Monday, 14 April 2014 09:53

ለአርቲስቶች ጫማ የሚጠበበው ባለሙያ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(7 votes)

በምዕራቡ ዓለም ለአርቲስቶችና ለዝነኞች አልባሳትንና መጫሚያዎችን በትዕዛዝ የሚሰሩ ባለሙያዎች (ዲዛይነሮች) ታዋቂዎች ናቸው፡፡ ታዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ሃብታሞችም አንደሆኑ ይነገራል፡፡ በአገራችን በተለይ ለአርቲስቶች የሚጠበቡ ባለሙያዎችን እምብዛም አናውቅም፡፡
የተለያዩ ጫማዎችን በትዕዛዝ የሚሰራው ቸርነት - ግን ለዕውቅ አርቲስቶች በስማቸው ጫማ እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ ከአርቲስቶችም በተጨማሪ ትላልቅ ባለስልጣናትም ደንበኞቹ ናቸው። በልጅነቱ የጥበብ ፍቅር የነበረው ቢሆንም አርቲስት መሆን እንዳልቻለ የሚናገረው ቸርነት መንገሻ፤ በሁለተኛ ደረጃ በፍቅር ወደሚወደው የጫማ ስራ ሙያ እንደገባ ይናገራል። አርቲስትነት ባይሳካለትም ለአርቲስቶች መስራት ችሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ከጫማ ባለሙያው ቸርነት ጋር በህይወቱና በሙያው ዙርያ እንዲህ አውግታለች፡፡

የልጅነት ህልምህ ምን ነበር?
በልጅነቴ ብዙ መሆን የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ከነዚያም ውስጥ አንዱ አርቲስቶችን በቅርበት ማወቅ ነበር፡፡ ቲያትር ተምሬያለሁ - ተስፋዬ አበበ እና ሽመልስ አበራ ዘንድ፡፡ ማክሲኮጊ የተባለ የቲያትር ትምህርት ቤት ገብቼም ቲያትር አጥኝቻለሁ፡፡ ከሙዚቃ መሳሪያም ኪቦርድ ተምሬያለሁ፡፡ ሆኖም አርቲስት መሆን አልቻልኩም፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የጫማ ስራን በፍቅር ነበር የምወደው፡፡ በመሀል የእንጨት ስራም ሞክሬያለሁ፡፡
የጫማ ስራ በስንት ዓመትህ ጀመርክ?
በ12 ዓመቴ፡፡ በጫማ ስራ ውስጥ አዘጋጅ የሚባል አለ፡፡ አንዱን ቆዳ ከሌላው ቆዳ፣ ዋናውን ቆዳ ከገበሩ ጋር አጣብቆ ለሰፊው የሚሰጥ ነው፡፡ የእኔ የስራ ድርሻ አዘጋጅ ነበር፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ቴክኒክ ነገር እወድ ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ይሄን ያውቁ ስለነበር ነው ከትምህርቴ ጐን ለጐን የጫማ ስራን እንዳሳድገው የፈቀዱልኝ፡፡ አንድ በቀለ የሚባል ጎረቤታችን ሃብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በሚገኝ ጫማ ቤት ይሰራ ነበር፡፡ እዚያ ይዞኝ እየሄደ የሚያዙኝን ነገር እሰራ ነበር፡፡ እቃ ከማቀበል ጀምሮ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ነው ስራውን የጀመርኩት፡፡
ክፍያ ነበረው?
የሳሙና በ15 ቀን 8 ብር ይሰጠኝ ነበር። በጣም ብዙ ነበር ለእኔ፡፡ ግን ለገንዘቡ ሳይሆን ስራውን በፍቅር ነበር የምወደው፡፡ እዛ ቤት ወደ ሁለት ዓመት ያህል ሰራሁ፡፡ አዲሱ ገበያ አካባቢ አሰግድ አድማሱ የሚባል ሰው፣ የአካል ጉዳተኞችን ጫማ ይሠራ ነበር፡፡ የታላቅ ወንድሜ ጓደኛ ነው። እሱ ጋ ቁጭ ብዬ የሚሠራውን እከታተል ነበር፡፡ የጫማ ስራ ሙያን የበለጠ እያዳበርኩት መጣሁ። በመሀል ስራ መፍታት ስለማልወድ ሌሎች ሙያዎችን እሞክር ነበር፡፡ የተዋጣልኝ የኤሌክትሪክ ባለሙያ ነኝ። እዛው ሰፈር ደረጀ ፀጋዬ የሚባል ኤሌክትሪሽያን ነበር፤ በእድሜ ይበልጠኛል፡፡ እሱ ይዞኝ ይዞር ነበር፡፡ እኔ እና እሱ አዲሱ ገበያ አካባቢ የገጠምነው የኤሌክትሪክ ምጣድ እስከዛሬ ይሰራል። ይሄ እንግዲህ ከ1978 ዓ.ም ገደማ ጀምሮ ማለት ነው። አንድ ሴትዮ በቅርቡ አግኝተውኝ “እስከአሁን የናንተ ምጣድ አለ፤ አክንባሎው ብቻ ዝጐብኝ አስቀየርኩት” ብለውኛል፡፡
በጫማ ሥራ ሙያ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን አግኝተሃል?
እሱ ሁሉ  ቀርቶ ብሔራዊ ውትድርና ዘመትኩ እኮ፡፡ ነፍሴንም ያተረፍኩት ኤሌክትሪክሽያን ነኝ ብዬ ነው፡፡ የስንት ሺ ወታደር ምግብ የሚዘጋጅበት ሚንስ ቤት ነበር፤ እዛ ገብቼ በኤሌክትሪሽያንነት መስራት ጀመርኩ፡፡
የት ነበር የዘመትከው?
ኤርትራ፤ ሰሜን ግንባር ነው የዘመትኩት፡፡ ከረን  ሳሊት ግንምባርና በተለያዩ ግንባሮች ተዋግቻለሁ፡፡ በመሃል እጄን ቆሰልኩና ለህክምና አስመራ መጣሁ፡፡ ከታከምኩ በኋላ ማገገሚያ ቦታ ወሰዱኝ፡፡ በርቦሬላ የሚሊሻ ማገገሚያ ይባላል፡፡ በርቦሬላ የጣሊያኖች ምሽግ የነበረ ነው፡፡ እዛ እያለሁ ወይ ኃላፊዎቹ ጠጋ እያልኩ “እንደዚህ እሰራለሁ እኮ” በማለት አንዳንድ ችግሮችን በሙያዬ መፍታት ጀመርኩ፡፡ የአዛዦች ቢሮም እየሄድኩ እሰራ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ዝውውር ጠየቁልኝና ወደ ከተማ መጣሁ፡፡
በመጨረሻ ከውትድርና እንዴት ወጣህ?
በ1984 ዓ.ም ደርግ ሲወድቅ ነው የወጣሁት። ከአስመራ ሻቢያዎች አምጥተው ለቀይመስቀል አስረከቡን፡፡ ቀይ መስቀሎች ደግሞ በእግራችን መቀሌ ግቡ አለን፡፡ ከዚያ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ ወደ 700 ኪ.ሜ ገደማ በእግራችን ተጉዘናል።
አዲስ አበባ ምን ገጠመህ?
አዲስ አበባ ስመጣ ስራ የለም፤ አዲስ መንግስት ነው፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ አሰብኩ፡፡ ያቺ የጫማ ስራ ፍላጐቴ አልሞተችም ነበር፡፡ ራስ ዳሽን ጫማ ፋብሪካ የሚባል ነበር፤ እዛ ሄድኩኝና “ምን ትችላለህ ወታደር ነበርክ አይደል?” ሲሉኝ የምችለውን ሁሉ ነገርኳቸው፤ ተገረሙ፡፡  ድሮም ጫማ ስራ ላይ እንደነበርኩ ገለጽኩላቸው፤ በጫማ ሥራ የሙያ ቋንቋ፡፡ የጫማ ሙያ መሠረታዊ ቋንቋዎች አሉት፡፡ እናም ሙያዊ ትንታኔ ሰጠኋቸው።
ተቀበሉህ?
አዎ፤ በቀን ስድስት ብር ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡ በሙያው በደንብ ጎለበትኩ፡፡ አንድ አብሮኝ የተማረ ጓደኛዬ… አሁንም “ክሮኮዳይል” የሚባል የጫማ ፋብሪካ አለው፡፡ እሱ የቆዳ ፋብሪካ እንዳለው ሰማሁኝ፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ ፋብሪካው ሄጄ አገኘሁት፤ የጫማ ባለሙያ መሆኔን ነገርኩት፤ “ወጣሪ ነኝ” አልኩት፡፡ አራት ቀን ያህል አሰራኝና የወንድሙ ፋብሪካ ጋ ወሰደኝ፡፡ ያኔ ለወጣሪ ከ40 ብር በላይ ነበር የሚከፈለው፡፡ የእርሱም ወንድም ቆዳ ፋብሪካ ያለው ትልቅ ሰው ነው። እሱ ጋ ረዥም ጊዜ ሰራሁ፡፡ ጫማ መስፋት ሁሉ ተማርኩ። ጫማ ሰሪ ሲባል በአብዛኛው ሰፊ ነው። እኔ ግን ወጣሪ ነበርኩ፡፡ የቤተሰብ ቤት ስለነበረ እየዘለልኩ ሲንጀር ላይ ነው… የማልሰራው ነገር አልነበረም፡፡ ሁሉንም ጠንቅቄ አወቅሁኝ፡፡ በኋላ ዘርአብሩክ ከሚባል ጓደኛዬ ጋር “ዘርቸር” የተባለ ጫማ ቤት አዲሱ ገበያ አካባቢ ከፈትን፡፡ በትዕዛዝ ጫማ የሚሰራ ማለት ነው፡፡ ሰፈሬ ስለነበር በቀላሉ ገበያ ለመደልኝ። ጓደኛዬ እንዴት ጐበዝ ልጅ ነበር መሰለሽ፡፡ የጫማ ስራ ምስጢር አለው፤ ያልኩት ያኔ ነው፡፡ በፋብሪካ ደረጃ በቅብብል ሲሰራና አንድ ሰው ተጀምሮ እስኪያልቅ ብቻውን ሲሰራው ይለያያል፡፡ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ የበቃሁት ከዘርአብሩክ ጋር በመስራቴ ነው፡፡ ገበያ ሄዶ ቆዳውን መምረጥ በራሱ ትልቅ ሙያ ነው፡፡ ራሱ ቆርጦ፣ አዘጋጅቶ፣ ሰፍቶ፣ ወጥሮ፣ ገርዞ፣ አልብሶ፣ ማስቲሽ ቀብቶ፣ አጣብቆ … አንድ ጫማ ለብቻው ሰርቶ ያጠናቅቅ ነበር፡፡ አብዛኛው ባለሙያ ሁሉንም ነገር መስራት አይችልም፡፡ ቆራጭ ከሆነ ቆራጭ ነው፡፡ በቃ!
መቼ ነው የየራሳችሁን የጫማ ቤት ከፍታችሁ መስራት የጀመራችሁት?
አቅም ስናገኝ ነው ለየብቻ መስራት የጀመርነው። ለሁለታችንም 11ሺ ብር እቁብ ደረሰን፡፡ “ዘርቸር” የሚለው ብራንድ ስለሆነ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ብለን፣ እኔ አየር ጤና ሄጄ ከፈትኩ፡፡ ጓደኛዬ አዲሱ ገበያ ቀረ፡፡ በኋላ በቻይና ምርቶች የተነሳ ስራው ሲሞት፣ አቋርጨው በሌላ ስራ ተሰማራሁ፡፡
የቻይናን ፉክክር መቋቋም አቃታችሁ ማለት ነው?
ዋናው እኮ የሸማቹ ግንዛቤ ነው፡፡ የእኛን ስራ ገና ሲያዩት “ሎካል ነው” ብለው ነው የሚጀምሩልሽ፡፡ አንድ ገዢ “ይሄ እኮ ሎካል ነው” ሲል “ቀሽም ነው” እንደ ማለት ነው … ይሄ …የዛሬ 13 ዓመት ነው፡፡ አሁን ግንዛቤው ተቀይሯል፡፡
በነገርሽ ላይ መርካቶ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ግን ማንም አያውቃቸውም፡፡ ብዙዎቹ ከክፍለሀገር የመጡ ናቸው፡፡ ማሽን የሚሠራውን ስራ በእጃቸው ሲሰሩ ስመለከት፣ ቆሜ ነው ያጨበጨብኩላቸው፡፡ በእርግጥ የፊኒሺንግ ችግር አለ፡፡ የጥራት ቁጥጥር ክፍሉ ስራው ካለቀ በኋላ ምርቱን በደንብ መፈተሽ አለበት፡፡ በተለይ ትልቅ ፋብሪካ ያላቸው በጥብቅ መከታተል አለባቸው፡፡ ጫማ ከመጫሚያነቱ ባሻገር የቅንጦትም ነገር ነው፡፡ ካላማረ ማንም አይገዛሽም፡፡
እንዴት ነው እንደገና ወደ ጫማ ሥራህ የተመለስከው?
እንዳልኩሽ የቻይና ጫማ ሲመጣ ለተወሰነ ጊዜ ሥራውን አቁሜ ወደ ሌላ የሙያ ዘርፍ ገባሁ፡፡ ሆኖም ጫማ የመስራት ፍቅሬ ሌት ተቀን አላስቀምጥ ብሎኝ ነበር፡፡ ለጫማ ስራ እጠቀምባቸው የነበሩ ማሽኖችን ሁሉ አንድ ቀን እመለስባቸዋለሁ ብዬ አስቀምጫቸው ነበር፡፡ ከስራው ብለያይም የማውቀው የጫማ ፋብሪካ እየሄድኩ ሥራዎችን ማየቴ አልቀረም፤ ለአንዳንድ ጓደኞቼም ሞዴል አወጣላቸዋለሁ፤ እቃዬን ሁሉ አውሳቸው ነበር፡፡ እናም ግንኙነቴ አልተቋረጠም፡፡
መስቀል ፍላወር አካባቢ ያለው ሱቄ፣ (አሁን ያየሽው) የሚስቴ ሱቅ ነበር፡፡ የዛሬ 4 ዓመት ከሚስቴ ሱቅ በላይ “ባናቱ ሆቴል” የሚባል ነበር። በርካታ አርቲስቶች ይሰባሰቡበታል፡፡ አንድ ቀን በሆቴሉ በኩል ሳልፍ ብርሃኑ ተዘራ፣ ማዲንጐ አፈወርቅና ሌሎችም አርቲስቶች ተመለከትኩና ገብቼ ተዋወቅኋቸው፤ ተቀራረብን፡፡
የሆነ ቀን ራሴ የሠራሁትን ጫማ አድርጌ ሄጄ፣ እንቁ የሚባል ጓደኛችን… “ይሄ ጫማ ሲያምር” ሲል አደነቀልኝ፡፡ “እኔ ነኝ የሰራሁት” አልኩት፡፡ በሌላ ጊዜም እንዲሁ ሌላ ጫማ ሰርቼ አድርጌ ሄድኩኝ። አሁንም በጣም እንደሚያምር ነገረኝና “ለእኔም ስራልኝ” አለኝ፡፡ በሌላ ቀን አራት ጫማ ስራልኝ ብሎ 4መቶ ብር ቀብድ ሰጠኝ፡፡ በ15ኛው ቀን አንድ ደርዘን (አስራ ሁለት) ጫማዎች ሰርቼ ሄድኩ - በሽሚያ ወሰዱት፡፡
አሁን “አቻሬ ጫማ” ቤት የሆነው የዛሬ አራት ዓመት የሚስቴ ሱቅ ነበር፡፡ ያኔ የሚስቴ ሱቅ አሻንጉሊቶች ላይ የሰራኋቸውን ጫማዎች አስቀምጥ ነበር - ለማስተዋወቅ፡፡ ገና ማስቀመጥ የጀመርኩ ጊዜ ሚስቴ ደውላ፤ “ይሄ ጫማ እዚህ ነው ወይ የሚሠራ ብለው፤ ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ወሰዱት” አለችኝ። ከዚያም በተለያዩ ሞዴሎች ጫማ እየሰራሁ ስደረድር ሽሚያ ሆነ፡፡ ያ ዕንቁ ያልኩሽ ጓደኛችን፣ ቅፅል ስም ወጥቶለታል… “አስከፋች” የሚል፡፡ እሱ ነው ገበያውን የከፈተልኝ፡፡
ለምንድነው “አቻሬ ጫማ” ያልከው?
አቻሬ የሚባል ስም ከየት መጣ መሰለሽ … አሸናፊ የሚባል ጓደኛዬ “አቻሬ” ብሎ ይጠራኝ ነበር፡፡ “አቻሬ” ማለት በስፓኒሽ ቋንቋ “እንትና” ማለት ነው። አቻሬ፤ ቸርነት ከሚለው ስሜ ጋር  ይመሳሰላል፡፡ ዛሬ የቅርብ ጓደኞቼ እንኳ ስሜ ይደናገራቸዋል፤ በአብዛኛው “አቻሬ” ነው የሚሉኝ። ለዚያ ነው ጫማውንም “አቻሬ ጫማ” ያልኩት፡፡ አርቲስቶቹ ጓደኞቼ እነ ማዲንጎ ሁሉ “አቻሬ ነው አሪፍ” ብለው ስሙን አፀደቁልኝ፡፡ ኤፍሬም ታምሩ እንደውም የድሮ የህንድ ፊልም ውስጥ “አቻሬ…የሚል ዘፈን አለ” እያለ ያንጎራጉራል፤ ሊቀልድ ሲፈልግ፡፡
የአገሪቱ አርቲስቶች የጫማ ደንበኞችህ ሆነዋል ልበል?
አዎ!! ሁሉም በራሱ ጊዜ ነው መስመር የያዘው። ቴዲ አፍሮ፣ ማዲንጎ፣ ብርሃኑ ተዘራ፣ መሳፍንት፣ ግርማ ተፈራ፣ ጥበቡ ወርቅዬ፣ ጎሳዬ ተስፋየ፣ ግርማ (ጌሪ) .. ደንበኞቼ ናቸው፤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ እንደውም ውጪ አገር ድረስ ይዘውልኝ እየሄዱ ይሸጡልኛል - ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፡፡ ብርሃኑ ተዘራ  መድረክ ላይ  እየዘፈነ.. “ወደ ኢትዮጵያ ግቡ ኢትዮጵያ አድጋለች፤ እንደዚህ ዓይነት ጫማ የሚሰራው የእኛ ወዳጅ ነው” እያለ ያስተዋውቀኛል።
አሜሪካ የሚኖሩ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶችም የአቻሬ ጫማ ደንበኞች ናቸው ይባላል፡፡ እስቲ እነማን ናቸው?
እነ ታማኝ በየነ፣ ተቦርነህ በየነ፣ አለምፀሀይ ወዳጆ፣ ይሁኔ በላይ … እዛ ላሉ ፓትሪያርክም ሰርቼላቸዋለሁ፡፡ ስማቸውን የማልጠቅስልሽ የሀገራችን ባለስልጣኖች ሁሉ፤ እኔ የምሰራውን ጫማ ያደርጋሉ፤ ደንበኞቼም ናቸው፡፡
በጫማ ስራ ዕውቀት ምን ደረጃ ላይ ነኝ ትላለህ?
ጥሩ ዕውቀት ላይ ደርሻለሁ ብዬ አስባለሁ። በካፒታል ግን ገና ነኝ፡፡ በስራዬ እጠቀማለሁ የምልበት ጊዜ ላይ ነው ያለሁት ፡፡ አሁን ትንሽ ትርፍ፣ በጣም ብዙ ደንበኞች ይዣለሁ፡፡
ዓለማቀፍ የጫማ ደረጃዎችን ታውቃለህ?
በትምህርት ቤት ደረጃ የጫማ ስራን አላውቀውም፡፡ እርግጥ በዓለማቀፍ ደረጃ በጥራትና በብራንድ የሚጠቀሱትን ነገሮች አውቃለሁ፡፡ በመማር ሳይሆን በልምድ ነው ያገኘሁት፡፡  አንድ የውጭ ጫማ አይቼ የጥራት ደረጃውን በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ጫማን በትኖ መልሶ መስራት “የበቃ ባለሙያ” አያሰኝም፡፡ በጫማ ስራ የበቃሽ ከሆንሽ፣ በማየት ብቻ ቁጭ ታደርጊዋለሽ፡፡ የጫማ ስራ ደግሞ መሰረቱ አንድ ነው፡፡
እግር እግር ማየት ትወዳለህ አሉ …
(ሳቅ) በጣም! የሥራው ባህሪ እኮ ነው፡፡ ካሌብ የሚባል አርቲስት ጓደኛ አለኝ፡፡ “ጀመረህ እንግዲህ እግር እግር ልታይ” ይለኛል፡፡ ክለብ ውስጥ በደበዘዘ ብርሃን እንኳ አይኔ ፍልፍል አድርጎ የሚያየው እግር ነው… ጫማ፡፡ አንዴ አንድ ሰውዬ የሚያምር ጫማ አድርጎ አየሁትና  አስፈቅጄው በሞባይሌ ፎቶ አነሳሁት.. በተረፈ በአእምሮ የሚያዝ ነገርም አለ፡፡
የሴት ነው የወንድ እግር  የምታየው?
የሁለቱንም ነው፡፡ ግን የሴት ስልሽ ፍላት ጫማ ከሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ባለተረከዝ (ሂል) ጫማ አልሠራም፡፡ የወንድ ግን በደንብ ነው የማየው፡፡ ሴቶቻችን ሂል ጫማ ነው  በብዛት የሚፈልጉት፡፡ እሱ ደግሞ ብዙ ነገር ይጠይቃል፡፡ ብዙ ጊዜ የአገር ውስጥ ሂሎች ይወዛወዛሉ፡፡ ተረከዝ ያለው ጫማ ለመስራት ይከብዳል፡፡ ውጭ አገር በማሽን ሞቆ ነው የሚሠራው፡፡ እኛ አገር በሚስማር ስለሆነ ቶሎ ይነቀላል፡፡ ያንን ሰርቼ ስሜ እንዲበላሽ አልፈልግም።
አንዳንድ  ጫማዎችህ በዕውቅ አርቲስቶች ስም የተሰየሙ ናቸው፡፡ እንዴት ነው አሰያየሙ?
አንድን ሞዴል መጀመሪያ ባሰራው አርቲስት ነው የሚሰየመው ነው፡፡ የመጀመሪያው ጫማ በስሙ የተሰራለት አርቲስት ማዲንጐ ነው፡፡ ትንሳኤ የሚባል አርቲስትም አለ፡፡ ኤፍሬም ታምሩ ደግሞ አንድ ጓደኛችን የእኔን ጫማ አድርጐት ያይና “ጫማው ያምራል ከየት ነው የገዛኸው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ “ከጀርመን ሚስቴ ልካልኝ ነው” ይለዋል፡፡ በኋላ ግን እዚሁ እንደሚሠራ ይነግረዋል። እሱም አሰራ፡፡
ምን አስተያየት ሰጠ…ኤፍሬም?
“I am sorry ራሳችንን እኮ ስለማናከብር ነው፤ ከዚህ ወዲያ ምን ጫማ አለ!” ነው ያለው፡፡ አንዷን ሞዴል በተለያየ ከለር እያሰራ ወሰዳት፡፡ የሸዋንዳኝ፣ የቴዲ አፍሮ… ብዙ አርቲስቶች በስማቸው አሰርተዋል፡፡ ከሴት ሳያት ደምሴ፣ ትዕግስት አፈወርቅ አሉ፡፡ ሳያት የምትገርም የዲዛይን ሰው ናት፡፡ በራሷ ዲዛይን ያሰራቻቸው ብዙ ጫማዎች አሉ፤ ፍላት ጫማዎች፡፡
ጫማዎችህ በትላልቅ ቡቲኮች ይሸጣሉ፤ አንተ ከምትሸጠው በሶስት እጥፍ እንደሚሸጡም ሰምቻለሁ…
ቡቲኮች ጫማዎቼን ይወስዳሉ፡፡ ግን የሌላ አገር ስም ጠርተው ነው የሚሸጡት፡፡ እስከ 2ሺ ብር ድረስ የሚሸጡ አሉ፡፡ አየሽ…  “የስፔን ነው” ሲባልና “የኢትዮጵያ ነው” ሲባል አንድ አይደለም። አብዛኛው ሰው የስፔን ነው የተባለውን ነው የሚገዛው፡፡ ሰው የሚገዛው ስሜቱን ነው፡፡ ቦሌ ምድር ላይ “ይህ የኢትዮጵያ ጫማ ነው” ብሎ በድፍረት የገባው “አቻሬ ጫማ” ብቻ ነው፡፡
የምትሰራቸው ጫማዎች ዋጋቸው እንዴት ነው?
ከፍተኛው 650 ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ እስከ ሁለት መቶ ብር ነው፡፡ ከቻይናና ከቱርክ መቶ በመቶ ይበልጣል፡፡ የት ጋ መሰለሽ የምንበለጠው? ግንዛቤ ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ህዝቡ እየገባው ነው፡፡      
ስንት ሰራተኞች አሉህ?
ስድስት ሰራተኞች አሉኝ፡፡ ስራ ሲበዛ ግን ሰዎች እጨምራለሁ፣ የራሴ ወርክሾፕ አለኝ - ፒያሳ ጣሊያን ሰፈር፡፡
በቀን ስንት ጫማ ትሠራላችሁ?
በዛ ሲባል አስር፤ ትንሽ ሲባል ሁለት እንሰራለን፡፡
ወደፊት እቅድህ ምንድነው?
የራሴ የሆነ ሶል ማምረት እፈልጋለሁ፤ እንደነጃማይካና ከረን ጫማ ፋብሪካዎች፡፡ ለታዋቂ ሰዎች  በስማቸው ጫማ መስራቴን መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ለ “ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ” (ጆሲ) በስሙ ጫማ እየሠራሁለት ነው፡፡ እሱ መኪናውን እና የመኪና መደገፊያውን በራሱ ስም እያሠራ ነው፡፡  ሌሎችም አሉኝ፤ ቀስ እያሉ ይወጣሉ፡፡

Read 6037 times