Print this page
Monday, 07 April 2014 15:40

“የንጉሡ ገመና” ተረት-ተረት ነው

Written by  አክሊለ ብርሃን መኮንን ኃ/ሥላሴ
Rate this item
(21 votes)

      በአቶ ሥዩም ጣሰው ተጽፎ በአቶ ግርማ ለማ ለህትመት የበቃውን “የንጉሡ ገመና”ን ያነበብኩት በመገረምና በማዘን ሲሆን ይህንኑ ስሜቴን ለኢትዮጵያዊያን በማንፀባረቅ የልጅ ልጅነቴን፣ የውዴታ ግዴታ ለመወጣት በማሰብ በአጭሩ መልስ መስጠትን ወሰንኩ፡፡
በመሠረቱ የአያቴ የቀ.ኃ.ሥ. አልባሽ ነበር የተባለውት ሟች አቶ ስዩም ጣሰው፤ ከበርካታ የንጉሱ አልባሾች መካከል አንዱ እንጂ ብቸኛ አልባሽ ስላልነበር፣ የእሱን ምስክርነት እንደ ወንጌል ቃል ወስዶ አሜን ማለት ኃላፊነት ከሚሰማውና የቀ.ኃ.ሥ(ን) ሥራ ከሚያውቅ ዜጋ የሚጠበቅ ስላልሆነ፣ ህዝብ በመጽሐፉ ላይ የሰፈሩትን በቃለ አጋኖ የተዋቡ መሠረተ ቢስ ወሬዎች ይቀበለዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይልቁንም መጽሐፉን ካለአቅሙ በማግነንና በማጦዝ ለመቸብቸብ የታቀደ መሆኑን በሚገባ የሚያመለክት ክስተት ነው፡፡
የቀ.ኃ.ሥ የግል ኑሮ ከሚወዱትና ይወዳቸው ከነበረው ሕዝብ የተሰወረ አልነበረም፡፡ ስለሆነም ደራሲው በስም ላጲስ ብዕራቸው ያሰፈሯቸው አስነዋሪ ድርጊቶች፣ ከቀ.ኃ.ሥ ማንነት ጋር ግንባር ለግንባር የሚጋጩ እንጂ የሚዋሃዱ አይሆኑም፡፡
ቀ.ኃ.ሥ(ን) አንቆ ገድሎ አልባሌ ቦታ ለ16 ዓመታት ቀብሯቸው የነበረው ደርግና የደርግ ተከታዮች፤ እንደ ከአሁን በፊቱ ዛሬም የቀ.ኃ.ሥ ስምና ሌጋሲን ጥላሸት ለማልበስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ “እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም” እንደሚባለው ዛሬ የቀ.ኃ.ሥ እውነተኛ ማንነት ከትውልድ አገራቸው ባሻገር፣ በዓለም ዙሪያ እየተዘከረ የሚገኝበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
“ዘር ከሐረግ ይጎትታል” ተብሎ እንዳይፈረጅብኝ፣ የኔን መልስ እዚህ ላይ በመግታት፣ ዛሬ በሕይወት ያሉ የቀ.ኃ.ሥ የቅርብ ረዳቶች፣ አልባሾች፣ የቤተ መንግሥቱ ሹማምንቶች መጽሐፉ ላይ ስለሰፈሩት አስጸያፊ “ድርሰቶች” የእውነተኛ ምስክርነታቸውን በመስጠትና ለእውነት በመቆም፣ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ላበረታታቸው እወዳለሁ፡፡
ቀ.ኃ.ሥ መላ ሕይወታቸውን ለሀገራቸውና ለሚወዱት ህዝባቸው ትርጉም ያለው ሥራ ሰርተው ያለፉ ናቸው፡፡ እንደ ማናቸውም መሪ፤ ታሪክ የራሱ የሆነ ፍርድ ወቅቱን እየጠበቀ ይሰጣል፡፡ ሰዎችን ስም በማጥፋት የሚገኝ ሀብት ግን እንደ ጉም የማይጨበጥ መሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ አዲስ አድማስ ጋዜጣ አስተያየቴን ተቀብሎ ለማውጣት በመፍቀዱ የተሰማኝን እርካታ የምገልጸው በታላቅ ምስጋና ነው፡፡

Read 11458 times