Monday, 14 April 2014 09:11

የአንድነት ፓርቲ ‹‹የእሪታ ቀን›› ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(1 Vote)

6 የፓርቲው አባላት የቅስቀሳ ወረቀት ሲበትኑ ተይዘው ታሰሩ
ዛሬ በአዳማ የውይይት መድረክ ያካሂዳል  
አንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ‹‹የእሪታ ቀን›› በሚል በዛሬው ዕለት ለማካሄድ ያቀደው ሠላማዊ ሰልፍ፤ በመንግስት ትእዛዝ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው አስታወቁ፡፡  
ፓርቲው በዛሬው እለት ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ፤ የቅስቀሳ በራሪ ወረቀቶችን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ሲበትኑ የነበሩ ስድስት ወጣት አባላት በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ኃላፊው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ አንድነት “የእሪታ ቀን” በሚል በዛሬው እለት ለማካሄድ አቅዶት ለነበረው ሰላማዊ ሰልፍ፣ ቀደም ብሎ ለመስተዳድሩ የሠላማዊ ሠልፍ ፈቃድ አሰጣጥ ቢሮ ማስታወቁን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ሁለት የተለያዩ ደብዳቤዎች ከቢሮው እንደደረሳቸው ተናግረዋል - አንድ ጠዋት፣ አንድ ከሰዓት በኋላ፡፡ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደሚሉት፤ የጠዋቱ ደብዳቤ ሠላማዊ ሰልፉ መፈቀዱን የሚገልፅ ነበር፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ የሚካሄድበትን አካባቢ በተመለከተ ግን እነሱ ያቀረቡትን እንዳልተቀበላቸው ይናገራሉ፡፡ የአንድነት እቅድ፤ ሰልፉ ከፅ/ቤቱ ከቀበና ተነስቶ በአራት ኪሎ፣ ቤልየር፣ አዋሬ፣ ሲግናል----አድርጎ ዳያስፖራ አደባባይ ላይ የሚያጠቃልል ሲሆን የሰልፍ ፈቃድ አሰጣጥ ቢሮ በበኩሉ፤ ሰልፉ ከቀበና ተነስቶ በምኒልክ በኩል አድርጎ፣ ጃን ሜዳ እንዲጠቃለል ነው የፈቀደው ብለዋል። እሱም ቢሆን ግን ከሰዓት በኋላ በሌላ ደብዳቤ ተሽሯል ይላሉ - አቶ ሀብታሙ። ሰልፉ መፈቀዱን የሚጠቁመው ሁለተኛው ደብዳቤ፤ ቀኑንና ቦታውን በተመለከተ ግን በሚቀጥለው ሳምንት በደብዳቤ እናሳውቃለን እንደሚል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  
የሠላማዊ ሠልፉ ዋነኛ አጀንዳ በአዲስ አበባ የተፈጠረውን የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ እና የትራንስፖርት ችግሮች ማስተጋባት እንደሆነ ተገልጿል። በሌላ በኩል ፓርቲው ‹‹ሥነ-ፅሑፍ ለነፃነት›› በሚል ርዕስ፣በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት  ዶ/ር ዳኛቸው ወርቁ በርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ፅሑፍ እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1555 times