Monday, 07 April 2014 15:36

የኢትዮጵያን ህልም በአሜሪካ አየሁት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሁለት ታላላቅ ግድቦች ወግ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ እና ታላቁ ‹‹ሁቨር ዳም››

   የህዳሴው ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 3ኛ ዓመት ሲከበር፤ ከስድስት ወር በፊት በአሜሪካ በነበረኝ ቆይታ የተደነቅሁበትን የሁቨር ግድብ አስታወሰኝ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የገባንበት ያህል ችግርና ውድቀት ባይገጥማቸውም፤ አሜሪካዊያን ያኔ በ1923 ዓ.ም ከባድ ቀውስና ጭንቀት ውስጥ ነበሩ። እኛ ከስልጣኔ ማማ ላይ ሳናውቀው ተንሸራተትን ከወደቅን ወዲህ፣ ለሺ አመታት ከከበበን ድቅድቅ ጨለማ ለመገላገል ስንመኝ ኖረናል፡፡ ጥንታዊውን የስልጣኔ ጉዞ እንደገና የሚያድስና የብልፅግና ዘመንን የሚያበስር ነገር እንፈልጋለን - የህዳሴ ግድብ ትርጉምም የዚህን ያህል ግዙፍ ነው - ‹‹ታላቅ ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን›› እንዲሉ፡፡
የሁቨር ግድብም እንዲሁ ለአሜሪካውያን ተቀራራቢ ትርጉም አለው፡፡ እስከ 20ያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ድረስ ለመቶ አመታት በስልጣኔና በብልጽግና ጐዳና ታይቶ የማይታወቅ ታሪክ የሰራችው አሜሪካ፣ ብዙም ሳይቆይ ነው በታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ የተመታችው፡፡ የ1920ዎቹ ዓመታት ለአሜሪካ ክፉ ዓመታት ናቸው፡፡ ብርሃኗ የደበዘዘባት፤ ፋና ወጊ መንፈሷ የቀዘቀዘባት ዘመን!
የረሃብና የግጭት አዘቅት ውስጥ ባይዘፈቁም፤ የስልጣኔና የብልጽግና ጉዟቸው ተብረክርኮ፤ የ‹‹ይቻላል›› መንፈስ የተዳከመባቸው አሜሪካዊያን፣ የጨለማ ድባብ ሲያንዣብብባቸው ጊዜ ህዳሴ አስፈለጋቸው፡፡ “ሁቨር ዳም” የዚያ ፍላጎት ውጤት ነው፡፡ በትግል ቋንቋ እንግለፀው ቢባል፤ “ብሶት የወለደው ጀግናው የአሜሪካ ህዝብ” እንደማለት ነው! እኛ ለአባይ የዘፈንለትን ያህል አሜሪካዊያን ለኮሮላዶ ወንዝ አላዜሙም፡፡ ነገር ግን እኛ ለአባይ ስንቆጭ እንደኖርነው፤ እነሱም በኮሮላዶ ወንዝ መቆጨታቸው አያጠራጥርም፡፡
ወንዙ ከአፍንጫቸው ስር እንደ ጅብራ ተገትሮ ሳይጠቀሙበት መፍሰሱ ሳያንስ፤ በየአመቱ ገጠር ከተማውን ሲያማርጥ በጐርፍ ያጥባቸዋል፡፡ በሸለቋማው ወንዝ፣ ከፍቅረኛው ተለያይቶ የቅርብ ሩቅ ለመሆን የተገደደ ጎረምሳ፤ “አንቺ ከአባይ ማዶ” እያለ እንደሚያንጎራጉረው ሁሉ፣ የኮለራዶ ወንዝም አሜሪካያውንን ሲያራርቅ ኖሯል፡፡
አሪዞናን ከወዲህ ማዶ፣ የኔቫዶ በረሃን ወዲያ ማዶ ሰንጥቆ የሚያልፈው የኮለራዶ ሸለቋማ ወንዝ፤ በርካታ ግዛቶችን እያቆራረጠ ይገሰግሳል፡፡ ዛሬ ግን እልም ካለው የኔቫዳ በረሃ ላይ ጉብ ካለችው ሽቅርቅሯ ላስ ቬጋስ ከተማ፣ ወደ አሪዞና በሚወስደው ምቹ መንገድ በመኪና ለሰላሳ ደቂቃ እንደተጓዙ፤ ፊት ለፊት ከአይንዎ ጋር የሚጋጨው ተራራና ገደል ሳይሆን ሰማይ ጠቀስ ግድብና ድልድይ ነው፡፡
በኦሪዞና ግዛት የፊኒክስ ከተማንና በኔቫዳ ግዛት ላስ ቬጋስን የሚያገናኘው ሰማይ ጠቀስ ድልድይ በየእለቱ በሰዎች ሲጥለቀለቅ ይውላል፡፡ “ከወንዝ ማዶ ያለሽው” እና “ከወዲያ ማዶ ያለኸው” እያሉ ናፍቆታቸውን የሚያንጐራጉሩ ፍቅረኞች አይደሉም በድልድዩ የሚተላለፉት፡፡ ሁቨር ዳምን ለማየት የሚመጡ ጐብኚዎች፣ እንጂ፡፡ ግድቡን ለመመልከት በየቀኑ የሚመጡ በርካታ ሺህ የዓለም ጐብኝዎች ረዥሙን ግድብ ላይ ላዩን አይተው አይመለሱም፤ ውስጥ ለውስጥም ይጐበኙታል፡፡ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ የሚገኙት ከግድቡ ስር መሬት ውስጥ በጥልቅ ቦታ ነው፡፡ በሊፍት ወደ መሬት ውስጥ ቁልቁል ብዙ ርቀት መግባት ያስፈልጋል፡፡
ሊፍት ከመያዛችን በፊት ከአስጐብኛችን አንደበት የወጡ ቃላት ፍርሃት ለቀቁብኝ፡፡ “ከመሬት በ5ሺህ ጫማ ርቀት ወደ ታች እንዘልቃለን፡፡ ይህ ግድብ ሲገነባ የዘጠና ስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል” አለች፡፡
“አውቃችሁ ግቡበት” አይነት አባባልዋን እየሰማን በዝምታ ስንተያይ፤ እሷ በጣቷ የሊፍቱን መቆጣጠሪያ ተጫነች፤ ወደ መሬት እንብርት ይዞን እንዲሸመጥጥ፡፡ እንጀራዋ ነው፡፡ እንደ ባልደረቦቿ ጐብኚዎችን በቡድን እያሰባሰበች ስታስተናግድ ትውላለች፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ በሚፈጀው መስተንግዶ፤ በቀን አምስት ጐብኚ ቡድኖችን ተቀብላ ዙሪያውን ታስቃኛለች፡፡ ሰማይ ጠቀስ ግድቡንና ድልድዩን፤ እንደ አገር የተንሰራፋውን ሃይቅና ዙሪያ ገባውን ካስጎበኘች በኋላ፣ ነው የሃይል ማመንጫ ጣቢያውን ለማሳየት ቁልቁል ከአንድ ኪሎሜትር ጥልቀት በታች ይዛን የጠለቀችው፡፡ ወደ ምድር ስር የሚዘልቅ ባለ ሦስት መቶ ፎቅ ያህል እንደማለት ነው፡፡ ሳስበው አሁን ድረስ ያስፈራኛል። ከላያችን ላይ ግዙፍ ግድብ ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ሃይቅ አለ፡፡ እዚያ ስር ነው፤ በየአመቱ 4.5 kwh የኤሌክትሪክ ሃይል የሚመነጨው፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላላ አመታዊ የኤሌክትሪክ ሃይል ከአንድ ግድብ ይመነጫል፡፡
በየአመቱ የ18 ሚሊዮን አሜሪካዊያን መኖሪያ አካባቢዎችን በጐርፍ እያጥለቀለቀ ከፍተኛ ጥፋት ሲያደርስ የነበረው ኮሎክራዶ ወንዝ፤ ዛሬ ለሚሊዮኖች የኤሌክትሪክና የብርሃን መፍለቂያ፤ ለሚሊዮኖች የመጠጥና የመስኖ ውሃ አስተማማኝ ምንጭ ሆኗል፡፡ እንደ አገር የሚሰፋው ሰው ሰራሽ ሃይቁም በዓለም ላይ የመጀመሪያው ትልቁ ሰው ሰራሽ ሀይቅ በመባል በመዝናኛነቱ ለመታወቅ በቅቷል፡፡ ነገር ግን፣ ግንባታው አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ለግድብ ግንባታ ተስማሚ የሆነ ቦታ ስላልተገኘ፣ የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየር የግድ ነበር፡፡ የስራው ክብደት ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ከሁሉም በፊት ግን የይገባኛል ውዝግቦችን በድርድር መፍታትና መስማማት ያስፈልግ ነበር፡፡ በርካታ ግዛቶችን የሚያካልለው ትልቅ ወንዝ፣ አቅጣጫውን እንዲቀይር ሲደረግ፤ በውሃ ክፍፍልና ድርሻ ላይ ከየግዛቱ ክርክሮች ተፈጥረዋል፡፡ እንዲያውም ውዝግቡ ከመካረሩ የተነሳ፣ የግድቡ ግንባታ ‹‹ህልም ሆኖ ይቀራል›› እስከመባል ደርሷል፡፡
ደግነቱ ስልጡን ሰዎች፣ እድሜ ልክ እየተወዛገቡ አይቀጥሉም፡፡ ይወያያሉ፤ ይደራደራሉ፡፡ ለዚህም ነው፤ የአሜሪካ 31ኛው ፕሬዚዳንት ኸርበርት ሁቨር ከየግዛቱ አስተዳዳሪዎችና ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት ሚዛናዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖር የተወያዩት፡፡ አስጐብኚያችን ከ90 አመት በፊት ስለነበሩት ፕሬዚዳንት ስትናገር፤ የአጐቷን ታሪክ የምትተርክ ትመስላለች፡፡
“ኸርበርት ሁቨር ከፖለቲከኛነቱ በተጨማሪ መሃንዲስ ነው፡፡ ወግ አጥባቂ ቢሆንም ደግ ሰው ነው፡፡ የታታሪነቱ ያህል አሳ በማጥመድ መዝናናትን የሚወድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ‘የሰው ልጅ በአካባቢው የሚገኙ ተፈጥሯዊ ነገሮችን ወደ መልካምና ጠቃሚ ነገር የመለወጥ ችሎታ አለው’ የሚል ጠንካራ እምነትና ራእይ የያዘ ሰው ነው፡፡” … አስጎብኚያችን ፕሬዚዳንቱን በቅርብ የምታውቃቸው ሆኖ ሰተማኝ፡፡
የሆነ ሆኖ በውይይቱ ወደ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው፤ በአንድ በኩል ተራሮችን በድማሚት መናድና የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየር፤ በሌላ በኩል በሸለቆ የተራራቁትን ተራሮችን ለማገናኘት የግድብ ግንባታ የተጀመረው፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ታላቁን ግድብ በመስራት እውቀትና ችሎታቸውን ለማሳየት የተዘጋጁት አሜሪካዊያን መሃንዲሶች ከፈተና አላመለጡም። የኔቫዳ በረሃ፣ የኛው ህዳሱ ግድብ ከሚገነባበት ከቤኒሻንጉል ክልል ባልተናነሰ የሙቀት መጠን የሚታወቅ ቦታ እንደመሆኑ፣ ለግዙፍ የኮንክሪት ስራ በፍፁም አይመችም፡፡ የፎቅ ግንባታ ላይ እንደሚታየው፤ ቀጫጭን ምሰሶዎችና ግድግዳዎችን በኮንክሪት መስራት አያስቸግርም፡፡ ትንሽ ውሃ ከተረጨበት ኮንክሪቱ ብዙም ሳይቆይ ይቀዘቅዛል። ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ፣ ላይና ታች የተደፈነ የኮንክሪት ተራራ ሲገነባ ግን፣ ኮንክሪቱ በፍጥነት የመቀዝቀዝ እድል የለውም፡፡
ኮንክሪቱ እስኪቀዘቅዝ እየጠበቀን እንስራ ከተባለ ግንባታው 100 ዓመት እንደሚፈጀ ነበር የተገመተው፡፡ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ኮንክሪቱ እንዲቀዘቅዝ የሚደረገው ላዩ ላይ በረዶ በማፍሰስ ነው፡፡ የሁቨር ግድብ ሲገነባ ግን፣ እንደዛሬ በረዶ ማምረቻ ማሽን በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ ቢሆንም መሃንዲሶቹ ውሃ በመጠቀም ኮንክሪቱን የሚያቀዘቅዝ መላ ዘየዱ፡፡ ስራውም ሳይጓተት ቀጠለ፡፡ እንዲያውም ሰባት አመት ይፈጃል የተባለው ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ ቀደም ብሎ በአምስት ዓመት ተጠናቀቀ፡፡  
ግድብ ለመስራት የፈሰሰው ሲሚንቶና ኮንክሪት፤ 4674 ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ ሰፊ የአስፓልት መንገድ ሊሰራ ይችላል፡፡ ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚዘልቅ አስፋልት መንገድ ማለት ነው፡፡ በምን ያህል ወጪ እንደተገነባ አትጠይቁኝ፡፡
ለካ በኛ አገር ብቻ ሳይሆን በአሜሪካም፣ ያኔ ድሮ ሁሉም ነገር ርካሽ ነበር፡፡ ለግድቡ የወጣው ገንዘብ 49 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በዛሬ ገንዘብ ቢሰላ ከቢሊዮን ዶላር ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ በሦስት ፈረቃ ተፍ ተፍ ለሚሉት 3500 አሜሪካዊያን ሰራተኞች የሚከፈለው ደሞዝ፤ እንደ የሙያቸው ቢለያይም፣ ዝቅተኛው ክፍያ በቀን አራት ዶላር ነበር፡፡ ቀላል ይመስላል፡፡ በዛሬ ሂሳብ ከ100 ዶላር ሊበልጥ ይችላል፡፡
አስተማማኝ የኤሌክትሪክና የውሃ ምንጭ ከመሆን አልፎ፣ ለበርሃማው አካባቢ አዲስ ሕይወት የሚሰጥ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ለመፍጠር የበቃው ግድብ ሲጠናቀቅ፤ ኸርበርት ሁቨር ስልጣን ላይ አልነበሩም። እንደመታደል ሆኖ የእኛው የቀድሞ ጠ/ሞኒስትር መለስ ዜናዊም የግድቡን የመሰረት ድንጋይ ጥለው ግንባታውን ቢያስጀምሩም መርቀው ለመክፈት ሳይታደሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡
በኮሰራይ ወንዝ ላይ፣ በኛው ቋንቋ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታውን ያስጀመሩት ሁቨር፤ የስልጣን ዘመናቸው በምርጫ ተቋጭቷል። በምትካቸው ስልጣን የተረከቡት ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 30ቀን 1935 ዓ.ም ግድቡን መርቀው ከፈቱት። “ቦልደርስ ዳም” ነበር የሚባለው፡፡ ስሙ የተለወጠው በ1947 የአሜሪካ ኮንግረስ ሁቨር ዳም ተብሎ እንዲሰየም ባሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡ የኛ ግድብ ግን፣ ገና ሳይጀመር ነው ስሙ የተለወጠው፡፡ “ሚሌኒየም ግድብ” የሚለው ስያሜ ተቀይሮ “ህዳሴ” ግድብ ተብሎ የተሰየመ፡፡     
  አስጎብኛችን በመሬት ውስጥ ቆይታችን የአስራ ሁለት ደቂቃ ትንተናዋን ጨርሳ ወደ ምድር ወለል ለመውጣት ሽቅብ ስንገሰግስ ፍርሃቴ አላገረሸም። ‘አንድ ነገር ቢመጣኮ እዚሁ ድፍት ብለን መቅረታችን ነው’ የሚለው ስጋቴ ለቆኝ ወደሌላ ሃሳብ ተጉዣለሁ። ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ!!  
የህዳሴው ግድብ ምርቱ ተትረፍርፎ፣ በድርቅና በረሃብ ለምትታወቀው አገራችን የጥንት ስልጣኔዋ እንዲታደስና የብልፅግና ዘመን እንዲበሰር ያደርግ ይሆን? የአገራችንን ገፅታ ይቀይር ይሆን? ግንባታው ሲጠናቀቅና እልፍ አእላፍት ሲጐበኙት፤ ኤሌክትሪክ ሲያመነጭና ለመስኖ ሲያገለግል ማየት ናፈቀኝ፡፡
“ይሁን!!” ብያለሁ፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ከአገር አልፎ ለጎረቤትም ያብራ!! ለመብላት የሚዘረጉ እጆች፣ ከአንድም ሶስት ጊዜ ጦም አይደሩ!! ስደትንና ድርቅን ያስወግዱ!!

Read 1681 times