Monday, 07 April 2014 15:43

የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ባለሙያና ኢንቬስተር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

         በአንድ እጇ አሜሪካ ውስጥ በሌላው እጇ አፍሪካ ውስጥ ስኬታማ ሥራ ፈጣሪ የቢዝነስ ባለሙያ የሆነችው ሶፊያ በቀለ እሸቴ፣ ወንዶች በገነኑበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኩባንያ አስተዳደር፣ እንዲሁም በስጋት አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ አንቱ የተሰኘች ባለሙያ ነች። በመረጃ (በኢንፎርሜሽን) ደህንነት፣ ጥበቃና ምርመራ ዙሪያ በአለማቀፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ውስጥ ለበርካታ አመታት የሰራችው ሶፊያ፤ እጇን ወደ አፍሪካ በመዘርጋት እንደ አገር ግንባታ ሊቆጠሩ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አከናውናለች። ለአፍሪካ ህብረት እና ለኢትዮጵያ ፓርላማ የተቀናጀ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓቶችን ዘርግታለች።
ከዚያም የኢንተርኔት ግንኙነትን ከአደጋ ለመጠበቅ በሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎችና እርምጃዎች ዙሪያ የኩባንያ አስተዳደርና የስጋት አያያዝ አማካሪ ሆና ሰርታለች። የኩባንያ ግንባታና የኮሙኒኬሽን አማካሪ በመሆን የአሜሪካ ኩባንያዎችን ከማገልገሏ በተጨማሪ፣ በአለማቀፍ ደረጃም የኢንተርኔት ፖሊሲ አማካሪ ሆናለች። በቅርቡ ደግሞ፣ ዶትኮኔክት አፍሪካ ትረስት (ባለአደራ) እንዲሁም ዶትኮኔክትአፍሪካ ረጂስትሪ ሰርቪስስ ሊሚትድ የተሰኙ ተቋማትን መስርታለች። በዚህም በመላው አለም የሚኖሩ አፍሪካዊያንን በመወከል .africa የተሰኘ የኢንተርኔት አድራሻ ስርወ-ስያሜ ለመፍጠርና በበላይነት ለማስተዳደር ጥያቄ አቅርባለች።  በሰኔ 2004 ዓ.ም ማመልከቻ ያስገባችው፤ አሜሪካ ለሚገኘውና የኢንተርኔት አድራሻዎችን ለሚያስተዳድረው አትራፊ ያልሆነ አለማቀፍ ድርጅት ICANN ነው። ድርጅቱ ውስጥ በምክር ቤት አባልነት ትሰራ በነበረበት ወቅት ነው የዶትአፍሪካ ፕሮጀክቷን የጀመረችው። ዶትኮኔክትአፍሪካ የተሰኙ ተቋሞቿ፤ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። ተቋሞቿ Yes2dotAfrica  በሚል መሪ ቃል ለስድስት አመታት ያካሄዱት አለማቀፍ የግንዛቤ ማስፋፊያ ዘመቻ ተቀባይነትን አስገኝቶላቸዋል። ዘመቻው፤ በአፍሪካ ስም የኢንተርኔት አድራሻ የመፍጠር ጉዳይ ብቻ አይደለም። በመላው አለም የአፍሪካን መልካም ገፅታ ለመገንባት ልዩ እድል ይሰጣል። በዚያ ላይ፤ የአፍሪካ ሴቶችንና ወጣቶችን፣ በኢንተርኔት አብዮት ውስጥ በዋና ተዋናይነት የሚያሳትፉ በርካታ ፕሮጀክቶችንና እቅዶችን ለማፍለቅ ጥሩ መነሻ ይሆናል።
በአዲስ አበባ የተወለደችው ሶፊያ፣ በወላጆቿ የተደላደለ ኑሮና በጥሩ ትምህርት ነው ያደገችው። ኢትዮጵያ ውስት በተለያዩ የቢዝነስ መስኮች ስኬታማ በመሆን የሚታወቁት አባቷ አቶ በቀለ እሸቴ፤ የህብረት ባንክ እና የህብረት ኢንሹራንስ መስራችና የቦርድ አባል ነበሩ። በአገሪቱ በትልቅነታቸው ከሚታወቁ የገንዘብ ተቋማት መካከልት ህብረት ባንክና ኢንሹራንስ ተጠቃሽ ናቸው። ሶፊያ ከቢዝነሱ ዓለም ጋር የተዋወቀችው፣ ከአባቷ አፍ ነው። ስለ ራሳቸው ስራ ከጓደኞችና ከቤተሰብ አባላት ጋር ሲያወሩ እየሰማች፣ የቢዝነስን አሰራር ትምህርት ቀስማለች። ራስን ችሎ የመወሰንና የመኖር ጥቅምን ከአባቷ የተማረችው ሶፊያ፤ ከስጋት የፀዳ የቢዝነስ ሥራ እንደሌለና ከበርካታ ስጋት አዘል የቢዝነስ አማራጮች መካከል የተሻለውን መርጦ የመግባት ድፍረት አስፈላጊ እንደሆነም መሰረታዊ እውቀት አስጨብጠዋታል።
እናቷ ሲስተር ሙሉዓለም በየነ፣ በሙያቸው ለበርካታ ዓመታት የሰሩ ነርስ ሲሆኑ፣ የማምለክ ያህል በፍቅር ታከብራቸዋለች። ርህራሄንና ደግነትን የተላበሱ በጣም ሃይማኖተኛ ሴት ነበሩ።  በተደላደለ ኑሮ ውስጥ ምንም ሳይጎድልባት ያደገችው ሶፊያ፤ ጥራት ያለው ትምህርት በማግኘትም እድለኛ ነች። ከታላቅ እህቷ ጋር የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በአዲስ አበባ ናዝሬት ስኩል ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች፣ ከታላቅ እህቷ ጋር አሜሪካ ሄደው ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ስፖንሰር ስለተገኘላቸው፤ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያ በረረች። በእርግጥ የዩኒቨርሲቲ ወጪያቸውን የሸፈኑት ወላጆቻቸው ናቸው። ከአሜሪካ ኑሮ ጋር መላመድ ለእህትማማቾቹ ፈተና እንደነበር ሶፊያ ስታስታውስ፤ ከተማ ውስጥ ወዲህ ወዲያ ለማለት እንኳ እንደተቸገሩ ትናገራለች። ወቅት የሚከተል የአሜሪካ ዘመነኛ ባህልን በቅጡ ለመገንዘብና መውጪያ መግቢያውን ለማወቅ ጊዜ የፈጀባቸው ሶፊያና እህቷ፤ የራሳቸውን ባህል እንደያዙ የአሜሪካዊያን ሕይወት ውስጥ መቀላቀል ቀላል አልሆነላቸውም። ደግነቱ፤  ጥራት ባለው የናዝሬት ስኩል ትምህርት የታነፁት እህትማማቾች፣ በሳን ፍራንሲስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከሌሎች ተማሪዎች ልቀው ለመገኘት አልተቸገሩም። ለነገሩማ ለተወሰነ ጊዜ ቢደነጋገርባቸውም ከአሜሪካ ኑሮ ጋር መቀላቀላቸው አልቀረም። ከጊዜ በኋላማ ሶፊያ የአሜሪካን ሕይወት መውደድ ጀመረች። ለካ አሜሪካ ልዩ ፀጋ አላት። የአገሪቱ የነፃነት መንፈስ ግሩም ነው፤ ሕይወትን ለማሻሻልና ለመሥራት  ሰፊ እድል የሚገኝባት አገር መሆኗም ድንቅ ነው። ባየችውና ባስተዋለችው መልካም ህይወት ለአሜሪካ ፍቅር ያደረባት ሶፊያ፤ ወደፊትም ያንን አገር ሳትለቅ ነው አፍሪካ ውስጥ እግሯን መትከል የምትሻው። በቢዝነስ አናሊሲስና በመረጃ ሥርዓት (በኢንፎርሜሽን ሲስተምስ) የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከያዘች በኋላ፤ በጎልደን ጌት ዩኒቨርስቲ በማኔጅመንት የመረጃ ሥርዓት ማስተርስ ዲግሪ አግኝታለች። ሥራ ፍለጋ ላይ ታች አላለችም። ሥራው ራሱ ነው እሷን ፍለጋ ዩኒቨርሲቲው ድረስ የመጣላት። በዩኒቨርስቲ እጅግ የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተመራቂዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው ሳይወጡ ነው በተለያዩ ምርጥ ኩባንያዎች ተመልምለው ሥራ የሚቀጠሩት። ሶፊያም በወቅቱ በግዙፍነታቸው ከሚታወቁ ባንኮች መካከል አንዱ በሆነው ባንክ ኦፍ አሜሪካ ለኮምፒዩተር ኦዲቲንግ ሥራ ተቀጠረች። በእርግጥ በቀጥታ ሥራ አልጀመረችም። የመረጃ ሥርዓት ደህንነትና ቅልጥፍና፣ በተለይ ደግሞ የመረጃ አጠቃቀምና ጥበቃ ላይ ያተኮረው የኮምፒዩተር ኦዲቲንግ ሥራ፣ ልዩ እውቀት የሚያስፈልገው በጣም አዲስ የሙያ መስክ ስለነበረ፤ ሶፊያና አብረዋት የተቀጠሩ ባልደረቦቿ ባንክ አሜሪካ ውስጥ ተጨማሪ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። እዚህ ወንዶች የገነኑበት ሙያ ውስጥ ነው፤ ሶፊያ ስለ ወንዶች ብዙ ማወቅ የጀመረችው። ወንዶች በበዙበት ድባብ ውስጥ እንዴት ስኬታማና ውጤታማ መሆን እንደምትችል ትምህርት የቀሰመችውም፤ በዚሁ ሥራዋ ነው። ዩኒየንባንካል ወደ ተሰኘው ኮርፖሬሽን ከተሻገረች በኋላ፣ ወደ ሥራ አስኪያጅ የሃላፊነት ደረጃ እድገት አግኝታ ሠርታለች። ከዚያም በአለም በትልቅነታቸው ከሚታወቁ የአካውንቲንግ አገልግሎትና የኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅቶች መካከል አንዱ በሆነው ኩባንያ ተቀጠረች - በፕራይስ ወተርሃውስ ኩፐርስ። ኢንሹራንስና ባንክ የመሳሰሉ ድርጅቶች ገንዘብ ወይም የዋስትና ሰነድ ታቅፈው አይቀመጡም፤ በትርፋማ ነገር ላይ ሊያውሉት ይሞክራሉ እንጂ። ግን ደግሞ፤ ገንዘብ ሲፈልጉ ወዲያውኑ መልሰው ሊያገኙት ይገባል። መፍትሄው፤ ከበርካታ ኩባንያዎችና ተቋማት አክሲዮን ወይም ቦንድ መግዛት ነው። ገንዘባቸውን ትርፋማ ያደርግላቸዋል፤ በአፋጣኝ ገንዘብ ካስፈለጋቸውም የገዙትን አክስዮንና ቦንድ መሸጥ ይችላሉ። እንዲህ በአክስዮንና  በቦንድ ግብይት ገንዘብን ውጤታማ የማድረግ አሰራር፣ ፓርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት ይሉታል። ነገር ግን እጅግ አዋቂነትንና ብልህነትን ስለሚጠይቅ፤ በባለሙያ አማካሪዎች አማካኝነት መመራት ይኖርበታል። ፕራይስ ወተርሃውስ ኩፐርስ በተሰኘው ኩባንያ ውስጥ የሶፊያ ዋና ሥራም፣ ለተለያዩ ደንበኞች የፖርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት አማካሪ ሆና በበላይነት መቆጣጠር ነበር። የሶፊያን ምክር ከሚቀበሉ ደንበኞች መካከልም በእንግሊዝ ከአራቱ ትልልቅ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው በርክለይ ባንክ ይገኝበታል። ከጤና አገልግሎት ኢንሹራንስ ጋር ለተያያዙና ለሌሎች ኩባንያዎችም የአማካሪነትን ስራ በበላይነት መርታለች። እዚህ ነው ሥራ መምራትን የተካነችው። በአይነትና በመጠን ከሚለያዩ በርካታ ባለሙያዎችና ቡድኖች ጋር የመስራት ችሎታዋ፣ ውስብስብና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመምራት ጥበቧና ብቃቷ ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋገረ። ይሄኔ ነው የራሷን ድርጅት ለመክፈት የሚያስችል ክህሎትና በራስ የመተማመን መንፈስ መጎናፀፏን እርግጠኛ የሆነችው።
ኩባንያውን ከለቀቀች በኋላ፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስትዟዟር አንድ አመት አሳለፈች። የሥራ ፈት ዙረት አይደለም። ከአሜሪካ አውሮፓ፣ ከኤስያ ላቲን አሜሪካ ድረስ ወደ ተለያዩ አገራት የተጓዘችው፣ በየአገሩ ያለውን የቢዝነስ አሰራርና ባህል እንዲሁም፤ የኢንተርኔትና የቴክኖሎጂ ደረጃ ለመመልከት ነው። አሜሪካ ውስጥ ሆና በየአህጉሩ ገና በመመንደግ ላይ ለሚገኙ አገራት የቴክኖሎጂ ሽግግር የማካሄድ አላማና የቢዝነስ ውጥን የያዘችው ሶፊያ፣  በ1990 ዓ.ም ሲቢኤስ ኢንተርናሽናል በሚል ስያሜ የራሷን ኩባንያ መሰረተች። በተመሳሳይ አላማም ኢትዮጵያ ውስጥ በ”ሲስተም ኢንተግሬሽን” ሥራዎች ላይ ያተኮረ “ኤስቢኮሙኒኬሽንስ ኔትዎርክ” የተሰኘ ኩባንያ አቋቋመች። ለአፍሪካ ህብረት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በጨረታ ተወዳድራ ያሸነፈችው ሶፊያ፣ ለጨረታው የመረጠችው የቢዝነስ ዘዴ፣ በኢትዮጵያ ያን ያህልም የተለመደ አልነበረም። የፕሮጀክት አመራር ላይ በተመሰረተ የቢዝነስ ዘዴ ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሙያዎችንና የተለያዩ ድርጅቶችን አሰባስባ በማስተባበር ጨረታውን ካሸነፈች በኋላ፤ ስራውንም በተመሳሳይ መንገድ አጠናቅቃ ለአገልግሎት አብቅታለች። ገና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባላደገበት አገር፣ በግዙፍነቱ ተጠቃሽ የሆነ የአፍሪካ ህብረት ፕሮጀክት ላይ ውጤታማነቷን ያስመሰከረችው ሶፊያ፤ ወደ ሌላ ትልቅ ፕሮጀክት አመራች። ለኢትዮጵያ ፓርላማ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት፤ እንደገና ዳይሜንሽን ዳታ የተባለ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጣ ቡድን በመፍጠር ጨረታ አሸንፋ ፕሮጀክቱን በስኬት ፈፅማለች። ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ውዝግብ የተነሳ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰፊ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ የውዝግቡ መነሻ አድሎአዊ አሰራርን በመቃወም ሶፊያ ያቀረበችው ጥያቄ ነው። የግዢና የኮንትራት ሥርዓቱ ላይ ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራር መኖሩን በመቃወም ተከራክራ ለማሸነፍ የበቃችው ሶፊያ፤ የመንግስት የግዢና የኮንትራት አሰራር እንዲሻሻል፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትንም እንዲላበስ ክርክሯ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ታምናለች። በ1994 ዓ.ም በግሉ ዘርፍ የተቋቋመ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ የአክሲዮን ገበያ ለመመስረት በማቀድ ለመንግስት ያቀረበው ሃሳብ ስህተቶችና ጉድለቶች እንደነበሩት የምትገልፀው ሶፊያ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ ተቃውሞ እንዳስተጋባች ታስታውሳለች። በዚያው አመት መጨረሻ ላይም ለአክሲዮን ገበያ የቀረበው ሃሳብ በመንግስት ውድቅ ተደርጓል። ምናልባትም በወቅቱ ባስተጋባችው አቋም፣ የኋላ ኋላ የኢትዮጵያ እህል ገበያ እንዲመሰረት መንገዱን የሚጠርግ ነበር ብላ ታስባለች። ኢትዮጵያ ውስጥ አዘውትራ የሰራችበት ያንን ጊዜ ትወደዋለች። ከዘመድ አዝማድም ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ አስችሏት ነበር። በእርግጥ እያሰለሰች ወደ አሜሪካ መመላለሷ አልቀረም። ኩባንያ ወደሚገኝበት ወደ ካሊፎርኒያ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ቁሳቁስ አቅራቢዎቿ ወደሚገኙበት ሚያሚ በተደጋጋሚ ተመላልሳለች። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለአገሯ ተጨባጭ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ፕሮጀክት ያከናወነችበት ወቅት ስለሆነ ግን ያንን ጊዜ ትወደዋለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረችውን የፓርላማ ፕሮጀክት እንዳጠናቀቀች፣ ብዙም ሳይቆይ አሜሪካ ውስጥ ሌላ የቢዝነስ እድል ታያት። በአሜሪካ በግዙፍነቱ 7ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ኢንሮን ኩባንያ እንዲሁም በቴሌኮሙኒኬሽንና በኢንተርኔት ቢዝነስ በትልቅነቱ የሚታወቀው ዎርልድኮም ኩባንያ በኪሳራ መዘፈቃቸው በድንገት ይፋ የወጣበትና የዓለም መነጋገሪያ የሆኑበት ወቅት ነበር - ጊዜው።  በእርግጥ ኩባንያዎቹ በድንገት አልከሰሩም። ቅጥ ባጣ የኩባንያ አመራርና በአሳሳች የመረጃ አቀራረብ ለበርካታ አመታት ኪሳራቸው እንዲደበቅ ተደርጓል። የተደበቁት ጉዶች ሲያብጡ ከርመው ድንገት ሲፈነዱ፤ በቢዝነስ ዓለም ከታዩት ትልልቅ ቅሌቶች ተርታ የሚመደቡ ሆነው አረፉት። ታዲያ ለእንዲህ አይነት የመረጃ አጠቃቀምና የኩባንያ አመራር ችግሮች መፍትሄያቸው ምንድነው? ችግሮች ሲኖሩ፣ መፍትሄ ይዞ የሚመጣ ሰው የቢዝነስ እድል ያገኛል።  ሶፊያም በዚህ ምክንያት ነው የቢዝነስ እድል የታያት። የመረጃ ስርዓት ቅልጥፍናንና አጠቃቀምን የመመርመር ሙያዋ ይታወቃል። በትልልቅ ኩባንያዎች ውስጥ በሥራ አመራር የሃላፊነት ደረጃ ሠርታለች። የኩባንያ ንብረቶችን በአግባቡ ለማስተዳደርና ለመምራት፤ የመረጃ ሥርዓት የቱን ያህል ቁልፍ እንደሆነ ታውቃለች። በዚህ ዙሪያ በአማካሪነት ለመስራት በከፈተችው የቢዝነስ ሥራ፣ ካሊፎርኒያ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ የሲልከን ቫሊ ኩባንያዎች የምክር አገልግሎት ሰጥታለች - ለኢንተል፣ ጀኔነቴክ፣ ኦንስክሪን ወዘተ።  ለአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ (ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ) እንዲሁም ለሌሎች ተቋማትም አገልግሎቷን በማስፋፋት ስኬታማ ቢዝነስ ገንብታለች። በኩባንያ ግንባታና በኮሙኒኬሽን እቅዶች ላይም ለበርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች በአማካሪነት የሰራችው ሶፊያ፣ የሥራ ፈጠራ ኢንቨስትመንት (ቬንቸር ካፒታል)፣ የኮንትራት ሃላፊነትና አፈፃፀም፣ የገበያ እድል ማመቻቸትና ማስፋት፣ የገበያ ድርድር፣ የቢዝነስ እቅድ አመዛዘንና አፈታተሽ፣ የዓለማቀፍ  ትስስር ስትራቴጂያዊ እቅድ አዘገዳጃጀት፣ የሕዝብ ግንኙነት ስትራቴጂ አዘገጃጀትና አፈፃፀም፣ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ የአማካሪነት አገልግሎት አስፋፍታለች።
አዲሱ የአማካሪነት ቢዝነሷን እያስፋፋች ሳለ ነው ተጨማሪ የሥራ አቅጣጫ የሚፈጥርላት አጋጣሚ የተፈጠረው። የኢንተርኔት አድራሻዎችን በሃላፊነት ለማስተዳደር፣ በዓለማቀፍ ደረጃ በመንግስታዊና በግል ዘርፍ ተቋማት ትብብር የተመሰረተው ድርጅት (ICANN)  ውስጥ የምክር ቤት አባል እንድትሆን ተመረጠች። ምክር ቤቱ አንዱ ትኩረት የኢንተርኔት አድራሻ ስርወ-ስያሜ ነው። ለምሳሌ .com, .edu, .gov, .net, .org... የመሳሰሉ አዳዲስ ስርወ-ስያሜዎች ስራ ላይ የሚውሉት በምክር ቤቱ ከታዩና ውይይት ከተካሄደባቸው በኋላ ነው። በስርወ ስያሜዎች አጠቃቀም ላይ በአማካሪነት እንድትሰራ ሃላፊነት የተሰጣት ሶፊያ፣ የኢንተርኔት አድራሻ አሰያየም ላይ መላው የዓለም ማህበረሰብ የመሳተፍ እድል እንዲያገኝ የሚያግዝ የፖሊሲ መመሪያ በማርቀቅ አቅርባለች። ላበረከተችው አስተዋፅኦም በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷታል - Internationalized Domain Resolution Union (IDRU) በተሰኘ ቡድን። ሶፊያ የኢንተርኔት አድራሻዎች ላይ በአማካሪነት በምትሰራበት ወቅት ነው፣ ለአፍሪካ ልዩ ትርጉም የያዘ ሃሳብ የመጣላት። .africa የተሰኘ የኢንተርኔት አድራሻ ስርወ-ስያሜ መፍጠርና ሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል በመገንዘብም፣  በ1998 ዓ.ም ዶትኮኔክትአፍሪካ የተሰኘ እቅዷን ማስተዋወቅ ጀመረች። እቅዷም፣ በተለይም በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ፈጣን ድጋፍ አግኝቷል። የመሪነቱን ሃላፊነት በመውሰድ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎችን አሰባስባ ማመልከቻ በማዘጋጀት፣ በ2004 ዓ.ም ጥያቄዋን ICANN አስገብታለች። .africa የሚል የኢንተርኔት ስርወ-ሥያሜ ሥራ ላይ እንዲውል የቀረበው ማመልከቻ ላይ  በ2005 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል። ሶፊያና ባልደረቦቿ አወንታዊ ምላሽ ያግኙ እንጂ፣ የአፍሪካን መልካም ገፅታ በሚገነባ መንገድ ስርወ-ሥያሜውን ለማስጀመር ዝግጁ ነች። ከዚህም ጋር በማያያዝ፤ የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች በቴክኖሎጂ መስክ ብቃትና አቅም የሚያዳብሩበት፣ እንዲሁም ቢዝነሳቸውን በቴክኖሎጂ የሚያጎለብቱበት ብዙ አይነት እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል እያለች በጉጉት ታስባለች። የተራቀቀ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ጨምሮ ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን የመሰለ ሃያል መሳሪያ ወደ ታዳጊ አገራት ለማሸጋገር ባከናወነችው ሥራ ላይ ገለፃ እንድትሰጥ በተደጋጋሚ እየተጋበዘች ተመክሮዋን በተለያዩ መድረኮች አካፍላለች። በኒውዮርክ በተካሄደ የተባበሩት መንግስትት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደ የአፍሪካ መሪዎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስብሰባ፣ እንዲህም በካሊፎርኒያ የስታንፎርድ ሴት የቢዝነስ ባለሙያዎች ስብሰባ ላይ ተሞክሮዋን አቅርባለች።
ሶፊያ ከሙያ ሕይወቷ በተጨማሪ በማህበራዊ አገልግሎቶች ውስጥም ለመሳተፍ ጊዜ አላጣችም። በሮታሪ ክለብ፣ በመረጃ ሥርዓት ኦዲትና ቁጥጥር ማህበር፣ በጎልደን ጌት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ማህበር የዳሬክተሮች ቦርድ ውስጥ የምትሳተፈው ሶፊያ፣ የሳን ፍራንሲስኮ ቤይ የኢንተርኔት ማህበረሰብን ከመሰረቱት ሰዎች አንዷ ከመሆኗም በላይ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ናት።
በአብዛኛው ወንዶች በገነኑበት የሙያ ዘርፍ ውስጥ በመስራት ካስተዋለችው ተነስታ ስትናገር፣ ሴቶች ተቀባይነት ለማግኘት በላቀ ብልሃትና ትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ትላለች። ዋናው ነገር፣ በቁርጠኝነት የሙጢኝ ብሎ መሥራት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሥራዎችሽ እንዲታወቁና እንዲታዩ ማድረግ ያስፈልጋል። ስራዎችሽ ተደብቀው ከቀሩ፣ መልካም ስምንና ዝናን መገንባት አትችይም። የራስሽን ታሪክና የራስሽን ስም ለመገንባት ኢንተርኔትና ማህበራዊ ድረገፆች በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው በማለት እሷም እንደምትጠቀምባቸውና እንደምታደንቃቸው ትገልፃለች።
ሶፊያ ለኢትዮጵያ ያላት የወደፊት ተስፋ ብዙ ነው። ከፍተኛ የኢኮኖሚ እምቅ አቅሟን ተጠቅመው እድገትን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ፣ በትምህርትና በፈጠራ ችሎታ የበለፀጉ ኢትዮጵያውያን ይታይዋታል። ኢትዮጵያዊያን ጥልቅ ሃይማኖታዊ ትውፊት የታደሉ በመሆናቸው፣  ስርዓትን የሚከተሉና የህግ የበላይነትን የሚያከብሩ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ሰፊ የመናገር ነፃነት እንዲሁም ሰፊ የግል ኢንቨስትመንት ነፃነት እንዲኖራቸው ትመኛለች። በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ አገራቸውን ለመጥቀም የሥራ ፍሬያቸውንና ትምህርታቸውን ይዘው መምጣት ይፈልጋሉ። የኢንቨስትመንት ነፃነት በተሻለ ደረጃ እንዲስፋፋላቸውም ምኞቷ ነው።
ምንጭ፤-
www.ethiopianwomenunleashed..org

Read 3698 times