቸው ነው፡፡
“ሀብትና ዕውቀት አይገኙም አንድነት፣” የሚሏት ነገር እንዴት አሪፍ አባባል ነች!
ስሙኝማ…በቀደም አንድ ከተማ ወጣ ያለ ‘ፖፑላር’ መዝናኛ ውስጥ ገና ሃያ ያልተጠጉ ወጣቶች የሚሆኑትን ነገር ላየ…አለ አይደል…ተስፋ ቢቆርጥ ምንም አይገርምም፡፡ በከተማችን ውስጥ በየቦታው የሚሰሙ ነገሮች ሁሉ አንዳንዴ እንደ ልብ ወለድ ነገርም የሚቃጣቸው ናቸው፡፡ የምር ግን ሉሲፈር ከሙሉ ጦሩ ጋር እየሰፈረ ያለበት የሚመስል ስፍራ ቢኖር እዛ አካባቢ ነው፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር የሚያሳስቧችሁ ብላቴናዎች ሞልተዋል፡፡
እናማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ ሉሲፈር ራሱ… “እንደው ስለ ነገረ ሥራችን ምን ታስባለህ?” ተብሎ ቢጠየቅ…አለ አይደል…ምን የሚል ይመስለኛል መሰላችሁ…  “አሁንስ አበዛችሁት!  እንደውም አይደለም ላሳስታችሁ ቀርቶ እኔ ራሴ እየፈራኋችሁ ነው…” የሚል ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…ብዙዎቻችን እኮ ‘ቀላል አልባሰብንም!’
እናላችሁ…ፍጹም ቅዱስ እንደሆንን የምናስመስል ሰዎች…አለ አይደል…ራሱ ሉሲፈር ሊፈራን የሚገባን አይነት ነን፡፡ ሰውየው “ከወዳጆቼ ጠብቀኝ ጠላቶቼን እኔ እጠብቃቸዋለሁ…” ነው ምናምን አለ እንደተባለው ዘንድሮ ሉሲፈር ሰተት ብሎ የሚመጣው በወዳጅ በኩል ነው፡፡
ሉሲፈር በጥበቃ ሠራተኛ ተመስሎ ይመጣባችኋል፡፡ የሚገርም እኮ ነው…ለጥበቃ ሠራተኞች “ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ” አይነት ስልጣን በሰርኩላር ተላልፎላቸዋል እንዴ! አንዳንድ ጊዜ እኮ እዛ መሥሪያ ቤት የሄዳችሁት ለጉዳይ ሳይሆን እርጥባን ልትጠይቁ  ያስመስሉታል። ስሙኝማ… የአንዳንድ ጥበቃ ሠራተኞችን የ‘ንቀት’ አስተያያት ልብ ብላችሁልኛል… ምን አለፋችሁ… ከጫማችሁ ጀምሮ ‘ስካን’ ሲያደርጓችሁ ሥራ አስኪያጁ ዘንድ ወረቀት ለማስፈረም የምትሄዱ ሳይሆን ለርቢ የታጫችሁ ኮርማ ነገር ያስመስሏችኋል፡፡
“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…”  የሚያስብል ነገር የሚያሳስባችሁ የጥበቃ ሠራተኛ ሞልቷል፡፡
ሌላውን “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” የሚያስብል ነገር እንዲያስብ የምናደርግ፣ ሉሲፈር ተንሰራፍቶ ለሽ ያለብንን ሁሉ አንድዬ ልቦናውን ይስጠንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3791 times