Monday, 14 April 2014 10:01

የታላቁ የሥነጥበብ ባለሙያ ሁለተኛ ዓመት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ ethmolla2013@gimal.com
Rate this item
(1 Vote)

የሰዓሊው ሐውልት እስካሁን አልተሰራም

ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ሁለተኛ ዓመታቸውን ቢያስቆጥሩም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚገኘው መቃብራቸው እስካሁን ሐውልት አልተሰራለትም። እኛ ግን የሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን ሁለተኛ ሙት ዓመት ለመዘከር አርቲስቱ ከማለፋቸው ከ25 ዓመት በፊት የታተመውን “አፈወርቅ ተክሌ፤ አጭር የሕይወት ታሪኩና ምርጥ ሥዕሎቹ” የተሰኘ መጽሐፍ ለመቃኘት እንሞክራለን።
በመፅሃፉ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የአርቲስቱን የትውልድ፣ የትምህርትና የሥራ ታሪክ በዝርዝር አቅርበዋል። በርካታ ሥዕሎች፣ ፎቶግራፎችና ደብዳቤዎችን በማካተት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀው መጽሐፍ፤ ከያዛቸው ቁምነገሮች ጥቂቱን እነሆ:-
የሲልቪያ ፓንክረስት ውለታ
ሲልቪያ ፓንክረስት፤ በሥነ ጥበብ በትምህርት የዳበረ ዕውቀት ቢኖራቸውም ለሴቶች መብት መከበርና የፋሽስት ኢጣሊያን ወረራ ለመመከት ከኢትዮጵያ አርበኞች ጎን ቆመው ሲታገሉ ስለነበር በሙያው አልገፉበትም፡፡ የሙያውን ሰዎች ግን ሲረዱ ነው የኖሩት፡፡ የሲልቪያ ፓንክረስትን እገዛ ካገኙ የሥነጥበብ ባለሙያዎች መካከልም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ አንዱ ነበሩ፡፡
ሲልቪያ በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጉብኝት ሲያደርጉ ነበር አፈወርቅ ተክሌ በደብተር ላይ የሳላቸውን ሥዕሎች አይተው የተደነቁት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ታዳጊውን ያግዙትና ይደግፉት ጀመር፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ይሄን አስመልክቶ በሰጡት ምስክርነት፤ “ሚስ ፓንክረስት ሁለተኛ የመንፈስ እናቴ፣ መካሪዬ፣ አስተማሪዬና በተለይ ስለጥበቤ ከፍተኛ እንዲሁም ኃይለኛ ሂሰኛዬ ነበሩ። ከዚህም በላይ ለሀገሬና ለሰው ልጅ ከፍተኛ ፍቅር እንዲኖረኝ፤ በስራዬ ተደናቂ ውጤትን በማገኝበት ጊዜ ከመኩራራት በጥብቅ እንድቆጠብና መሥራት፣ መሥራት፣ አሁንም መሥራት እንዳለብኝ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ጎትጓቼ ነበሩ፡፡” ብለዋል - በመፅሃፉ ውስጥ፡፡
ጥቅምት 12 ቀን 1925 ዓ.ም በአንኮበር ከተማ የተወለዱት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፤ ከልጅነታቸው አንስቶ በፍቅር የወደቁለትን የሥዕል ጥበብ፤ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶችም ገፍተውበት፣ ወደ እንግሊዝ ምህንድስና እንዲማሩ ሲላኩም ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት ፍላጎታቸውን በዕውቀት ካዳበሩ በኋላ፣ ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፤ በ1947 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የሥዕል ኤግዚቢሽን አቅርበው ብዙዎችን አስደመሙ፡፡
ይህንን የተመለከቱት ንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴ፤ አርቲስቱ ወደ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ፖርቹጋል፣ ግሪክ እና ሌሎች አገራት ሄደው እዚያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ብራናና ሥዕላዊ ሥራዎችን ለሁለት ዓመት እንዲያጠኑ ድጋፍ አድርገውላቸዋል። ይሄም የንጉሡ መንግሥት ለሥነ ጥበብ ሙያና ባለሙያ ትልቅ ቦታ ይሰጥ እንደነበር አመላካች ነው።
በመፅሃፉ ውስጥ ከተካተቱት የሥነ - ጥበብ ሥራዎች መካከል የአርቲስቱ የሥዕል ንድፎች፣ የቀለም ቅቦች፣ ሞዛይኮች፣ የመስታወት ቅብ ሥዕሎች፣ ቅርፃ ቅርፆች፣ የቴምብር ሥራዎች፣ በመጫወቻ ካርታ የተሰሩ ሥዕሎችና ፖስተሮች ይገኙበታል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽና ሌሎች ቦታዎች ታላላቅ የሥነጥበብ ሥራዎችን ሲሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የፈረንሳይና ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችን በረዳትነት ይቀጥሩ እንደነበር መፅሃፉ በፎቶግራፍ አስደግፎ ይገልፃል፡፡
ለሥዕሎቻቸው ሞዴል ሆነው ያገለገሉ ሰዎችን ፎቶግራፎችም አካትቷል መፅሃፉ፡፡ የአንዳንዶቹን እስከነማንነታቸውም ጭምር ያስተዋውቃል፡፡ ለኢትዮጵያዊት ሴት ሥራቸው ሞዴል የሆነችው የሮም ነዋሪ አንዷ ናት፡፡ አለቃ ለማ ሌላኛው ናቸው። “ለእናት ኢትዮጵያ” ስዕል ሞዴል የሆነችው ሴት እንዲሁም “ፀደይ” በሚል ርዕስ ለሚታወቀው “ኢትዮጵያዊት ወ/ሮ” ሥራቸው ሞዴል የሆኗቸው እንስቶች ፎቶግራፍ ቀርቧል፡፡
የብሔራዊ ክብረ በዓል ልብሶች ንድፍ
“አፈወርቅ ተክሌ አጭር የሕይወት ታሪኩና ምርጥ ሥዕሎቹ” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት የመግለጫ ስዕሎች መካከል አርቲስቱ ጥናት ያደረጉባቸውና ጥናቱ እንዴት እንደተካሄደ የሚያስቃኙ ይገኙበታል፡፡ በእስክርቢቶ፣ በእርሳስ፣ በጠመኔ፣ በአንድ ቀለም…ወዘተ ጥናት ከተሰራባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አርበኛ፣ “ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማ፣ ባህላዊ የእጅ ሥራ፣ የድርቁ ሰቆቃ፣ ለበገና ቅኝት፣ የአፍሪካ አንድነት ባንዲራ…” የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
“አፍሪካዊያን ላደረጉት የነፃነት ትግል አፈወርቅ በጥበብ ሥራዎቹ አግዟል፡፡ ለአፍሪካ አንድነት ዓርማና ባንዲራም አያሌ ጥናቶችን ካደረገ በኋላ፣ ከአሥር በላይ ንድፎችን ሰርቶ አውጥቷል” ይላል - መጽሐፉ፡፡
የኢትዮጵያውያን የአገር ባህል አልባሳትን በተመለከተም በአርቲስቱ የተሰራውን ንድፍ “ሰዓሊው በማዕረግና የሽልማት ልብሶቹ” በሚል ፎቶግራፍ ቀርቧል፡፡
“ሥርዓተ ቅዳሴ፣ የሂሳብ ተማሪው፣ ዝናብ ያዘለ ደመና፣ ጫማ ጠራጊዎች በአዲስ አበባ፣ የተሰበረው ጀበና፣ ሻምላ ተጫዋቾች፣ እንቁላል ቤት፣ ጥንታዊ ሮማ፣ የወይፈን ውጊያ፣ ጉግስ ጨዋታ፣ የጦርነት ሰቆቃ፣ ደመራ፣ የመስቀል አበባ፣ ነርሷና ሕመምተኛው፣ ሚሊሺያ፣ የታመሙና የተራቡ…” የተሰኙ በርካታ ሥዕሎችን የያዘው መጽሐፉ፤ እስከ 1979 ዓ.ም ድረስ ያሉትን የሰዓሊውን ሥራዎች ብቻ ያካተተ መሆኑ ሲታሰብ በእጅጉ ያስደንቃል፡፡
ከ1979 እስከ 2004 ዓ.ም ባሉት 25 ዓመታት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የሰሯቸው ሥዕሎች ብዛትና አይነት በእጅጉ ማጊጓቱ አይቀርም፡፡  የአርቲስቱን ሙሉ የሕይወትና የሥራ ታሪክ በመጽሐፍ ሰንዶ ለሕዝብ ማቅረብ የግድ ነው፡፡ ቪላ አልፋ ሳይከፈት፣ የባለታሪኩም ሐውልት ሳይሰራ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የአርቲስቱ አድናቂዎች ጥያቄና ምኞት ምላሽ የሚያገኘው መቼ ይሆን?
“አፈወርቅ ተክሌ፡ አጭር የሕይወት ታሪኩና ምርጥ ሥዕሎቹ” የተሰኘው መጽሐፍ ለጊዜው እንደ ሐውልት መታሰቢያ ሆኖ፤ የአርቲስቱን ሁለተኛ ሙት ዓመት ለመዘከር ስለረዳን፣ በመጽሀፉ ዝግጅትና ሕትመት ሥራ ላይ የተሳተፉትን ሁሉ ልናመሰግን እንወዳለን፡፡

Read 2348 times