Monday, 14 April 2014 09:42

“ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰላምታዬን ማስተካከል አለብኝ መሰለኝ…“ሠፈራችሁ መብራት አለ?”
ይቺን ስሙኝማ…ሦስት ሆነው አንዲት ደከም ያለች ‘ካፌ’ ውስጥ ሻይና ቦምቦሊኖ ነገሮች ይቀማምሳሉ፡፡ እናላችሁ፣ አንደኛው መቶ ብር ከኪሱ ያወጣና ይከፍላል፡፡ (እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ከዓመታት በፊት ማለትም ያኔ የብሩ ቁጥርና የመግዛት አቅሙ አቅም ተቀራራቢ በሆኑበት ዘመን ቢሆን ኖሮ…አለ አይደል…“መቶ ብሩን ከኪሱ መዠረጠው!” “አታምነኝም፣ መቶ ብሩን ከኪሱ ላጥ ሲያደርገው የደነገጥነው መደንገጥ!” ነበር የሚባለው!)
እናላችሁ…የሆኑ ለቲፕ የተተዉ የሚመስሉ ሳንቲሞችና የተጎሳቆሉ አንድ፣ አንድ ብሮች መልስ ተብለው በሳህን ላይ ይመጡላችኋል፡፡ እና ከፋይ ምን ቢል ጥሩ ነው… “መቶ ብር በሻይና በቦምቦሊኖ ብን ትበል! በቃ… መቶ ብራችን እኮ ሁሴን ቦልት ሆና አረፈችው!”
እውነትም ሁሴን ቦልት! አለች ስትሏት ውድም! የምር... የዘንድሮ መቶ ብር እኮ “ምን ገዛሁባት!” ሳይሆን “የት ጥያት ይሆን!” የምታሰኝ ነች!
እንግዲህ በዓልም እየመጣ ነው… ይሄኔ ‘ሞኞቹ’ ነጋዴዎች አሮጌ መሀረብ ይሁን የመጸዳጃ ቤት ወረቀት ያሳበጠው ኪሳችንንና ለምናልባቱ “ሆዴን ቢረብሸኝ…” ብለን ድንገተኛ ቢጤ የቋጠርንበት መቀነታችን በብር የተሞሉ ይመስላቸዋል፡፡ ባዶ ነው! እንደውም…አለ አይደል…ኪስን ‘ለመጋዘንነት’ ማከራየት ቢቻል ኖሮ፣ ስንቱ የሀበሻ ልጅ ፍራንክ በፍራንክ ይሆን ነበር!
ስሙኝማ…አንዳንዴ ነገረ ሥራችን እኮ ለፈለገ ‘ጥይት’ የሆነ ተመራማሪ እንኳን ቢሆን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር መሀል ከፍስኩ በኋላ በየክትፎ ቤቱ የሚኖረውን ግፊያ ስታስቡት…ድንገተኛ ጎብኚ “ኧረ እነሱ ጥጋብ በጥጋብ ናቸው፣” ቢል አይገርምም፡፡ (እንደውም…“አመጋገባቸው የሁለት ዲጂት ዕድገት አሳይቷል ባይል ነው!”  ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…ምድረ ምግብ ቤት ሲሳይ ሊወርድለት ነው፡፡ የምር ግን የብዙ የምግብ ቤቶቻችን ነገር ግርም አይላችሁም…የምግብ ዝርዝሩ ላይ ሠላሳ ሦስት ምግብ አይነቶች ተደርድረዋል፡፡ የምታገኙት ግን ግፋ ቢል አምስትና ሰባቱን ነው፡፡
“ስቴክ አለ?”
“ስቴክ የለም! እስቲ ጠይቄ ልምጣ!”
“የቤቱ ስፔሻል ምን ምን አለበት?”
“እ…ጠይቄ ልምጣ፡፡”
“ጠይቄ ልምጣ…” የሚያበዙ አስተናጋጆች፤ “ጠይቄ ልምጣ…” የሚለውን ሀረግ እንዳይጠቀሙ እገዳ ይጣልልን፡፡ (መቼም ለ‘እገዳ’ና ‘ክልከላ’ የሚችለን የለም አይደል!)
 ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…ምን የሚያካክሉት ሆቴሎች በእንግሊዝኛ የሚጽፏቸው የምግብ ስሞች ‘በምን ቋንቋ እንደተጻፉ’ ይነገረን! ቂ…ቂ…ቂ… ገና ለገና “የፈረንጅ አፍ አያውቁም…” እየተባለ አታሞኙና!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሞኝነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… (ይህን ክፍል ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች ማንበብ የተከለከለ!…ቂ…ቂ…ቂ…) ሰውየው ለካስ ከሰው እርቆ ከርሞ ኖሯል፣ እናላችሁ… ራሱ ላይ ‘ያልወጣበት’ ነገር የለም! ታዲያላችሁ…አንድ ቀን ሰው በሌለበት አካባቢ የሆነች ግመል ያይና ‘እርኩስ መንፈስ’ ያድርበታል፡፡ (ዝርዝሩን በቦታ ጥበት ምክንያት አልጻፍነውም!)
እናማ… ግመሊት ሆዬ ያዝ ሲያደርጋት ትሸሻለች፣ ያዝ ሲያደርጋት ትሸሻለች፡፡ እሱዬው ሊፈነዳ (ጭንቅላቱን ለማለት ነው!) ምንም አይቀረው፡፡ ይሄኔ ‘የከፈተውን ጉሮሮ ሳይደፍን’ የማያድረው ፈጣሪ ምስጋና ይግባውና አንዲት ሴት ብቅ ትልላችኋለች፡፡
“እባክህ አንድ ውለታ እንድትውልልኝ ፈልጌ ነው…” ትለዋለች፡፡ እሱዬውም “ምን ላድርግልሽ?” ይላታል፡፡ እሷም “አገሬ የምደርስበት ገንዘብ አጠረኝ፣ ትንሽ ብትረዳኝ…” ትለዋለች፡፡ ከዛ ምን ይላታል… “ገንዘቡን ብሰጥሽ የፈለግሁትን ነገር ታደርጊልኛለሽ?” ይላታል፡፡
እሷም “በደንብ አድርጌ…” ትለዋለች፡፡ እሱም ለማረጋገጥ እንደገና… “ምንም ነገር ቢሆን ያልኩትን እሺ ብለሽ ትፈጽሚያለሽ?” ይላታል፡፡ እሷም “ምንም ነገር ቢሆን እፈጽማለሁ፣” ትለዋለች፡፡ ከዛላችሁ…ገንዘቡን ይሰጣታል፡፡
እሷዬዋ ገንዘቧን ከተቀበለች በኋላ… “እሺ፣ ምን እንድፈጽምልህ ነው የምትፈልገው?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
አጅሬው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “አንድ ጊዜ ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!”
እኔ የምለው…የፈለገው አይነት ቢሆን እዚህም የሚደርስ ሞኝነት አለ? ነው ሰውየው ስለ ‘ባዮሎጂ’ የሚያውቀው ነገር የለም!
እናላችሁ…በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሞኝነትን የሙጥኝ ያልን ያለን አለን፡፡ ደግሞላችሁ “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምንል አይነት ሞኞች የሚያደርጉን ግለሰቦችና ተቋሟት መአት ናቸው፡፡
አሳላፊውን ትጠሩታላችሁ… “ያዘዘኩት እኮ ጭቅና ጥብስ ነው…”
“እሱ እኮ ጭቅና ጥብስ ነው፡፡”
የቀረበው ሥጋ እኮ አይደለም ሊለሰልስ…ምን አለፋችሁ፣ ኤክሲሞዎች ከሦስት መቶ ዓመት በፊት በረዶ ውስጥ የቀበሩት የጎሽ ሥጋ እንኳን እንደዛ አይጠነክርም፡፡ እናማ… “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ ሞኝ ሲያደርጓችሁ አያበሽቅም!
“ድርጀቱ ምርቱን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው…” ይሏችኋል፡፡ ወይ ምርት ማሳደግ!... ሰውየው ካለፉት አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ አሥራ አንዱን እኮ በስብሰባ ነው ያሳለፉት!
ዘንድሮ እንደሆነ መሰብሰቢያ ምክንያት አይጠፋም፡፡ የምር እኮ… አለ አይደል… ስብሰባ ራሱን ችሎ ‘የኤክስፖርት ምርት’ ቢሆን ኖሮ ባዶ አቁማዳችንን አንጠልጥለን በየጄኔቫውና በየዋሽንግተኑ  “እርጠቡን!”  “ጽደቁብን!” እያልን ባልተንከራተትን ነበር፡፡
እናላችሁ…አይደለም ምርት ሊያድግ… አንዲት ደቂቃ ሳይሠሩ የዛጉ መሣሪያዎች በሞሉበት “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ አይነት ሞኞች ሲያስመስሏችሁ የምር ያበሽቃል፡፡  
ብዙ ጊዜ ሪፖርት ምናምን የሚሏቸው ነገሮች ሲቀርቡ… “በሠራተኞቹ መካከል ያለው ከፍተኛ የሥራ ፍቅር…” ምናምን የሚሏት ነገር አለች፡፡ አይደለም የሥራ ፍቅር ሊኖር…አለ አይደል… ሰዉ ተናክሶ፣ ተናክሶ ምናልባትም… “በሠራተኞች የእርስ በእርስ ቁርሾ ሦስተኛ ዓለም ጦርነት መነሻ የሆነችው የመጀመሪያዋ አገር…” አስብለው የአልጀዚራ የዘጋቢ ፊልም ሲሳይ ሊያደርጉን የሚችሉ ናቸው እኮ። ሰዉ ሥራ ከመሥራት ይልቅ ሁሉም ሰላይ፣ ሁሉም ተሰላይ በሆነበት “የሥራ ፍቅር…” ምናምን ነገር እየተባለ “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ አይነት ሞኞች ሲያስመስሏችሁ የምር ያበሽቃል፡፡  
ደግሞ ሌላ አለላችሁ፡፡ “እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የዴሞክራሲ፣ የልማትና ፍትህ ተግባራት ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ…” (ስለደከመኝ አቋረጥኩት) የሚባል እንደ ዕለታዊ ጸሎት ተደጋጋሞ
የምትሰሙት ነገር አለ፡፡ እኔ እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… አንዳንዴ ሳስበው የሰው ልጅ ላይ ተጠናቆ የተዘጋጀ ‘ሶፍትዌር በመጫን’ ዓለምን እንደምንቀድም ማንም ያየልን የለም፡፡ አሀ…ሶፍትዌር ካልሆነ እስከ ነጠላ ሰረዝ ድረስ ተመሳሳይ ነገር መናገር የሚቻለው በምን ተአምር ነው!  
እናላችሁ… የማርያም መቀነትን በአሥር እጥፍ የሚያስከነዳ ዓረፍተ ነገር የሚያነበንቡት ‘ሶፍትዌር እንደተጫነባቸው’ የሚጠረጠሩት (ቂ…ቂ…ቂ…) ዴሞክራሲ ምናምን ማለት ተጀምሮ የሚያልቅው “ስሙኝማ…” እያሉ በመጻፍ ብቻ የሚመስላቸው አይነት ናቸው። እናማ… በለመድናት ‘ቋንቋ’… “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ አይነት ሞኞች ሲያስመስሏችሁ የምር ያበሽቃል፡፡  
የምር ግን ምንም አይየነት ነገር ቢያደርጉን ተፍቆ የማይለቅ፣ ታጥቦ የማይጠራ… ‘ሞኝነት’ ተሸክመን የምንዞር መአት ነን፡፡
እንትናዬ…ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝማ!  ማለትም…ስለ ባዮሎጂ የሚያስረዳ ደግ ሰው እስካገኝ ድረስ!
መልካም የበዓል መዳረሻ ሰሞን ይሁንላችሁ።
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6397 times