Monday, 07 April 2014 15:44

እነዚህ መረጃዎች ይበጁ ይሆን? እናትና ልጅ

Written by  አበበ ተሻገር abepsy@yahoo.com
Rate this item
(1 Vote)

          አለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) የእናቶችን ጡት ወተት በተመለከተ የሚከተሉትን እውነቶች ይነግረናል፡፡ ልጁ ከተወለደ (ለፁ ቢጀምር ከዚሁ ጋር የእናቱ ጡት ወተት ቢቀጥል ጤናማ የአካልና የአእምሮ ሥርዐት ይኖረዋል፡፡ ይህ ሂደት ደግሞ ለሁለት ዓመታትና ከዚያም በላይ ቢቀጥል ደግ ነው፡፡  
ሁፍ እንዲመቸን በወንድ ፆታ እንግለፀው እንጂ መረጃው ሁለቱንም ፆታ ይመለከታል እስከ ስድስተኛው ወር የእናት ጡት ወተት ብቻ ሌላ ምንም ነገር (ንፁህ ውኃም ቢሆን)  ሳይጨምር መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ከሥድስት ወራት በኋላ የተፈጨ አትክልትና ፍራፍሬ ጋር መተዋወቅ
የእናት ጡት ወተት ልጅ ከተወለደ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ መጀመር ይቻላል፡፡ የእናት ጡት ወተት በመጀሪያዎቹ ስድስት ወራት የግዴታ ጉዳይ እንጂ የምርጫ አይደለም፡፡ ልጁ በእነዚህ ጊዜያት በመጠን ምን ያህልና በምን ያህል ሰዓት ልዩነት የእናቱን ጡት ወተት ማግኘት አለበት ከተባለ የቻለውን ያህልና በፈለገው ሰዓት ያውም ቀንም ማታም በሚል መረጃውን የአለም አቀፍ የጤና ድርጅት ያሰምርበታል፡፡
የእናት ጡት ወተት በዚህ ደረጃ በተደጋጋሚ በተለያዩ ድርጅቶች በመንግስታትና በባለሞያዎች በአንክሮ ልጆች በተቻለ መጠንና ለረዥም ወራት እንዲያገኙ ይጎተጎታል እኔስ ይህን ተከትዬ በዚህ ገፄ ላይ ለምን ማስነበብ ፈለኩ?
እንዲህ ነው... የእናት ጡት ወተት ትርፉ ለሁለቱም ለልጅም ለእናቱም ነው፡፡ ለልጁ ሠውነትና ጤንነት ነው። የተመጣጠነ፣ የተመጠነ፣ የተጣራ፣ ንፅህናው የተጠበቀ ምግብ ነው፡፡ ለልጅ ከእናት ጡት ጋር የሚወዳደር ምንም ዓይነት ምግብ የለም በሁሉም መግለጫ የተዋጣለት (ideal food) ምግብ ነው፡፡ በልጆች ላይ ተቅማጥና (diarrhara) የሳንባ ምች (Pneumonia) አዘውትረው የሚከሰቱ አደገኛ በሽታዎች ናቸው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ለልጆች ሞት በዋነኛነት የሚጠቀሱ በሽታዋችም እነዚሁ ናቸው፡፡ ታዲያ የእናት ጡት ወተት በውስጡ እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል ንጥረ ነገር የያዘ ነው። ስለዚህ አዘውትራ በፈለገችው መጠንና ሰዓት የእናቷን ጡት ማግኘት የቻለች አራስ ልጅ ለእነዚህ በሽታዎች አትጋለጥም፡፡ በሌላ አንፃር የእናት ጡት ወተት ምንም ዝግጅት የማይፈልግ፣ ላሙቀው ውሃ ውስጥ ልንከረው የማይባል በዋጋም የተሻለ (እናት ለወተት የሚረዳትን ከተመገበች) ነው ሊባል ይችላል፡፡ (የእናትና የልጅ ፍቅር በዚሁ ገመድ ይያያዝ ይሆን የዚህ ፀሁፍ አቅራቢ ሌላ ሞያ በሆነው ሥነ ልቦና (Psychology)  ምግብ (nourishment) በእናትና በልጁ መሃከል የፍቅር ሰንሰለት ይዘረጋል የሚለውን የቀደመ የፍሮይድ ሃሣብ በያዝነው ክፍለ ዘመን የተከሰተው ሌላው ሳይኮሎጅስት ጆን ቦልቢ በፍፀም በሚል የራሱን ቲዮሪ ይዞ ተነስቷል። ይህን በተመለከተ ሌላ ሰፋ ያለ ወግ ይዥ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡ በጥቅሉ ግን የእናት ጡት ወተት ለልጅ ምግብ ብቻ ነው የሚለው ሃሳብ በሙከራዎች ሁሉ ሊረጋገጥ ችሏል፡፡)
ለእናቶችስ... በኋለኛው እድሜ እናቶች ለጡትና የማህጿን ካንሰር እንዳይጋለጡ ያግዛል፡፡ ልጁ የእናትን ጡት ወተት በመጥባቱ ወይም እናት ልጇን በማጥባቷ በእርግዝና ወቅት የጨመረችውን ክብደት እንድትቀንስ ይረዳታል ወፍራም ከሆነች ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ነው ባይባልም ልጅ በተወለደ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ እናት የምታጠባ ከሆነ እርግዝና እንዳይከሰት ይረዳል፡፡
እነዚህን በአብይነት ጠቀስን እንጂ የእናት ጡት ወተት ለልጆች በልጅነታቸው ላለው እድሜ ብቻም ሳይሆን በወጣትነታቸውና በጉልምስናቸውም የራሱ የሆነ ጥቅም አለው፡፡ የእናት ጡት ወተት በተገቢው ሁኔታ ያገኘ ልጅ በወጣትነቱ ለክብደት ወይም ውፍረት ችግርና ለሥኳር በሽታ የመጋለጥ እድሉ የቀነሰ ሲሆን የአእምሮ ብስለቱ የተሻለ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
አፍላነት
እስክ 16 ሚሊዩን የሚደርሡ እድሜአቸው ከ16 እስከ 19 ያሉ ታዳጊ ውጣቶች በየአመቱ ይወልዳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በታዳዊዎቹ ሀገራት የሚገኙ ናቸው፡፡ በአብዛኛው በወሊድ ጊዜ ለሚከሰት ሞትና ውስብስብ የጤና እክል የሚጋለጡትም ከጎልማሳ ሴቶች ይበልጥ በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ ጠለፋ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ስለ ወሊድ መከላከያዎች በቂ እውቀት አለመኖርና መከላከያዎቹን አለማግኘት ችግሩን የሚያባብሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡
***
በአለማችን አባዛኞዎቹ አጫሾች ማጨስ የሚጀምሩት በአፍላ የእድሜአቸው ጊዜ ነው ከ16-19 ዓመት፡፡ በዚሁ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እስከ 150 ሚሊዬን የሚደርሱ አፍላ ወጣቶች ሲጋራ አጫሾች ናቸው፡፡ የሲጋራ ማስታወቂያ መከልከል፣ ዋጋውን ማስወደድ፣ ከፍተኛ ታክስ መጣል፣ በአደባባይና ሰዎች አገልግሎት በሚያገኙባቸውና በሚበዙባቸው ቦታዎች እንዳይጨስ ማቀብ ብዙ ሀገራት አጫሻችን ለመቀነስና የሚያጨሱትን ሲጋራ ቁጥር መጠን ለመቀነስ ይጠቀሙበታል፡፡
ልጅነት
የመማሩን ያህል ሞት የሚበዛበት የእድሜ ክልል መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ልብ መንካቱ የማይቀር ነው፡፡ ህፃናት በሚወለዱበትና ከተወለዱ አንድ ወር እስኪሞላ ያለው ጊዜ ለህይወታቸው ከፍተኛ አደጋ ያለበት ወቅት ነው፡፡ መወለድ ከሚገባቸው ጊዜ ቀድሞ መከሰት ይህም ያለ ባለሞያ እርዳታ ሲሆን፣ በወሊድ ጊዜ በሚያጋጥም የንፁህ አየር (ኦክሲጅን) እጥረት ወይም መታፈንና ከባክቴሪያ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ኢንፌክሽን ምክንያት ህፃናት በመጀመሪያው ወር ላይ የሞት አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ ከባክቴሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ በአለማችን ከ700,000 በላይ የሚሆኑ ህፃናትን እናጣለን። ይህ ችግር በተለይ ከንፅህና ጉድለት በተያያዘ የሚከሰት መሆኑ ይገለፃል፡፡  
የመጀመሪያውን ወር ተሻግረው እስከ አምስት አመታቸው ድረስ ደግሞ ህፃናት ህይወት አደጋ የሚሆኑት የሳንባ ምች (Pneumonia) ተቅማጥ (diarrhea) እና ወባ ናቸው በእያንዳንዱ ደቂቃ በዚችው በእኛዋ አለም አንድ ህፃን በወባ ምክንያት ይሞታል፡፡ እንዲህ ያለ ገለፃ ግራ አያጋባም? ይህ ማለት በሰዓት 60 ህፃናን በቀን ደግሞ...
እናት/ሴት
እናትነት ፀጋ ነው፡፡ እናት ወይም ሴት በመሆኗ በተሰጣት የእናትነት ፀጋ ምክንያት ደግሞ ትሞታለች። ያውም ብዙዎች፡፡ እናትነት ፀጋም ሞትም፡፡ እናቶችን ለሞት የሚዳርጉ አራቱ ዋና ዋና ምክንያቶች በወሊድ ጊዜ የደም መፍሰስ አደጋ፣ ከወሊድ ጋር የተያያዙ ኢንፌክሽኖች፣ ጤናማ ያልሆነ የጽንስ ማቋረጥ ተግባርና ጥንቃቄ የጎደለው መረጃ፣ በእርግዝናና ወሊድ ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት ችግር (hypertensive disorder) ናቸው፡፡ ይሁንና በጤና ክትትልና በጥንቃቄ በእነዚህ ችግሮች የሚመጣን ሞት ፀጋውን የሚቀማ አደጋን መከላከል ይቻል ነበር። የሚገርመው ሴቶች በጠቀስናቸው ምክንያቶች ሲሞቱ ወንዶች ደግሞ በከፍተኛ ቁጥር ከሚሞቱባቸው ስምንት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሁለቱ በመኪና አደጋና ራስን በማጥፋት በድብድብ እንደሆነ ይጠቀሣል፡፡ ከዚህ አንፃር ሞት ወደ ሴቶች ወይም እናቶች ራሱ ይሄዳል፣ ወንዶች ግን ራሳቸው ይሄዱለታል ልንል እንችላለን፡፡
በአመት በአለማችን 136 ሚሊዮን እናቶች ይወልዳሉ፡፡ ቢያንስ ያንኑ ያህል ቁጥር ህፃናት ይወለዳሉ ብለን ልንገምት እንሞክራለን፡፡ ይሁንና ቀደም ሲል በጠቀስናቸው ምክንያቶች በርካቶች የመጀመሪያውን ወራት አይሻገሩም፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታ እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ እናቶች ደግሞ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሚከሰት የጤና እክል ይዳረጋሉ፡፡ የሚሞቱባቸው ምክንያች በርካታ ናቸው፡፡
የእናቶች ሞትና ህይወት ከድህነትና ከባለፀጋነት ጋር መያየዙ አይቀርም፡፡ በኢኮኖሚ ባደጉት ሀገራት ወይም ከፍተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መሀከል የእናቶች ሞት አንድ በመቶ ያህል ብቻ ነው የሚከሰተው፡፡
በተመሳሳይ በድህነትና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚኖሩ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የጤና እክሎችና ሞት የበለጠ ተጋላጮች ናቸው፡፡ የትምህርት እድል ባላገኙ የገጠር እናቶች መካከል ደግሞ ችግሩ የበለጠውን እያመረረ ይሄዳል፡፡ እነዚህ እናቶች የሚኖርባቸው የአለማችን ክፍሎች ደግሞ ከሣሀራ በታች ያሉ የአፍሪካና የደቡብ እሲያ ባሉ ሀገራት ነው፡፡ ሳምንት በዚሁ አምድ እንገናኝ፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡

Read 4544 times