Monday, 14 April 2014 09:54

“ሙቀቱ ፈታኝ ቢሆንም ተቋቁመነዋል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

የታላቁ የህዳሴ ግድብ
የስራ ድባብ-  በሰራተኞች አንደበት

አቶ ተመስገን አበበ ይባላሉ፡፡ ከሰሜን ጎጃም አጨፈር ወረዳ፣ ከጣና በለስ አካባቢ እንደመጡ ይናገራሉ፡፡ የህዳሴው ግድብ አካባቢ ያለው መሸጋገሪያ ድልድይ ሳይሰራ በፊት ሰዎችን በጀልባ በማሻገር ነበር የመተዳደሪያ ገቢያቸውን የሚያገኙት። ቦታው ለግድቡ መስሪያ በጂኦሎጂስቶች ሲጠና እሳቸው ሰዎችን በጀልባ ያሻግሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ጥናቱ ተጠናቆ ስራ ሲጀመር የህዳሴውን ግድብ ተቀላቀሉ፡፡ በመጀመሪያ በጉልበት ሰራተኝነት ተቀጥረው ሰሩ፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ በጥረታቸው ረዳት የክሬን ኦፕሬተር ለመሆን በቁ፡፡ አሁን ዋና የክሬን ኦፕሬተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሶስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ዕለት እሳቸው ሲሰሩ ነው ያደሩት፡፡ ቢሆንም የመኝታቸውን ሰዓት ሰውተው፣ የክት ልብሳቸውን ለብሰው ለበዓሉ በተደኮነው ድንኳን ውስጥ ተገኙ፡፡
የሚገርመው ደግሞ የ23 ዓመት ዕድሜ ያለው የመጀመሪያ ልጃቸውም እዚያው ነው የሚሰራው። በሜካኒክነት “በዓሉን ማክበር አለብኝ ብዬ እንጂ አሁን የመኝታ ሰዓቴ ነበር፤ ሌሊት ተረኛ ስለነበርኩ” አሉኝ አቶ አበበ፡፡ ታዲያ ስራ እንዴት ነው አልኳቸው፡፡ “ስራውም ክፍያውም ጥሩ ነው፤ ብቻ ሙቀቱ አስቸጋሪ ነው፤ እሱንም ቢሆን አሁን እየለመድነው ረስተነዋል” ሲሉ መለሱልኝ። የምግብ፣ የጤናና የእንቅልፍ ሁኔታን የተመለከቱ ጥያቄዎች አነሳሁ፡፡ አብዛኛው ሰራተኛ በየመኝታ ክፍሉ አብስሎ ነው የሚበላው፡፡ ለምን ቢባል? በሬስቶራንቱ የሚሸጠው ምግብ ውድ ነው ይላሉ። የጤና ሁኔታ እዚያው  ህክምና ስለሚያገኙ እንደማያሳስባቸው የተናገሩት አቶ አበበ፤ “ወባም ብትሆን በሁለት ክኒና ድራሿ ይጠፋል” በማለት ፈገግ አሰኙኝ፡፡
ወጥ ራሳቸው ሰርተው እንጀራ “ባምዛ” ከተሰኘ ከተማ በኮንትራት እንደሚያስመጡ የገለፁልኝ ክሬን ኦፕሬተሩ፤ ምግብ ማብሰሉ ትንሽ ጊዜያቸውን እንደሚሻማቸው ይናገራሉ፡፡ በተረፈ ስራው ሌትም ቀንም በትጋት እየተሰራ እንደሆነና የዚህ ስራ አካል መሆናቸው ደስተኛ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ከሰሜን ጎንደር ከደልቂ አካባቢ እንደመጣች የምትናገረው የ22 ዓመቷ አብነት አዋዝ፤ በመኪናና በግቢ ደህንነት ስራ ላይ ከተሰማራች ሁለት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ በአጠቃላይ በስራው ደስተኛ ነኝ የምትለው ወጣቷ፤ “በዚህ ግድብ ስራ ላይ የሚሰሩት ሁሉ ደሞዛቸው ቢለያይም ስራውን ግን ሁሉም እኩል ይሰራሉ” ብላለች፡፡ ሁሉም በየዘርፉ በንቃትና በትጋት ስለሚሰራ ደስ ይላል፤ የመኝታው ደረጃ፣ የምግቡ አይነትና ደሞዙ ግን ልዩነት አለው ያለችው አብነት፤ በመኝታ በኩል ለስምንት ሰዎች፣ ለአራት ሰዎች፤ ለሶስት ሰዎና ለሁለት የሚሰጥ የመኝታ ክፍል እንዳለ ጠቁማ ይህም እንደየስራ ደረጃቸው የተመደበ መሆኑን ትናገራለች፡፡ መኝታው ኤሲ (የአየር ማቀዝቀዣ) ያለውና የሌለው እንደየደረጃው የተከፋፈለ መሆኑን የምትገልፀው ወጣቷ፤ ያም ሆኖ ሰራተኛው ግድቡን በማሰብ ሳይለግም እየሰራ ነው ብላለች፡፡”
ሻምበል ታደሰ ረጋሳ ይባላሉ፡፡ ትውልድና እድገታቸው ጅማ ነው፡፡ በህዳሴው ግድብ በጥበቃ ስራ ላይ ከተሰማሩ አንድ ዓመት እንደሆናቸው ይናገራሉ፡፡ በስራ ላይ የሙቀቱ ከፍተኛነትና  ውሃ ጥሙ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ችግር እንደሌለ ገልፀው፣ ስራቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል። በስራው ላይ ከእለት እለት ለውጥና ግስጋሴ እያስተዋሉ መሆናቸው እንደሚያስደስታቸው ሻምበል ታደሰ፤ ወደ ግድቡ ስራ የመጡ ሰሞን ፀሐዩና ውሃ ጥሙ ፈትኗቸው እንደነበር ይናገራሉ። “ሆኖም በስራ ባልደረቦቼ ማበረታቻና አይዞህ ባይነት አሁን ሁሉንም ተላምጄው በንቃት እየሰራሁ ነው” ብለዋል፡፡
የ28 ዓመቱ ወጣት ስሙን መጥቀስ አልፈልገም። ወደ ህዳሴው ግድብ በጉልበት ሰራተኝነት የሄደው ከሁለት ዓመት በፊት ከጎጃም ሉማሜ ከተባለ ቦታ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአካባቢው አባቱን በእርሻ እያገዘ ትምህርቱን ጎን ለጎን በመከታተል እስከ 10ኛ ክፍል መዝለቁን አጫውቶኛል፡፡ አባቱ እድሜ እየተጫናቸው ሲመጣ፣ ኃላፊነቱ እሱ ላይ ስለወደቀ፣ ትምህርቱን ከ10ኛ ክፍል በላይ መቀጠል አልቻለም። በአካባቢው ወግና ባህል መሰረት ትዳር ቢይዝም አባቱ ቆርሰው የሰጡት መሬት ኑሮውን የሚያሻሽል ሆኖ ስላላገኘው፣ ወደ ህዳሴው ግድብ በጉልበት ሰራተኝነት ለመሰማራት መሄዱን ይናገራል፡፡
“ከሙቀቱ ጋር የጉልበት ስራ ይከብዳል፤ በማሽን እየታገዙ መስራትና የጉልበት ስራ ይለያያል” የሚለው ወጣቱ፤ ከሁሉም በላይ በጉልበታቸው የሚሰሩ ሰራተኞች ሊደነቁ እንደሚገባ በአፅንኦት ይናገራል፡፡ “ለተማረና እውቀት ላለው ሰው ስራው አይከብድም፤ ብዙ ደሞዝ ያገኛሉ፤ የሚንቀሳቀሱት በመኪና ነው፤ መኖሪያቸው የሙቀት ማቀዝቀዣ አለው” ይላል፡፡ በስራውና በአባይ ግድብ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ወጣቱ፤ “የጉልበት ሰራተኛው ሲሰራ ውሎ ወደ ማረፊያው ሲሄድ ሙቀት ይቀበለዋል፤ የተወሰነ የአየር ማቀዝቀዣ ቢኖር በደንብ አርፎ ጉልበት ለመሰብሰብና ነገ የበለጠ ለመስራት ያግዝ ነበር” በማለት ለጉልበት ሰራተኛው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡
“ይህን የምነግርሽ በስራው ደስተኛ አይደለሁም ተበድያለሁ ለማለት ሳይሆን ስራው የጉልበት ስራ በመሆኑ በምግብና በማረፊያ በኩል የተሻለ ነገር ካላገኘሽ ለነገ ስራ ለመዘጋጀት ይከብዳል ለማለት ነው” ያለው ወጣቱ፤ እንደዚያም ሆኖ ሁሉም በየፊናው ስራውን በአግባቡ እየሰራ ስለመሆኑ እማኝነቱን ሰጥቷል፡፡   
መጋቢት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሶስተኛ ዓመት ክብረ በዓል የተከበረው፡፡ በእለቱም ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽ/ቤት ብሔራዊ ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለሥልጣናትና የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኃላፊዎች የግድቡን ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ አስመልክተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንጋፋውን ድምፃዊ ነዋይ ደበበን ጨምሮ ሌሎችም በስፍራው ተገኝተው በግድቡ ዙሪያ ያቀነቀኑ ሲሆን፣ የተለያዩ ግጥሞችም ቀርበዋል፡፡
ጉዞ በጀመረ በሶስተኛው ቀን ጉባ የደረሰው የጋዜጠኛ ቡድን በራሱ ጥረት ተዘዋውሮ ነገሮችን ለማየት ሙከራ ከማድረጉ በስተቀር የተዘጋጀለት የጉብኝት ፕሮግራም አልነበረም፡፡ በእርግጥ በዓሉ እየተከበረም ስራ አልተቋረጠም፡፡ ተራራ የሚንደው ማሽን ተራራ ይንዳል፡፡ በድማሚት የሚፈርሰውም ይፈርሳል፣ የኮንክሪት ሙሌቱ ይካሄዳል፣ ሆደ ሰፊዎቹ አፈርና አሸዋ አመላላሽ መኪኖች እንደጉንዳን ይርመሰመሱ ነበር፡፡
በዓሉ እየተከበረ አንድ ድማሚት ፈነዳ፡፡ የእለቱ የመድረክ መሪዎች ከነበሩበት አንዷ አርቲስት ሜሮን ጌትነት “አሁን በስራ ላይ ያለው ድማሚት ሲፈነዳ፣ ለበዓል እንደሚተኮስ መድፍ ቁጠሩት” በማለት ተናገረች፡፡ ድማሚቱ አካባቢውን አናጋው፣ ጉሙን እያትጎለጎለና እያሰፋ ወደ ሰማይ ወጣ፡፡ ስራው በዚህ መንገድ ቀጥሏል፡፡ በቅርብ ሆኖ ስራውን ለማየት ለበዓሉ የተጣለው ድንኳን ኮንክሪቱ ከሚሞላበት ቦታ ይርቃል፡፡
በዚያ ላይ በዓሉ እየተከበረ በነበረበት ወቅት ሙቀቱ ከ48-49 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ ስለነበር፣ በእግር ተዘዋውሮ ለመጎብኘት አዳጋች ነበር፡፡ በስፍራው በዓሉን በካሜራቸው እየቀረፁ የነበሩ አንድ የፎቶግራፍ ባለሙያ በሙቀቱ ሩሃቸውን ስተው ወድቀዋል፡፡
በእለቱ ከተጋበዙት አርቲስቶች አንዱ ደምሴ ዋኖስ፤ “አዲስ አበባ በ28 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ ነበር የምዘፍነው፤ አሁን በ42 ድግሪ ሴንቲግሬድ ነው” በማለት ሲቀልድ፣ ሠራተኞች እቺን ተቀብለው “የሙቀቱ መጠን ተጭበርብሯል፤ 490C ገብቷል እኮ” ሲሉ አስተባበሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ በዓሉ ወደ መጠናቀቁ ሲቀርብ፣ “የሳሊኒ አርማ ያለበት ማንጠልጠያ ያለው ባጅ ያደረጋችሁ እንግዶች እባካችሁ ወደ ተዘጋጁት ቢሾፍቱ አውቶብሶች ግቡ” ተባለ፡፡ በአንገት ላይ ባጅ ያደረገ ጋዜጠኛ የለም፤ እንግዶች ወደ አውቶብሱ የገቡት የመስክ ጉብኝት ለማድረግ ነው፤ ጉብኝቱ ጋዜጠኞችን ያገለለበት ምክንያት ባይታወቅም አስገርሞናል፡፡
በነጋታው አሶሳ ባምቡ ሆቴል ግቢ ውስጥ ለ25 ደቂቃ ገለፃ ያደረጉት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ማናጀር ኢ/ር ስመኘው፤ “በትላንትናው እለት ልጁን እንደሚድር አባት ሆኜ ሁሉንም ማስተናገድ አልቻልኩም፤ ይቅርታ አድርጉልኝ” በማለት ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡
“አሁን የተለየ ዘመን ላይ ነው ያለነው፤ ጥላቻን ቅያሜን፣ ዘርን፣ ሀይማኖትን ማዕከል ያላደረገ አገራዊ ፋይዳ ያለው ስራ እየተሰራ በመሆኑ የሚዲያው ሚና ትልቅ ነው፤ አቅማችን ናችሁ” አሉ፡፡ “የዚህ የተለየ ዘመን አካል በመሆናችሁ ስለመጣችሁ ደስ ብሎናል። ስትዘግቡም ግብፅ የምትለውን እረስታችሁ ስለግድቡ የምታውቁትንና ያያችሁትን በትክክል መረጃ አቅርቡ” ሲሉም ምክራቸውን ለገሱ፡፡
“ለምሳሌ ግብፅ የግድቡ ቁመት ወደ ዘጠና ሜትር ዝቅ ይበል ትላለች፤ እናንተ ግን 145 ሜትር ቁመት እንደሚኖረው እንጂ የግብፅን ድምፅ ማስተጋባት የለባችሁም” በማለት አከሉ፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብን በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ለማስመዝገብ ንቅናቄ እንደሚጀመር ኢ/ር ስመኘው በንግግራቸው ገልፀዋል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ 246 ኪ.ሜትር ውሃው ወደ ኋላ እንደሚተኛ፣ ውሃው የሚተኛው 1874 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ እንደሆነ፣ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንደሚይዝ፣ 59 ቢሊዮን ኪዩቡ ለኃይል ማመንጨነት ሲውል ቀሪው በተጠባባቂ ክምችትነት እንደሚውል ኢ/ር ስመኘው የገለፁ ሲሆን ግድቡ በውሀ ምርምር ትልቅ ማዕከል እንደሚሆን፣ ለቱሪስት ፍሰትና ለእንስሳት ማርቢያነት እንደሚውል እንዲሁም በጎርፍ መጥለቅለቅ ቀርቶ ሰላማዊ የውሃ ፍሰት እንደሚኖር አብራርተዋል። የህዳሴው ግድብ አራተኛ አመቱን ሲያከብር 750 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የግድቡ ስራ 30 በመቶ መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡


Read 4203 times